በመጀመሪያ ባለፈው ጊዜ በተሰጡት ምልከታዎች ላይ አብረን ቆይታ አድርገን፣ ዛሬ ወደ አዲሱ ርዕሳችን እንገባለን፡፡ በመጀመሪያ ምልከታ እንድናደርግ የተሰጠው የሉቃስ ወንጌል ነበር፡፡ ሉቃስ ወንጌሉን ሲጽፍ ለኢየሱስ ለልደቱ፣ ለእድገቱ፣ ለአገልግሎቱና ለመከራው ታሪክ የሰጠውን መጠን ለመረዳት ምልከታ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

ምዕራፍ4.5684.51
ዓመት30218 ቀን50 ቀን

በዚህ ሠንጠረዥ ላይ ሉቃስ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ለኖረበት 33 ዓመት ታሪኩ የሰጠውን መጠን ስንመለከት፣ ለጸሐፊው   የጽሑፉ ዋና ሐሳብ የቱ እንደሆነ መረዳት እንችላለን፡፡ ለሠላሳ ዓመቱ ታሪክ አራት ምዕራፍ ተኩል፣ ለሁለት ዓመት አገልግሎቱ ስድስት ምዕራፍ፣ ለአንድ ዓመት አገልግሎቱ ስምንት ምዕራፍ፣ ለስምንት ቀን መከራው አራት ምዕራፍ ተኩል፣ ለሃምሳ ቀን ታሪኩ አንድ ምዕራፍ ሲሰጠው፣ የጽሑፉ ክብደት (ዋና ዓላማ፣ ሐሳብ) የት ላይ እንዳለ መረዳት አያስቸግርም፡፡ ለስምንት ቀን ታሪኩ አራት ምዕራፍ ተኩል ከሰጠ፣ ለሠላሳ ዓመት ታሪኩ  ስንት መስጠት እንደ ነበረበት እሰቲ አስቡ፡፡ ለአንድ ዓመት (52 ሳምንት) ስምንት ምዕራፍ ሳይሆን፣ 208 ምዕራፍ መስጠት ነበረበት፡፡ ለአንድ ዓመት ይህን ያህል ከሰጠ፣ ለሠላሳ ዓመቱ ስንት ምዕራፍ እንደሚሆን ገምቱ፡፡ ነገር ግን ለሉቃስ ዋና አንገብጋቢውና ትኩረት ሰጥቶት የነበረው የአንድ ሳምንት ታሪኩ እንደሆነ፣ ከሰጠው የጽሑፍ መጠን እንረዳለን፡፡

  ያም ሳምንት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መከራ መቀበሉ፣ በመስቀል ላይ መሞቱ፣ በመቃብር ውስጥ መሆኑና በሦስተኛው ቀን መነሣቱ ሲሆን፣ ይህም የታሪኩ ዋና እምብርት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህ አንድን ክፍል በምናጠናበት ጊዜ ጸሐፊው ለአንድ ነገር የሰጠው መጠን፣ የጽሑፉን ዋና ሐሳብ ጠቋሚ ሆኖ ስለምናገኘው ትኩረት እንድንሰጠው ያስፈልጋል፡፡

  በሁለተኛ ምልከታ እንድታደርጉ የተሰጠው የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 15 ነበረ፡፡ ይህን ክፍል ከዚህ በፊት በድግግሞሽ፣ በተከታታይና ጠቅላላ/ዝርዝር በሚለው ምልከታ ማድረጋችን የሚታወስ ነው፡፡ አሁን ግን የተሰጠው ማብራሪያ (Illustration)፣ ምሳሌ፣ ወይም ማስረጃ በሚለው እንድንመለከተው ነበር፡፡ ይህን ክፍል ደጋግሜ ያነሳሁትና የሰጠሁት አንድን ክፍል ስናጠና የተለያዩ ምልከታዎች በማድረግ፣ ከአንድ ክፍል ብዙ ነገሮችን ማውጣት እንደምንችል ለማሳየት ስለተመቸኝ ነው፡፡

 ስለዚህ የዚህ ክፍል ዋና ሐሳቡ ያለው ከቁጥር 1-2 ላይ ነው፣ ‹‹ይህስ ኃጢአተኞችን ይቀበላል ከእነርሱም ጋር ይበላል›› የሚለው ሲሆን፣ የጠፋው በግ፣ የጠፋው ድሪምና የጠፋው ልጅ ማብራሪያ (Illustration) ምሳሌ፣ ወይም ማስረጃ ሆነው ገብተዋል፡፡ ማብራሪያው የዋና ሀሳቡ ዝርዝር፣ ተከታታይና ድግግሞሽ መሆኑንም ያሳየናል፡፡

  የመጨረሻው ሦስተኛው ምልከታ እንድናደርግበት የተሰጠን ክፍል የዕብራውያን መጽሐፍ ከምዕራፍ 1 እስከ 5 ያለውን  በዕድገት (Progression) እንድናየው ነበር፡፡ በምልከታችሁ ጊዜ ምን አገኛችሁ? በዚህ ክፍል ውስጥ ያለውን የሐሳብ ዕድገት ስንመለከት ኢየሱስ ከመላእክት፣ ከሙሴና ከአሮን እንደሚበልጥ ያሳየናል፡፡ ይህን ክፍል በሁለት መልኩ ማየት እንችላለን፡፡ የመጽሐፉ ዋና ሐሳብ በሚለው ከሄድን የአዎንታዊ ዕድገት እናገኛለን፡፡ መላእክትና ሙሴ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን በመግባት ወደ እግዚአብሔር ህልውና የመግባት መብት አልነበራቸውም፤ አሮን ግን ነበረው፡፡ ኢየሱስ ከአሮን የሚበልጥ ሆኖ በመምጣቱ ወደ ሰማያዊቷ ቅድስት ገባ፡፡

 በተፈጥሮ ካየነው ኢየሱስ ከመላእክት ያነሰ ሆኖ ነው የመጣው፡፡ ‹‹…በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አንሶ የነበረውን ኢየሱስን ከሞት መከራ የተነሣ ክብርና የምስጋናን ዘውድ ተጭኖ እናየዋለን›› (ዕብ. 2፡9) በማለት የአሉታዊ ዕድገት ውስጥ ማለፉን ያሳየናል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው መላእክት አይሞቱም፣ እርሱ ግን የሚሞት ሥጋ ይዞ በመምጣቱ ከመላእክት ያነሰ ሆነ፡፡ አንድ ነገር ከትንሽ ወደ ትልቅ እያደገ ሲሄድ ወይም ከትልቅ ወደ ትንሽ እየቀነሰ ሲመጣ ዕድገት ይባላል፡፡ በሁለቱም ለውጥ ሲያሳይ የመጨመር ወይም የመቀነስ ዕድገት ሲያሳይ በውስጡ ቁም ነገር/ዋና ሐሳብ መያዙን ያመለክተናል፡፡    

  1.  የሐሳቡን መዋቅር(Structure) ማየት

 በመመልከት ሥር ከምናያቸው ሦስት ዋና ዋና ነገሮች አንዱ የሆነውን ‹የሐሳብ መዋቅር› (Structure) ማየት የሚለውን አሁን እንጀምራለን፡፡ በዚህ ርዕስ ሥር ሁለት ነገሮች እንዳሉ በአስተዋፅዖው ላይ ቀደም ብለን አይተናል፡፡ እነርሱም ‹ሰዋስው› እና ‹የሥነ-ጽሑፉ ቅርጽ (ዐይነት)› የሚባሉት ናቸው፡፡ ሐሳብ መዋቅር አለው እንዴ የሚል ጥያቄ በውስጣችን ሊፈጠር ይችላል? አዎን! የሐሳብ መዋቅር ስንል በአእምሮአችን ውስጥ ያሉትን ሐሳቦች በንግግርም ሆነ በጽሑፍ የምናስቀምጥበት የሐሳብ አቀማመጥ ሥርዓት ማለታችን ነው፡፡ ይህ ማለት ጸሐፊው የምንባብ ክፍሎችን በዕቅድና በዓላማ አብሮ ሲያስቀምጥና ተመሳሳይ የሆኑ የምንባብ ክፍሎችን የሥርዓት አንድነት ሲያሳይ ነው፡፡

አንድ ነገር የራሱ የሆነ መዋቅር፣ ቅርጽ ወይም ይዘት ይኖረዋል፡፡ ለምሳሌ ሰው፣ ዛፍ፣ መኪና፣ አንበሳና ወፍ የራሳቸው ቅርጽ  እንዳላቸው ሁሉ፤ እንዲሁም ሐሳብ የራሱ የሆነ መዋቅር/ስትራክቸር አለው፡፡ በማንኛውም ቋንቋ ቢሆን ቃላት ያለ ዓላማና ዕቅድ አብረው ቢቀመጡ ምንም ትርጉም አይሰጡም፡፡ እስቲ ይህን የቃላት ስብስብ ትርጉም ከሰጣችሁ ተመልከቱት፡፡ ‹ላሉት በክርስቶስ የለባቸውም እንግዲህ ኩነኔ አሁን ኢየሱስ›፣ ያለ ሥርዓት ተቀምጦ የነበረውን በሰዋስው ሥርዓት ስናስቀምጠው ይህን ይመስላል ‹‹እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም›› (ሮሜ 8፡1)፡፡  ሁሉም ሕዝብ በቋንቋው የራሱ የሆነ የሰዋስው ሥርዓት አለው፡፡ ያለ ሰዋስው ሥርዓት መግባባት በፍጹም አስቸጋሪ ነው፡፡ ለምሳሌ በእንግሊዝኛ የሰዋስው ሥርዓት በሚከተለው ዐረፍተ-ነገር እንመልከት፣ (Abebe went to school) መጀመሪያ ባለቤት (Abebe)፣ ግሥ (went) እና ቀጥሎ ተሳቢ (to school) የሚሉትን በሰዋስው ሕግ እንደዚህ ተቀምጠው የምናገኝ ሲሆን፤  በአማርኛችን የሰዋስው ሥርዓት ደግሞ መጀመሪያ ባለቤት፣ ተሳቢና መጨረሻ ላይ ግሥ ይቀመጣል፡፡ (አበበ ወደ ትምህርት ቤት ሄደ)፡፡ በዚህ ሥፍራ ስንመለከት እንግሊዝኛውና የአማርኛው ግሥና ተሳቢ ሥፍራቸውን ለዋውጠው እናገኛለን፡፡

  በሐሳብ አወቃቀር/አቀማመጥ ውስጥ የምንመለከታቸው አስፈላጊ መዋቅሮች ሁለት ዐይነት ናቸው፤ እነርሱም ሰዋስውና የሥነ-ጽሑፍ ቅርጽ የሚባሉት ናቸው፡፡ እነዚህን ሁለቱን ትተን ወይም አያስፈልጉንም ብለን መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት አስቸጋሪ ይሆንብናል፡፡  ወደድንም ጠላንም በየዕለቱ የምንጠቀምባቸው ስለሆኑ፣ መጠቀም ነው ያለብን፡፡

 3.1 ሰዋስው፡- ሰዋስው ማለት ምን ማለት ነው ብለን ብንጠይቅ፣ ሰዋስው በየዕለቱ በንግግራችን የምንጠቀምባቸው  ስምንቱ የንግግር ክፍሎች ናቸው፡፡ ሰዋስው በምንልበት ጊዜ የእያንዳንዱን የቃላት አንድነት ማለታችን ነው፡፡ አንድ ዐረፍተ ነገር ቢያንስ ከስምንቱ የንግግር ክፍሎች በሁለቱ ይመሠረታል፡፡ ስለዚህ አንድ ዐረፍተ ነገር ቢያንስ ሁለት ነገሮችን መያዝ አለበት፤ ባለቤትና ማሠሪያ አንቀጽ (ግሥ) የግድ መኖር አለባቸው፡፡ አለበለዚያ ግሥ ከሌለው የባለቤቱ ድርጊት ምን እንደ ሆነ አይታወቅም፡፡ ‹‹ኢየሱስ ሄደ›› ብለን ብንጽፍ ባለቤትና ግሥ ይሆናል፡፡ ‹‹ኢየሱስ በርጤሜዎስን ፈወሰ›› ብለን ብናስቀምጥ ባለቤት ተሳቢና ግሥ ይሆናል፡፡ አንድ አንቀጽ (Pharagraph) ባለቤትን፣ ግሥን፣ ተውሳከ ግሥን፣ ቅጽልን፣ ተሳቢን፣ ገላጭ፣ አገናኝ/አያያዥና ንዑስ አንቀጽ (Phrase) የመሳሰሉትን ይይዛል፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት በየዕለቱ በምንጠቀምበት የሰዋስው ሕግ ላይ ሁላችንም መጠነኛ ዕውቀት እንዲኖረን ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ተውላጠ ስምና ግሥ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ብናደርግ የምናነበውንና የምናጠናውን ክፍል በሚገባ ልንረዳው እንችላለን፡፡

  ተውላጠ ስም ላይ የበለጠ ትኩረት ማድረግ ያለብን፣ ስምን ተክተው ስለሚገቡ ማንን እንደተኩ ካልገባን ሐሳቡን  በትክክል መረዳት ያስቸግረናል፡፡ ለምሳሌ 1ኛ ዮሐንስ 3፤24 ላይ ያለውን እንመልከት፡፡ ‹‹ትእዛዙንም የሚጠብቅ በእርሱ ይኖራል እርሱም ይኖርበታል፤ በዚህም በእኛ እንዲኖር ከሰጠን ከመንፈሱ እናውቃለን›› የሚለው ጥቅስ ውስጥ በእርሱእርሱም የሚሉ ተውላጠ ስሞች ማንን ነው የሚያመለክቱት ብለን ዐውዱን በሚገባ እየተመለከትን ብንጠይቅ መልሱ ‹እግዚአብሔር› የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በቁጥር 20 እና 21 ላይ እግዚአብሔር የሚለውን ስም እናገኘዋለን፣ እንዲሁም ቁጥር 23 ላይ ‹በልጁ› የምትለው ቃል በዐውዱ የትእዛዙ ባለቤት ክርስቶስ እንዳልሆነ ይጠቁመናል፡፡ በዚህ ሥፍራ እርሱ የሚለውን ተውላጠ ስም ብዙ ጊዜ  ክርስቶስ ነው ብለው የሚያስቡና የሚተረጉሙ አጋጥሞኛል፡፡

 ሁለተኛው ከፍተኛ ትኩረት ልናደርግበት የሚገባው ግሥ ላይ ነው፣ ምክንያቱም ግሥ ድረጊትን ገላጭ ስለሆነ ነው፡፡ የድርጊቱ ባለቤት ማን እንደ ሆነና ድርጊቱ ምን እንደ ሆነ ያለ ግሡ ማወቅም አንችልም፡፡ ድርጊቱ የኃላፊ፣ የአሁንና የወደፊት መሆኑን የምናውቀውም በግሡ ነው፡፡ ሁሉም የንግግር ክፍሎች አስፈላጊዎች ቢሆኑም ይበልጥ ትኩረት ልንሰጣቸው የሚገቡ እንዳሉ ልንረዳ ይገባናል፡፡

 በዚህ ክፍል ዓላማዬ ሰዋስው አስፈላጊ መሆኑን ለማሳየት ነው እንጂ፣ ስለ ሰዋስው ሰፊ ትምህርት ለመስጠት ፈልጌ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ስም፣ ተውላጠ ስም፣ ግሥ፣ ተውሳከ ግሥ፣ ቅጽል፣ መስተዋድድ፣ መስተፃምርና ቃለ አጋኖ ሁሉ ጠቃሚዎች ናቸው፡፡ በትምህርት ቤት ተምረናቸው የረሳናቸው ቢሆኑም፣ ቃሉን በይበልጥ ለመረዳት አንዳንድ የሰዋስው መጻሕፍትን ብናይ የበለጠ ተጠቃሚዎች እንሆናለን፣ በተለይ ሌሎችን የምናስተምር አገልጋዮች ብዙ ስለሚጠበቅብን፣ የቃሉን የሰዋስው አገባብ በሚገባ እየተመለከትን ለማስተማር ጥረት ብናደርግ፣ የምናገለግላቸውን ምዕመናን በቃሉ ላይ እንዲመሠረቱ ማድረግ እንችላለን፤ እኛም በአገልግሎታችን ውጤታማና ፍሬአማ እንሆናለን፡፡

 የሚቀጥለውን የሐሳብ መዋቅር በሚለው ሥር ያለውን፣ ሁለተኛውን ‹የሥነ-ጽሑፍ ቅርጽ› የተባለውን  ከማየታችን በፊት፣ አሁን በተማርነው መሠረት ሁላችንም በራሳችን የምንሠራውን አቅርቤላችኋለሁ፡፡

1. ኢሳይያስ 7፡13 ላይ ተመልከቱ ‹‹እርሱም አለ፡- እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፡- ስሙ በውኑ ሰውን ማድከማችሁ ቀላል   ነውን? ‹‹እርሱም›› የሚለው ተውላጠ ስም ማንን ነው የሚያመለክተው?

2. ኤፌሶን 4፡1 ላይ ተውላጠ ስምና ቅጽል የሆነውን ቃል አውጡ፡፡ 3. በማርቆስ 1፡14-15 ላይ ያለውን ተመልከቱና የድርጊቱን ባለቤት፣ ግሥ፣ ተውሳከ ግሥና ቅጽል የሆኑትን አውጡ፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *