2.3 የእግዚአብሔር ባሕርያት

ቀደም ባሉት ጥናቶቻችን የእግዚዘብሔር መኖርና መገለጡ በሚሉት ርዕሶች ላይ ጥናት ማድረጋችን ይታወቃል፤ በመቀጠል ወደ አሥራ አምስት የሚሆኑትን የእግዚአብሔርን ባሕርያት እንመለከታለን፡፡ ስለ እግዚአብሔር በቃሉ የተገለጠውን ስንመለከት፤ መለኮታዊ ማንነቱን፣ ከሰው የሚለየውን የላቀ ችሎታውንና እንዲሁም ለሉዓላዊነቱ መሠረት የሆኑትን ጥቂቶቹን ባሕርያቱን ማየት እንጀምራለን፡፡ መለኮታዊ ባሕርያቱን የምናጠናበት ዋናው ምክንያት ስለ እግዚአብሔር የተገለጠውን ለማወቅ ብቻ ሳይሆን በራሳችን ሕይወትና አመለካከት ላይ የሚያስከትለውን ለውጥም ጭምር ለመረዳት ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስን በስፋት የሚያጠኑ ሊቃውንት ባሕርያቱን የሚተላለፉና የማይተላለፉ የእግዚአብሔር ባሕርያት ብለው በሁለት ከፍለው ያስተምራሉ፡፡ እኛም ባንከፍላቸውም ከዚህ በመቀጠል ሁሉንም ባይሆን የእግዚአብሔርን ማንነት የሚገልጹትን ባሕርያት በማጥናት ትምህርት እናገኝባቸዋለን ብዬ አምናለሁ፡፡

3.1)እግዚአብሔር መንፈስ ነው፡- የመጀመሪያው ጥናታችን የተመሠረተው፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ በሚለው በእግዚአብሔር ባሕርያት ላይ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ብለን እንዳየነው እግዚአብሔር እንደማይጨበጥ፣ እንደማይዳሰስ፣  በዓይንም እንደማይታይ ተመልክተናል፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች እግዚአብሔር ካለ ለምን አናየውም? ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ይህን ጥያቄ ሁላችንም ጠይቀን ይሆናል፤ ካላየሁት ግን በእርሱ መኖር አላምንም ማለት ትልቅ ችግር ነው፤ ምክንያቱም እግዚዘብሔር መንፈስ ስለሆነ ማየት አይቻለንም፡፡ በዘጸዓት ምዕራፍ 33፡17-23 ላይ ሙሴ የእግዚአብሔርን ክብር ለማየት ፈልጎ በጠየቀው ጊዜ፣ እግዚአብሔርም በፍጹም ማየት እንደማይችል ሲነግረው እንዲህ አለው፣ ‹‹… ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም … እነሆ ስፍራ በእኔ ዘንድ አለ በዓለቱም ላይ ትቆማለህ ክብሬም ባለፈ ጊዜ በሰንጣቃው ዓለት አኖርሃለሁ፣ እስካልፍ ድረስ እጄን በላይህ እጋርዳለሁ፣ እጄንም ፈቀቅ አደርጋለሁ፣ ጀርባዬንም ታያለህ ፊቴን ግን አታይም››፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርን ከአንድያ ልጁ በስተቀር ማንም ያየው እንደሌለ ይናገራል፡፡ ሙሴ እንኳን ያየው እግዚአብሔር ወልድን እንደሆነ፣ የቃሉ ሊቃውንት ይናገራሉ፤ እውነትም ነው፡፡  

እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን አንዳንድ ጊዜ በቲኦፈኒ (በሰው ወይም በመልአክ መልክ) የሚገለጥበት ሁኔታዎች እንደ ነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ የሚታይ የነበረውም ቀደም ብለን እንዳየነው ክርስቶስ ነበረ፤ ወደ ትምህርተ-ክርስቶስ ስንመጣ በስፋት እንመለከተዋለን፡፡

ዛሬም ቢሆን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ በተለያየ መንገድ የሚገለጥላቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ከዚያ በተረፈ ሐዋርያው ዮሐንስ በወንጌሉ እንዳለው እግዚአብሔርን በመንፈስና በእውነት እናመልካለን እንጂ በአካል ማየትና መዳሰስ በፍጹም አንችልም፡፡ ይህ ማለት እግዚአብሔር አካል የለውም ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የማይታይ፣ የማይጨበጥና የማይዳሰስ መንፈሳዊ አካል አለው (ዮሐ. 4፡24 የሐዋ.17፡29)፡፡

ከደቀ መዛሙርት አንዱ ‹‹ አብን አሳየንና ይበቃናል›› ብሎ በጠየቀው ጊዜ ያገኘው መልስ ‹‹እኔን ያየ አብን አይቶአል›› የሚል ሲሆን በመቀጠልም ‹‹እኔ በአብ እንዳለሁ፣ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን›› በማለት መለሰለት (ዮሐ. 14፡8-10)፡፡ ይህ ወደ ሥላሴ ትምህርት ስንመጣ በስፋት እንመለከተዋለን፡፡ ስለዚህ ማንም እግዚአብሔርን በአካል ለማየት ቢፈልግ ከእኛም በፊት የቻለ የለም፤ እኛም አንችልም፤ ወደፊትም ከእኛ በኋላ የሚኖሩትም አይችሉም፡፡ ሰውም እንደ እግዚአብሔር መንፈስ መሆንም አይችልም፤ እንደ ቶማስ ካላየሁ አላምንም ማለትን ትተን፤ በቃሉ የተጻፈውን ብቻ በእምነት እንቀበል፡፡ መንፈስ የሆነው እግዚአብሔር ቀድሞ ነበረ፣ አሁን አለ፣ ወደፊትም ይኖራል፡፡

3.2 ቅዱስ ነው፡- እግዚአብሔር መንፈስ ስለሆነ ከኃጢአት ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ባሕርይ ቅድስና ስለሆነ ኃጢአት አያውቀውም፣ አያደርግም፤ ከዚህ የተነሣ ከኃጢአት ጋር በፍጹም አይተባበርም፡፡ ቅዱስ ማለት የተለየ ማለት ሲሆን፣ እርሱ ባሕርዩ ስለሆነ ከሰው ውድቀትም በፊት፣ በኋላም ፍጹም ቅዱስ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቅድስና ከኃጢአት ጋር አይገናኝም፤ ነቢዩ ዕንባቆም ስለ እግዚአብሔር ቅድስና በሚገልጥበት ጊዜ እንዲህ ይላል ‹‹ዓይኖችህ ክፉ እንዳያዩ ንጹሐን ናቸው…›› ይላል፡፡ ኢሳይያስም እንዲህ ይላል ‹‹…ለዘላለም የሚኖር ስሙም ቅዱስ የሆነ …›› ሲል፣ (ኢሳ.57፡15) መዝሙረኛውም በመዝሙሩ ‹‹አምላካችን እግዚአብሔር ቅዱስ ነውና›› (መዝ.99፡9)፡፡ በማለት የእግዚአብሔርን ቅዱስ መሆን ያውጃሉ፡፡

ስለዚህ በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ (6፡3) እና በራዕይ መጽሐፍ (4፡8) ላይ የምናያቸው ሱራፌልና እንስሶቹ ‹‹ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ›› እያሉ እንደሚሰግዱለት ሁሉ እኛም እርሱ ቅዱስ እንደሆነ ቅዱሳን እንድንሆን ስለ ተጠራን እንደ እነርሱ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያልን ልንሰግድለት ይገባናል (1ኛ.ጴጥ.1፡15-16)፡፡ ሰው የሚቀደሰው በጌታ በራሱ፣ በመንፈስ ቅዱስና በቃሉ ቢሆንም፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ እግዚአብሔር ቅዱስ እንደ ሆነ ቅዱሳን ሁኑ ብሎ በሚናገርበት ጊዜ፤ ለሰው  ቅድስና ማለት ከኃጢአት ወይም ከክፉ ሥራ መለየት/መራቅ ብቻ ሳይሆን፤ ጽድቅንና በጎ ምግባርን የማድረግ የድርጊት ቅድስናንም ይጨምራል፡፡ (ዮሐ.17፡17-19፣ 1ኛ ቆሮ. 6፡11)

3.3 ኃያል ነው፡- እግዚአብሔር መንፈስና ቅዱስ ብቻ ሳይሆን ኃያልም ነው፤ ስለ እግዚአብሔር ኃያልነት እኛ ልንገልጸው ከምንችለው በላይ በቃሉ ተገልጾ እናገኛለን፡፡ ፍጥረትን በመፍጠር ሰውን ጨምሮ፣ ተፈጥሮን በማዘዝ፣ ሰዎችን በመቆጣጠር፣ በበሽታ ላይና በአጋንንት ላይ ሁሉ ሥልጣን አለው፡፡ ዝናብን በማዝነብ፣ እሳተ ገሞራን ከመሬት በማፍለቅ፣ … እንዲሁም የሰው ልጅ ያልደረሰበትን ታላላቅ ጋላክሲዎቸን፣ ህዋንና በህዋ ውስጥ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ ህልውና እንዲኖረውና በህልውና እንዲቀጥል ያደረገው የእግዚአብሔር ኃይል ነው፡፡ በአጠቃላይ የኃይሉን ታላቅነት የማናይበት ምንም ነገር በዚህኛውም ሆነ በላይኛው ዓለም ምንም የለም፡፡ በሰማይ ያሉ በምድር ያሉ በዓይን የሚታዩና የማይታዩ መናፍስት ሁሉ ይገዙለታል (ኢዮ.36፡5)፡፡ የዘመኑ የዓለም ችግር የሆነው ኮሮና ቫይረስም እንኳን ሳይቀር ይገዛለታል፡፡

በአሁኑ ጥናታችን ስለ እግዚአብሔር ባሕርያት የተመለከትነው፤ እግዚአብሔር መንፈስ፣ ቅዱስና ኃያል መሆኑን ሲሆን፤ በሚቀጥለው ጥናታችን የማይወሰን መሆኑን፣ እውነተኛና ቀናተኛ አምላክ መሆኑን እንመለከታለን፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *