የዛሬውን ትምህርት ስለ ጥበብ መጻሕፍት (ግጥም፣ ቅኔ) ከማየታችን በፊት፣ በባለፈው ትምህርት ምን አዲስ ነገር አገኛችሁበት፡፡ አሁን ለተጠየቁት ጥያቄዎች የተሰጡትን መልሶች አብረን እንመልከት፡፡

  1. ዘኊልቊ 24፡17 በሥነ-ጽሑፍ ቅርጹ ሕግ ሲሆን በይዘቱ ግጥምና ትንቢትን ይዞአል፡፡

              ‹‹አየዋለሁ አሁን ግን አይደለም፣

              እመለከተዋለሁ በቅርብ ግን አይደለም››፡፡ በለዓም ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከለኛው ትንቢት ከያዕቆብ ዘር ሥጋ ለብሶ እንደሚመጣ፣ እንዲሁም በሩቅ ትንቢትነቱ በትንሣኤ ጊዜ ጌታን ፊት ለፊት እንደሚያየው ይጠቁማል፡፡

  • ት. ኢሳይያስ 38፡9-20 በሥነ-ጽሑፍ ቅርጹ ትንቢት ሲሆን በይዘቱ ግጥምና ትረካ ነው፡፡

               ‹‹እኔ፡-በሕይወት ዘመኔ መካከል ወደ     ሲኦል በሮች እገባለሁ፣
   የቀረው ዘመኔ ጐደለብኝ አልሁ … ቁ. 10

 … እግዚአብሔር ያድነኛል፣
ስለዚህ በዕድሜአችን ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት፣
ቅኔዎችን አውታር ባለው ዕቃ እንዘምራለን››፡፡ ቁ. 20
ንጉሡ ሕዝቅያስ ታሞ ለሞት ቀርቦ በነበረበት ጊዜ፣ የአስራ አምስት ዓመት ዕድሜ በተጨመረለት ጊዜ የዘመረው ዝማሬ ነው፡፡
  • መጽሐፈ ኢዮብ 2  በሥነ-ጽሑፍ ቅርጹ ግጥም ሲሆን በይዘቱ ትረካ ነው፡፡ ምዕራፍ አንድ፣ ሁለትና አርባ ሁለት፣ የጽሑፉ መግቢያና ማጠቃለያ ትረካዊ ንባብ ነው፡፡    

ሐ. የጥበብ መጻሕፍት(የግጥምና ቅኔ)፡- በዛሬው ቀን ጥናታችን የግጥም የሆኑትን ጽሑፎች እንመለከታለን፡፡ እነዚህን መጻሕፍት የግጥምና ቅኔ መጻሕፍት ከማለት ይልቅ የጥበብ መጻሕፍት ማለት ይቀለኛል፣ ምክንያቱም የአይሁድ የጥበብ መጻሕፍት የምንላቸው እንደ እኛ የቅኔ/ግጥም መጻሕፍት ስላይደሉ ነው፡፡ የአይሁድን ግጥምና ቅኔ ከእኛ ልዩ የሚያደርጋቸው፣ የእነርሱ መስመር በመስመር የሚሄድና የሚገለጽ ሲሆን፣ የእኛው ቤት በመምታት የሚገለጽ ይሆናል፡፡ የአይሁድም ሆኑ የእኛ የቅኔ/ግጥም መጻሕፍት በሥነ-ጽሑፋዊ ቅርጻቸው ከሕግ፣ ከትረካ፣ ከትንቢትና ከመልእክት የተለዩ ናቸው፡፡ እነዚህን የግጥም ጽሑፎች በሁሉም የጽሑፍ ዓይነቶች ውስጥ እናገኛቸዋለን፡፡ በአማርኛው 1954 ዓ.ም ትርጉም በስድ ንባብ የተቀመጡትን ትርጉሞች  የመጽሐፍ ቅዱስ ማህበር የ1988 ዓ.ም እና አዲሱ መደበኛው የ1993 ዓ.ም ትርጉሞች በስድ ንባብ የነበሩትን ትርጉሞች፣ እንደ ጥንቱ ወደ ዕብራይስጡ የጽሑፍ ቅርጽ በመመለስ ግጥም አድርገዋቸዋል፡፡ በስድ ንባብ ሲቀመጥና በግጥም ሲቀመጥ የሚሰጠው ትርጉም ይለያያል፡፡ ግጥም በሕግ፣ በትረካ፣ በትንቢትና በመልእክት ጽሑፎች ውስጥ መገኘታቸውን እንመልከት፡፡

