1. 3 የቃሉ መገለጥ

 3.1መገለጥ ምንድን ነው ? 

 መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር መገለጥ ቢሆንም፣ ወንድም ምኒልክ እንዲህ ይላሉ ‹‹መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ቋንቋ የተጻፈ የእግዚአብሔር ሥልጣናዊ ቃል ነው›› ትርጉሙንም እንዲህ አስቀምጠውታል ‹‹መገለጥ መከሰት፣ መታወቅ፣ መታየት፣ በዚሁም መገኘት ማለት ነው›› (መጽሐፍ ቅዱስና የትርጓሜ ስልቱ ምኒልክ አስፋው ገጽ 51፣ 53) እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጆች ሲያሳውቅ፣ ባደረገው መገለጥ አማካኝነት፣ ቃል ኪዳን/ ስምምነት እንዳደረገ ቀደም ብለን ተመልክተናል፡፡ መገለጥ የሚለው ቃል በዚህ ዘመን ትርጉሙን እያጣ በመምጣቱ ብዙ ችግሮች ተፈጥረዋል፡፡ መገለጥ የሚለው ቃል በእንገሊዝኛው (Revelation) ማለት ሲሆን፣ የተሸፈነን ነገር መግለጥ ወይም የተደበቀውን ነገር ገሃድ ማድረግ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጆች  ሲገልጥ ወይም ሲያሳውቅ መገለጥ (Revelation) ይባላል፡፡ እግዚአብሔር ራሱን በተለያየ መንገድና ጊዜ ገልጾአል፡፡ እግዚአብሔር ለአዳም፣ ለአብርሃም፣ ለኖህ፣ ለንጉሥ ሳዖል፣ ለኤልያስ፣ ለኤልሳዕና ለሌሎችም ተገልጧል፤ ነገር ግን  የተገለጠላቸውን ሁሉ በጽሑፍ ባያሰፍሩልንም በእነርሱ ሕይወትና ተግባር አማካኝነት ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚገባውን ብቻ ማወቅ ችለናል፡፡

እንደ ሙሴ፣ ሳሙኤል፣ ዳዊት፣ ኢሳይያስ፣ ዳንኤልና ሌሎችም እግዚአብሔር የገለጠላቸውን እውነት በጽሑፍ ስላሰፈሩት ከትውልድ ወደ ትውልድ ተላልፎ፤ ዛሬ በእጃችን አግኝተን ልናነበውና ልንጠቀምበት ችለናል፡፡ በተለይ ሙሴ ስላልነበረበት የሁለት ሺህ ዘመን ታሪክ በሚጽፍበት ጊዜ፣ አንዳንዶች በእርሱ ዘመን ስነ ጽሑፍ አልነበረምና አልጻፈውም ብለው መከራከር ቢፈልጉም፣ የአርኪዎሎጂ የምድር የጥናት ምርመራ ሳይቀር፣ በሙሴ ዘመን ጽሑፍ እንደ ነበረ አረጋግጠዋል፤ ስለዚህ ቃሉን የጻፈው እግዚአብሔር በገለጠለት መገለጥ እንደሆነ ይታመናል፡፡ የእግዚአብሔር ሰዎች በመገለጥ ጻፉት ብለን ስንናገር፣ በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት የእግዚአብሔርን ሀሳብ (እውነት) በራሳቸው ስብዕና(ማንነት) በአእምሮአቸው በመረዳት በራሳቸው ባሕልና ቋንቋ መሠረት ጽፈውታል ማለታችን ነው፡፡ ስለ መገለጥ ወደ አስተምህሮተ እግዚአብሔር ስንደርስ በስፋት እንመለከተዋለን፡፡ አሁን በዚህ ሥፍራ ትኩረት የምንሰጠው የእግዚአብሔር ቃል በመገለጥ አማካኝነት እንዴት ወደ ሰው ልጆች እንደ ደረሰ ማየት ብቻ ይሆናል፡፡

 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት (Scripture) ተብሎ የሚጠራው በግሪኩ ‹‹ግራፌ›› ‹‹graphe›› ሲባል የሚያመለክተውም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ነው፡፡ ቃሉ በነጠላም በብዙም መጽሐፍ ወይም ቅዱሳት መጻሕፍት ተብሎ ተጠቅሷል፡፡ በአዲስ ኪዳን ወደ 51 ጊዜ ሲጠቀስ፣ በሙሉ የሚናገሩት ስለ ብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሲሆን፤ በተለይ በ2ጴጥ.3፡16 ላይ የምናገኘው ስለ አዲስ ኪዳን መጻሕፍት ይናገራል፡፡ መጽሐፍ ለሚለው የሚከተሉትን ጥቅሶች ይመልከቱ፡፡ (ማር.12፡10፣ ሉቃ.4፡21፣ ዮሐ.2፡22፣ 7፡38፣ 10፡35፣ 2ጴጥ.1፡20፤) ቅዱሳት መጻሕፍት ለሚለው ደግሞ የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡፡ (ማቴ.22፡29፣ ሉቃ.24፡27፣ ዮሐ.5፡39፣ የሐዋ.17፡11፣ ሮሜ.1፡2፣ 2ጢሞ. 3፡15፣)

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል እየተባለ ይጠራል፣ ምክንያቱም ምንጩ ራሱ ስለሆነ ነው፡፡ እግዚአብሔር  በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ቅርብ እንደ ሆነ ገልጦአል፡፡ ቃሉ የእግዚአብሔር ስለ መሆኑ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተሻለ ማረጋገጫ መስጠት አይቻልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ልዩ መገለጥ ለሰው ልጆች ሁሉ የሚያስረዳና የሚያስተምር መጽሐፍ ስለሆነ የእግዚአብሔር ቃል ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ጥቅሶቹን በሚገባ ያንብቧቸው፡፡ (ማቴ.15፡6፣ ሮሜ.10፡17፣ 2ቆሮ.2፡17፣ 1ተሰ.2፡13፣ ዕብ.4፡12.)

 3.2እስትንፋሰ እግዚአብሔር(Inspiration) ምንድን ነው ?

መገለጥ እግዚአብሔር ራሱ ተናግሮ፤ ራሱን ለሰው ልጆች ያሳወቀበት መንገድ እንደሆነ ቀደም ብለን ተመልክተናል፡፡ የእግዚአብሔር ሰዎች ተገለጠላቸውን መገለጥ፤ ቃሎች፣ እውነቶች ወይም ሀሳቦች በጽሑፍ አስፍረውት ሲገኝ እስትንፋሰ-እግዚአብሔር (Inspiration) ይባላል፡፡ በ2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡16 ላይ የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይህን ጽሑፍ፣  ‹‹የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ›› ሲለው፣ የግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ‹‹በእግዚአብሔር የተተነፈሱ መጻሕፍት ሁሉ›› ይለዋል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች እግዚአብሔር ተቆጣጥሮአቸው፣ መጽሐፍ ቅዱስን/ ቃሉን ያለ ምንም ስሕተት መጻፍ እንዲችሉ በመንፈሱ አእምሮአቸውን፣ ፈቃዳቸውን፣ ስሜታቸውንና አስተሳሰባቸውን በበላይነት ተቆጣጥሮ፤ ጸሐፊዎቹ የራሳቸውን የአጻጻፍ ስልት ተጠቅመው፤ በመንፈስ ቅዱስ የተጻፈ ሂደት ስለሆነ ከስሕተት ነፃ የሆነ ሕያው ቃል ነው፡፡ ሕያው ቃልም ስለሆነ እስከ ዛሬ ድረስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል፡፡ የእኛንም ሕይወት ለውጦ ስለ አየን፣ እኔም፣ እናንተም ሁላችንም ምስክሮች ነን፡፡  

 3.3 አብርሆት (Illumination) ምንድን ነው ?

መገለጥና እስትንፋሰ-እግዚአብሔር በእግዚአብሔር በራሱ ለተመረጡና ለተወሰኑ ሰዎች የተሰጡ መሆናቸውን፣ ቀደም ብለን  ባየነው ክፍል ተመልክተናል፡፡ እግዚአብሔር ራሱን ገልጦ የተናገራቸው ወይም ያሳያቸው ሰዎች መገለጡን በጽሑፍ ሲያስቀምጡት እስትንፋሰ-እግዚአብሔር (Inspiration) ሲባል፤ በጽሑፍ የተቀመጠውን ሰዎች በሚያነቡበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለውስጠኛው ልባቸው የሚሰጣቸው መገለጥ አብርሆት (Illumination) ተብሎ ይጠራል፡፡ ‹‹መጽሐፍ ቅዱስ ሲሰማ ወይም ሲነበብ እግዚአብሔር አእምሯቸው የተሰወረባቸው ኃጢአተኞች በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈውን ቃል መለኮታዊ ምንጭ፣ እውነተኛ ትርጉም እንዲያስተውሉና የተመሰከረላቸውን እውነት በእምነት እንዲቀበሉ ያስችላቸዋል፡፡›› (ትምህርተ እግዚአብሔር በቄስ ኮሊን ማንሰል ገጽ 160) በዕውቀትና በአብርሆት መካከል ልዩነት መኖሩን ብዙ ሰዎች አይገነዘቡም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ማንኛውም ያልተማረም የተማረም ሰው ማንበብ የሚችል፣ አእምሮ ያለው ሰው ሁሉ ቢያነበው የተወሰነ ዕውቀት ሊያገኝ ይችላል፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠን መረዳት የተለየ አብርሆት ነው የሚሆነው፡፡ በተለይም ኢየሱስን ጌታ አድርገው ተቀብለውና ከጌታ ጋር ሕብረት ያላቸው ክርስቲያኖች፣ በመንፈስ ቅዱስ ተደግፈው ቃሉን ሲያነቡ በሥጋቸው ከሚያውቁት በላይ ሲገለጥላቸው ይህ አብርሆተ-መለኮት ይባላል፡፡ ይህንም አብርሆት (መገለጥ) ክርስቲያኖች ሁሉ በግላችን ልንለማመደው የሚገባ እውነት ነው፡፡ (ዮሐ. 14፡26፣ 16፡12 15) ከሰዎች ሁሉጊዜ ከመጠበቅ ይልቅ ቃሉን ራሳችን በማንበብና በማጥናት ወደ መረዳትና አብርሆት መድረስ ይጠበቅብናል፡፡ ቃሉን ራሳችን በሚገባ ስንረዳው ከብዙ ስሕተትም ልንጠበቅ እንችላለን፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችን በመገለጥና በእስትንፋሰ-እግዚአብሔር ለተመረጡና ለተወሰኑ ሰዎች ተሰጠ፣ እነርሱ በኩል የመጣው ለእኛም ደረሰን፡፡ ዛሬም ልባቸውን ከፍተው በእውነት ወደ እርሱ ለሚቀርቡት ሁሉ፤ ቃሉ በአብርሆት መንገድ ወደ ሰው ልጆች እንደሚመጣ አምናለሁ፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *