የዛሬውን ትምህርት ስለ ሰዋስው ችግር ከማየታችን በፊት፣ ባለፈው ለተጠየቁት ጥያቄዎች የሰጣችሁትን መልስ፣ ዛሬ አብረን በአንድ ክፍል ውስጥ ባንሆንም በአጠገባችሁ ቆሜ እንዳለሁና እንደ ማስተምር አድርጋችሁ ተከታተሉ፡፡
በመጀመሪያ የተሰጡት የቃላት ጥናት በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 17፡17-22 ላይ የሚገኙት ሲሆኑ፣ ኤፊቆሮስና ኢስጦኢኮች የተባሉት በሦስተኛው ምዕተ ዓመት ላይ የተነሡ የግሪክ ፈላስፎች ሲሆኑ፣ ተከታዮቻቸውም በእነዚህ ስሞች ይጠሩ ነበር፤ አርዮስፋጎስ የሚባለውም በአቴና ከተማ የሚገኝ የተራራና የመሰብሰቢያ ሥፍራ ነበረ፡፡ በዚህ ሥፍራ ፈላስፋዎችና የሃይማኖት አስተማሪዎች ተማሪዎቻቸውን ይዘው ለውይይት፣ ለጥያቄና መልስ ለማድረግ፣ አንዱ ሌላውን ሳይቀዋወም ሁሉም ተከታዮቻቸውን የሚያስተምሩበትና የሚያሰለጥኑበት ሥፍራ ነበር፡፡ (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የተዘጋጀ የ1972 ዓ.ም እትም ገጽ 134፣ 150፣ 163 ላይ ተመልከቱ)፡፡
በሁለተኛ የተሰጠው ጥናት በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 4፡1 ላይ መጋቢዎች ለሚለው ቃል ትርጉም እንድትሰጡ ነበር፤ ምን ብላችሁ ተረጐማችሁት:: መጋቢዎች የሚለው ቃል በዘመኑ መጋቢ/ፓስተር ብለን የምንጠራቸውን አገልጋዮች የሚያመለክት አይደለም፡፡ አዲሱ መደበኛው ትርጉም በእንግዚዝኛ ‹Stwardship› የሚለውን ‹ባለ ዐደራዎች› ብሎ በትክክል ተርጉሞታል፡፡ ጳውሎስ በ1ኛ ጢሞቴዎስ ምዕራፍ 1፡4 ላይ መጋቢ የሚለውን ቃል ለፓስተር ሳይሆን የእግዚአብሔርን ሥራ የሚሠሩትን አገልጋዮች ሁሉ የሚያጠቃልል ቃል ነው፡፡ World English Bible ‹ባለ ዐደራ› ብሎ ተርጉሞታል፡፡
በመጨረሻ የተሰጠው ጥናት በኤፌሶን ምዕራፍ 4፡5 ላይ ጥምቀት የሚለው ቃል ምን ትርጉም እንዳለው እንድናይ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስንመለከት ጥምቀት የሚለው አንዱ ቃል ለውኃና ለመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ጥቅም ላይ ውሎ እናገኛለን፡፡ ነገር ግን ዐውዱን ስንመለከት የውኃ ይሁን ወይም የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት በቀላሉ ለመረዳትና ለመለየት እንችላለን፡፡ ለምሳሌ በማቴዎስ ወንጌል 3፡16 ላይ ‹‹ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ … ›› ሲል የውኃ ጥምቅት እንደ ሆነ ግልጽ ነው፤ በ1ኛ ቆሮንቶስ 12፡13 ላይ ‹‹ … እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና … ›› ብሎ ሲናገር በቀላሉ ከዐረፍተ ነገሩ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት እንደ ሆነ መረዳት እንችላለን፡፡
ወደ ተሰጠው ወደ ኤፌሶን ጥናት ስንመጣ ግን የትኛውን ትርጉም እንደሚይዝ በቀላሉ መረዳት አንችልም፤ ስለዚህ የትምህርተ-መለኮት ጥናት ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ትምህርተ-መለኮትን ወደ መተርጐም ስንመጣ በስፋት ትንተናውን ስለምንመለከተው ጠብቁ፡፡ የኤፌሶን 4፡5 መልስ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት የሚለውን ነው የሚያመለክተው፡፡
- የሰዋስው ችግር፡-
በዛሬው ጥናታችን የምንመለከተው ሰዋስውን ስለ መተርጐም ይሆናል፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን በሁለተኛ ደረጃ የሚገጥመን ትልቁ ችግር ሰዋስው ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በግል በምናጠናበት ጊዜ ከሚገጥሙን ችግሮች አንዱ የሰዋስው (ስምንቱ የንግግር ክፍሎች) ስለሆነ በሚገባ ትኩረት ልንሰጠው ያስፈልጋል፡፡ ጸሐፊው ሊያስተላልፍ የፈለገውን እውነት ሊያሳይ የሚችለውን አጠቃላይ ምንባቡን፣ ችግር ከተፈጠረበት ክፍል ጋር እንዴት ሊሄድ እንደሚችል ማጥናት ጠቃሚ ነው፡፡ ሰዋስው በትምህርት ቤት የረሳነው ሀሳብ ቢሆንም እንኳን፣ ቢያንስ መጠነኛ የሰውስው ሕግ እውቀት እንዲኖረን ግድ ይለናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን የበለጠ ለመረዳት ስለሚያስችለን የሰዋስው ክፍሎችን አገባብ ማየት በእጅጉ ተጠቃሚ ያደርገናል፡፡ እነርሱም ስም፣ ተውላጠ ስም፣ ቅጽል፣ ግሥ(ማሠሪያ አንቀጽ)፣ ተውሳከ ግሥ፣ መስተዋድድ፣ መስተፃምርና ቃለ አጋኖ የምንላቸው ናቸው፡፡ ቃላት በሥርዓት የሚቀመጡበትን መንገዶች የሚወስነው የሰዋስው ሕግ ነው፡፡
በሰዋስው ላይ ትኩረት ስናደርግ በተቻለ መጠን የድርጊቱ ባለቤት ማን እንደ ሆነ፣ ድርጊቱ ምን እንደ ሆነ፣ የት፣ መቼ፣ እንዴት እንደ ተፈጸመ የሚጠቁሙን እነዚህ የሰዋስው ክፍሎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ቀለል ያለ ጥቅስ ወስደን እንመልከት፡፡ ኤፌሶን ምዕራፍ 4 ቁጥር 1 ላይ ‹‹ እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ›› ይላል፡፡ በዚህ ጥቅስ ብቻ ተናጋሪው ማን እንደ ሆነ ማወቅ ያስቸግራል፡፡ ማን ተናገረው ብለን ስንጠይቅ ከዐውዱ ምዕራፍ 3፡1 ላይ ጳውሎስ እንደ ሆነ እንረዳለን፡፡ ወይም ‹እለምናችኋለሁ› የሚለውን ግሥ (ማሠሪያ አንቀጽ) በመያዝ፣ ማነው የሚለምነው? ለምን ይለምናል? የሚሉትን ጥያቄዎች ይዘን ስንጠይቅ የድርጊቱን ባለቤትና ምክንያቱን ስናገኝ፣ ዋናውን ድርጊት እንደሚያመለክቱ መረዳት እንችላለን፡፡ ጳውሎስ የአፌሶንን አማኞች ተገቢ የሆነ ክርስቲያናዊ ኑሮ እንዲኖሩ ይለምናቸዋል፡፡ በዚህ ዐረፍተ ነገር ውስጥ ‹‹እስር ሆንሁ›› የሚለው ቃል ጳውሎስ እስረኛ መሆኑን የሚያመለክት ቅጽል ነው፡፡ ሌሎቹንም የንግግር ክፍሎች በየተራ ማየት እንችላለን፡፡
ሰዋስውን በምናጠናበት ጊዜ ከሁሉ በላይ ለተውላጠ ስሞች ለግሦችና ለቅጽሎች ከፍተኛ ትኩረት መስጠት አለብን፡፡ ሰዋስውን በሚገባ ለመረዳት የሚጠቅመን ቨርቲካል ቻርት መሥራት ቢሆንም፣ አሁን በዚህ ጊዜ ስለዚህ ቻርት አሠራር አንመለከትም፣ ነገር ግን ሌሎችን መጽሐፍ አግኝታችሁ እንድታነቡና ስታነቡ አዲስ ነገር እንዳይሆንባችሁ ለማድረግ ብቻ ነው ያነሣሁት፡፡ ቨርቲካል ቻርት መሥራት ማለት ምንባቡን እንደገና በሥርዓት መጻፍ ማለት ነው፣ ከአማርኛው ይልቅ በእንግሊዝኛው መሥራት በጣም ይቀላል፡፡ ስለዚህ የቋንቋው ችሎታው ያላችሁ በሚገባ ተጠቀሙበት፣ በጣም ይረዳችኋል፡፡ በሠላሳ ዓመት አገልግሎቴ በአማርኛው ሰዋስውን ለመረዳት እስከ ዛሬ ጠቃሚ ሆኖ ያገኘሁትና የተረዳሁበት መንገድ ቢኖር፣ ከላይ እንዳየነው እያንዳንዳቸውን ግሦችን (ማሠሪያ አንቀጾችን) ወስደን በሰባቱ የመጠየቂያ ቃላት በመጠየቅ ሁሉንም ካየን በኋላ ወደ ዋናው ሐሳብ መድረስ እንደሚቻል ነው፡፡ ማን? እና ለምን? ብለን የምንጠይቃቸው ጥያቄዎች ዋናውን ሐሳብ ሊያስገኙልን ይችላሉ፡፡
ከዚህ በላይ የተመለከትነው በጥናታችን ጊዜ ሰዋስውን መተርጐም፣ የጥናት ክፍላችንን በሚገባ ለመረዳት እንደሚያስችለን ነው፡፡ አገልጋይ ያልሆናችሁ አሁን የምታገኙት ዕውቀት ለእናንተ በቂ ነው፤ አገልጋይ የሆናችሁ ግን፣ ይህን ሐሳብ የበለጠ የተለያዩ መጻሕፍትን በማንበብ አሳድጉት፤ በአገልግሎታችሁ ብቁ ያደርጋችኋል፡፡
እንደ ተለመደው የሚከተሉትን ጥያቄዎች ሠርተን በሚቀጥለው ጥናታችን በሰላም እንገናኝ፡፡
1. በ1ኛ ዮሐ 4፡8 ‹እግዚአብሔር ፍቅር ነው› በሚለውና ‹ፍቅር እግዚአብሔር ነው› በሚለው መካከል ያለውን ልዩነት አስረዳ
2. በሉቃስ 11፡37 ላይ ‹‹ይህንንም ሲናገር አንድ ፈሪሳዊ ከእርሱ ጋር ምሳ ይበላ ዘንድ ለመነው ገብቶም ተቀመጠ›› ማነው (እርሱ) የገባው? ‹እርሱ› የሚለውን ተውላጠ ስም ተርጉሙት? ወይም ማንን ነው የሚያመለክተው? 3. በዮሐንስ ራዕይ 12፡9 ላይ ‹‹ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ›› ይላል፡፡ መቼ ነው የተጣለው? የግሡን ጊዜያት ገለጽ?
0 Comments