መጽሐፍ ቅዱስ የቃል ኪዳን መጽሐፍ ነው፤ ቃል ኪዳኑም በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል የተደረገ ሲሆን፣ ከግለሰቦችና ከሕዝቦች ጋር ያደረገው ስምምነት እንደ ሆነ ከተጻፈው ቃሉ ማግኘትና መረዳት እንችላለን፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የመጣውና የተገለጠው በየጊዜው በሚያድግ መገለጥ (Progressive Revelation) እንደ ሆነ፣ ከሰዎች ጋር ባደረገው ቃል ኪዳን አማካኝነት ማየትና መረዳት ይቻላል፡፡ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ለአብርሃም የገባውን ቃል ኪዳን በኤርምያስ ትንቢት መሠረት እንደገና ከሕዝቡ ጋር አዲስ ኪዳን እንደሚገባ እንዲህ በማለት ይናገራል፤ ‹‹እነሆ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል … ሕጌን በልቦናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል፡፡›› (ኤር.31፡31-33፣ ዕብ.8፡8-12) በማለት መገለጡ ከብሉይ ኪዳን ወደ አዲስ ኪዳን እያደገ መምጣቱን ያሳያል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በየዘመናቱ ከሕዝቡ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን የያዘ መጽሐፍ መሆኑንና ሁለት ክፍሎች እንዳሉትም ቀደም ብዬ ገልጫለሁ፡፡ እነርሱም ብሉይ ኪዳን ከአይሁዶች ጋር በአብርሃም፣ በሙሴና በዳዊት እንዲሁም ከሌሎች ጋር የገባው ቃል ኪዳን ሲሆን፣ በቁጥር 39 መጻሕፍት ይሆናሉ፡፡ ለሙሴ የተሰጠውን ትእዛዝ በዘዳግም ስንመለከት ‹‹እስራኤል ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ ዘንድ እርሱ በመረጠው ስፍራ ሲከማች ይህን ሕግ በእስራኤል ሁሉ ፊት በጆሮው አንብበው፡፡ … በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ ይስሙ አምላካችሁን እግዚአብሔርንም መፍራት ይማሩ›› (ዘዳግም 31፡9-13) በማለት በየዘመናቱ ከሚመጣው ትውልድ ሁሉ ጋር ቃል ኪዳን መግባቱን ይናገራል፡፡ ስለዚህ እስራኤላውያን የቃል ኪዳን ሕዝቦች ተብለው ተጠርተዋል፤ ደግሞም ነበሩ፤ ዛሬም ናቸው፡፡
እግዚአብሔር ከቤተ ክርስቲያን ጋር ደግሞ በክርስቶስ በኩል የገባው ቃል ኪዳን አዲስ ኪዳን በማለት ሲታወቅ፣ የዕብራውያን ጸሐፊ የኤርምያስን ትንቢት በመጥቀስ እንዲህ ይላል ‹‹እነሆ ከእስራሔል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል ይላል ጌታ … ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ በልባቸውም እጽፈዋለሁ …›› (ዕብ. 8፡8-12፣ 9፡16 በማለት የአዲሱን ቃል ኪዳን ለቤተ ክርስቲያን መሰጠት ያመለክታል፡፡ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በቁጥር 27 ሲሆኑ በጠቅላላው ብሉይና አዲስ ኪዳን 66 መጻሕፍት ለሕዝቡ መመሪያ እንዲሆኑ ከእግዚአብሔር ተሰጥተዋል፡፡
እስራኤላውያን ይህን አዲሱን ኪዳን ባይቀበሉትም፤ የሮሜ መጽሐፍ ጸሐፊ ሐዋርያው ጳውሎስ በመልእክቱ ምዕራፍ 11፡፡17-24 ላይ ስለ እስራኤልና አሕዛብ በመልካምና በረሀ ወይራ መስሎ በሚናገርበት ጊዜ፣ ለጊዜው የተጣሉ የመሰሉት እስራኤላውያን ተመልሰው ወደ ግንዳቸው (ቃል ኪዳናቸው) እንደሚገቡ ይናገራል፡፡ በዚህ መሠረት አዲስ ኪዳን የብሉይ ኪዳን ቀጣይ ኪዳንና ያደገ መገለጥ (Progressive Revelation) እንደ ሆነ መረዳት እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር አብርሃምን ለራሱ የመጀመሪያው ሕዝብ አድርጎ ሲጠራውና ቃል ኪዳን ሲገባለት፤ በዘፍጥረት በመጀመሪያው መጽሐፍ ላይ ‹‹በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ›› ብሎ እንደ ተናገረው ማስተዋል ይኖርብናል፡፡ (ዘፍ.12፡3) ሐዋርያው ጳውሎስም በገላትያ መልእክቱ የሚከተለውን እንዲህ በማለት አቅርቦታል፤ ‹‹መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ፡- ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ›› (ገላ.3፡8)፡፡ ብሉይ ኪዳን ስለ ‹‹እግዚአብሔር መንግሥት›› ሲናገር አዲስ ኪዳን ስለ ‹‹ቤተ ክርስቲያን›› ያስተምራል፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ለሕዝቦቹ ቃል ኪዳን የገባበት የቃል ኪዳን መጽሐፍ ነው፡፡ ጳውሎስ በኤፌሶን ላሉ ለአሕዛብ ቅዱሳን በመልእክቱ ሲጽፍላቸው ‹‹ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግርግዳን በሥጋው ያፈረሰ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው›› (ኤፌ. 2፡15-16) በማለት ሕዝቦችን አንድ በማድረግ የሠራውን የቃል ኪዳኑን ዕድገት ያመለክተናል፡፡ ወንድሜና እህቴ ሆይ፡- ይህን የቃል ኪዳን መጽሐፍ (መጽሐፍ ቅዱስ) ታነባላችሁ? በቃሉ አማካኝነት ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት ፈጥራችኋል? የሕይወታችሁ መመሪያ አድርጋችሁታል? ይህን እርምጃ ያልወሰዳችሁ አሁኑኑ ጊዜ ሳታባክኑ፣ እርምጃ ውሰዱ፡፡ እርምጃ የወሰዳችሁ ጌታ የምትመሩበት መመሪያ ስለ ሰጣችሁ አመስግኑት፤ ሰላም ይብዛላችሁ፡፡
0 Comments