በባለፈው ጥናቶቻችን በተወሰኑ ክፍሎች ላይ በየጊዜው ምልከታዎች እንድታደርጉ መሰጠታቸው የሚታወስ ነው፡፡ ምን ያህል እንደ ጠቀማችሁ ባላውቅም፣ በትምህርቶቹ ጠቃሚ ነገር ካገኛችሁ፣ በየጊዜው ሠርታችሁ እንደምትጠብቁ እርግጠኛ ነኝ፡፡ አለበለዚያ ከዚህ የሚሰጠውን ብቻ የምትጠብቁ ከሆነ፣ ብዙ ተጠቃሚዎች ላትሆኑ ትችላላችሁ ብዬ አስባለሁ፡፡
በመጀመሪያ በዘዳግም ምዕራፍ 28 ላይ ትእዛዝና ማስጠንቀቂያ የሆኑትን እንድትመለከቱ በተሰጠው መሠረት ምን አገኛችሁ? በምዕራፍ 27 ከቁጥር 16-26 ያሉት ትዛዞች (ሕጎች) ከመሰጠታቸው በፊት በዘጸዓት፣ በዘሌዋውያንና በዘኊሉቅ ላይ ከተሰጡት ተጨማሪና የተደገሙ ሕጎች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ትእዛዛት ሲሰጡ አዎንታዊና አሉታዊ የሆነ ሁለት መልክ አላቸው፡፡ በዚህ ምዕራፍ ላይ አዎንታዊ የሆኑትን ትእዛዛት ሲገልጽ የተጠቀመባችው ቃላት፣ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 3፡2 ላይ የተጠቀመባቸውን ዓይነት ሳይሆን ለየት ባሉ ቃላቶች ተጠቅሞአል፡፡ ለአዎንታዊ ትእዛዝ ብትሰማ፣ ብታደርግ፣ ብትጠብቅ፣ ብትሄድ … ሲል ለአሉታዊው ደግሞ ፈቀቅ ባትል፣ ባትከተል፣ ባትሰማ፣ ባትጠብቅ፣ ባታደርግ … በማለት ያስቀምጣል፡፡ ስለዚህ ትእዛዝና ማስጠንቀቂያ የሆኑት ላይ ትኩረታችንን ብናደርግ ዋናውን ሐሳብ መረዳት እንችላለን፡፡ ትእዛዙን በመጠበቅ በረከት ሲኖር ባለመጠበቅ መርገም እንደሚኖር መረዳት እንችላለን፡፡
ሁለተኛው በኤፌሶን ምዕራፍ 1፡16-23 ባለው ክፍል ላይ ‹‹ጸሎትና ልመና›› የሆኑትን በማውጣት ምልከታ እንድናደርግ፣ በተሰጠው መሠረት ክፍሉን ስናየው በሙሉ ጸሎትና ልመና መሆኑን መረዳት አያስቸግርም፡፡ ጳውሎስ በእስር ቤት ሆኖ እንደሚጸልይ ‹‹ስጸልይ›› የምትለው ቃል መጸለዩን ስታመለክት፣ በሁለተኛ ደረጃ የታሠረው ጳውሎስ ላልታሠሩት ለኤፌሶን አማኞች እንደሚማልድ ‹‹ስለ እናንት ማሳሰብን አልተውም›› የሚለው ሐረግ ልመናውን ያመለክታል፡፡ በተጨማሪ ሌላውን የጳውሎስን ጸሎት በኤፌሶን ምዕራፍ 3፡14-19 ያለውን ተመልከቱ፡፡
ሦስተኛው በዮሐንስ ራዕይ 3፡12-13 ላይ ያለውን ‹‹የተስፋ ቃል›› ለመረዳት አያስቸግርም፡፡ ‹‹ድል የነሣው በአምላኬ መቅደስ ዓምድ እንዲሆን አደርገዋለሁ፣ ወደ ፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም ማለት ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን፣ አዲሱንም ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ›› ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በክብሩ ሲመጣ በታማኝነትና በጽናት በድል ለሚያልፉት የገባው ‹‹የተስፋ ቃል›› እንደሆነ እናያለን፡፡
10) ጥያቄና መልስ፡-
በዛሬው ዕለት በመቀጠል ሦስት አዳዲስ ምልከታዎችን እናደርጋለን፡፡ የመጀመሪያው ጥያቄና መልስ የሆኑትን ለይቶ ማውጣት ይሆናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና ጥያቄና መልስ የሆኑ ክፍሎችን እናገኛለን፡፡ ቃሉ ራሱ ጠይቆ ራሱ መልስ ስለሚሰጥ ለሚጠይቀው ጥያቄ መልስ መፈለግ አይጠበቅብንም፡፡ ኢሳይያስ ምዕራፍ 40 ከቁጥር 18-26 ባለው ክፍል ላይ ምልከታችንን እናድርግ፡፡ ቁጥር 18 ላይ ‹‹እንግዲህ እግዚአብሔርን በማን ትመስሉታላችሁ? ወይስ በምን ምሳሌ ታስተያዩታላችሁ? ብሎ ይጠይቅና ቁጥር 19 እና20 ላይ በሰው ስለ ተሠራ ምስል ገለጻ ከሰጠ በኋላ ከቁጥር 21-24 ባለው ክፍል መልሱን ይሰጣል፡፡ መልሱ ጥያቄያዊ መልስ ነው እንጂ ጥያቄ አይደለም፡፡ ‹‹አላወቃችሁምን? ወይስ አልሰማችሁምን? ከጥንትስ አልተወራላችሁምን? ወይስ ምድር ከተመሠረተች ጀምሮ አላስተዋላችሁምን?›› እያለ እስከ ቁጥር 24 ድረስ መልሱን ይቀጥላል፡፡
