- አስተምህሮተ ሥጋዌ (ኢየሱስ)
ባለፈው ጥናታችን የተመለከትነው ስለ ሰው ጅማሬና ውድቀት እንደ ነበረ የሚታወስ ነው፤ ሰው የተሰጠውን ትእዛዝ አፍርሶ፣ አምላክ ለመሆን የነበረው ምኞት ከስሞ፣ ከኤደን ገነት ተባሮ መኖር መጀመሩን ነበር፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ሰውን በሞት ሁኔታ እንዳለ ሊተወው ይችል ነበር፤ ነገር ግን ስለወደደው ሊያድነው ዐቀደ፤ ዕቅዱም አንድያ ልጁን ወደ ዓለም መላክ፤ በዓለምም ተገኝቶ ለሰው ኀጢአት ቤዛ መሆን ነው›› በማለት ቄስ ማንሰል በመጽሐፋቸው ይናገራሉ፡፡ ምንም እንኳን ሰው በኃጢአቱ ምክንያት የተለያዩ ርግማኖች ቢደርስበትም፤ አሁንም እግዚአብሔር ለሰው ያለው ፍቅር ሲታይ እጅግ አስደናቂና አስገራሚ ነው፡፡ ከዚህ በመቀጠል እግዚአብሔር የሰውን ልጅ በልጁ በኩል አድኖ፣ ከራሱ ጋር ኅብረት እንዲያደርግ የወሰደውን ርምጃ እንመለከታለን፡፡
2.1 ኢየሱስ ከፍጥረት በፊት
ኢየሱስ ከድንግል ማርያም ሥጋ ነስቶ ከመምጣቱ በፊት ይኖር እንደ ነበረ መጽሐፍ ቅዱስ በሚገባ ያስተምረናል፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ በወንጌሉ ምዕራፍ 1፡1-3 ላይ ‹‹በመጀመሪያው ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፣ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ›› በማለት ኢየሱስ ጅማሬ እንደሌለው ያሳየናል፡፡ በኢሳይያስ የትንቢት መጽሐፍም ስለ ኢየሱስ በተነገረው ትንቢት ውስጥ ‹‹የዘላለም አባት›› ተብሎ ሲነገርለት በትንቢተ ሚክያስ ደግሞ ምዕራፍ 5፡2 ላይ ‹‹…አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ… ›› በማለት ቅድመ-ህልውናው (Preexistence) በግልጽ ተነግሮለታል፡፡
ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ሲተርክ፣ ከፍጥረት በፊት እንደ ነበረና፣ እርሱ ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነና ‹‹ሁሉ በእርሱ ሆነ፣ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም›› በማለት አምላክነቱንና ፈጣሪነቱን ገልጾ እናገኛለን፡፡ ሚክያስም ከዘላለም የሆነ እያለ መግለጡ፣ ኢየሱስ መለኮት/አምላክ/ፈጣሪ በመሆኑ አይደክምም፣ አይራብም፣ አይጠማም፣ አያንቀላፋም፣ አይሞትም፤ እነዚህን ሁሉ ነገሮች እርሱ በፍጹም ሊሆናቸውና ሊያልፍባቸው የማይችላቸው፤ ከተፈጥሮው ውጭ ስለ ሆኑ፣ በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ለማለፍ እንዲችል ሰው ሆኖ መጣ፡፡ በምድር በነበረበት ጊዜ የድነትን ሥራ ሲሠራ እንደ ሰብዓዊነቱ ነገሮችን ሲያደርግ ቆይቶአል፡፡
2.2 ኢየሱስ በብሉይ ኪዳን
ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ከመምጣቱ በፊት በብሉይ ኪዳን ጊዜ በተለያየ መገለጦች ይገለጥ እንደ ነበረ ከመጽሐፍ ቅዱስ እናገኛለን፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ በሚል ‹‹ቲኦፈኒ›› (Theophanies) ይገለጥ እንደ ነበረ መረዳት እንችላለን፡፡ ለአጋር፣ ለአብርሃምና ለሙሴ የእግዚአብሔር መልአክ (ያህዌ) በሚል ይገለጥ እንደነበረ ከቃሉ መረዳት ይቻላል፡፡ አጋር ዘፍ.16፡7-14፣ ለአብርሃም ዘፍ.22፡15-18፣ ለሙሴ የሐዋ.7፡30-35
እግዚአብሔርን ከልጁ በስተቀር ማንም አላየውም፤ ሙሴም ያየው እንኳን እግዚአብሔር ወልድን (ኢየሱስ ክርስቶስን) ነው፡፡ ለዚያውም ሙሉ ክብሩን ሳይሆን በጨረፍታ ነበር (ዘጸ.33፡17-23)፡፡ ኢየሱስ በብሉይ ኪዳን ጥላዎችና ምሳሌዎች ነበሩት፡፡ ከሰዎች እንደ አሮን፣ ከሁኔታዎች እንደ መስዋዕቱ በግ፣ ከነገሮች እንደ ያቆጠቆጠችው የአሮን በትር፣ ከሥርዓቶች እንደ መማፀኛ ከተሞች፣ ከበዓላት እንደ ፋሲካ ያሉት ሁሉ ሊመጣ ላለውና ሊያከናውን ላለው ለድነት ሥራው የኢየሱስ መገለጫዎች ነበሩ፡፡
2.3 ኢየሱስ በአዲስ ኪዳን
ኢየሱስ ማነው?፡- ቀደም ብለን እንዳየነው፣ ሰው በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልቶ ኅብረቱ እንደ ተቋረጠ ተመልክተናል፤ በዚህ ጊዜ የሥላሴ ሁለተኛው አካል አምላክና ፈጣሪ የሆነው የጠፋውን የሰውን ልጅ ሊፈልግ እንደ መጣ፤ ጌታ ራሱ በቃሉ ‹‹የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአልና›› በማለት የመጣበትን ዋና ዓላማ ወደ ዘኪዎስ ቤት ሲገባ አውጆአል (ሉቃ. 19፡10)፡፡ ኢየሱስ የዓለም አዳኝ ለመሆን በመለኮታዊነቱ ላይ ሰብዓዊነትን ይዞ የተገለጠ ሰው ነው፡፡ ሰው በሠራው ኃጢአት ከመጣበት ፍርድ ራሱን ማዳን ስለማይችል፤ የሚያድነው አዳኝ ከሰማይ መጣለት፡፡ ኢየሱስ የሚለው ስም ሰብዓዊነቱን የሚያሳይ ሲሆን ትርጉሙም ‹‹አዳኝ›› ማለት ነው፡፡
የሰብዓዊነቱ አስፈላጊነት፡- በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ የክርስትና ትምህርት (ዶክትሪን) መሠረት ኢየሱስ ሰው የሆነበት መንገድ ተሠገዎ (Incarnation) ኢንካርኔሽን ተብሎ ይጠራል፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ በመልእክቱ በ1ኛ ጴጥ. ምዕራፍ 1፡1-2 ላይ ‹‹ … በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይረጩ ዘንድ … ›› የሚለው ሐሳብ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን የድነት ዕቅድ ለመፈጸም በመስቀል ላይ ደሙን በማፍሰስ በተግባር ላይ እንዳዋለው ያመለክተናል፡፡ ኢየሱስ ይህን የድነት ዕቅዱን እንዴት ፈፀመ? ብለን ብንጠይቅ መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ሐሳብ ይሰጠናል፡፡ ኢየሱስ ይህን የድነት ዕቅድ ለመፈጸም የመጣው አንዳንዶች እንደሚሉት መለኮታዊነቱን ትቶ ወይም በሰብዓዊነቱም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ቀደም ብለን እንደገለጽነው ‹‹ፍጹም አምላክ›› ‹‹ፍጹም ሰው›› ሆኖ ነው የመጣው፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ሰው ሆኖ የመጣባቸው ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩትም ሦስቱን ዋና ዋናዎቹን በመቀጠል እናያለን፡፡
1) ለመሞት እንዲችል፡- ቀደም ብለን እንዳየነው፣ ሰው በኃጢአት በወደቀበት ጊዜ፣ የፈረደው ፍርድ ሞት ነበረ (ዘፍ.2፡17)፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በጥፋቱ ሞት ቢፈርድበትም፣ የእጁ ሥራ በመሆኑና ስለሚወደው በጥፋቱ ሊተወው አልፈለገም፡፡ ለእግዚአብሔር መሞት በፍጹም የማይታሰብና የማይቻል ጉዳይ ነው፤ ስለዚህ ከሥላሴ ሁለተኛው አካል/ ወልድ የሚሞት ሰው ሆኖ መምጣት ነበረበት፡፡ ኢየሱስ መሞት ለምን አስፈለገው? ብለን ስንጠይቅ፣ የእግዚአብሔር ቃል በሕዝቅኤል ላይ ‹‹ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች›› (ሕዝ.18፡4)፣ በሮሜ ላይም ‹‹የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና…››(ሮሜ.6፡23) ይላል፡፡ ስለዚህ ያንን ሞት ራሱ መሞት እንዲችል የሚሞት ሰው ሆኖ መምጣት ነበረበት፡፡ የዕብራውያን ጸሐፊም መሞት እንዲችል በሥጋና በደም ተካፍሎ ወንድሞቹን ሊመስል እንደ ተገባው በመናገር፣ እንዲያውም የአብርሃምን ዘር ይዞ እንደ መጣ ማስረጃ አድርጎ በማቅረብ እንዲህ ሲል ጽፎአል፡፡ ‹‹እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፣ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፣… በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፣ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ፡፡ የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም፡፡ ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፣ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው›› (ዕብ.2፡14-18) በማለት ሥላሴ ያወጡትን ዕቅድ ለመፈጸም ወልድ የሚሞት ሰው ሆኖ መጥቶ ለሰው ልጆች ድነት ማስገኘቱን ይናገራል፡፡
2) በችግራችን ሊረዳን፡- ሰው ያልሆነ ፍጡር ሁሉ እንሰሳትም፣ መላእክትም… ሰው ስላይደሉ የእኛ ችግር ፈጽሞ አይገባቸውም፡፡ አንድ በጣም የምወዳትና የምትወደኝ የቤተ ክርስቲያን ድመት ነበረች፤ በሚርባት ጊዜ በጩኸት አዳራሹንና ግቢውን ታናውጠዋለች፣ እኔ ወደ ማድርበት ክፍል ስገባ፣ አይታ ቶሎ ብላ ወደ ክፍሌ ትገባለች፡፡ ከዚያ ቀስ ብላ አንድ እግሯን ጭኔ ላይ ታስቀምጥና ፊቴን ታያለች፣ ቀጥላም ሁሉንም እግሮቿን አውጥታ አርፋ ትቀመጣለች፡፡ እኔም ታሳዝነኝና ወጥቼ ሳምባ ገዝቼላት እመጣለሁ፤ ታዲያ እንዲህ እየተዋደድን አንድ ቀንም ችግሬን ነግሬአት አላውቅም፤ ምክንያቱም ሰው ስላይደለች ችግሬ አይገባትም፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ችግራችን አስቀድሞ የሚገባው አምላክ ቢሆንም የችግራችን ተካፋይ መሆኑ እንዲገባን የሚራብ፣ የሚጠማ፣ የሚደክም፣ የሚያንቀላፋና የሚያዝን ሰብዓዊነትን ይዞ በመምጣት የኃጢአታችንን ዋጋ በሞቱ በመክፈል የችግራችን ረዳት መሆኑን አረጋግጦአል፡፡ አሁን ባየነው የዕብራውያን መልእክት ላይ ‹‹እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና›› (ቁ.18) በማለት ሰው ሆኖ የመጣበትን ሁለተኛውን ምክንያት በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ በሰው ልጆች ሁሉ ላይ የሚደርሱትን ችግርና መከራ ሁሉ ስለ ቀመሰ በችግራችን ሁሉ ሊረዳን የሚችል ‹‹ … የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት›› እንደሆነ ያስረዳናል (ቁ.17)፡፡
3) ምሳሌ ሊሆነን፡- የእግዚአብሔር ወልድ ሰው ሆኖ መምጣት ለእኛ በአራት መንገዶች ልንከተለው የሚገባን ምሳሌያችን ነው፡፡ ሰው በዚህ ምድር ሲኖር የማይቀበላቸው ብዙ ነገሮች ቢኖሩም ጥቂቶቹን እንመለከታለን፡፡ የመጀመሪያው በተለያየ ምክንያት ራስን ያለ መቀበል ችግር ይታይብናል፤ ከዚህ ተነሣ ራሳቸውን በተለለያየ መንገድ የሚያጠፉ አሉ፡፡ ስለዚህ ይህን የምንጠላውን ማንነት፣ ራሱን ተቀብሎ፣ የአዳምን አስቸጋሪና ደካማ ሰብዓዊነት ይዞ ለሠላሳ ሦስት ዓመት ተኩል በዚህ ምድር ላይ በመኖሩ ራስን በመቀበል ታላቅ ምሳሌያችን ነው፡፡ ሁለተኛው ችግራችን የተወለድንበትን ቤተሰብ ያለ መቀበል ነው፡፡ ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ ቤተ ሰብ ነበረው፡፡ ቤተ ሰቦቹ ድሆች ስለ ነበሩ፣ በስምንተኛው ቀን የመንፃት ሥርዓት ለመፈጸም ወደ ቤተ መቅደስ ሲሄዱ፣ ለመስዋዕት ይዘውት የሄዱት፣ ድሆች የሚያቀርቡትን ርግብ ነበር፡፡ ከአስራ ሁለት ዓመቱ ጀምሮ ሰማያዊ አባቱን ለማገልገል ቢጀምርም፣ ሠላሳ ዓመት ሙሉ በሙሉ ማገልገል እስከሚጀምርበት ጊዜ ድረስ፣ ቤተሰቡ ምንም እንኳን ድኃ ቢሆኑም ሳያፍርባቸውና ሳይሸማቀቅባቸው እያገለገላቸው አሳልፎአል፡፡ ይህንንም ማርቆስ በወንጌሉ ‹‹የአናጺው ልጅ›› (ማር. 6፡3) በማለት ቤተ ሰቡን በአናጺነት ማገልገሉን ይገልጻል፡፡ የጌታ ሕይወት ቤተሰብን በመቀበልና በማገልገል ታላቅ ምሳሌያችን ስለሆነ፣ እኛም ወላጆቻችን በምንም ዓይነት ድህነት ውስጥ ይሁኑ መቀበልና ማገልገል ይጠበቅብናል፡፡
ሦስተኛው ችግራችን ኅብረተ ሰባችንን ያለመቀበል ነው፤ ጌታችን ኢየሱስ በተወለደበት ጊዜ አይሁዶች በሮማውያን ቅኝ አገዛዝ ሥር ነበሩ፡፡ ከባቢሎን ምርኮ ጀምሮ እስከ ዘመናችን 1948 ዓ.ም በተለያዩ መንግሥታት ሲገዙ ቆይተዋል፤ የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን ባለ መታዘዝ ባሳለፉት ሕይወት ለአሕዛብ መንግሥታት አልፈው የተሰጡ ነበሩ፡፡ በየዘመናቱ አሳዛኝ ሕይወት አሳልፈዋል፤ ኢሱስም ወደዚህ ምድር በሥጋ በመጣበት ጊዜ በጠላት አገዛዝ ሥር ስለ ነበሩ፣ የራሳቸው መንግሥት፣ መሪና ገንዘብ (currency) አልነበራቸውም፡፡ ጌታም ከዚህ ትውልድ በመገኘቱ፣ ይህን ኅብረተሰብ ተቀብሎ፣ ቤተ መቅደስ በመሄድና የሚገባውን በማድረግ፣ ግብር ገብር ሲሉት በመገበር ኖሮአል፡፡ ከአባቱ የተላከበትን ተልዕኮ ጨርሶ እስከ ሄደ ድረስ እያገለገላቸው ተመላለሰ፤ በዚህ ምክንያት በእርሱ ላይ ክስ የሚያቀርቡበት በቂ ምክንያት ማግኘት አልቻሉም፡፡ ጌታ የተወለደው ከዚህ በቅኝ አገዛዝ ሥር ከወደቀው ሕብረተ ሰብ ነበር፡፡ ጌታም ይህንን ሕብረ ተሰብ በማክበርና በማገልገል ትልቅ ምሳሌያችን ነው፡፡ ስንቶች እንሆን ድኃ ሕብረተ-ሰባችንን ተቀብለን የምንኖር? አራተኛው የምንኖርባትን ሀገር ያለመቀበል ችግር ነው፤ መንግሥትን በመቀበል ምሳሌያችን ነው፤ ከላይ እንደ ተገለጠው ኢየሱስ በተወለደበት ጊዜ አይሁዶችን ይገዛ የነበረው የሮም መንግሥት ነበር፡፡ ሕዝቡ ለሮም መንግሥት ይገብርና ይታዘዝ እንደነበረ ሁሉ ጌታም እንደ ሕዝቡ የሚጠበቅበትን ሁሉ እያደረገ ምሳሌነቱን አሳይቶአል፡፡ አንድ ጊዜ የሚገብረው ሲያጣ ጴጥሮስን ዓሣ አጥምዶ ከሆዱ ውስጥ የሚያገኘውን ገንዘብ ሄዶ እንዲከፍል ትእዛዝ ሲሰጠው መጽሐፍ ቅዱሳችን ይነግረናል (ማቴ. 17፡27)፡፡
ከዚህ በላይ ያሉትን ስንመለከት ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ የመጣው፣ ሥላሴ በአንድነት ሆነው ያቀዱትን (እግዚአብሔር አብ ያቀደውን) ለመፈጸምና ሁሉን በክርስቶስ ለመጠቅለል፣ አስታራቂ ለመሆን፣ ሊቀ ካህናችን ሆኖ ከአባቱ ጋር ለማስታረቅና በምሳሌነት ኖሮ ሕይወትን ለማሳየት ነበር፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ከፈጣሪነት ወደ አዳኝነት ለመምጣት ሰው ሆኖ እንደመጣ በሰፊው ተመልክተናል፤ በመቀጠልም ምድራዊ ሕይወቱን እናጠናለን፡፡
0 Comments