 በሕግ ጽሑፍ ውስጥ በዘፍጥረት ምዕራፍ 1፡27 እና 2፡23 ላይ ያሉትን እንመልከት፡፡

         ‹‹ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፣

          በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፣

          ወንድና ሴት አድረጎ ፈጠራቸው፡፡

በትረካ ጽሑፍ ውስጥ 1ኛ ነገሥት 12፡16

      በዳዊት ዘንድ ምን ክፍል አለን?

በእሰይም ልጅ ዘንድ ርስት የለንም፡፡

      እስራኤል ሆይ፣ ወደ ድንኳኖቻችሁ ተመለሱ፤

           ዳዊት ሆይ፣ አሁን ቤትህን ተመልከት፡፡

በትንቢት ጽሑፍ ውስጥ ኢሳይያስ 40 በሙሉ

     ‹‹አጽናኑ፤ ሕዝቤን አጽናኑ፤ ይላል አምላካችሁ፡፡

        ለኢየሩሳሌም ልብ ተናገሩ፤

      የተቀጠረችበት ወራት እንደ ተፈጸመ፤

        ኃጢአትዋም እንደ ተሰረየ፤

        ከእግዚአብሔርም እጅ ስለ ኃጢአትዋ ሁሉ

        ሁለት እጥፍ እንደ ተቀበለች፡፡

 በመልእክት ጽሑፍ ውስጥ ፊልጵስዩስ 2፡5-11

        በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ፣

           በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን፡፡

        እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ፣

           ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት

             እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፡፡

 ከዚህ በላይ ያየናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በ54 ዓ.ም ትርጉም ስድ ንባብ ሲሆኑ በአዲሱ መደበኛው ትርጉም እንደ ዕብራይስጡ ጽሑፍ በግጥም አስቀምጠውታል፣ (ተርጉመውታል)፡፡ በስድ ንባብና በግጥም በሚሆንበት ጊዜ የተለያየ ትርጉም/ሐሳብ ሊሰጥ ስለሚችል፣ ቃሉን በምናነብበትና በምናጠናበት ጊዜ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል፡፡ ግጥም የማይገኝባቸው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከሕግ ዘሌዋውያን፣ ከታሪክ መጽሐፈ ሩት፣ ዕዝራ፣ ነህምያና አስቴር ሲሆኑ፣ ከትንቢት ሐጌና ሚልክያስ ናቸው፡፡  ከእነዚህ መጻሕፍት በስተቀር በሁሉም የጽሑፍ ዐይነቶች ውስጥ ግጥምን እናገኛለን፡፡

 የግጥም (የጥበብ መጻሕፍት) አጻጻፍ አንዱና ብርቱ ጐን በዓይነ ህሊና የሚታይ ምስል መፍጠር መቻሉ ነው፡፡ ግጥሞች የሚገለጡበት መንገድ በጣም ብዙዎች ናቸው፣ ብዙ ዐይነት ዘይቤአዊ ወይም ፈሊጣዊ አነጋገሮችን በተጓዳኝ መስመሮች በመግለጥ፣ ሊያስተምሩ (ሊያስተላልፉ) የፈለጉትን እውነት ሥዕላዊ በሆነ መንገድ ይገልጻሉ፡፡

   አይሁዶች ብዙ ዐይነት ዘይቤአዊ አነጋገሮች ስለ አሉዋቸው፣ አሁን ሁሉንም ማየት ባንችልም፣ ዋናው ነገር የእነርሱ ግጥም/ቅኔ መስመር በመስመር በመጠቀም ሐሳባቸውን እንደሚገልጹ መረዳት ነው፡፡ አንድን ነገር በመጀመሪያው መስመር ላይ የገለጹትን ሐሳብ/እውነት በሁለተኛውና በሦስተኛው መስመር፣ አስፋፍተው ወይም አጥበው ይገልጹታል፡፡ 

  1. ፈሊጣዊ አነጋገሮች፡- ዘይቤአዊ አነጋገሮች ቀደም ብለን እንደ ገለጽነው፣ አንድን  ነገር ለመግለጽ በሚታይ ሥዕላዊ በሆነ መልኩ/መንገድ መግለጽ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ መዝሙር 18፡2 ላይ ስንመለከት ‹‹እግዚአብሔር ዓለቴ ነው ›› ይላል፣ ይህም እግዚአብሔር ድንጋይ ነው ማለት ሳይሆን፣ ለ.ዓለቴ የሚለው ቃል ጠንካራ፣ የማይነቃነቅ፣ ከባድ ለማለት ሲሆን ጌታ ቢታመኑበትና ቢደገፉት የጸና ነው የሚል ትምህርት እናገኝበታለን፡፡

በመዝሙር 6፡6 ላይ ‹‹ በጭንቀቴ ደክሜያለሁ፣
                  (ከመቃተቴ የተነሣ ዝያለሁ፣ አመት)   

                ሌሊቱን ሁሉ አልጋዬን አጥባለሁ፤

                በዕንባዬም መኝታዬን አርሳለሁ›› ይላል፡፡

 በመጀመሪያው መስመር የመከራውን ከባድነትና ጥልቀት ይገልጻል፣ በሁለተኛው መስመር ‹አልጋውን› አጥባለሁ ሲል፣ በሦስተኛው መስመር ይመጣና ‹መኝታዬን› አርሳለሁ በማለት የጭንቀቱን ከባድነት ያመለክታል፣ በሁለተኛው መስመር ‹አጥባለሁ› ያለውን በሦስተኛው መስመር ‹አርሳለሁ› በማለት በመጀመሪያ የተጠቀመበትን ቃላት እየለዋወጠና ሀሳቡን እያጠበበና እያሰፋ እንደ ተጠቀመበት ማየት ይቻላል፡፡  ይህን ጥቅስ የተጠቀምኩት ለሦስት ጉዳይ ነው፤ በመጀመሪያው ስለሚናገረው ምን ያህል ሥዕላዊ እንዳደረገው እንድታዩ ነው፣ ሁለተኛው ምን ያህል አግንኖ እንዳቀረበው ነው፡፡ ምን ያህል እውነት ነው? በየት ሀገር ነው አልጋ በዕንባ የሚታጠበው?፣ ሦስተኛው ሀሳቦቹ መስመር በመስመር መገለጻቸውን እንድትመለከቱ ብዬ ነው፡፡ እዚህ ላይ ንግግሩ ዘይቤአዊና ግነታዊ  መሆኑን በቀላሉ መረዳት እንችላለን፡፡    

  • ተመሳሳይ ተጓዳኝ ግጥም (synonymous)፡- በተጓዳኝ ግጥም ሥር ብዙ የተለያዩ የግጥም ዐይነት ቢኖሩም፣ አሁን ዋና ዋናዎቹን ብቻ እንመለከታለን፡፡ በሁለት መሥመሮች ላይ አንድ ዐይነት ሐሳብ ወይም ተመሳሳይ የሆኑ ሐሳቦችን በተለያዩ ቃላቶች ሰፍተው ወይም ጠበው ተገልጸው ሲቀመጡ ሐሳቦቹ ጎልብተው ሲገኙ የሚያሳይ ነው፡፡ ለምሳሌ መዝሙር 2፡1-6  ቁጥር 1 ‹‹አሕዛብ ለምን ያጒረመርማሉ፣

                   ወገኖችስ ለምን ከንቱን ይናገራሉ››፡፡

 አህዛብና ወገኖች የሚሉት ሐሳቦች አንድን ሕዝብ ነው የሚያመለክቱት፣ ግን አሕዛብ (ሕዝቦች) የሚለው በጣም ሰፊ ሲሆን፣ ወገኖች የሚለው ጠበብ ይላል፡፡ ሕዝብ ሲል በዓለም፣ በአህጉርና በአገር ደረጃ ያሉት ሠፊ ሕዝቦች ሲያመለክት ወገኖች የሚለው ደግሞ ጠብቦ በሥጋና በደም ያለውን የቅርብ ዝምድና ያመለክታል፡፡ አማራ፣ ጉራጌ፣ ኦሮሞ … አንድ ወገን ቢሆኑም እንደገና በቅርብ የዘር/የትውልድ ሐረግ እየጠበበ ይሄዳል፡፡

 በመጀመሪያው መስመር ላይ ‹ለምን ያጒረመርማሉ› ሲል በሁለተኛው መስመር ‹ለምን ከንቱን ይናገራሉ› በማለት ያንኑ ሐሳብ አጉልቶ ይገልጸዋል፡፡ ማጒረምረም የመናገር ጅማሬ ነው፡፡ ሰው መናገር አቅቶት ወይም መናገር ፈርቶ ያጒረመርማል፣ ሲደፍር ግን ያንን በንግግር ይገልጸዋል፡፡ ድምጹ ካለመሰማት ወደ መሰማት ይለወጣል፡፡

             ቁጥር 2 ‹‹የምድር ነገሥታት ተነሡ፣

             አለቆችም በእግዚአብሔርና በመሢሁ ላይ  

              እንዲህ ሲሉ ተማከሩ››፡፡

 በመጀመሪያው መስመር ላይ ‹ነገሥታት› ሲል ጠባብ ነው፣ በአንድ ሀገር አንድ ‹ንሡሥ› ወይም ፕሬዚደንት ወይም ጠ/ሚኒስቴር ብቻ ነው፣ ሊኖር የሚችለው፡፡ በሁለተኛው መስመር አለቆች ሲል በአንድ ሀገር ብዙ አለቆች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የትምህርት ቤት፣ የተለያዩ መንግስት መሥሪያ ቤቶች፣ የዕድር፣ የማህበር ኃላፊዎች ሁሉ አለቆች ናቸው፡፡ ስለዚህ ነገሥታት አለቆች ናቸው፣ የጠቀስናቸው አለቆች ሁሉ ግን ነገሥታት አይደሉም፡፡ ስለዚህ ነገሥታት ብሎ ጠባብ የነበረውን ሐሳብ በሁለተኛው መስመር ላይ አለቆች ብሎ አሰፋው፡፡ ይህ ሐሳብ በስድ ንባብ ቢሆን ኖሮ እንደዚህ ያለ ስሜት ሊሰጥ አይችልም ነበር፡፡

  • ተቃራኒ ተጓዳኝ ግጥም (antithetical)፡- በተቃራኒ ተጓዳኝ ግጥም በሁለት መስመሮችና ከዚያም በላይ፣ በመጀመሪያው መስመር ላይ የገለጹትን ሐሳብ በሁለተኛው መስመር ላይ ተቃራኒ የሆኑ ሀሳቦችን ገልጸው ሲገኙ የሚያመለክት ነው፡፡ ምሳሌ፡- መዝ. 32፡10፣

       ‹‹በኃጢአተኛ ብዙ መቅሠፍት አለበት፣

        በእግዚአብሔር የሚታመነውን ግን ምሕረት ይከብበዋል››፡፡

 በመጀመሪያ መስመር ላይ ‹ኃጢአተኛ› ብሎ የገለጸውን በሁለተኛው መስመር ላይ ‹በእግዚአብሔር የሚታመን›(ጻድቅ) ብሎ በመቃረን ይገልጸዋል፡፡ አሁንም ኃጢአተኛውና ጻድቁ በእግዚአብሔር ዘንድ ስለሚያገኙት ብድራት ሲገልጽ፣ በመጀመሪያው መስመር ላይ ‹መቅሠፍት› የሚለውን ቃል ሲጠቀም፣ በሁለተኛው መስመር ላይ የመቅሠፍት ተቃራኒ የሆነውን ‹ምሕረት› የሚለውን ቃል ተጠቅሞአል፡፡

  • ዕድገታዊ ተጓዳኝ ግጥም (climactic)፡- ዕድገታዊ ተጓዳኝ ግጥምን ስንመለከት በአንድ  መስመር ላይ አንድ እውነት ይመሠርትና በመቀጠል ባሉት መስመሮች ላይ ሐሳቡን አንዱ በአንዱ ላይ ተመሥርቶ እያደገ ተገልጾ ሲገኝ ነው፡፡ ምሳሌ፡- መዝሙር 2፡8፣ 24፡1-2

         ‹‹ለምነኝ፡- አሕዛብን (ሕዝቦች) ለርስትህ፣

           የምድርንም ዳርቻ ለግዛትህ እሰጥሃለሁ››፡፡

በመጀመሪያው መስመር ላይ የአንድ ሀገር ሕዝብን ለርስትህ አሰጥሃለሁ ብሎ አጥብቦ ይጀምርና፣ በሁለተኛው መስመር ላይ ‹የምድርን ዳርቻ› (ሕዝቦች) ለግዛትህ እሰጥሃለሁ ብሎ ያሳድገዋል፡፡ ‹ርስት› ከቤተሰብ በውርስ ወይም በስጦታ የሚገኝ ሲሆን ‹ግዛት› በሹመት ወይም ድል በማድረግ የሚገኝ ነው፡፡  በውርስ ያገኘውን ርስት ብቻ ሳይሆን ድል አድርጎ የያዘውን የራሱን ግዛት እሰጥሃለሁ በማለት ሐሳቡን ያሳድገዋል፡፡

 የጥበብ መጻሕፍት ስናነብና ስናጠና ከዚህ በላይ በተመለከትናቸው ነገሮች ላይ ትኩረት ብንሰጥ ቃሉን በሚገባ መረዳት፣ ማስተዋልና በሕይወታችን ልንኖረውና ወደ ክርስቶስ ሙላት ልናድግበት የምንችልበትን ጥበብ እናገኛለን፡፡

በባለፈው እንደምናደርገው በሰባት መጠየቂያ ቃላት መጠየቅ፣ የተለያዩ ምልከታዎች ማድረግ እንደተጠበቁ ሆነው፣ ዛሬ የተመለከትናቸውን የጥበብ መጻሐፍት በየግላችን የምንሠራቸው ሆነው እንደተለመደው ቀርበውላችኋል፡፡ በተቻለ መጠን ትኩረት ስጡትና ሠርታችሁ፣ መልሱን ከተሰጡት በመምረጥ አሳዩ፣ በሰላም እንገናኝ፡፡

 1. መዝሙር 5፡1             
‹‹አቤቱ ቃሌን አድምጥ፣                         ጩኸቴንምአስተውል››፡፡ 
ሀ.ተመሳሳይ ተጓዳኝ 
ለ. ተቃራኒ ተጓዳኝ           
ሐ. ዕድገታዊ ተጓዳኝ
2. መዝሙር 34፡10  ‹‹ባለጠጎችደኸዩተራቡ፣              
  እግዚአብሔርን የሚፈልጉት ግን
ከመልካም ነገር ሁሉ አይጐድሉም››፡፡
ሀ.ተመሳሳይ ተጓዳኝ 
ለ. ተቃራኒ ተጓዳኝ        
ሐ. ዕድገታዊ ተጓዳኝ
3. መዝሙር 29፡1-2  ‹‹የአምላክ ልጆች ሆይ፣ ለእግዚአብሔር አምጡ፣                       
ክብርና ምሥጋና ለእግዘዚአብሔር አምጡ፣
የስሙን ክብር ለእግዚአብሔር አምጡ፣
በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ። ሀ.ተመሳሳይ ተጓዳኝ  ለ.ተቃራኒተጓዳኝ                          
ሐ.ዕድገታዊ ተጓዳኝ

        


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *