የዛሬውን ትምህርት ስለ መልእክት ከማየታችን በፊት፣ በባለፈው በትንቢት ዙሪያ ለተጠየቁት ጥያቄዎች የምናገኛቸውን መልሶች በአካል ክፍል ውስጥ ሆነን እንዳለ በማሰብ አብረን እንመልከታቸው፡፡

 በመጀመሪያ የተሠጠው ኢሳይያስ ምዕራፍ 7 ቁጥር 14 ላይ የተነገረው ሲሆን፣ የቅርብና የሩቁን ትንቢት ለይታችሁ አውጡ የሚል ነበር፡፡ መልሱም የቅርቡ ትንቢት የኢሳይያስን ሚስት ወንድ ልጅ መውለድን ሲያመለክት፣ የሩቁ ትንቢት የማርያምን ወንድ ልጅ መውለድ ያመለክታል፡፡ ትክክለኛ መ7ልሱን እንዳገኛችሁ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ለማንኛውም ዐውዱን በስፋት እየተመለከትን መልሳችንን እንደገና ማስተካከል እንችላለን፡፡

  ዐውዱን ስንመለከት የምናገኘው መረጃ ይህን ይመስላል፤ በምዕራፉ የመጀመሪያ ቁጥሮች ላይ ስንመለከት የሶርያ ንጉሥ ረአሶን እና የእስራኤልም ንጉሥ ፋቁሔ (የአስሩ ነገዶች) ሁለቱ ንጉሦች ተባብረው፣ የኢየሩሳሌምን ንጉሥ አካዝን (ሁለቱን ነገዶች ይሁዳንና ብንያምን) ሊወጉ እንደወጡ ይናገራል፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሡ አካዝ ሊወጉት የመጡበትን ነገሥታት በማየቱ በጣም ስለ ፈራ፣ የግብፅን ንጉሥ ርዳታ ለመጠየቅ እየተዘጋጀ ሳለ፣ እግዚአብሔር ነብዩ ኢሳይያስን ላከበት፡፡

 ኢሳይያስም መልእክተኛ ሆኖ የተላከው ያሱብ ከተባለው ልጁ ጋር እንደሆነ ቁጥር 3 ላይ ይናገራል፡፡ አካዝም የተላከለትን መልእክት ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም፤ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር እንደገና በኢሳይያስ በኩል ሌላ መልእክት ላከበት፡፡ መልእክቱም በቁጥር 13-14 ላይ እንዲህ ይላል፣ ‹‹…ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፣ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፣ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፣ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች›› የሚለው ሲሆን፣ ዐውዱን ቀጥለን ስንመለከት የእግዚአብሔር ዋና ሐሳብ ለአካዝ፣ እንዲህ የሚል ነበር፡፡ አንተ ምልክት ለመጠየቅ ፈቃደኛ ባትሆንም፣ እኔ ምልክት እሰጥሃለሁ ነው የሚለው፡፡ አንተን ሊወሩ (ለመውጋት) ለመጡት ነገሥታት መጥፋት ምልክቱ ያንተ ሚስት ድንግል (በዕብራየስጥ አልማህ-ያገባች ሴት ማለት ነው) ፀንሳ ወንድ ልጅ መውለዷ ሲሆን፣ ይህ የመጀመሪያው የቅርብ ትንቢት ፍጻሜ ነው፡፡ ለዚህም ፍጻሜ ማረጋገጫ ምዕራፍ 8፡3፣18 ላይ ስንመለከት ኢሳይያስ ‹‹ ወደ ነቢይቱ (ሚስቴ) ቀረብሁ እርስዋም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደች›› ‹‹እነሆ፡- እኔና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች ለእስራኤል በጽዮን ተራራ ከሚኖረው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክትና ተዓምራት ነን›› በማለት ትንቢቱ በዘመኑ ለነበሩት ሰዎች ምልክት ሆኖ እንደ ተፈጸም ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡

 በሁለተኛ ደረጃ ትንቢቱ የሩቅ ፍጻሜ እንዳለው፣ ማቴዎስ በወንጌሉ ምዕራፍ 1፡23 ላይ ‹‹እነሆ ድንግል (የግሪኩን ፓርቴኖስ የሚለውን ቃል ይጠቀማል) ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፡- ስሙንም አማኑኤል ይሉታል›› ተብሎ በነቢዩ ኢሳይያስ የተነገረውን በመጥቀስ ፍጻሜውን እንዳገኘ ይናገራል፡፡ የትንቢት መጻሕፍት ስናነብ ብዙ ጊዜ አንዱ ፍጸሜ ላይ ብቻ ነው ትኩረት የምናደርገው፣ በዚህ ምክንያት ብዙ እውነቶችን ስተን እንገኛለን፤ ወደ ፊት የትንቢት መጻሕፍትን ስናጠና ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን ክፍሉ ያስተምረናል፡፡

