የዛሬውን ትምህርት ስለ ትረካ ከማየታችን በፊት፣ ስለ ሕግ በባለፈው ለተጠየቁት ጥያቄዎች የተሰጡትን መልሶች እንመልከት፡፡ መልሱ በምርጫ የሚሰጥ ቢሆንም ሠፋ አድርጋችሁ እንዳያችሁትና እንደተጠቀማችሁበት አምናለሁ፡፡

  1. ዮሐንስ ወንጌል 15፡10  በሥነ-ጽሑፍ ቅርጹ ትረካ ሲሆን በይዘቱ የሚናገረው ስለ አዲስ ኪዳን ሕግ ነው፡፡ ‹‹እኔ የአባቴን ትእዛዝ (ሕግ) እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፣ ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ፡፡›› ጌታ የጠበቀው ሕግ በብሉይ ኪዳን የተሰጠውን ሲሆን፣ ለእኛ ጠብቁ ያለን በአዲስ ኪዳን የተሰጠውን የፍቅር ሕግ ነው፡፡
  2. ሮሜ 2፡25 ይህ ክፍል በሥነ-ጽሑፍ ቅርጹ መልእክት ሲሆን በይዘቱ የሚናገረው ስለ ብሉይ ኪዳን ሕግ ነው፡፡ ‹‹ሕግን ብታደርግ መገረዝስ ይጠቅማል ሕግን ተላላፊ ብትሆን ግን መገረዝህ አለመገረዝ ሆኖአል›› በማለት የብሉይ ኪዳንን  ሕግ በመጠበቅና ባለ መጠበቅ መካከል ያለውን ልዩነት ለአይሁድ አማኞች ይናገራል፡፡
  3.  መዝሙር 119፡18 በሥነ-ጽሑፍ ቅርጹ ግጥም ሲሆን በይዘቱ የሚናገረው ስለ ብሉይ ኪዳን ሕግ ነው፡፡   ‹‹ዓይኖቼን ክፈት ከሕግህም ተአምራትህን አያለሁ›› መዝሙረኛው ስለ ብሉይ ኪዳን ሕግ ጠቃሚነት ያመለክታል፡፡                   

  ለ. ትረካ፡- በዛሬው ጥናታችን ትረካ መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈበት ሥነ-ጽሑፋዊ ቅርጽ አንዱ እንደሆነ እናያለን፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ትረካ/ታሪክ ከሌላው የዓለም ታሪክ የተለየ አይደለም፣ ታሪኩን የተለየ የሚያደርገው የታሪኩ ባለቤት እግዚአብሔር ራሱ በመሆኑ ነው፡፡ ታሪክ በባለፈው ዘመን የተፈጸመውን ድርጊት ሳይዛባ ትክክለኛ ትንተና በማድረግ ግንዛቤ መስጠት ነው፡፡ ትረካዊ ምንባቦች የምንላቸው ብዙዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡ ዘፍጥረት፣ ዘጸዓት ግማሹ፣ ኢያሱ፣ ሩት፣ ፣ ሳሙኤል፣ ነገሥት፣ ዜና፣ ዕዝራ፣ ነህምያና አስቴር፤ ከአዲስ ኪዳን ወንጌሎችና የሐዋርያት ሥራ ናቸው፡፡

የትረካ ጽሑፎች ዓላማቸውና ግባቸው ዝርዝር ታሪክ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ለወቅቱ ሁኔታዎች ለእስራኤል መነሣት ወይም መውደቅ ምክንያቱን በግልጽ ማስቀመጥ ነው፡፡ በተለይም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከሁሉም በላይ የሚያስተላልፉት ነገረ መለኮታዊውን እውነት ነው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ራሱን እየገለጠ በመካከላቸው ስለ ሠራ ያንን የሠራውን ተዓምራቶች ትልቅ ትኩረት ሰጥተው ተርከውታል፡፡ በዚህም መሠረት የእስራኤልና የእግዚአብሔር ታሪክ ሳይነጣጠሉ አብረው ተተርከዋል፡፡ ከዚህ የተነሣ የታሪክ መጻሕፍት የነገረ መለኮታዊ ትረካ ናቸው፣ የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ትረካዎቹ በግለሰብ፣ በአገር፣ በማህበራዊና በሃይማኖታዊ ገለጻዎች ታጅበው ቀርበዋል፡፡

የታሪክ ዐቢይ ዓላማ ያለፈውን ዘመን በማስታውስ፣ የአሁኑን ያለንበትን ዘመን ግንዛቤ በመስጠት፣ ከወደፊቱ ዘመን ጋር አስተሳስሮ ተግባራዊውን መግለጽ ነው፡፡ የታሪክ መጻሕፍቱ የሚተርኩት የእስራኤልን ብርታትና ውድቀት ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔር በመካከላቸው በመገኘት የሠራውን ታሪክም ያሳዩናል፡፡ የብሉይ ኪዳን የትረካ መጻሕፍት እንደ ሌሎቹ የታሪክ መጻሕፍት ገጸ ባሕርይ፣ ሤራና መቼት አላቸው፡፡

 ወደ አዲስ ኪዳን የታሪክ ምንባባት ስንመጣም ትረካው የሚያጠነጥነው በክርስቶስ ዙሪያ እንደ ሆነ ማየትና መረዳት እንችላለን፡፡ የታሪኩ ባለቤት ኢየሱስ ራሱ ነው፡፡ ወንጌላቱን ስንመለከት ከብሉይ ኪዳኑ ታሪክ የሚመሳሰሉበትና የሚለያዩበት ነገር አላቸው፡፡ ወደፊት ትምህርታችንን አስፍተን ስንመለከት የምናገኘው ይሆናል፣ አሁን ለጊዜው ሁሉንም በአንድ ዓይን እንመለከታቸዋለን፡፡

 ታሪካዊ ምንባቦች የምንላቸውን የብሉይና የአዲስ ኪዳን ጽሑፎች ዝርዝር ተመልክተናል፡፡ እነዚህን ጽሑፎች ለመረዳት ወደ መተርጐም ከመሄዳችን በፊት ምን ምልከታዎች ማድረግ እንዳለብን እናያለን፡፡ ቀደም ብለን እንዳየነው ማንኛውንም ጽሑፍ በሰባት የመጠየቂያ ጥያቄዎች መጠየቅ እንዳለብን፣ ቀጥሎም የተለያዩ ምልከታዎች ማድረግ እንዳለብንና በመቀጠልም የሐሳቡን መዋቅር ማየት እንዳለብን እያየን ቆይተናል፡፡

 የሐሳቡን  መዋቅር ስንመለከት በሁለት ከፍለን መመልከታችን የሚታወስ ነው፣ ይኸውም ሰዋስውንና የሥነ-ጽሑፉን ዓይነት ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ብለን የሕግ መጻሕፍትን ለየት ባለ መነጽር እያየን እንደ ቆየነው ሁሉ፤ አሁን ደግሞ የትረካ መጻሕፍትን ለየት ባለ መነጽር ማየት እንጀምራለን፡፡ መነጽሮቻችንም ወደ አምስት የሚደርሱ ናቸው፡፡

  1. መክፈቻ ጥቅስ፡- አንድን የታሪክ መጽሐፍ ለማጥናት ስንጀምር፣ ሙሉውን እያነበብን መክፈቻ ጥቅሱን እንፈልግ፡፡     ሥራ ውለን ከውጭ ወደ ቤታችን ስንመለስ፣ በመክፈቻ ቁልፍ ተጠቅመን ወደ ቤት ውስጥ መግባት እንደምንችለው ሁሉ፣ መክፈቻ ጥቅስም የንባቡን ዓላማውን ለማግኘት እንድንችል የሚረዳን ዋና ቁልፍ መሣሪያ ነው፡፡ ጸሐፊው ለምን ጻፈው ብለን ለምንጠይቀው ጥያቄም ፍንጭ ሊሰጠንና መልስ ሊያስገኝልን የሚችለው መክፈቻ ጥቅሱ ነው፡፡ ለምሳሌ የዮሐንስን ወንጌል ብንመለከት የመጽሐፉ መክፈቻ ጥቅስ የሚገኘው ምዕራፍ 20 ቁጥር 31 ላይ ሲሆን፣ ቃሉም እንዲህ ይላል ‹‹ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል››

ዮሐንስ በእያንዳንዱ ምዕራፍ ውስጥ ለአይሁድ ሕዝብ የሚነግራቸው በመንደራቸው የተወለደው ኢየሱስ፣ ክርስቶስ (መሲህ) እና የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ በማሳየት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅነቱንና መሲህነቱን ቢቀበሉ ሕይወት (መዳን) እንደሚሆንላቸው በማስገንዘብና በማስረዳት ጽፎላቸዋል፡፡

  • ዓላማ፡- አትሌቶች ሌሊት ተነስተው በጨለማ፣ በዳገት፣ በቁልቁለትና በብርድ የሚሮጡት ለሀገራቸውና ለራሳቸው ወርቅ የማግኘት ዓላማ እንዳላቸው ሁሉ፤ እንደዚሁም ጸሐፊዎች ሲጽፉ ዓላማ አላቸው፡፡ ዓላማ እጅግ አስፈላጊ ስለሆነ፣ የታሪክ ጽሑፎችን ስናነብና ስናጠና፣ የመጀመሪያው ሥራችን ሊሆን የሚገባው፣ ጸሐፊው የጻፈበትን የጽሑፉን ዓላማ ማወቅ ነው፡፡ ስለዚህ ዓላማን ሊያስገኝ የሚችለውን ትርጉማዊ ጥያቄዎች በመጠየቅ ዓላማን ማግኘት ይኖርብናል፡፡ ሰባቱን የመጠየቂያ ጥያቄዎች ታስታውሳላችሁ፣ ከእነዚያም አንዱ ‹ለምን› ብለን የምንጠይቅበት ቃል ነው፡፡ ለምን ተጻፈ ብለን ስንጠይቅ፣ ወደ ተጻፈበት ምክንያት መድረስ እንችላለን፡፡ ዓላማውን ከተረዳን እያንዳንዱን የመጽሐፉን ክፍሎች ለመረዳት ያስችለናል፡፡ ወደ ትክክለኛ ትርጉምም ሊያደርስን የሚችለውም ዓላማውን ስንረዳው ነው፡፡

መጻሕፍት የተጻፉበትን ዓላማ ለማወቅ ትንሽ ሥራ ይጠይቃል፣ ምክንያቱም ከጥቂት መልእክቶች በስተቀር ሁሉም መልእክቶች የተጻፉበትን ዓላማ ስለሚናገሩ ይቀላሉ ፡፡ ነገር ግን የሕግ፣ የታሪክ፣ የሥነ-ጥበብና የትንቢት ጽሑፎች ግን የተጻፉበትን ዓላማ ስለማይናገሩ አይገቡንም፡፡ ስለዚህ ዓላማውን ፈልገን የማግኘት ሥራ ጸሐፊዎች ለእኛው ለራሳችን ትተውልናል ማለት ነው፡፡ ዓላማውን መረዳት ከቻልን እያንዳንዱን የመጽሐፉን ክፍሎች ለመረዳት ያስችለናል፡፡    

  • መሪ ሐሳብ(ቲም)፡- የመጽሐፉን መሪ ሐሳብ ማወቅም በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ አንድን ጥቅስ፣ ሐረግ፣ ክፍልና መጽሐፍ ለመረዳት መሪ ሐሳቡም ይጠቅማል፡፡ መሪ ሐሳቡም ብዙ ጊዜ ከመክፈቻው ጥቅስ ውስጥ ይወጣል፡፡  
  • ቁልፍ ሰዎችና ቦታዎች፡- ታሪካዊ ምንባቦችን በምናነብበትና በምናጠናበት ጊዜ ቁልፍ ሰዎችና ቦታዎች ላይ ትኩረት ስናደርግ ቁልፍ ድርጊቶችንም እናገኛለን፣ ስለዚህ ቁልፍ ሰዎችና ቦታዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ለምሳሌ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን ብናጠና ቁልፍ ሰዎች ጴጥሮስ (ምዕራፍ 1-12) እና ጳውሎስ (ምዕራፍ 13-28) ሲሆኑ፣  በቁልፍ ቦታዎች ብናጠናው ደግሞ ኢየሩሳሌም፣ ይሁዳ፣ ሰማርያና ዓለም ዳር ዋና የጥናታችን መሠረት ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡
  • የወንጌል ምሳሌዎች (ፓራብልስ)፡- ወንጌሎችን የተለዩ ታሪካዊ ጽሑፎች አድርገን መመልከቱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ከብሉይ ኪዳን ትረካዎች የሚለዩበት ነገር ቢኖር የግል ትረካ (ባዮግራፊ) ላይ በማተኮራቸው ነው፡፡ በተለይም በወንጌሎች ውስጥ ላሉት ምሳሌዎች (ፓራብልስ) ለምንላቸው ለየት ያለ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ‹‹ምሳሌዎች ነገሮችን የመፈልቀቅና የመፈንተው ኀይል አላቸው፡፡ አንድን ሐሳብ በደረቁ ከመተንተን ይልቅ በምሳሌ እያዋዙና እያነጻጸሩ መተንተን ነገሩን ይበልጥ ይከስተዋል፤ ማለት ያበራዋል፤ ደምቆ እንዲታይ ያደርገዋል፡፡›› (ምኒልክ አስፋው መጽሐፍ ቅዱስና የትርጓሜ ስልቱ ገጽ 270) በዚህ ምክንያት ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ  ትምህርቱን ሰዎች በሚያውቁት ዕለት በዕለት ካላቸው ግንኙነትና ንኪኪ በመነሣት እንዲገባቸው ለማድረግ በቤተሰብ፣ በንግድ፣ በበግ፣ በወይን፣ በዓሣና በዕንቁ በመሳሰሉት ምሳሌዎች በመመሰል መልእክት አስተላልፎአል፡፡ በወንጌሎቹ ውስጥ ያለውን ሦስት እጅ የሚሆኑትን ትምህርቶቹን ያስተማረው በምሳሌዎች ነው፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 13 ላይ ከዘሪው ምሳሌ ተነስቶ ሁሉንም ምሳሌዎች ብንመለከት አስደናቂ ትምህርቶች መተላለፋቸውን እንመለከታለን፡፡

 እንግዲህ የትረካ ጽሑፎች ከሌሎች ጽሑፎች የሚለዩበትን በጥቂቱም ቢሆን ተመልክተናል፤ ስናነብና ስናጠና ከላይ በተመለከትነው መሠረት፣ ሳንታክትና ሳንሰለች የተለየ ትኩረት ሰጥተናቸው ብንመለከታቸው የበለጠ ልንረዳቸው እንችላለን፡፡ መንፈስ ቅዱስም ጥረታችንን በመባረክ፣ መረዳቱን እንደ መሻታችን ይሰጠናል፡፡   

 በባለፈው እንደምናደርገው በሰባት መጠየቂያ ቃላት መጠየቅ፣ የተለያዩ ምልከታዎች ማድረግ እንደተጠበቁ ሆነው፣ ዛሬ በተመለከትነው ሥነ-ጽሑፍ (ትረካ)፣ በየግላችን የምንሠራው ሆኖ ቀርቦላችኋል፡፡ በተቻለ መጠን ሁላችሁም ትኩረት ስጡትና ሠርታችሁ በሰላም እንገናኝ፡፡

  1. ዘኊልቊ 24፡17       ሀ. ሕግ       ለ. ትረካ  ሐ. ትንቢት   መ. ግጥም
  2. ት. ኢሳይያስ 38፡9-20  ሀ. ትንቢት   ለ. ትረካ   ሐ. ግጥም     መ. መልእክት

መጽሐፈ ኢዮብ 2       ሀ. ግጥም     ለ. ትረካ   ሐ. ትንቢት   መ. መልእክት


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *