1.4 ቀኖና (Canon)

  4.1 የብሉይ ኪዳን

መጽሐፍ ቅዱስ በቀኖና (ካኖን) ያለፈ መጽሐፍ ሲሆን፣ ቄስ ኮሊን ማንሰል ‹‹ቀኖና (Canon) ከግሪክ የተገኘ ቃል ሆኖ ሕግ፣ መለኪያ፣ መገምገሚያ ማለት ነው›› እንግሊዝኛውም ቃል የመጣው ከግሪክ ነው ይላሉ፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍት ቀኖና ማለት ለክርስትና እምነት መመሪያ የሚሆኑትን እስትንፋሰ-እግዚአብሔር ያለባቸውን መጻሕፍት መሰብሰብና መምረጥ ማለት ነው፡፡ (2ጢሞ.3፡16-17) የመጽሐፍ ቅዱስ ቀኖና መደረግ እጅግ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት፣ በእግዚአብሔር ሥልጣን የተሰጡትንና በሰዎች የተጻፉትን ለመለየት እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህም መሠረት እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸው ታውቆ የተለየበት ሂደት ቀኖና (ካኖን) ሲባል፣ የብሉይና የአዲስ ኪዳን ቀኖናበተለያየ ጊዜ  መደረጋቸው የታወቀ ነው፡፡ 

የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በአንድ ጊዜ ከሰማይ የወረዱ ወይም በአንድ ጊዜ የተጻፉ ሳይሆኑ፤ እሥራኤላውያን ካሳለፉት ታሪካቸው ጋር ቁርኝት ያላቸው ጽሑፎች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር በመጀመሪያ የተገለጠውና የሠራው ከእነርሱ ጋር ስለ ነበረ የብሉይ ኪዳኑ ቀኖና የተሠራውም በአይሁዶች በራሳቸው ነበር፡፡ መጻሕፍቱም ከሙሴ ጀምሮ በየዘመናቱ በተነሱና እግዚአብሔር መርጦ በተጠቀመባቸው ሰዎች የተጻፉ ሲሆኑ፣ አይሁዶች ራሳቸው የእግዚአብሔር ቃል የሆኑትንና ያልሆኑትን በመለየት በቀኖና ያለፉትን መጻሕፍት አስቀምጠዋል፡፡ እነዚህ መጻሕፍት በመጀመሪያ በ5 መቶ ዓ.ዓ በጸሐፊው በዕዝራ እንደ ተሰበሰቡ ታሪክ ይጠቁማል፡፡ ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የእግዚአብሔርን ስም ስለማይጠቅስ  ቀኖና ውስጥ ለማስገባት ጥያቄ የነበረበት መጽሐፍ ቢኖር መጽሐፈ አስቴር ብቻ ነበር፡፡ ያም ቢሆን የአይሁድ ሊቃውንት ቀኖና ሠርተው በማስተላለፋቸው፤ ለአዲስ ኪዳን አማኞች ችግሩ የጎላ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ዛሬ አዋልድ ተብለው የሚጠሩት መጻሕፍት በዕዝራ ዘመን አልተጻፉም፤ እንዲሁም በዕብራይስጡ ትርጉም ውስጥ በጭራሽ አይገኙም ነበር፡፡ በአዲስ ኪዳን ወደ ቤተ ክርስቲያን ዘመን ስንመጣ በብሉይ ኪዳን ላይ ሌላ ቀኖና መሥራት አላስፈለጋትም፤ እንዳለ የተቀበለቻቸው ቢሆንም፣ የአይሁዶችና የክርስቲያኖች የመጻሕፍቱ አቀማመጥ ግን ይለያያል፡፡

አዋልድ ማለት ምን ማለት ነው? ብለን ብንጠይቅ፣ አዋልድ ማለት እግዚአብሔር ምንም ነቢያት ባላስነሳበት በአራት መቶ የጸጥታው (ዝምታ) ዘመን ጊዜ የተጻፉ የእግዚአብሔር መንፈስ የሌለባቸውን ጽሑፎች ያመለክታል፤ የሚለውን መልስ እናገኛለን፡፡ የመጨረሻው የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ትንቢተ ሚልክያስ ሲሆን፣ የተጻፈውም በ435 ዓ.ዓ አካባቢ እንደሆነ ብዙ ሊቃውንት ይስማማሉ፡፡ አይሁዶች ከነቢዩ ሚልክያስ በኋላ እንደ ብሉይ ኪዳን ነቢያት የሚቆጠር በሥልጣን የሚናገር ነቢይ እንደ ተነሣ ዕውቅና አይሰጡም፡፡ እነዚህን የአዋልድ መጻሕፍት ግን መጻፍ የጀመሩት በ200 ዓ.ዓ አካባቢ ጀምሮ ስለ ነበር፤ የአዋልድ መጻሕፍት ከእውነተኞቹ የእግዚአብሔር ቃል ተብለው ከተለዩት ጋር ተመሳስለው በመገኘታቸው ለአዲሱ ትውልድ የሚያደናግሩ ሆነው ተገኙ፡፡

በአራተኛው ክፍለ ዘመን የቤተ ክርስቲያን አገልጋይና ቃሉን ከዕብራይስጥ ወደ ላቲን ቋንቋ ተርጓሚ የነበረው፤ ጄሮም ራሱ እነዚህ መጻሕፍት አማኞችን የሚጠቅሙ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት እንጂ የቀኖና መጻሕፍት ስላልመሆናቸው ቢናገርም፤ ቮልጌት በተባለው የላቲን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም (በ404ዓ.ም በተጠናቀቀው) ውስጥ እንዲካተቱ በመደረጉ፣ በቀኖና ውስጥ እንዲጨመሩ አበረታቶአል፡፡ ቢሆንም ግን በዕብራይስጡና በአዲስ ኪዳን ትርጉም ውስጥ ያለ መጠቀሳቸው በአብዛኛው ሊቃውንት ዘንድ ተቀባይነታቸውንና ሥልጣናቸውን አጥተዋል፡፡

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በ1546 እ.ኤ.አ በትሬንት ከተማ በካሄደችው ጉባኤ ላይ የአዋልድን መጻሕፍት ቀኖናውያት አድርጋ ተቀብላለች፤ በዚህም ውሳኔ ቤተ ክርስቲያን የሥነ ጽሑፍ ውጤቶችን ቅዱስ መጽሐፍ አድርጋ የመቀበል ሥልጣን አላት የሚለውን አቋማቸውን በመያዝ፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በአቋማቸው ጸንተው ቆይተዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን (ፕሮቴስታንት) የአዋልድን መጻሕፍት በቅዱሳት መጻሕፍት ተርታ የማታካትትባቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉዋት፡፡ የመጀመሪያው የአዋልድ መጻሕፍት ጸሐፊዎች እንደ ብሉይ ኪዳኑ ጸሐፊዎች ሕግ ሰጪ፣ ነቢይና የእሥራኤል መሪ መሆናቸውንና ሥልጣን እንዳላቸው የሚያሳይና የሚናገር ምንም ማስረጃ ባለ ማግኘታቸው፤ በሁለተኛ አይሁዶች ራሳቸው እንደ እግዚአብሔር ቃል አድርገው ምንም ሥፍራ ባለ መስጠታቸው፤ በሦስተኛ ኢየሱስም በምድር በነበረው አገልግሎቱ ጊዜ ከእነዚህ መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል እንደሆኑ ምንም ባለ መጥቀሱ፤ በአራተኛ  የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎችም የእግዚአብሔር መገለጥ በጽሑፎቹ ውስጥ እንዳለባቸው በጽሑፋቸው ምንም ማስረጃ ባለ ማግኘታቸውና እንዲሁም ዝርዝር ውስጥም ባለ ማስገባታቸው፤ አምስተኛ የአዋልድ መጻሕፍት ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የሚጣረሱ ብዙ ሀሳቦች በመያዛቸውና በመጨረሻም እነዚህ መጻሕፍት በአብዛኛው ጊዜ የተጻፉጽት በ400 መቶ የጸጥታው ዘመን ስለሆነ፣ ይህ ጊዜ ደግሞ እግዚአብሔር ነቢያቱን ልኮ መናገር ያቆመበት ጊዜ ስለ ነበር፣ መጻሕፍቱ ተቀባይነት አጥተዋል፡፡ 

በዚህ ምክንያት ከነብዩ ሚልክያስ በኋላ የተጻፉ የአዋልድ መጻሕፍት በሙሉ በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት (ፕሮቴስታንት) ዘንድ ተቀባይነት አላገኙም፡፡ እኔም ቤተ ክርስቲያኔም የምንቀበለው 66ቱን መጻሕፍት ብቻ ነው፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *