አብርሃም ልጁን እንዲሠዋ በእግዚአብሔር መታዘዙን ከሕይወታችሁ ጋር አዛምዱት? በተግባር ግለጡት? የሚለውን ይህን አንድ ክፍል ወስደን በተማርነው መሠረት እየተመለከትን፣ እየተረጐምን ከሕይወታችን ጋር አዛምደን ተግባራዊ ለማድረግ በምትጀምሩበት ጊዜ ቀላል ሆኖ አገኛችሁት?፡፡ ዘፍጥረት ምዕራፍ 22 ቁጥር 2 ላይ ‹‹ … የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያም ምድር ሂድ፤ እኔም በምነግርህ በአንድ ተራራ ላይ መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው አለ›› የሚለውን ቃል ወስደን በተማርናቸው መንገዶች ሁሉ በማጥናት ለራሳችን ትምህርት ወስደንበት ተግባራዊ እንድናደርገው ነበር፡፡
ይህን የአብርሃምን ታሪክና ሌሎችንም በመጨመር፣ በጥናታችን/በትምህርታችን መጀመሪያ በመግቢያው ላይ ‹የአብርሃምን ልጁን ለመሠዋት መዘጋጀት፣ በሕይወታችሁ እንዴት ትተገብሩታላችሁ? ብዬ ጠይቄ ነበር፡፡ በጊዜው ምንም ትኩረት ሳትሠጡት አንብባችሁ ብቻ አልፋችሁት ይሆናል፡፡ አሁን እንደገና ትኩረት እንድትሰጡት በፊታችሁ ቀርቦ ነበር፡፡ አሁን አብረን ክፍሉን በመመልከት፣ በመተርጐምና በሕይወታችን የምናዛምድበትንና ተግባራዊ የምናደርግበት መንገድ እንፈልግ፡፡
በሰባቱ የመጠየቂያ ቃላት ተጠቅመን እየጠየቅን፣ ለምንጠይቀው ጥያቄ መልስ እንስጥ፡፡ ማን ጻፈው? ሙሴ፣ ማን ተናገረው? እግዚአብሔር፣ በየት ተናገረው? በቤርሳቤህ፣ መቼ ተናገረው? ከአቤሜሌክ (የጌራራ ንጉሥ) ጋር ቃል ኪዳን ካደረጉ በኋላ፣ እንዴት ተናገረው? በድምጽ (ከሰማይ ቁ.15)፣ ለምን ተናገረው? ሊፈትነው፣ አብርሃም ምን አደረገ? ልጁን ሊሠዋ ተዘጋጀ፣ ከዚያስ በኋላ? አብርሃም በመታዘዙ ልጁን በሕይወት አገኘው፡፡
በተማርናቸው መሠረት የተለያዩ ምልከታዎች የምናገኛቸው ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉና እንመልከት፡፡ በዚህ ጥቅስ ውስጥ ልናያቸው የሚገቡ ብዙ ምልከታዎች ቢኖሩም፣ እንደ ዋና አድረገን ልናየው የሚገባን ቢኖር ‹አድርግ (ሠዋ)› የሚል ትዕዛዝ እናገኛለን፡ ወደ ሐሳቡ መዋቅር ስንመጣ ብዙ የምናወጣው ነገር ቢኖርም፣ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባው ‹የምትወደውን› እና ‹አንድያ ልጅህን› የሚሉት ‹ቅጽሎች› ላይ ይሆናል፡፡ መጽሐፉ በቅርጹ በሕግ መጻሕፍት ውስጥ የሚመደብ፣ ሲሆን በይዘቱ ትረካ ነው፡፡
ወደ መተርጐም ስንመጣ ቃላቶቹ፣ ሰዋስው፣ ታሪካዊ መሠረቱና ትምህርተ-መለኮቱም ሁሉም ብዙ የሚያስቸግር ነገር የለውም፡፡ ሕግ ከመሰጠቱም በፊትም ሆነ በኋላ በአይሁድ ልጅን መሥዋዕት አድርጎ የማቅረብ ባሕል አልነበራቸውም፡፡ እግዚአብሔር ከሚጠየፈው ነገር አንዱ ነበረ፡፡ እግዚአብሔር የአብርሃምን መታዘዝ ለማየት በዚህ መንገድ ፈተነው፡፡ አብርሃምም የጠራውን አምላኩን በሚገባ ያውቅና ይፈራ ስለ ነበረ ታዞ የተባለውን ለማድረግ ተዘጋጀ፡፡ እግዚአብሔርም መታዘዙን በተመለከተ ጊዜ የመሥዋዕቱን በግ አዘጋጅቶለት፣ ይስሐቅ ከመሠዋት ዳነ፡፡
በመጨረሻ ወደ ማዛመድ እንምጣና ከሕይወታችን ጋር አዛምደን ተግባራዊ እናድርገው፡፡ ብዙ ጊዜ ችግሩ ያለው ማዛመድ ላይ ነው፡፡ ስንቶቻችን ነን ልጆቻችንን መሥዋዕት ለማድረግ አቅርበን የምናውቅ እንኳን ለማቅረብ ቀርቶ ሐሳቡንም ወደ አእምሮአችን አምጥተነውም አናውቅም፡፡ አብርሃም የታዘዘውን ትእዛዝ ሰው ሁሉ መታዘዝና ማድረግ አለበት ማለት አይደለም፡፡ ለዚህ ነው ለዘመናት ሁሉ የሚሆነውን መልእክት (Timeless truth or princples) ማግኘት/ማውጣት ያለብን፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በሚጻፍበት ጊዜ፣ በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን ጊዜ ለአንድ ችግር መፍትሔ ለመስጠት የተጻፈ ነው፡፡ ስለዚህ ለዘመኑ ችግር መፍትሔ እንዲሆን ከተሰጠው ውስጥ መመሪያ ማውጣት አለብን፡፡ በዚህ መንገድ ስንሄድ አብርሃም ልጁን መሥዋዕት እንዲያደርግ እንደ ተጠየቀው፣ ሁላችንም በየዘመናቱ እንደዚያ እንጠየቃለን ማለት አይደለም፡፡ ከዚህ የምንማረው ዋናው ነገር መታዘዙን ነው እንጂ ልጆቻችንን እንደ እርሱ ልንሠዋ እግዚአብሔር አይፈልግብንም፡፡ ከአብርሃም በኋላ እንዲህ ዓይነት ትእዛዝ በቃሉ ውስጥ ለማንም አልጠየቀም፣ ወደፊትም አይጠይቅም፣ ምክንያቱም በሕጉም የተከለከለ ስለ ነበር ነው፡፡ በአዲስ ኪዳንም ልጁን መሥዋዕት አድርጎ ስላቀረበልን፣ አሁን ከእኛ የሚፈለግ መሥዋዕት የለም፡፡ ስለዚህ መጠየቅ ያለብን በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ስላለው ግንኙነት ቃሉ ምን ይናገረናል፣ በተግባር ልንገልጸው የሚገባን ነገር አለ፣ ብለን መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡
አንድን ክፍል ካጠናን በኋላ ልንጠይቃቸው የሚገቡ ጥያቄዎችን መጠየቅ አለብን፡፡ ይህ ክፍል ምን ይላል? (የመመልከት ጥያቄ)፣ ይህ ምን ማለት ነው? (የመተርጐም ጥያቄ)፣ የምንባቡ ዋና ሐሳብ ምንድን ነው? (የማዛመድ ጥያቄ) የማዛመዱን ጥያቄዎች ሠፋ አድርገን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ልታዘዘው የሚገባኝ ትእዛዝ አለ? ጌታ የገባልኝ የተስፋ ቃል አለ? ልከተለው የሚገባኝ ምሳሌ አለ? ላስተካክለው የሚገባኝ ነገር አለ ንስሐ የምገባበት ነገር አለ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ በመቀጠልም ከቤተሰቤ ጋር ከቤቴ ክርስታኔ ጋርና ከህብረተ-ሰቤ ጋር ባለኝ ግንኙነት እንዲሁ ተመሳሳይ ጥያቄዎችን መጠየቅ ይገባናል፡፡
በመጨረሻ በመጀመሪያ ወዳነሣነው ጥያቄ እንመለስና ማጠቃለያ እንስጠው፣ አብርሃም ልጁን መሥዋዕት እንዳደረገ እኛም መሥዋዕት ለማድረግ መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ ዛሬ ከእግዚአብሔር የምናስቀድመው ነገር እንዳይኖር፣ ጌታ ሲጠይቀን እንደ አብርሃም መታዘዝ በሚገባን ጉዳይ ላይ በመታዘዝ መተው (መሥዋዕት ማድረግ) ይገባናል፡፡ ቤተሰብ፣ ሥልጣን፣ ዕውቀት፣ ገንዘብ፣ ዘመድ፣ የመሳሰሉት ሁሉ በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ጣልቃ እንዳይገቡ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር አብርሃምን የጠየቀውን ጥያቄ በየዘመናቱ ላሉ አማኞች ሁሉ ባለ መጠየቁ ስሙ የተመሰገነ ይሁን፡፡ የሚቀጥለው የጥናት ክፍላችን የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 2፡41-52 ሲሆን፣ በመመልከትና በመተርጐም ሂደት አልፋችሁ፣ የምታገኙትን ትምህርት ከሕይወታችሁ ጋር አዛምዱትና በተግባር አውሉት፡፡
0 Comments