እንደገና ቁጥር 25 ላይ ‹‹እንግዲህ እተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ?›› በማለት ሌላ ጥያቄ ያቀርብና ቁጥር 26 ላይ ‹‹ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ›› ብሎ ‹‹እነዚህን የፈጠረ ማን ነው?›› በማለት እንደ መጀመሪያው ጊዜ ጥያቄያዊ መልስ ሰጥቶ ሐሳቡን ይቀጥላል፡፡ በዚሁ ምዕራፍ በመቀጠል ቁጥር 27 ላይ ሌላ ጥያቄ ይጠይቅና ከቁጥር 28 እስከ 29 መልሱን ያቀርባል፡፡ እነዚህ ጥያቄዎችና መልሶች ዋናውን ሐሳብ/ትልቅ ቁም ነገር እንድንረዳ ይጠቁሙናል፡፡
ስለዚህ በንባባችሁና በጥናታችሁ ጥያቄና መልስ የሆነ ክፍል ስታገኙ ዋናውን ሐሳብ ጠቋሚዎች ስለ ሆኑ ትኩረት ስጡት፡፡
11) ቃላት አገናኝ፡-
ቃሉን ስናጠና በምልከታችን ቃላትን ከቃላት፣ ሀሳብን ከሀሳብ የሚያገናኙትን ፊደልና ቃላት ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የተለያዩ የውድድር፣ (እንደ፣ ተመሳሳይ፣ ደግሞ፣ ና፣ ም) የንጽፅር፣ (ነገር ግን፣ ሆኖም፣ ቢሆንም፣ ይሁንና) የምክንያትና (ስለ፣ ስለዚህ፣ እንግዲህ) ጊዜን የሚያመለክቱ (በፊት፣ በዚያን ጊዜ፣ በኋላ) ቃላት አገናኝ የምንላቸው አሉ፡፡ አንድ ፊደል ምን ያህል ትርጉም እንደምትሰጥና እንደምታዛባ ቀጥለን እንመልከት፡፡ ‹‹ና›› የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 13፡46 ላይ ‹‹ጳውሎስና በርናባስም ገልጠው የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ ይነገር ዘንድ ያስፈልጋል …›› በሚለው ጥቅስ ውስጥ ‹ና› የምትለው ፊደል ጳውሎስንና በርናባስን አያይዛለች፡፡ ማነው ቃሉን የገለጠው ብለን ብንጠይቅ ጳውሎስ ነው የሚል መልስ ብቻ ሳይሆን፣ በርናባስም ጭምር እንዳለበት ‹ና ›የምትለው ፊደል ታሳየናለች፡፡
ከቃላት ያነሱት ፊደሎች ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑና ትርጉም ሊያዛቡ እንደሚችሉ ሌላም ጨምረን እንመልከት፡፡ በሐዋርያት ሥራ 1፡8 ላይ ቀደም ብለን በሌላ መልኩ፣ በሰባት የመጠየቂያ ቃላት በመጠቀም ምልከታ ማድረጋችን ይታወሳል፡፡ ‹‹…ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፣ በኢሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ›› በዚህ ክፍል ውስጥ ‹ም› የተባለችው ፊደል የምትሰጠውን የተለየ ትርጉም እንመልከት፡፡ የታላቁ ተልዕኮ ትእዛዝ አሰጣጥን ስንመለከት፣ ከኢሩሳሌም ጀምሮ እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ የሚለው፣ በቅደም ተከተል መከናወን እንዳለበት ያመለክተናል፡፡ እኛም ስለ ለመድነው ሁልጊዜ በቅደም ተከተል ነው ፣ የምንረዳው፣ የምናስቀምጠውና የምንሰብክበት፡፡ ከዚህ በላይ ከፍና ጐላ ብላ በእያንዳንዱ ስም ላይ ያለችው ‹ም› ደግሞ የምታመለክተው ወንጌሉ በአንድ ጊዜ በሁሉም ሥፍራ መሰበክ እንዳለበት የምትጠቁም ናት፡፡ (በእንግሊዝኛው አንዳንዶች ‹both› ሲሉ፣ ሌሎች ‹all› ብለው ይጠቀማሉ፡፡) ወንጌሉ በቅደም ተከተል ተራና በአንድ ጊዜ በሁሉ ሥፍራ መሰበክ እንዳለበት የቃሉ የሰዋስው አገባብ ያመለክተናል፡፡
12) የግሥ ጊዜያት፡-
መጽሐፍ ቅዱስን በምናጠናበት ጊዜ የግሥ ጊዜያት ላይ ትኩረት ማድረግ አስፈላጊና ተገቢ ነው፡፡ ወደፊት ስለ ሰዋስው ስናጠና በስፋት የምናየው ቢሆንም፣ በዚህ ጊዜ የግሥ ጊዜያትን እንደ አንድ ምልከታ አድርጌ መውሰድ እፈልጋለሁ፡፡ አንድ ድርጊት ከእነዚህ ሦስት የግሥ ጊዜያቶች በፍጹም ሊወጣ አይችልም፡፡ ስለዚህ አንድን ድርጊትን ስናጠና በኃላፊ፣ በአሁንና በወደፊት የተነገረ ወይም የተደረገ መሆኑን ማስተዋል እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ይህን ሐሳብ የበለጠ ለመረዳት ባለፈው የተመለከትነውን በሐዋርያት ሥራ 1፡8 ላይ ያለውን መመልከቱ ቀላል ያደርገዋል፡፡ ‹‹…ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፣ በኢሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ›› አንድን ክፍል ደጋግሜ የምጠቀመው ሐሳቡን የተመለከትነው ስለሆነ በቀላሉ ቶሎ ወደ መረዳት እንድንመጣ ብዬ ነው፡፡ የዚህን ክፍል የግሥ ጊዜያት ስንመለከት ለሐዋርያት የወደፊት መሆኑን የሚያሳዩት ቃላቶች ‹በወረደ ጊዜ› እና ‹ትቀበላላችሁ› የሚሉት ሲሆኑ፣ ለእኛ ደግሞ ‹በወረደ ጊዜ› ኃላፊ ነው፡፡ ይህ ማለት መንፈስ ቅዱስ የሚወርደው አንድ ጊዜ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ በበዓለ ኀምሳ ቀን የወረደው መንፈስ ቅዱስ ተመላሶ አልሄደም፤ ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ በመጨረሻ በፋሲካው በዓል አብሯቸው ከተካፈለ በኋላ፣ በዮሐንስ 14፡16 ባለው ክፍል ስለ አጽናኙ ሲናገር እንዲህ አለ፡፡ ‹‹እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል›› ስለዚህ ከዚህ ቀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ ተለይቶአቸው አያውቅም፡፡
ዛሬ ይህን ጥቅስ ስናነብ የመንፈስ ቅዱስ መውረድ ለእኛ ኃላፊ ነው፤ በየዘመናቱ ሰዎች በጌታ ሲያምኑ በበዓለ ኀምሳ ቀን የወረደውን መንፈስ ቅዱስ ይቀበላሉ እንጂ በበዓለ ኀምሳ ቀን እንደ ወረደው ዓይነት እንደ አዲስ በየጊዜው አይወርድም፡፡ እኛ ስናምን መንፈስ ቅዱስ ጌታ በገባው የተስፋ ቃል መሠረት የአካሉ ብልት እንድንሆን ያጠምቀናል፣ ምስክሮቹ እንድንሆን በኃይሉ ይሞላናል፡፡ ጌታ መጥቶ እስኪወስደን ድረስ እርሱ (መንፈስ ቅዱስ) በምድር ሥራውን እያከናወነ አለ፡፡ ስለዚህ እንድን ክፍል ስናጠና የግሥ ጊዜያት ላይ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባ እንደሆነ መረዳት ይኖርብናል፡፡
በሚቀጥለው ጊዜ የመጨረሻዎቹን ምልከታዎች ከማየታችን በፊት ከዚህ በላይ ባደረግናቸው ምልከታዎች አንዳንድ ተጨማሪ ምልከታዎችን አድርገን እንምጣ፡፡ በተቻለ መጠን ጊዜ ሰጥታችሁ ለመሥራት ሞክሩ፣ ታድጉበታላችሁ፡፡
- በሮሜ 6 ላይ ምዕራፉን በሙሉ ተመልክታችሁ ‹ጥያቄና መልስ› የሆኑትን አውጡ፡፡
- በሐዋርያት ሥራ 11፡30፣ 15፡6፣22፣ ሮሜ 8፡1-11 ላይ ምልከታ አድርጋችሁ አያያዥ ፊደልንና ቃላትን ጠቁሙ፡፡
3. በማቴዎስ 1፡21-23 ያለውን ክፍል ተመልከቱና የግሥ ጊዜያቱን አውጡ፡፡
0 Comments