ክርስታናዊ አስተምህሮን ወይም መሠረታዊ የክርስትና አስተምህሮን (ዶክትሪን) ለመጻፍ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች መጽሐፍ ቅዱስ፣ እግዚአብሔር፣ ክርስቶስ፣ መንፈስ ቅዱስ፣ ድነት፣ ቤተ ክርስቲያን፣ መላእክት፣ የመጨረሻው ዘመን እያሉ ርዕስ ሰጥተውና ከፋፍለው አልጻፉትም፤ ምክንያቱም ጸሐፊዎቹ በየዘመናቱ ለተነሱ ችግሮች የመንፈስ ቅዱስን ድምጽ እየሰሙ መፍትሔ ለመስጠት በጽሑፍ የወሰዱትን ርምጃ ነው፣ በቃሉ ተጽፎ የምናገኘው፡፡

ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትንና ያልተዘረዘሩት ርዕሶች ጨምሮ፣ በአንድ ርዕስ ላይ ተወስነው ቢጽፉ ኖሮ እኛም መሠረታዊ የክርስትና አስተምህሮን ለማወቅ አንቸገርም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት በየዘመናቱ የተነሱ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ በተለይም የቃሉ አስተማሪዎች (የሥነ መለኮት) የሆኑት ክርስቲያናዊ አስተምህሮን ለማዘጋጀት ሁሉም ከፍተኛ ጥረት አድርገው ሠርተው አልፈዋል፤ ወደፊትም የሚሠሩ ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ አሁንም በተለያየ ሥፍራ/ቦታ የተጠቀሱትን ጥቅሶች በአንድነት ሰብስበውና አስማምተው፣ በርዕስ በማስቀመጥ ክርስቲያናዊ አስተምህሮን(ዶክትሪን) ይመሠርታሉ፡፡

 እኔም የመጀመሪያ ዓላማዬ የተለያዩ ጥቅሶችን፣ ስለ አንድ ነገር የሚናገሩትን  በአንድ ላይ በመሰብሰብ፣ እነርሱ እንዳደረጉት በማድረግ፤ መሠረታዊ አስተምህሮን (ትምህርተ-መለኮትን) ማዘጋጀት ነው፡፡ ሁለተኛው ዓላማዬ በዚህ ትምህርት እግዚአብሔርን ማወቅ፣ ለፈቃዱ መታዘዝና እርሱን  ማምለክ እንድንችል መርዳት ነው፡፡ ሦስተኛው እኔ ብቻ ተጠቃሚ ሳልሆን፣ የአሁኑና የሚቀጥለው ትውልድ ጭምር እንዲማርበትና  እንዲያገለግልበት ሠርቼ ማስተላለፍ ነው፡፡

የካቶሊክ፣ የኦርቶዶክስና የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ሁሉም የየራሳቸውን ክርስቲያናዊ አስተምህሮን ቀርጸው በመጠቀም ላይ ይገኛሉ፡፡ እኔም የፕሮቴስታንት እምነት (የጴንጠቆስጤ /ፔንተኮስታል) ተከታይ አማኝ ሆኜ፣ ጌታን ለአርባ አምስት ዓመት በወንጌላዊነት ሳገለግል ቆይቻለሁ፡፡ በእነዚህ ዓመታት  በቤተ ክርስታኔ በቀንና በማታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ኃላፊ በመሆንና በማስተማር፣ እንዲሁም በኢቲሲና በሌሎችም አብያተ ክርስቲያናት በማስተማር  አሳልፌአለሁ፡፡ እነዚህን ያገኘኋቸውን ዕውቀቶች ጌታ በረዳኝና ጸጋውን ባበዛልኝ መጠን፣ በቀረኝ ዘመኔ አካፍዬ ለማለፍ ጥረት እያረኩኝ እገኛለሁ፤ እስከ አሁንም ጌታ እየረዳኝ ነው፡፡

 በእነዚህ ስድስት ዓመታት ሦስት መጻሕፍት፣ በግሌ ለራሴ አንድና ለቤተ ክርስቲያኔ ሁለት መጻሕፍት በመጻፍ አሳልፌአለሁ፡፡ አሁን ደግሞ እግዚአብሔር በር ከፍቶልኝ በዌብ ሳይት ጽሑፎችን እያዘጋጀሁ መላክ ከጀመርኩ ሁለት ዓመት ሆኖኛል፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ተልዕኮው የት ደርሷል?፣ የዕብራውያን መልእክትና የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ የሚሉትን ስለቅ (ፖስት) ሳደርግ ቆይቻለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ‹‹ክርስታናዊ አስተምህሮን ወይም መሠረታዊ የክርስትና አስተምህሮ ›› በሚለው ርዕስ ላይ ትምህርት እንዳዘጋጅና እንድለቅ ብዙዎች በጠየቁኝ መሠረት፣ በቅደም ተከተል ለመልቀቅ ዝግጅት አድርጌ፤  በዚሁ ተልዕኮ በሚለው ድህረ ገጽ ፖስት ማድረግ ጀምሬአለሁ፡፡ ከዚህ በፊት ስትከታተሉ የነበራችሁ፤ ለሌሎችም በማካፈል በዚህ ጥናት ራሳችሁን ጠቅማችሁ፤ ሌሎችንም ጥቀሙበት፤ በማለት እመክራለሁ፡፡

 ይህን ትምህርት የማዘጋጀው፣  የስልታዊ ሥነ-መለኮት ጸሐፊ መ/ቢ ዌይን ግሩደም በመጽሐፋቸው እንዳሉት ‹‹ሥነ-መለኮትን በጥልቀት ማወቅ የሚያስፈልጋቸው መጋቢያንና አስተማሪዎች ብቻ አይደሉም፤ አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን አባላት ጭምር ሥነ-መለኮትን ማጥናትና ማወቅ ይጠበቅባቸዋል›› (ግሩደም ስልታዊ ሥነ-መለኮት ቅጽ 1 ገጽ 13) ብለው እንደጻፉት ዕድሉን አግኝተው ለተማሩ ብቻ ሳይሆን፣ መማር እየፈለጉ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ገብተው ለመማር ዕድሉን ላላገኙ፤ አገልጋዮችና ለምዕመና እንዲጠቅም በማሰብ ያዘጋጀሁት ትምህርት ነው፡፡

በዚህ ምክንያት ወደፊት የአማርኛ ተጨማሪ መጽሐፍት አግኝተው ማንበብና ዕውቀታቸውን ማሳደግ እንዲችሉ፣ አልፎ አልፎ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፤ የምጠቅሳቸው መጻሕፍት ከቄስ ማንሰል (ከሦስቱ )፣ ከግሩደም ስልታዊ ሥነ-መለኮት እና ከራይሪ መሠረታዊ የክርስትና አስተምህሮ መጽሐፍ ይሆናል፡፡

 ስለ መሠረታዊ የክርስትና አስተምህሮ የጻፉ ሰዎች ብዙ ጊዜ ትምህርታቸውን የሚከፍሉት በተለመደ መንገድ ነው፤ እኔ ደግሞ ቄስ ኮሊን ማንሰል ትምህርታቸውን የከፈሉበት መንገድ ትኩረቴን ስለ ሳበኝና ስለ ተስማማኝ፣ ‹‹ክርስቲያናዊ አስተምህሮ›› የሚለውን ጥናቴን ‹‹አስተምህሮተ እግዚአብሔር፣ አስተምህሮተ ክርስቶስ እና አስተምህሮተ መንፈስ ቅዱስ›› ብዬ በመክፈል ሙሉ በሙሉ  የእርሳቸውን ዝርዝር ርዕሶች ሳልከተል የራሴን መንገድ ተከትዬ አቅርቤአለሁ፡፡

ሀ) አስተምህሮተ እግዚአብሔር

  1. አስተምህሮተ መጽሐፍ ቅዱስ
  2. አስተምህሮተ እግዚአብሔር
  3. አስተምህሮተ መላእክት

ለ) አስተምህሮተ ክርስቶስ

  1. አስተምህሮተ ሰው
  2. አስተምህሮተ ስብዕና
  3. አስተምህሮተ መለኮት

ሐ) አስተምህሮተ መንፈስ ቅዱስ

  1. አስተምህሮተ መንፈስ ቅዱስ
  2. አስተምህሮተ ድነት/ደህንነት
  3. አስተምህሮተ ቤተ ክርስቲያን
  4. አስተምህሮተ ፍጻሜ/የመጨረሻው ዘመን የሚሉት ርዕሶች ናቸው፡፡

 ከዚህ በላይ ያየናቸውን ርዕሶች አንድ በአንድ በዝርዝር እንደ ቅደም ተከተላቸው እናጠናቸዋለን፤ እናንተም መጽሐፍ ቅዱሳችሁን በማውጣት የተሰጡትን ጥቅሶች በግላችሁ እያያችሁ ቃሉ የሚለውን በሚገባ ማጥናት ይኖርባችኋል፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *