የዛሬውን ትምህርት ስለ ቃላት ችግር ከማየታችን በፊት፣ ባለፈው ለተጠየቁት ጥያቄዎች የሰጣችሁትን መልስ፣ ዛሬ አብረን በአንድ ክፍል ውስጥ ባንሆንም በአጠገባችሁ ቆሜ እንዳለሁና እንደ ማስተምር አድርጋችሁ ተከታተሉ፡፡ 

የመጀመሪያው ጥያቄ የተመሠረተው በማቴዎስ ምዕራፍ 5፡21-48 ባለው ክፍል ውስጥ ሲሆን፣ ስድስት የተለያዩ ነገሮችን አንድ ላይ አድርጎ ጸሐፊው የጻፈበትን ዓላማ ለመረዳት የሚደረግ ጥናት ነው፡፡ ይህን ክፍል ካስታወሳችሁ የተደጋገሙ ነገሮች ስናጠና በሚገባ ተመልክተነው ነበር፡፡ ካስታወሳችሁ መልካም ነው፤ ካላስታወሳችሁም ምንም አይደለም ጥናታችንን እንቀጥል፡፡ እነዚህን የማይገናኙ የተለያዩ ነገሮች በማከታተል አስፍሮና አገናኝቶ ያስቀመጣቸው እውነተኛና እውነተኛ ባልሆኑ ሕጎች መካከል ያለውን ልዩነት አጉልቶ ለማሳየት ፈልጎ ነው፡፡ እውነተኛ ባልሆኑና ሰው ሠራሽ ስለ ሆኑት ሕጎች (በሚሽናና በሚድራሽ ላይ የተጻፉ) ሲናገር እንዲህ ይላል ‹‹እንደ ተባለ ሰምታችኋል››፣ በሌላ ሥፍራ ቃሉ ስለ እውነተኛው ሕጎች ሲናገር በሙሴ፣ በመዝሙራትና በነቢያት እንደ ተባለው በማለት ነው የሚጠቅሰው፡፡ ጸሐፊው የተለያዩ የሆኑትን ሐሳቦች በሕግ ሥር አብረው የሚሄዱትን በዓላማ እንጂ፣ ያለ ዓላማ የማይሄዱ ነገሮችን አልጻፈም(አላስቀመጠም)፡፡    

በሁለተኛው የጥናት ክፍላችን የተሰጠው በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 10፡38-42 ላይ የሚገኘው ነበር፤ በዚህ ክፍል ያለውን ስንመለከት፣ በእኛም ሆነ በአይሁድ ባሕል እንግዳ ወደ ቤት ሲመጣ፣ ታላቅ ቁጭ ብሎ ማጫወት፣ ታናሽ ደግሞ የሚጠጣና የሚበላ፣ ቡናና ቁርስ የማዘጋጀት ልማድ አለን፡፡ በእነ ማርታና ማርያም ቤት የተፈጸመውም፣ ይኸው ተግባር ነው፡፡  በእነርሱ ቤት ለየት የሚያደርገው የማርታ እርዳታ መጠየቅ ነው፡፡ ይህን ‹‹… የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው … ›› የሚለውን ክፍል ብዙ ጊዜ ሰባኪዎች ከዐውዱ ለየት ባለ መንገድ ስናቀርበው እንገኛለን፡፡ ይህ አባባል መተርጐም ያለበት ከማርያም አንጻር ነው ወይስ ከጌታ ነው? የሚለውን በሚገባ ዐውዱን ማየት ይኖርብናል፡፡

 በመጀመሪያ ልንጠይቀው የሚገባን ጥያቄ ቢኖር፣ ኢየሱስ ለምን ወደ እነ ማርታና ማርያም ቤት መጣ የሚለውን መሆን አለበት፡፡ ሊያስተምር ነው? የመጣው ወይስ ዕረፍት ፈልጎ ነው? የመጣው የሚለውን ጥያቄ መመለስ ይኖርብናል፡፡ የዚህን ምዕራፍ አስርና ዘጠኝን ዐውድ ስንመለከት፣ 9፡18 ላይ ‹‹ለብቻው ሲጸልይ ነበር››፣ በመቀጠልም ከቁጥር 21-22 ባለው ላይ የሰው ልጅ መከራ እንደሚቀበል፣ በሦስተኛውም ቀን እንደሚነሣ ይናገራል፡፡ አሁንም በመቀጠል ቁጥር 28 ላይ ‹‹ከዚህም ቃል በኋላ ስምንት ቀን ያህል ቆይቶ››፣ ጴጥሮስን፣ ዮሐንስንና ያዕቆብን ይዞ ወደ ተራራ ሊጸልይ በወጣበት በታላቅ ክብር እንደ ተገለጠ ይናገራል፡፡

 በዚያም ጊዜ በቁጥር 31 ላይ እንደምናነበው ሙሴና ኤልያስ በክብር ተገልጠው፣ ‹‹… በኢየሩሳሌም ሊፈጽመው ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር›› ይላል፡፡ ቁጥር 44 ላይም ‹‹የሰው ልጅ በሰው እጅ›› የሚሰጥበት ጊዜ እንደ ቀረበ ይናገራል፤ ቁጥር 51 ላይም ‹‹የሚወጣበትም ወራት በቀረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፊቱን አቀና…›› በማለት ይናገርና በምዕራፍ 10 ቁጥር 38 ላይ ‹‹ሲሄዱም  እርሱ (ጌታ) ወደ አንዲት መንደር ገባ … ›› በማለት ይቀጥላል፡፡

 ከምዕራፍ ዘጠኝ ጅምሮ ሲናገር የነበረው ወደ ኢየሩሳሌም ስለ መውጣቱ፣ ስለ መከራውና ሞቱ እየተናገረ ቆይቶ፣ ወደ ማርታና ማርያም ቤት እንደ መጣ እንመለከታለን፡፡ ወደ ቤታቸው የመጣው ለማስተማር ወይስ ለማረፍ?፣ እናንተ ምን ትላላችሁ?፡፡ አንድ ሰው በተለያየ መከራና ፈተና ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ ችግሩን የሚካፈልለት ሰው ይፈልጋል፤ ኢየሱስም ሰው ስለ ነበረ ወደዚህ የመጣው ለማስተማር ሳይሆን ሲናገረው የነበረውን ሐሳብ ለወዳጆቹ በማካፈል ለማረፍ ነበር፤ በመሰቀል ላይ ሊሸከም ያለውን የመከራ ሐሳብ ለማጋራት ፈልጎ ወደዚህ ቤት ጎራ እንዳለ ግልጽ ነው፡፡

 በዚህ ቤት የተገኘው ለማስተማር ቢሆን ማርታንም ቁጭ በይና ቃሌን ስሚ ማለት ነበረበት፣ ግን አላደረገም፡፡ ማርታ መጥታ እህቴ እንድታግዘኝ ለምን አትነግራትም ባለችው ጊዜ ግን እንዲህ አለ፣ ‹‹ … የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው … ›› ማለቱ እኔ አሁን የሚያስፈልገኝ መብልና መጠጥ ሳይሆን የሚያደምጠኝ፣ ሸክሜን የሚካፈልልኝ ሰው ነው የምፈልገው ማለቱ ነበር፡፡  የጸሐፊውን ዓላማ መረዳት የምንችለው ከጥቅሱ ተነስተን ሳይሆን፣ ከዐውዱ ተነስተን መሆን አለበት፡፡        

በመጨረሻ የተሰጠው ጥናት ሐዋርያው ዮሐንስ በመጀመሪያ መልእክቱ ምዕራፍ 3፡8 ላይ ‹‹ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው›› ብሎ በተናገረው ላይ የተመሠረተ ነበር ፡፡ ይህን ሐሳብ ለመረዳት መጽሐፉን በሙሉ መመልከትና መዳሰስ ይጠይቃል፡፡ ዮሐንስ መልእክቱን ለአማኞች በሚጽፍበት ጊዜ፣ በምዕራፍ አንድ እና ሁለት ላይ ስለ አማኞች ማንነት ብቻቸውን አድርጎ ሲጽፍ፣ ከእግዚአብሔር የተወለደ አማኝ ሁሉ ኃጢአት መሥራት እንደሌለበት ከተናገረ በኋላ፣ ቀጠል አድርጎ ኃጢአት ያደርጋል/ይሠራል፣ ስለ ኃጢአቱም የሚሟገትለት ጠበቃ እንዳለውም ይናገራል፡፡ ከዚህ የምንረዳው አማኝ በማወቅም ሆነ ባለማወቅም ኃጢአት እንደሚሠራ ነው፡፡ ኃጢአቱን ግን ኑዛዜ በማድረግ መታጠብ እንዳለበት ያስተምራል፡፡

 በመቀጠልም ምዕራፍ ሦስት ላይ አማኝንና አማኝ ያልሆነውን ጎን ለጎን በማስቀመጥ በሚናገርበት ጊዜ፣ ከእግዚአብሔር የተወለደ አማኝ ሁሉ ኃጠአት እንደማያደርግ፣ ዳግም ያልተወለደው ሰው ደግሞ ኃጢአት መሥራት ባሕርዩ እንደ ሆነ ያስተምራል፡፡ ስለዚህ ‹‹ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው›› ብሎ ዮሐንስ በሚጽፍበት ጊዜ አማኝ ኃጢአት በሚሠራበት ጊዜ ከዲያብሎስ ነው ለማለት ሳይሆን፣ ያላመነው ኃጢአት በሚሠራበት ጊዜ ከዲያብሎስ ነው ይልና 3፡10 ላይ ‹‹የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው›› በማለት ልዩነታቸውን በግልጽ ያስቀምጣል፡፡

በዚህ የጸሐፊው ዓላማ አማኝ ኃጢአት በሚሠራበት ጊዜ ከዲያብሎስ ነው ለማለት ሳይሆን፣ አማኝ ያልሆኑት ኃጢአት ሲሠሩ ከዲያብሎስ እንደሆኑና በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ስለዚህ የአንድ ጥቅስ ሐሳብ የሚገባን የጸሐፊው ዓላማ በግልጽ ሲገባንና ስንረዳው እንደ ሆነ መረዳት ስንችል እንደ ሆነ ያሳየናል፡፡        

  1. የትርጉም ችግር፡-

በዛሬ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን የምንመለከተው የትርጉም ችግሮችን ይሆናል፤ መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብና ስናጠና፣ በምንባቡ ውስጥ የሚገጥሙን የትርጉም ችግሮች በአስተዋፅኦችን ላይ እንደ ተመለከትነው አራት ናቸው፡፡ እነርሱም የቃላት፣ የሰዋስው፣ የባሕልና የትምህርተ-መለኮት ችግሮች ናቸው፡፡ ስለዚህ እንተረጉማለን ስንል እነዚህን ችግር የሚፈጥሩብንን በሚገባ ለመረዳትና ለመፍታት ጥረት እናደርጋለን ማለታችን ነው፡፡

  1. የቃላት ችግር፡-

በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን በመጀመሪያ የሚገጥመን ችግር የቃላት ነው፤ ቃላት በትክክል ካልገቡን ትርጉማችን የተዛባ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በቃላት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ልናደርግ የሚገባበት ምክንያቱ፣ ‹‹ቃላት የሐሳብ የንግግርና የግንኙነት መገንቢያ ናቸው፡፡ ትርጉም ባለው ሥርዓት የተቀነባበሩ ቃላት የሰው ልጆች ዋና መግባቢያዎች ናቸው፡፡ ከሁሉም ይልቅ እግዚአብሔር ከሰው ጋር ለመገናኘት በአብዛኛው በተለመደ ቋንቋ ነው በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀመው›› (መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ መረዳት በቲ. ኖርተን ስቴሬት፣ ተርጓሚ ተክሉ መንገሻ ገጽ.44)፡፡ ስለዚህ የቃላትን ችግር ለማስወገድ የቃላት ጥናት በማድረግ ከምንባቡ ጋር የሚሄድ ትርጉም መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ጸሐፊው በምንባቡ ውስጥ እንዴት እንደ ተጠቀመበትና ከምንባቡ ሐሳብ ጋር እንዴት እንደሚሄድ በጥንቃቄ ማየት ይኖርብናል፡፡ ትርጉም ያለው (የምናገኘው) ቃላት ውስጥ ስለ ሆነ፣ ከፍተኛ ዋጋ ስለ አላቸው፣ ለቃላት ከፍተኛ ትኩረት ልንሰጥ ይገባናል፡፡ ቃላት ካልገቡን ዋናው ሐሳብም ሊገባን ስለማይችል፣ አስቀድመን ቃላትን መተርጐም ያስፈልገናል፡፡

