ሀ) አስተምህሮተ እግዚአብሔር
መግቢያ፡- በዚህ አስተምህሮተ እግዚአብሔር በሚለው ርዕስ ሥር አስቀድመን የምናጠናው፤ ስለ አስተምህሮተ መጽሐፍ ቅዱስ ይሆናል፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር መገለጥ (Revelation) የሚገልጽና የሚያስረዳ መጽሐፍ በመሆኑ ነው፡፡ እግዚአብሔር ራሱ በመንፈስ ቅዱስና በሰዎች ሆኖ የተናገረው የራሱ ቃል ስለ ሆነ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ በላይ ስለ እግዚአብሔር ሊያስረዳን የሚችል ምንም ነገር የለም፡፡ በእግዚአብሔር (መንፈስ ቅዱስ) ደራሲነትና በሰዎች ጸሐፊነት የተዘጋጀውን መለኮታዊ መጽሐፍ ነው የምናጠናው፡፡ እግዚአብሔርን በሚገባ ለማወቅ ከተፈለገ ራሱን ከገለጠበት መንገድ አንዱ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና በማጥናት ማወቅና መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያዘጋጀውን የማዳን ዓላማውን፣ ፍቅሩን የሚያሳይና ከዘላለም ሞት የሚዋጅበትን አስደናቂ እቅዱንና የሰውን የመጨረሻ መዳረሻ የሚገልጽና የያዘ በመሆኑ፡፡
ይህን የራሱን የመገለጥ ቃል በማንበብና በመረዳት ወደ መዳን እንመጣ ዘንድ እግዚአብሔር ራሱ መጽሐፍ ቅዱስን በታሪክ ሂደት ውስጥ ለሰው ልጅ ሰጥቷል፡፡ እግዚአብሔር ራሱን በቃሉ ባይገልጽልን ኖሮ፣ በተፈጥሮ በምናገኘው መገለጥና በራሳችን ጥረት በምናደርገው ምርመራ ፈጽሞ ልናውቀውና ልንረዳው አንችልም ነበር፡፡ እግዚአብሔርን የበለጠ ለማወቅና ለማምለክ ረጋ ብለን፣ መጽሐፍ ቅዱስን ብናነብና ብናጠና፣ እግዚአብሔር ማን እንደሆነ፣ እኛ ከየት እንደመጣን፣ ወዴት እንደምንሄድ ላለን ጥያቄ ሁሉ መልስ ሊሆነን ይችላል፡፡ ዛሬም ምን ማድረግ እንዳለብን ቃሉ ለመንፈሳዊ የሕይወት ጉዟችን መመሪያ ካርታ፣ በጨለማው ዓለም ለምንጓዝበት መንገዳችን ብርሃን፣ በምድር ስንኖር ለሚገጥመን ፈተና ሁሉ፣ መውጫውን ሊያሳየንና ድልን ሊያስገኝልን የሚችል የጦር ዕቃችን ነው፡፡
ሃይማኖቶች ሁሉ የእምነታቸው መሠረትና የሥልጣናቸው ምንጭ የሆነ የራሳቸው መጽሐፍ ይኖራቸዋል፡፡ በክርስቶስ ለሚያምን ክርስቲያን አማኝ ሁሉ፣ የመጨረሻው የሥልጣን ምንጫቸው አድርገው የሚቀበሉት መጽሐፍ ቅዱስን ነው፡፡ ምክንያቱም ቃሉ ሰዎች እንደሚሉት የሰው ወይም አንድ አገር ሌሎችን በቅኝ አገዛዝ ሥር አድርጋ ለመግዛት ያወጣችው መመሪያ ሳይሆን፤ የእግዚአብሔር መለኮታዊ መገለጥ ነው፡፡ ስለዚህ አስተምህሮቶቻችን፣ ልምምዶቻችን ሁሉ በዚህ መለኮታዊ ሥልጣን ባለው መጽሐፍ መመሥረትና መቃኘት ይኖርባቸዋል፡፡
- መድሀፍ ቅዱስ
ቀደም ብዬ ጥናታችንን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደምንጀምር የተናገርኩት፤ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው የአማርኛው ቃል፣ በእንግሊዝኛ አጠራር ባይብል (Bible) ሲባል ከግሪኩ ቢብሎስ (Biblos) ተብሎ ከሚጠራው ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም ‹‹ጥቅልል›› ወይም ‹‹መጽሐፍ›› ማለት ነው፡፡ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 4፡17 ላይ እንዲህ ይላል ‹‹ የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት፣ መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው…›› ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ እንዳገኘ ይናገራል፡፡ በዚህም ጥቅስ ውስጥ ‹‹በተረተረ ጊዜ›› የሚለው ቃል በብሉይ ኪዳን ጊዜ የሚጠቀሙበት መጽሐፍ ጥቅልል እንደ ነበረና የተጠቀለለውን ያንን መጽሐፍ እንደ ከፈተው ያመለክተናል፡፡ቃሉ በተለያየ መልክ እየተጻፈ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ፤ እኛ ዘመን ድረስ ደርሷል፡፡
ወደፊት በምናጠናው ጥናት መጽሐፍ ቅዱስ በሁለት ታላላቅ ክፍሎች ብሉይና አዲስ ኪዳን ተብሎ መከፈሉን በስፋት እንመለከታለን፡፡ በዚህም መሠረት የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፣ ብሉይ ኪዳን የተሠጠው ለአይሁዶች እንደሆነ የሮሜ መልእክት ጸሐፊ ሐዋርያው ጳውሎስ በምዕራፍ 3፡2 ላይ እንዳስቀመጠው ግልጽ ያደርግልናል፡፡ ‹‹አስቀድሞ የእግዚአብሔር ቃላት አደራ ተሰጡአቸው›› ይላል፡፡ (ማር.12፡26) እነርሱም በነቢያት አማካኝነት ከእግዚአብሔር ያገኙትን መገለጥ በመጠበቅና ከትውልድ ወደ ትውልድ በመንፈስ ቅዱስ እገዛ ማስተላለፍ በመቻላቸው ቃሉ ወደ ዘመናችን ሊደርስ ችሎአል፡፡ ወደ አዲስ ኪዳንም ስንመጣ ሐዋርያት በክርስቶስ በኩል የመጣውን ቃልና በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የመጣላቸውን መገለጥ በጽሑፍ አስፍረው በማቆየታቸው፣ የቃሉ መገለጥ ወደ እኛም ሊደርስ ችሎአል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ ዘመናትን አቋርጦ፤ ወደ እኛ ዘመን በመድረሱ ዕድለኞች ነን፡፡ ስለዚህ ሙሴ በዘዳግም ለሕዝቡ ‹‹… ለልጆችህም አስተምረው፣ በቤትህም ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም፣ ስትነሳም ተጫወተው›› (ዘዳግም 4፡6-7) እንዳለው በቃሉ ሁሉጊዜ ተጠቃሚዎች መሆን አለብን፡፡ ምክንያቱም ዛሬ ከወረቀትም አልፎ በስማርት ስልኮቻችን ሁሉ ቃሉ ስለ ቀረበልን፣ ቃሉን የማግኘት ችግር የለብንም፡፡ ስለዚህ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ይነበብ፣ ይሰበክ፣ ይሠራጭ፤ ለሚቀበሉት ሕይወት ሲሆን ለማይቀበሉት ደግሞ ፍርድ ይሆንባቸዋል፡፡ እኛም ቃሉን በማንበብና በማጥናት ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ፣ ከእርሱም ጋር በመታረቅ ሕይወት፣ ሰላም፣ ዕረፍትና ደስታ እናገኝበታለን፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ሁላችንም ሕይወት አግኝተንበት፣ ተጠቅመንበት፣ ኖረንበትና ጠብቀነው ለሚቀጥለው ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት እንዳለብን እንወቅ፤ እናጥናው፤ እንኑረው፡፡
0 Comments