የመላእክት ሥራቸው፡- ስለ መላእክት ማንነታቸውንና ስሞቻቸውን ከዚህ ቀደም ብለን የተመለከትን  ሲሆን፤ አሁን ደግሞ በክርስቶስና በአማኞች ሕይወት የሰጡትን አገልግሎትና ሥራ እናጠናለን፡፡ መላእክት የማይታዩ ከሆነ ሥራቸውን ማን ሊመለከት ይችላል ተብሎ የሚጠየቅ ጥያቄ ሊኖር ይችላል? እኛ ሥራቸውን አየን አላየን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሥራ እንዳላቸው ከነገረን መቀበል አለብን፡፡ ስለዚህ መላእክት እግዚአብሔርን ከማገልገል ውጭ የተለያዩ ሥራዎች እንዳሉዋቸው ከቃሉ እንረዳለን፡፡ ክርስቶስ በምድር በነበረበት ጊዜ እርሱን ማገልገል፣ ወደ ሰዎች መላክ፣ ሰዎችን በተለይም አማኞችን መጠበቅ፣ ያላመኑትን መቅጣት የመሳሰሉትን ተግባራት ፈጽመዋል፣ እየፈጸሙም ይገኛሉ፡፡

በሉቃስ ወንጌል እንደምንመለከተው፣ ‹‹… መልአኩ ገብርኤል … ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፣ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ፡፡ መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ፡- ደስ ይበልሽ፣ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፣ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት›› በማለት ከራሷ ከማርያም ክርስቶስ እንደሚወለድ አመልክተዋል (ሉቃ.1፡26-33)፡፡ በተወለደ ጊዜም መላእክት ለእረኞች ተገልጠው፣ ‹‹… እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና›› ብለው መወለዱን ተራ ለነበሩ እረኞች አብስረዋል (ሉቃ.2፡8-14)፡፡

መላእክት ክርስቶስን በመወለዱ ብቻ ሳይሆን በፈተናውና በመከራው ጊዜም አገልግለውታል፡፡ በማቴዎስ ወንጌል እንደምናገኘው፣ የይሁዳ ገዥ የነበረው ንጉሡ ሄሮድስ፣ የክርስቶስን መወለድ ሳይሰማና ሳያውቅ ወደ ሁለት ዓመት ያህል ካለፈ በኋላ፣ በሰብአ ሰገል አማካኝነት መወለዱን ሲሰማ ሊገድለው አቀደ፡፡ በዚህ ጊዜ የጌታ መላእክ ተገልጦ፣ ‹‹…ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው›› በዚህ ሥፍራ የምንመለከተው ኢየሱስን ከመገደል መታደጋቸውን ነው (ማቴ.2፡13)፡፡ ሰይጣን በሄሮድስ በኩል ሊያጠፋው አልሳካ ሲለው፣ በቀጥታ ራሱ ወደ ኢየሱስ በመምጣት በምዕራፍ አራት ላይ የምናገኛቸውን ወደ ሦስት የሚሆኑ ታላላቅ ፈተናዎችን ባመጣበት ጊዜ፣ ቃሉ እንደሚነግረን መላእክት ቀርበው አገለገሉት(ማቴ.4፡11)፡፡

በሌላ ሥፍራ ማቴዎስ እንደሚነግረን ክርስቶስ በተያዘ ጊዜ፣ ጴጥሮስ ሰይፉን መዝዞ የሊቀ ካህኑን ጆሮ ሲቆርጥ፣ ጌታ ሰይፉን ካስጣለው በኋላ፣ ‹‹አባቴን እንድለምን እርሱም አሁን ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት እንዲሰድልኝ የማይቻል ይመስልሃልን? በማለት ጌታ ቢፈልግና ቢጠራቸው መላእክቶች ሊያግዙትና ከጠላቶቹ ሊያድኑት እንደሚችሉ፣ ለጴጥሮስና ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው (ማቴ.26፡53)፡፡

መላእክቶች ሊያግዙት የሚያስፈልገው ጌታ ኃይል ስለሌለው ሳይሆን፣ የእርሱ አገልጋዮቹ ስለ ሆኑ ነው፤ ቢሆንም  በዚህ ጊዜ የእነርሱን እርዳታ አልፈለገም፡፡ በሉቃስ ወንጌል እንደምንመለከተው በጌቴሴማኒ በጸሎት የደም ላብ እያላበው በሚያጣጥርበት ጊዜ መልአክ መጥቶ አበርትቶታል (ሉቃ.22፡43)፡፡ በትንሣኤውም ጊዜ ቃሉ እንደሚለው፣ እነሆም የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ›› በማለት መላእክት ያላቸውን ኃይልና ጌታን ማገልገላቸውን ያመለክተናል (ማቴ.28፡2)፡፡ በመቀጠልም የተቀበረበትን ሥፍራ ለማየት ለሄዱት ሴቶች፣ ‹‹እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፣ እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ›› በማለት ትንሣኤውን ለሴቶቹ አውጀዋል (ማቴ.28፡6)፡፡

ከዚህ በላይ ካየነው የእግዚአብሔር ቃል ምንም እንኳን መላእክት የማይታዩ ቢሆኑም፣ በኢየሱስ ሕይወት ከሠሩት ሥራዎች፣ ምን አዲስ ነገር አገኛችሁ? ምን ተማራችሁ? መላእክቶች በእኛ ሕይወት ውስጥ ያላቸውን አገልግሎት በግልጽ ባንረዳም፣ በክርስቶስ ሕይወት እንደ ሰጡቱት፣ በአማኝ ሕይወትም ትልቅ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡

የመላእክት አገልገሎት በብሉይ ኪዳን እንደ ተገለጠ እንዲሁም በአዲስ ኪዳንም ተገልጦ እናገኛለን፡፡ በሉቃስ ወንጌል እንደምናገኘው ድሪም የጠፋባት ሴት ድሪሙን ባገኘችው ጊዜ፣ እንዴት እንደምትደሰት ከተናገረ በኋላ ‹‹እላችኋለሁ፣ እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል›› በማለት ሰዎች ሲድኑ መላእክት እንደሚደሰቱ ይናገራል (ሉቃ.15፡10)፡፡ በድነታችሁ ቀን ስንት መላእክት ተደስተው ይሆን ገና  ወደ ጌታ ያልመጣችሁ ብትኖሩ ከሰውም አልፎ በእናንተ መዳን መላእክቶችም ይደሰታሉና ወደ ጌታ ኑና ሕይወታችሁን ስጡ፡፡

መላእክት በመዳናችን መደሰት ብቻ ሳይሆን በችግራችንና በመከራችን ጊዜ ሁሉ ይረዱናል፤ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ጴጥሮስ ታስሮ በነበረበት ጊዜ መልአክ ወደ እስር ቤቱ በመግባት፣ ‹‹… ጴጥሮስንም ጎድኑን መትቶ አነቃውና፣ ፈጥነህ ተነሣ አለው፡፡ ሰንሰለቶቹም ከእጁ ወደቁ፡፡ … ልብስህንም ልበስና ተከተለኝ አለው፡፡ …የሁለተኛውንም ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደሚወስደው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ፣ እርሱም አውቆ ተከፈተላቸው ወጥተውም አንዲት ስላች አለፉ ወዲያውም መልአኩ ከእርሱ ተለየ›› (የሐዋ.12፡6-11)፡፡ በዚህ ቃል ላይ እንደምናገኘው፣ አማኞችን ከእስር ያስፈታሉ፣ በዕብራውያን 1፡14 መሠረት ይረዳሉ፣ ያጽናናሉ፣ ያበረታታሉ፣ ለዚህም ሐዋርያው ጳውሎስ ምስክርነቱ እንዲህ በማለት ይሰጣል፡፡ ‹‹የእርሱ የምሆንና ደግሞ የማመልከው የእግዚአብሔር መልአክ በዚች ሌሊት በአጠገቤ ቆሞ … አትፍራ በቄሣር ፊት ልትቆም ይገባሃል … ›› ብሎ እንዳበረታው ይመሰክራል (የሐዋ.27፡23-24)፡፡ መንፈሳዊ ዓይኖቻችን ተከፍተው የመላእክትን ጥበቃና እርዳታ ብናይ፣ ጌታን እጅግ አድርገን እናመሰግን ነበር፡፡

መላእክት በሕይወት እያለን መርዳት ብቻ ሳይሆን በሞታችን ጊዜም እንክብካቤ እንደሚያደርጉልን፣ ጌታ በአልዓዛር ታሪክ ላይ ተንተርሶ፣ ‹‹ድሀውም ሞተ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት›› በማለት በሞታችን ጊዜ እንኳን የጌታ እርዳታ በመላእክት በኩል እንደሚደረግልን ይናገራል (ሉቃ.16፡22)፡፡ መላእክት ከዚህ በላይ ያየናቸውን አማኞችን እንደሚያገለግሉ ሁሉ፣ በጌታ ያልታመኑትንም በመቅጣት አገልግሎት ይሰጣሉ፤ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ንጉሡ ሄሮድስ ያዕቆብን በሰይፍ ከገደለ በኋላ አይሁድን ደስ ለማሰኘት ብሎ ጴጥሮስን ጨምሮ ይዞ አሠረው፡፡ በዚህ ጊዜ ከጢሮስና ከሲዶና ሰዎች ጋር በተነጋገረ ጊዜ፣ ‹‹ሕዝቡም፣ የእግዚአብሔር ድምፅ ነው የሰውም አይደለም ብለው ጮኹ›› ወዲያው ‹‹ለእግዚአብሔር ክብር ስላልሰጠ ያን ጊዜ የጌታ መልአክ መታው በትልም ተበልቶ ሞተ›› በማለት ሞት የሚገባቸውን ሰዎች፤ መላእክት የመቅጣት ሥልጣን ሲሰጣቸው እንደሚቀጡ ያሳየናል (የሐዋ.12፡23)፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ መላእክት በዚህ በምድር ያላቸውን አገልግሎት ብቻ ሳይሆን፣ በሚቀጥለው በፍዳ ዘመን ፍርድን እንደሚያስፈጽሙ፣ በራዕይ ምዕራፍ 8 እስከ 16 ድረስ፣ ሰባቱን ማኅተም በመፍታትና ሰባቱን ጽዋዎች በማፍሰስ አገልግሎት እንደሚሰጡ መመልከት እንችላለን፡፡ በመጨረሻም፣ በማቴዎስ ወንጌል ተጽፎ እንደምናገኘው በመጨረሻው ዘመን ጻድቃንን ከኃጥአን በመለየት እንደሚሳተፉ ቃሉ ያመለክተናል፤ ‹‹እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል፡፡ የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል፡፡ በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ፡፡ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ›› (ማቴ.13፡39) በማለት በመጨረሻው ዘመን የሚሰጡትን አገልግሎት ያመለክተናል፡፡

እግዚአብሔር መላእክትን ለምንና መቼ እንደ ፈጠረ፣ የፈጠረበት ዋና ምክንያት በመጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ተቀምጦ በሰፊው ባናገኘውም፣ ዓላማውን ሊያሳዩን የሚችሉትን ከተግባራቸው በመጠኑ ለማየት ሞክረናል፡፡ የመላእክት መኖርና ለሰዎች መገለጥ፣ የእግዚአብሔርን ፍቅርና ታላቅነት ያሳዩናል፡፡ የማይታየው ዓለም እውን መሆኑን የበለጠ ያረጋግጡልናል፡፡ መላእክት እግዚአብሔርን ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ እያሉ በማምለክ፣ በማክበር፣ ዕቅዱን በመፈጸምና በታዛዥነታቸው መልካም ምሳሌዎቻችን ናቸው፡፡ ስዚለህ መላእክት ከእኛ ጋር አብረውን እንዳሉ አውቀን ወደ ተሳሳተ አምልኮ እንዳንሄድ መጠንቀቅ እንዳለብን ግንዛቤ መውሰድ አለብን፡፡

ቅዱሳን መላእክት ከእኛ ጋር አሉ ስንል፣ የእኛ ተላላኪዎች አይደሉም፤ ከእግዚአብሔር ወደ ሰው እንጂ ከሰው ወደ እግዚአብሔር አይላኩም፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ ለተገለጠለት መላእክ ሊሰግድ ሲል እንደ ተከለከለ ሲናገር፣ ‹‹እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፣ ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ ለእግዚአብሔር ስገድ፤›› ተባልኩኝ ይላል (ራዕ.19፡10፣ 22፡8-9)፡፡ ስለዚህ መላእክት ፍጡራን እንጂ አምላክ ስላይደሉ ሊመለኩና ሊሰገድላቸው፣ እንደ አማላጅ ሊቆጠሩና በስማቸው ጸሎት ሊደረግም አይገባም፡፡ መላእክት ምንም እንኳን ባናያቸውም እግዚአብሔር እንዲያገለግሉን ስላዘጋጀልን ልናመሰግነው ይገባናል፡፡

            የመላእክት አምልኮ፡- በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን መላእክት ለሰዎች እንደሚገለጡ ከቃሉ ተመልክተናል፡፡ ከዚህ በመነሣት በየዘመናቱ ለሰዎች ከመገለጣቸው የተነሣ፣ ሰዎች በድንጋጤና በፍርሃት፣ በዚያው ጊዜ ስግደት ያቀረቡ እንደነበሩ ከቃሉ እንመለከታለን (ኢያሱ 5፡13-15፣ ዘኁ.22፡31፣ ሉቃ.1፡12-13፣28-30)፡፡ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ እግዚአብሔር የመላእክትን አምልኮ የፈቀደበትን ሥፍራ አናገኝም፡፡ መላእክት ለሰዎች በተለይም ለአማኞች ከእግዚአብሔር መልእክት ማምጣትን፣ ጥበቃን፣ ምሪትን፣ … ቢያደርጉም፤ እኛ ሰዎች ግን መላእክትን ማዘዝና ወደ እግዚአብሔር መልእክት እንዲያደርሱልን መላክ አንችልም፤ ወደ እነርሱም ጸሎት ማድረግ፣ ማምለክና መሥዋዕት ማቅረብ አልተፈቀደም፤ ቃሉም በፍጹም አያስተምረንም፡፡ ስለዚህ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን ለመላእክት አምልኮ መስጠት በፍጹም የተከለከለ  መሆኑን ያስተምረናል፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስም በቈላስይስ መልእክቱ በምዕራፍ 2፡18 ላይ የመላእክትን አምልኮ በመቃወም እንዲህ ብሎ ጽፎአል፣ ‹‹ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፣ ባላየውም ያለ ፈቃድ እየገባ፣ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ›› በማለት የሰዎችን የተሳሳተ ልምምድ ተቃውሞ ጽፎአል፡፡ ቀደም ብለን ባየነው ክፍልም፣ መላእክቶችም ራሳቸው አምልኮና ስግደት እንደማይቀበሉ ሐዋርያው ዮሐንስ በዮሐንስ ራዕይ ምዕራፍ 19፡10 ላይ ‹‹ልሰግድለትም በእግሩ ፊት ተደፋሁ፡፡ እርሱም፡- እንዳታደርገው ተጠንቀቅ ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፣ ለእግዚአብሔር ስገድ … ›› እንደተባለ ጽፎአል፡፡ ስለዚህ ዛሬም ቢሆን ፍጡር ለሆነና በአንድ ቦታ ተወስነው ለሚገኙ መላእክትና ቅዱሳን ሰዎች መስገድና አምልኮ ማቅረብ ተገቢ እንዳልሆነና እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ድርጊት እንደሆነ ከቃሉ መረዳት እንችላለን፡፡

ከዚህ በላይ ከተመለከትነው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አንድ ትልቅ እውነት መረዳት እንችላለን፤ የመላእክት መኖር እርገጠኛ ነው፣ እነርሱም እግዚአብሔርን ለማምለክና ለማገልገል ተፈጥረዋል፡፡ እግዚአብሔር ሰዎችንም እንዲያገለግሉ በሚፈቅድበት ጊዜ ፈቃደኛ ሆነው አገልግሎት ለመስጠት ሁልጊዜ ዝግጁ መሆናቸውን ያስተምረናል፡፡ ስለዚህ በማንኛወም ጊዜ በእግዚአብሔር ታምነን በፊቱ እንመላለስ፣ የእነርሱ እርዳታ ሲያስፈልገን፣ እኛ ባናያቸውም፣ ባናዛቸውም ጌታ ራሱ ያዝልናል፤ ብቻ ከጌታ ጋር የቀረበ ኅብረት ይኑረን፡፡ የሚቀጥለው ጥናታችን የተመሠረተው በጠላታችን በሰይጣን ላይ ስለሆነ ከምናውቀው በላይ ብዙ እንማርበታለን ብዬ አምናለሁ፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *