4.2 የአዲስ ኪዳን
በአዲስ ኪዳን ያሉትን 27 መጻሕፍት ቤተ ክርስቲያን ቀኖና (መለኪያ) አዘጋጅታ የአዲስ ኪዳንን መጻሕፍት ለመቀበል የተጠቀመችበትንና የሄደችበትን የሂደት መለኪያዎች እንመልከት፡፡ አንድ መጽሐፍ በቀኖና ውስጥ ገብቶ የሚቆጠረው ደራሲው እግዚአብሔር ራሱ ሆኖ ሰው ጽፎት ሲገኝ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የቀኖና መጻሕፍትን ከአዋልድ መጻሕፍት እንዴት እንደለዩና ቀኖና መቼ እንደ ተወሰነ በመቀጠል እንመለከታለን፡፡
በመጀመሪያ በአዲስ ኪዳን አንድ መጽሐፍ ተቀባይነት እንዲያገኝ፣ ከጌታ ሥልጣን የተሰጠው ሐዋርያ ወይም ከሐዋርያ ጋር አብሮ ያገለገለ መሆኑና የፊርማቸው መገኘት እጀግ አስፈላጊ መሥፈርት ነበር፡፡ በሁለተኛ ደረጃ መጽሐፉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት፣ ስለ እግዚአብሔር መገለጥ መናገር የሚችል መሆኑን በማረጋገጥ ሲቀበሉ፤ በሦስተኛ አዲስ ኪዳንን በቀኖናዊነት ለመወሰንና ለመመዝገብ የቤተ ክርስቲያን ውሳኔ አስፈላጊ ነበር፡፡ በአራተኛ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በቀኖና ውስጥ ለመግባት የሚያስችላቸው ሌላው መለኪያ መጻሕፍቱ ሲሰበሰቡ የክርስትና ዋና ማዕከላት (ሥፍራዎች) ከተባሉት ዘንድ መገኘትና ምሥክርነት ማግኘት ነበረባቸው፡፡ የክርስትና እምብርት (ማዕከል) የሚባሉት
ሀ) ኢየሩሳሌም፡- ክርስቶስ ከተወለደባትና አገልግሎት ከጀመረባት፣ ሐዋርያትም በተሰጣቸው ትእዛዝ መሠረት ወንጌልን የማወጅ ተልዕኮአቸውን ከጀመሩባት ከተማ ከኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ነበር፤
ለ) አንጾኪያ፡- ጳውሎስና በርናባስ የመጀመሪያዎቹ ሚስዮናውያን ሆነው አገልግሎት ጀምረው ከተላኩባት ከተማ፤ ከአንደኛው እስከ አራተኛው የወንጌል ጉዞ ካደረጉባት ከአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ነበር፤
ሐ) ሮም፡- ፖፑ (Pope) የቤተ ክርስቲያን አባት የተባለው (የጳጳሳት ሁሉ የበላይ የሆነው) ከሚኖርባት የሮማውያን ዋና ከተማ፣ በ330 ዓ.ም ቆስጠንጢኖስ የተባለው ንጉሥ በክርስቶስ አምኖ ብዙዎችን እንዲያምኑ ካደረገባት ከተማ ነበር፤
መ) ቆስጠንጥኒያ፡- የሮም ንጉሥ የነበረው ቆስጠንጢኖስ ራሱ ክርስትናን ተቀብሎ ዋና ከተማውን ከሮም ወደ ባዛንታይም ባዛወረ ጊዜ ከተማውን በራሱ ስም እንድትጠራ አድርጎ ለምሥራቁ አብያተ ክርስቲያናት የክርስትና እምብርት እንድትሆን ካደረጋት ቤተ ክርስቲያን ነበር፤
ሠ) እስክንድርያ፡- የግብፅ ከተማ ስትሆን መጽሐፍ ቅዱስ ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክ የተተረጎመባት ከተማ ነበረች፡፡ በዚያ ይኖሩ ከነበሩ አይሁዶች፣ ሰባ የአይሁድ ሊቃውንት የተረጐሙት መጽሐፍ ስያሜው ሰብቱጀንት ይባላል፡፡ ይህች ከተማ ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ያፈራች ከነበረች ቤተ ክርስቲያን፤
ረ) ካርቴጅ፡- በሰሜን አፍሪካ የምትገኝ እንደ ተርቱሊያን ያሉ ብዙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያፈራች ቤተ ክርስቲያን ነበረች፡፡ እነዚህ ከተማዎች የሜትሮፖሊያን ጳጳሳት (ከፖፑ ሥር ያሉ ጳጳሳት) የሚኖሩባቸውና በበላይነት ከሥራቸው የሚመሯቸው የአውራጃ ከተማዎች ስለ ነበሩ፣ ተቀባይነታቸው ከፍተኛ ነበር፡፡
ከዚህ በላይ ባየነው መሥፈርት መሠረት፣ ቀደም ባለው ጊዜ እንደ ዕብራውያን፣ ያዕቆብ፣ 2ኛ.ጴጥሮስ፣ ይሁዳና ራዕይ የተባሉት መጻሕፍት በምሥራቁ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተቀባይነት አግኝተው፣ በምዕራቡ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተቀባይነት ሳያገኙ የቆዩት ሁሉ ተቀባይነት አገኙ፡፡ ስለዚህ በውስጣዊና በውጫዊ ይዘታቸው ያዘጋጁትን ቀኖና/መለኪያ በማለፋቸው ምክንያት የእግዚአብሔር ቃል አድርገው ተቀበሏቸው፡፡ ተቀባይነት ያገኙት ከ367 ዓ. ም በተደረገው የሎዶቅያ ጉባኤ ጀምሮ ሲሆን በ397 ዓ.ም በካርቴጅ የተሰበሰበው የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ 27ቱን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ለመጨረሻ ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸውን አረጋግጠው በመቀበል፣ አሁን ባለው ቅደም ተከተል መሠረት እንዲቀመጡ አድርገዋል፡፡
በዚህ መሠረት የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት (ፕሮቴስታንት) 39ኙን የብሉይ ኪዳንና 27ቱን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በመቀበል፤ የእምነታችን መመሪያ 66ቱ ብቻ የእግዚአብሔር ቃል ናቸው ብለው ተቀብለዋል፡፡ እኔም ቤተ ክርስቲያኔም ይህን እውነት ተቀብለን በመጠቀም ላይ እንገኛለን፡፡
0 Comments