      ሁለትና ከዚያ በላይ ትርጉም ሊሰጡ የሚችሉ ቃላት ስለ ሚገጥሙን ትኩረት ሰጥቶ ትክክለኛውን ትርጉም ለመረዳት ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ለምሳሌ 1ኛ ቆሮንቶስ 11፡27 ላይ ‹‹ሳይገባው›› የሚለውን ቃል ስንመለከት ሁለት ትርጉም አለው፡፡ ይህም በማጥበቅና በማላላት የሚገኝ ትርጉም ሲሆን፣ የመጀመሪያው ሲጠብቅ ‹‹ተገቢ ሳይሆን›› የሚለውን ሲያስገኝ፣ ሲላላ ደግሞ ‹‹ሳያውቅ›› ማለት ይሆናል፡፡ ከሁለት አንዱ ትክክለኛውን ለማወቅ በዐውዱ መሠረት ተረድቶ መተርጐምና መምረጥ፣ በዚህ መንገድ ወደ መረዳት ካልተመጣ በተለያዩ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ትርጉሞች ማየት፣ አሁንም ትክክለኛውን ሐሳብ መረዳት ካልቻልን፣ በዕብራይስጡና በግሪከኛው ትርጉም ማየት፣ እነዚህን ቋንቋዎች የማንችል ከሆነ ከሚችሉ አስተማሪዎች በመጠየቅ መረዳት ይኖርብናል፡፡

       መጽሐፍ ቅዱስ ስናጠና አንድ ቃል ሁል ጊዜ ተመሳሳይ ትርጉም ላይኖረው ይችላል፣ በተለይም በምሳሌነትና በዘይቤአዊ አነጋገር የተነገሩት ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል፡፡ በራዕይ 5፡5 ላይና በ1ኛ ጴጥሮስ 5፡8 ላይ ‹‹አንበሳ›› የሚለው ቃል መተርጐም ያለበት በዐውዱ መሠረት ሲሆን የትርጉም ልዩነት ያመጣል፤ አንበሳ የሚለው ቃል በራዕይ ክርስቶስን ሲያመለክት በጴጥሮስ ላይ ዲያብሎስን ያመለክታል፡፡

      አንድ ቃል በዘመናት መካከል ትርጉሙን ሊያጣ፣ ሊለውጥና ሊጨምር ይችላል፡፡ በመጀመሪያ በመግቢያችን ላይ በተርጓሚዎችና በአንባቢዎች መካከል ስላለው ለአንድ ቃል በሚሰጡት ትርጉም መለያየት እንዳለ ተመልክተን ነበር፡፡ የተመለከትነውን እንደገና የማነሣው በቀላሉ ቶሎ እንድንረዳው ስለምፈልግ ነው፡፡ ያንን ቃል ራሱን ለዚህ ምሳሌ አድርገን እንመልከት፡፡ ቃሉ ‹‹ተሰቅለዋል›› የሚል ነበር በማቴዎስ 22፡40 ላይ፣ ይህን ቃል ስናነብ ቶሎ የሚመጣልን ትርጉም የመሞት ጉዳይ ነው፣ ነገር ግን በተርጓሚዎቹ ዘንድ ግን ያለው ሐሳብ የመሞት ጉዳይ ሳይሆን መመሥረትን፣ መጠቅለልንና መቀመጥን  የሚያመለክት ነው፡፡

 ስለዚህ ‹‹ሳይገባው›› (ተገቢው ሳይሆን) እንደሚሉት ያሉ ቃላት በሚገባ ሳይገቡን ወደ ትርጉም ድምዳሜ አንምጣ፡፡ ቃላት እንደ ካርታ(ማፕ) የሚመሩን ስለሆነ፣ አስቀድመን በትክክል ልንተረጉማቸው  እንድንችል፣ የቃላት ጥናት ለማድረግ የሚረዱን መጻሕፍት ስላሉ፣ ገዝተንም ሆነ ተውሰን ትርጉማችንን ለማስተካከል በእነርሱ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በነበረን  ጥናት ምን ያህል እንደተጠቀማችሁ ባላውቅም፣ አሁን የሚሰጡትን የቤት ሥራ ጥናቶች በሚገባ ትሠራላችሁ ብዬ አምናለሁ፡፡    

  1.   በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 17፡17-22 ላይ ኤፊቆሮስ፣ ኢስጦኢኮችና አርዮስፋጎስ ለሚሉት ቃላት ትርጉም እንስጥ?  
  2.   በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 4፡1 ላይ መጋቢዎች ለሚለው ቃል ትርጉም ስጡ?

  በኤፌሶን ምዕራፍ 4፡5 ላይ ጥምቀት የሚለው ቃል የትኛውን ትርጉም ነው የሚይዘው? የውኃ ወይስ የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት ነው የሚያመለክተው? ማስረጃ ስጡ፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *