ተልዕኮው የእግዚአብሔር ሰዎችን የማዳን ዕቅድ እንደሆነ ከዚህ በፊት ቀደም ብለን አይተናል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተልዕኮን ከአባቱ ተቀብሎ ወደዚህ ዓለም በመምጣት ደቀ መዛሙርቱን ለሦስት ዓመት ተኩል በማሰልጠን ካሳለፈ በኋላ ተልዕኮውን ለእነርሱ አስተላለፈው፡፡ ይህን ተልዕኮ ወንጌላት በጹሑፋቸው በሚከተሉት ሁኔታ በተለያየ መንገድ ገልጸውታል፡፡ ማቴዎስ ታላቁ ተልዕኮ ብለን የምንጠራውን እንዲህ አስቀምጦታል፡፡ ‹‹እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው›› 28፡19. ማርቆስ ‹‹ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ›› (16፡15) ሲል ሉቃስ ደግሞ ‹‹… በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል … እናንተም ለዚህ ምስክሮቼ ናችሁ›› (24፡47-48). በማለት ገልጸውታል፡፡ ዮሐንስም ደቀ መዛሙርት በወልድ፣ ወልድም በአብ መላካቸውን እንዲህ ሲል ጽፎታል ‹‹… አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ›› (20፡21)
ሉቃስም በሐዋርያት ሥራ በሌላ መልኩ እንዲህ በማለት ያስቀምጠዋል፡፡ ‹‹… መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፣ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ፡፡›› (ሐዋ.ሥራ 1፡8) ታላቁ ተልዕኮ በዚህ መልክ ተቀምጦ ስናይ በጣም ቀላል ይመስላል እንጂ ከባድ ኃላፊነትን የሚጠይቅ አገልግሎት ነው፡፡ ኃላፊነቱንም በሁለት መልኩ ማየት ይቻላል፣ የመጀመሪያው ኃላፊነት የእግዚአብሔር ሲሆን ሁለተኛው የሰው ነው፡፡ ይህም ተልዕኮው እንዲሳካ ሁለት አስፈላጊ ነገሮች በዚህ ጥቅስ ውስጥ ተጠቅሰው እናገኛለን፡፡ የመጀመሪያው የመንፈስ ቅዱስ መውረድ ኃላፊነት የጌታ ሲሆን፣ ሁለተኛው ምስክር መሆን የሚለው ኃላፊነት የሰዎች መሆኑን ማየት እንችላለን፡፡ በመቀጠል በዚህ ክፍል የተልዕኮው መነሻና መድረሻ በግልጽ ተቀምጦ እናገኛለን፡፡
እነዚህን ሁሉ ወደ ፊት በስፋት የምናያችው ይሆናል፣ ይህን ተልዕኮ ለመወጣት ስንት ዓመት ይፈጅ ይሆን? እንዴትስ ይወጡት ይሆን? ምንስ ችግር ይገጥማቸው ይሆን? የተሰጠውስ ተስፋ ሲፈጸም ምን ለውጥ ይመጣ ይሆን? ትኩረታችንን ጠበብ አድርገን ሁለት ቤተ ክርስቲያናትን ብቻ በስፋት እንደምናይ ቀደም ብዬ ገልጫለሁ፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዋና ትኩረት በኢየሩሳሌምና አንጾኪያ ቤተ ክርስቲያናት ብርታት እንዲሁም ድካም በምናገኛቸው ትምህርቶች ዙሪያ ላይ የተመሠረተ ሲሆን፤ በዚህ ዘመን የምንገኝ ግለሰቦችና ቤተ ክርስቲያናት ከሁለቱ ቤተ ክርስቲያናት የምንማራቸውን ቁም ነገሮች በጹሑፌ ለማካተት እሞክራለሁ፡፡ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን ታሪክ ዋና ጭብጥ ባጭሩ ከማስቀመጤ ባሻገር ክርስቲያኖችን ለወንጌል አገልግሎት (ታላቁ ተልዕኮ) ማነሣሣት ነው፡፡
0 Comments