2.1 የእግዚአብሔር መኖር
አስተምህሮተ-እግዚአብሔር በሚለው ዋና ርዕስ ሥር አሰቀድመን የተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ነበር፤ ይህን ርዕስ ያስቀደምኩበት ምክንያት ስለ እግዚአብሔር መኖር፣ ስለ ማንነቱና ሥራው ማወቅ የምንችለው ከተገለጠው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሆነ ነው፡፡ እግዚአብሔር የተገለጠላቸው ሰዎች ታሪክ በቃሉ ባይጻፍ ኖሮ ስለ እግዚአብሔር ማወቅ በፍጹም አይቻልም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ከአስተምህሮተ-እግዚአብሔር በፊት አስተምህሮተ-መጽሐፍ ቅዱስን ማስቀደም ግዴታ ነበር፣ ስለ እግዚአብሔር የበለጠ ለማወቅ ማስረጃዎቹ የሚገኙት በቃሉ ውስጥ ስለ ሆነ፤ በሥሩ የተለያዩ ጥናቶችን ማድረጋችንም የሚታወቅ ነው፡፡
አስተምህሮተ-እግዚአብሔር በሚለው ጥናታችን ሥር ከምናያቸው ትምህርቶች፣ የመጀመሪያውን ክፍል ዛሬ እንጀምራለን፡፡ ዛሬም እግዚአብሔር እንደ ብሉይ ኪዳኑ ራሱን የሚገልጥላቸው ሰዎች አሉ፤ ቢሆንም ሁላችንም እግዚአብሔርን ማወቅ፣ መረዳትና ከእርሱ ጋር ሕብረት ለማድረግ ሊረዳን የሚችለው መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ እግዚአብሔር በቃሉ ስለ ራሱ፣ ፍጥረት፣ ሰው የሚያስተምረውን እንድናውቅ፣ እንድንረዳና ከእርሱ ጋር ሕብረት ማድረግ እንድንችል ቃሉን ሰጥቶናል፡፡ ቃሉን ማወቅና በተረዱትም መሠረት መኖር ሕይወትን ይሰጣል፣ ያንጻል፣ ከስሕተትና ከባዕድ አምልኮም ይጠብቃል፡፡ ጳውሎስም በሮሜ መልእክቱ ምዕራፍ 1፡19 ላይ ‹‹እግዚአብሔር ስለ ገለጠላቸው፣ ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው በእነርሱ ዘንድ ግልጽ ነውና›› በማለት እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጆች ሁሉ ግልጽ ማድረጉን ይናገራል፡፡
ትርጉም፡– ስለ እግዚአብሔር ስናጠና ከትርጉም መነሣት ግዴታችን ነው፤ እግዚአብሔር የሚለው ስም በመሠረታዊ ቋንቋው ምን ማለት እንደ ሆነ ከማየታችን በፊት አስቀድመን በአማርኛችን ያለውን ትርጉም እንመለከታለን፡፡ እግዚአብሔር የሚለው ቃል ከሁለት የግዕዝ ቃል የተገኘ ቃል ነው፤ ‹‹እግዚእ›› ጌታ ማለት ሲሆን ‹‹ብሔር›› ደግሞ ሕዝቦች ማለት ነው፡፡ (ግዕዝ ከአማርኛ በፊት የኢትዮጵያ የመግባቢያ ቋንቋ የነበረ ነው) ስለዚህ በግዕዝ እግዚአብሔር ማለት ‹‹የሕዝቦች ጌታ›› ማለት ነው፡፡ ሁላችንም በቋንቋችን እግዚአብሔርን የምንጠራበት ቃል ሊኖረን ይችላል፡፡ ታዲያ በእርግጥ እግዚአብሔር የሕይወታችን ጌታ ነው?
የእግዚአብሔር ማንነት፡- እግዚአብሔር አለ? ካለስ የት ነው? ምን ይሠራል? ምን ይመስላል? እግዚአብሔር ማነው? የሚለውን ጥያቄ በየዘመናቱ ሰዎች ሁሉ ሲጠይቁት የነበረ ጥያቄ ነው፤ ዛሬም ብዙዎቻችን ይህን ጥያቄ ይዘን እየጠየቅን የምንከራከርና ሀሳቡን ከራሳችን ጋር በመኝታችንም በመንገዳችንም በሥራችንም ቦታ የምናወጣ የምናወርድ አንጠፋም፡፡ ብዙዎችም ለጥያቄአቸው መልስ ሳያገኙ እስከ ወዲያኛው ያሸለቡ፤ አንዳንዶች ደግሞ እግዚአብሔር የለም ብለው፣ በመጨረሻ ሕይወታቸው በሞት አፋፍ ላይ ሲሆን፣ መኖሩን መስክረው አልፈዋል፡፡ እናተስ ይህን የምታነቡ ሁሉ ጥያቄ አላችሁ? ጥያቄ ያላችሁ ለጥያቄአችሁ ከቃሉ መልስ እንድታገኙ በጸሎት በጌታ ፊት ቅረቡ፡፡
ስለ እግዚአብሔር ማንነት ስናጠና፣ እግዚአብሔር ሰውን ሁሉ በመልኩና በአምሳሉ መፍጠሩን ከቃሉ እናገኛለን፤ በፈጠራቸው ሰዎች ዘንድ እንዲታወቅ የሚፈቅድ አምላክ በመሆኑ፣ ለሰው ሁሉ ፈጣሪውን እንዲያውቅበት የሚያስችለውን ሕሊና እንደ ሰጠው ቃሉ ይናገራል፡፡ አንተም ከጠያቂዎቹ አንዱ ብትሆን፣ ምንም ችግር የለም፣ ወደ ቃሉ ቅረብ ራሱን ለአንተም ይገልጥልሃል፡፡ የዘፍጥረት መጽሐፍ ገና ሲጀምር ምዕራፍ 1፡1 ላይ ስለ እግዚአብሔር መኖር በማስረዳት አይጀምርም፡፡ አጀማመሩ ልክ ሁሉም ሰው ስለ እግዚአብሔር መኖር እርግጠኛ እንደ ሆነ አድርጎ ‹‹በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ›› በማለት ይጀምራል፡፡ በዚህ መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን እውነት ሁላችንም ልንቀበለው ይገባናል፡፡ ፈጣሪን በራሳችን ጥረትና ዕውቀት ልናውቀው አንችልም፤ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ራሱ እርሱነቱን በመጀመሪያ ለሰው በመግለጡና ከሰው ጋር ግንኙነት ማድረግ በመጀመሩ፤ እኛም እግዚአብሔርን ማወቅ፣ ለማምለክና ሕብረት ለመፍጠር እንችላለን፡፡
ስለ እግዚአብሔር ማንነት ለማወቅ፤ ሐዋርያው ዮሐንስ በወንጌሉ የሚለውን መመልከት ይኖርብናል፤ ‹‹እግዚአብሔር መንፈስ ነው፣ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል›› በማለት እግዚአብሔር መንፈስ ስለሆነ ማንም ሊያየው፣ ሊቀርበው፣ ሊዳስሰውና ሊጨብጠው እንደማይችል በማስረዳት የማይዳሰስና የማይታይ አምላክ መሆኑን ይናገራል (ዮሐ. 4፡24) ሉቃስ ደግሞ ‹‹አምላክ በሰው ብልሃትና አሳብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ እንዲመስል እናስብ ዘንድ አይገባም›› (የሐዋ.17፡29) በማለት በሚታይ ነገር እግዚአብሔርን መወሰን እንደሌለብን ያሳስበናል፡፡ ሙሴ በጸሎቱ እግዚአብሔር ዘላለማዊ እንደሆነ ሲናገር (መዝ.90፡2)፣ አብርሃም ደግሞ በቤርሳቤህ የዘላለሙን አምላክ እንደ ጠራ እንመለከታለን (ዘፍ.21፡33)፤ በሐዋርያት ሥራ 17፡24 ላይ ‹‹ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም›› ብሎ ከሰው ግምት በላይ የሆነ አምላክ መሆኑን ያሳያል፡፡ ቃሉ በእነዚህ ጥቅሶች ሁሉ ላይ ሲናገር፣ እግዚአብሔር ዘላለማዊ ከአብርሃም በፊት የነበረ፣ ዛሬም ያለ፣ ወደፊትም የሚኖር አምላክ እንደሆነ ያስረዳናል፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ዐይነት አምላክ ቢሆንም ግን የእግዚአብሔርን ማንነትና ባሕርዩን ከተጻፈው ከቃሉ/ ከመጽሐፍ ቅዱስ በማንበብ፣ በማጥናት፣ ለማወቅ፣ ለመረዳትና ሕብረት ወደ ማድረግ ልንመጣ እንችላለን፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በዘፍጥረት ሲጀምር ስለ እግዚአብሔር መኖር ማስረጃ እንደማይሰጥ አይተናል፤ ይሁን እንጂ ጠለቅ ብለን ስናየው በውስጡ ስለ እግዚአብሔር መኖር ማረጋገጫ በመስጠት ሲከራከር እናያለን፡፡ ብሉይ ኪዳን በኢሳይያስ ትንቢት ምዕራፍ 40፡26 ላይ ‹‹ዓይናችሁን ወደ ላይ አንስታችሁ ተመልከቱ እነዚህን የፈጠረ ማነው ሠራዊታቸውን በቁጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፣ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም›› በማለት የእግዚአብሔርን መኖር ለተጠራጠሩት ትውልዶች ያስረዳል፡፡
በአዲስ ኪዳንም በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 14፡17 ላይ ጳውሎስና በርናባስ እንደ አምላክ መሥዋዕት ሊሠዋላቸው በነበረ ጊዜ እንዲህ አሉ፣ ‹‹ከዚህም ሁሉ ጋር መልካም ሥራ እየሠራ ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም›› በማለት ዓይናቸውን ከሰው አንስተው፤ ወደ ትክክለኛው አምላክ እንዲያነሱ አደረጉ፡፡ ከዚህ በላይ ባሉት ጥቅሶች ሁሉ ስንመለከት እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ሁሉ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ በመስጠት ራሱን ያለ ምስክር እንዳልተወ እንመለከታለን፡፡ ስለዚህ ሰው እግዚአብሔርን ማወቅ ቢፈልግ ስለ እግዚአብሔር ማንነት ሁሉን ማወቅ ባይችልም በቃሉ የተገለጠለትን ያህል ብቻ ማወቅ እንደሚችል መረዳት እንችላለን፡፡ አሁንም ጳውሎስ በመልእክቱ እንዲህ ይላል ‹‹በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና›› (1ቆሮ.1፡21) በማለት እግዚአብሔር ራሱን ሲገልጥለት ካልሆነ በስተቀር ሰው በራሱ ጥበብና ዕውቀት እግዚአብሔርን ማወቅ እንደማይችል ያስረዳል፡፡ ስለዚህ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ የእግዚአብሔር ህልውና በተለያየ መልኩና መንገድ ለሚያስተውል ሰው ሁሉ ተገልጦ እናገኘዋለን፡፡ የእግዚአብሔርን መኖርና ማንነት በቃሉ አማካኝነት በእምነት የሚቀበሉ ሰዎች ሁሉ ሌላ ማረጋገጫ አያስፈልጋቸውም፡፡ ቀደም ብለን እንዳየነው የእግዚአብሔር ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር መኖርና ማንነት በሰፊው ስለሚገልጽ ይበልጥ ስለ እርሱ መረዳት፣ ማወቅና ሕብረት መፍጠርና ማምለክ ይቻላል፡፡
0 Comments