በሁለተኛ የተሰጠው የጥናት ክፍል ዘዳግም 18፡15-19 ላይ የተነገረው ትንቢት ሲሆን፣ የቅርብ እና የሩቅ የትንቢቱ ፍጻሜ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 3፡22 ላይ ‹‹ … ጌታ አምላክ እኔን እንዳስነሣኝ ነቢይን ከወንድሞቻችሁ ያስነሣላችኋል በሚነግራችሁ ሁሉ እርሱን ሰሙት›› የሚለው ትንቢት የተፈጸመው በነቢዩ ሳሙኤልና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሆነ መረዳት እንችላለን፡፡ የቅርብ ትንቢቱ የነቢዩ ሳሙኤል መነሳትን ያመለክታል፡፡ ሳሙኤል የመጀመሪያው ነቢይና የነቢያትን ትምህርት ቤት በማቋቋም በር ከፋች ነቢይ ነበር፡፡

 በሩቅ ትንቢትነቱ ደግሞ፣ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ላይ፣ ይህ ሐሳብ ከሳሙኤል ጀምሮ በተለያዩ ነቢያት እየተነገረ ቆይቶ አሁን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተፈጸመ እንዲህ በማለት ‹‹… ከእርሱም በኋላ የተናገሩት ነቢያት ሁሉ ደግሞ ስለዚህ ወራት ተናገሩ›› ብሎ ይገልጸዋል፡፡ በዚህ መሠረት ትንቢቱ በሁለት ጊዜ የሚፈጸም ክፍል እንዳለው እንመለከታለን፡፡  

በመጨረሻም ሕዝቅኤል 26፡1-14 ላይ ስለ ጢሮስ የተነገረውን እንድናጠናው መሰጠቱ ይታወሳል፤ የተነገረውን የቅርብና የሩቁን ትንቢት ለመረዳት ትንሽ ከበድ የሚል ክፍል ነው፡፡ የዚህ ክፍል የመጀመሪያው ትንቢት ፍጻሜ ያገኘው በናቡከደነፆር ጊዜ የጢሮስ ወደብ የከተማዎቿ ግንቦች ፈራርሰው ወደ ባሕር ተጠራርገው ተጣሉ፣ በሁለተኛ ጊዜ በትልቁ እስክንድር ዘመን አፈርዋ በወጀብ ታጥቦ በማለቁ ምክንያት፣ ድንጋዮቿ ከመራቆታቸው የተነሣ ዓሣ አጥማጆች እንደ ትንቢቱ መረባቸውን ያሰጡበት ነበር፡፡ በቁጥር 3-5፣14 ላይ የትንቢቱን ፍሬ ነገር ማየት እንችላለን፤ ስለዚህ የትንቢት መጻሕፍትን በሚገባ ለመረዳት እንድንችል፣ መርጃ መጻሕፍትን በተለይም ማብራሪያዎችን መጠቀምን ይጠይቃል፡፡ (ኢሳ. 23፡1) በተጨማሪ ተመለከቱ፡፡

ሠ. መልእክት፡- ዛሬ በጥናታችን የምናየው የጽሑፍ ዓይነት መልእክት ሲሆን፣ ሁሉንም ጽሑፎች የምናገኘው በአዲስ ኪዳን ውስጥ ነው፡፡ ቀደም ብለን እንደ ተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱሳችን በተለያዩ የሥነ-ጽሑፍ ዓይነቶች እንደ ተጻፉ ተመልክተናል፡፡ በዚህም ምክንያት አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለመረዳት ስንፈልግ የሥነ-ጽሑፉን  ዓይነት በመረዳት መሆን እንዳለበት ባለፉት ጥናቶቻችን ተመልክተናል፡፡

ከአዲስ ኪዳን ሃያ ሰባት መልእክቶች ውስጥ ወንጌሎች፣ ከሐዋርያት ሥራና ራዕይ በስተቀር ሁሉም ሃያ አንዱ መልእክቶች ናቸው፡፡ መልእክቶች ከሕግ፣ ከታሪክ፣ ከግጥምና ከትንቢት መጻሕፍት ሁሉ ለመረዳት በጣም ቀላሎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ዓላማቸውን በቀላሉ ስለሚናገሩ፣ በማን ለማንና ለምን እንደ ተጻፉም ምክንያታቸውን አብዛኞቹ ስለሚናገሩ ነው፡፡

 መልእክቱን ከሌሎች ሥነ- ጽሑፋዊ ቅርጽ  የተለዩ የሚያደርጋቸው፣ የመልእክቱን ጸሐፊ ስምና የመልእክቱን ተቀባዮች መጥቀሳቸው፣ በሰላምታ መጀመራቸው፣ ጸሎትና ምስጋና ማቅረባቸው፣ የመልእክቱን ዋና አካል በግልጽ ማስቀመጣቸውና የስንብት ሰላምታ መያዛቸው ከሌሎች ጽሑፎች ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡

 መልእክት የመጨረሻው የሥነ-ጽሑፍ ምልከታችን ሲሆን፣ እነዚህ መልእክቶች ለግለ ሰብና ለቤተ ክርስቲያን የተላኩ መሆናቸውን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ጸሐፊው ለማን እንደ ጻፈው፣ ለምን እንደ ጻፈው፣ መቼና የት ሆኖ እንደ ጻፈው መረዳት መጻሕፍቱን ይበልጥ ለመረዳት ይረዳል፡፡ ብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አንድ ለተፈጠረ ችግር መፍትሔ ለመስጠት የተላኩ (የተጻፉ) ናቸው፡፡ ስለዚህ ጸሐፊው በደብዳቤው ለሚያነሳቸው ችግሮች የሰጠውን መፍትሔ ጠንቅቆ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

 ለምሳሌ ፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2፡2 ላይ ያለውን ‹‹ ደስታዬን ፈጽሙልኝ›› የሚለውን ሐሳብ ለመረዳት ብዙ ነገሮችን ማየት  ይጠይቃል፡፡ በመጀመሪያ ጸሐፊው ማነው? ለማነው የጻፈው? የት ሆኖ ነው የጻፈው? መቼ ነው የጻፈው? ለምን ጻፈው? ብለን በመጠየቅ መልሱን ማግኘት ይኖርብናል፡፡ ጸሐፊው ሐዋርያው ጳውሎስ (1፡1)፣ የጻፈላቸው ለፊልጵስዩስ ለሽማግሌዎች፣ ለዲያቆናትና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱሳን በሙሉ፣ የተጻፈበት ቦታ ከሮም እስር ቤት፣ (በቂሣርያ፣ በኤፌሶን፣ በፊልጵስዩስና በሮም የሚሉ የተለያዩ አመለካከቶች ቢኖሩም) እንደ ሆነ እኔ አምናለሁ፡፡ የጻፈበት ምክንያት ሐዋርያው ጳውሎስ መታሠሩን የፊልጵስዩስ አማኞች ሰምተው ገንዘብ አዋጥተው በአፍሮዲጡ በኩል ላኩለት፡፡

 ሐዋርያው ጳውሎስም ስለ ላኩለት የገንዘብ ስጦታ ደስ በመሰኘት ለማመስገን ይህን ደብዳቤ ጻፈላቸው፡፡ በደብዳቤውም በጸሎት እንደሚያስባቸው፣ ስለ ተቀበለው መከራ ደስ መሰኘቱን፣ ለወንጌል እንደሚገባ እንዲኖሩ ከመከራቸው በኋላ በቀረውስ ወንድሞቼ ሆይ በጌታ ደስ ይበላችሁ በማለት ይጽፍላቸዋል፡፡

 የጳውሎስ የደስታው ምክንያት በመጀመሪያ ጌታን በማመኑ ያገኘው ሲሆን፣ ሁለተኛው እነርሱ ገንዘብ አዋጥተው በላኩለት ስጦታ መሆኑን ከምዕራፍ 4፡10 ላይ ‹‹ … ስለ እኔ እንደ ገና ልታስቡ ስለ ጀመራችሁ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል›› የሚለውን ሐሳብ እናገኛለን፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ወደ 11 ጊዜ ደስ ብሎኛል ደስ ይበላችሁ በማለት ጽፎ የምናገኘው ጳውሎስ፣  ቀደም ብለን በ2፡2 ላይ እንዳየነው ‹‹… ደስታዬን ፈጽሙልኝ … ›› በማለት ተናግሯል፡፡ ለምንድነው እንዲህ ብሎ የተናገረው? የሚለውን ጥያቄ መልስ ለማግኘት አጠቃላይ ምዕራፉንና መጽሐፉን  ማየት ይጠቅማል፡፡

 የምዕራፍ ሁለትን ዐውድ ስንመለከት ከቁጥር 1 እስከ 4 ባለው ክፍል ውስጥ የሚከተሉትን ችግሮች እናገኛለን፡፡ የመጀመሪያው የወገናዊነት ችግር፣ ሁለተኛው ራስን ከሌሎች ማስበለጥና ሦስተኛው የራስን ጥቅም ማስቀደም እንደሆኑ እንመለከታለን፡፡ እነዚህን ችግሮች የፈጠሩት እነማን እንደሆኑ ለማወቅ ወደ ምዕራፍ አራት ከቁጥር ሁለት ጀምረን ብንመለከት፣ የችግሩን ምንጭ ጠቋሚ የሆኑ ሐሳቦችን እናገኛለን፡፡ በዚህ መንገድ አንድን ክፍል ብናጠናው ዋናውን ችግር በቀላሉ እየተረዳን መሄድ እንችላለን፡፡

 ‹‹ስለዚህ የምወዳችሁና የምናፍቃችሁ፣ ደስታዬና አክሊሌ የምትሆኑ ወንድሞቼ ሆይ፡- እንዲሁ በጌታ ቁሙ፣ ወዳጆች ሆይ፡፡ በአንድ አሳብ በጌታ እንዲስማሙ ኤዎድያንን እመክራለሁ ሲንጤኪንንም እመክራለሁ፡፡ አንተም ደግሞ በሥራዬ አብረህ የተጠመድህ እውነተኛ ሆይ፣ እንድታግዛቸው እለምንሃለሁ፡፡ ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት ከቀሌምንጦስና ደግሞ ከእኔ ጋር አብረው ከሠሩት ከሌሎች ጋር በወንጌል ከእኔ ጋር አብረው ተጋድለዋልና››፡፡

 በዚህ ክፍል ውስጥ ጐላ ብለው የምናገኛቸው ጽሑፎች ችግሮቹን ጠቋሚ ናቸው፡፡ በጌታ መቆም ያቃታቸው፣ በጌታ ያልተስማሙና የአገልጋይ እገዛ የሚያስፈልጋቸው መሆናቸውን ያመለክቱናል፡፡ ጳውሎስ በአገልግሎታቸው ስለ ወንጌል እንደ ተጋደሉ ድንቅ የሆነ ምስክርነት በመስጠት፣ በአገልጋዩ እገዛ ወደ አንድ ፍቅር፣ አንድ ልብና፣ አንድ አሳብ እንዲመጡና በአንድ አሳብ እንዲስማሙ ያሳስባል፡፡ ይህን ቢያደርጉ ‹‹ደስታው ፍጹም›› እንደሚሆን ይናገራል፡፡

 ጳውሎስ ወደሚፈልገው ሐሳብ እንዲመጡ ከክርስቶስ ራስን ዝቅ መድረግን (ትህትናን)፣ ከራሱ ከጳውሎስ ለሌላው መሥዋዕት መሆንን፣ ከጢሞቴዎስ ስለ ሌላው መኖርን፣ ከአፍሮዲጡ ስለ ሌላው ወገን ዋጋ እየከፈሉ ማገልገልን እንዲማሩ ያሳስባቸዋል፡፡ ይህን ቢያደርጉ ከላይ የጠቀስናቸው ችግሮች በቀላሉ መወገድ ይችላሉ፡፡

 አንድን አንቀጽ፣ ክፍል፣ ምዕራፍና መልእክት (መጽሐፍ) ስናጠና በዚህ መልኩ መመልከት ብንችል በቀላሉ ወደ መረዳት መምጣት እንችላለን፡፡ የመልእክት ሥነ-ጽሑፎች ከሌሎቹ ሥነ-ጽሑፎች ለመረዳት በጣም ቀላል መሆናቸውን የተረዳን ይመስለኛል፣ ምክንያቱም ለምንጠይቀው ጥያቄ ሁሉ መልስ በቀላሉ ከጽሑፉ ውስጥ ማግኘት ስለምንችል ነው፡፡

   በባለፈው እንደምናደርገው በሰባት የመጠየቂያ ቃላት መጠየቅ፣ የተለያዩ ምልከታዎች ማድረግ እንደተጠበቁ ሆነው፣ ዛሬ በተመለከትነው የመልእክት መጻሕፍት ላይ በየግላችን የምንሠራው ሆኖ እንደተለመደው ቀርቦላችኋል፡፡ በተቻለ መጠን ትኩረት ስጡትና ሥራችሁን ሠርታችሁ በሰላም እንገናኝ፤ የጌታ ጸጋ ይብዛላችሁ፡፡

  1. ፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2፡27 ላይ ‹‹በእውነት ታሞ ለሞት እንኳ ቀርቦ ነበርና፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ማረው ኀዘን በኀዘን ላይ እንዳይጨመርብኝ … ›› በማለት የሚናገረው ሁለቱ ኀዘኖቹ ምንና ምን ነበሩ?
  2. ገላትያ ምዕራፍ 1፡16 ላይ ‹‹… ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ … ›› ሲል ምን ለማለት ፈልጎ ነው?
3.  ዕብራውያን ምዕረፍ 2፡6-8 ላይ ያለው
     ሀ. መልእክት ለ. ግጥም ሐ. ትንቢት
     መ. ሁሉም     መልስ ነው፡፡

0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *