ባለፈው ጥናታችን ‹‹ተከታታይ›› በሚለው ምልከታችን ማቴዎስ 13 መስጠቴን አስታውሳለሁ፤ እናንተም ምልከታ አድርጋችሁ እንደ መጣችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አስቀድሜ የምትሠሩትን መስጠቴ የበለጠ እንድትማሩበት ያደርጋችኋል ብዬ ነው፡፡ እናንተ አስባችሁበት ካልመጣችሁ ተቀባይ ብቻ ትሆናላችሁ፡፡ ሠርታችሁ ከመጣችሁ ልክ  ያልሆናችሁትን መለየት ትችላላችሁ፡፡ በዚህ ማቴዎስ 13 ላይ ስለ መንግስት ሰማያት ለመግለጥ ቁ.3 የዘሪውን ቁ.24 የስናፍጭዋን፣ ቁ.33 የእርሾውን፣ ቁ.44 የተሰወረውን መዝገብ፣ ቁ.45 የዕንቁ ነጋዴውን፣ ቁ.47 ወደ ባሕር የተጣለውን መረብ ምሳሌ በማከታተል አቀረበላቸው፡፡ ስለዚህ በዚህ ክፍል ውስጥ ‹‹መከታተል›› በሚለው ምልከታችን የተከታተሉት ነገሮች ጐልተው ይታያሉ፡፡

 በሁለተኛ ‹‹በድርጊትና ውጤት›› ምልከታ እንድናደርግ የተሰጠን ክፍል ቲቶ 2፡11-12 ላይ ነበር፡፡ ይህን ክፍል ስንመለከት ‹‹ድርጊቱ›› የእግዚአብሔር ጸጋ መገለጡ ሲሆን፣ ‹‹ውጤቱ›› እግዚአብሔርን በመምሰል መኖራችን ነው፡፡ በመደበኛው ትርጉም በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት መኖራችን ይለዋል፡፡ (ወደፊት ስለ ተለያዩ ትርጉሞች አመጣጥና አጠቃቀም መቼና ለምን መጠቀም እንዳለብን በስፋት እናያለን፡፡)

በሦስተኛ እንድንሠራው የተሰጠን ክፍል ማቴዎስ 5፡17-48 ሲሆን ቀደም ብለን በድግግሞሽ ያየነውን፣ አሁን ደግሞ በጠቅላላና በዝርዝር ምልክታ እንድናየው ነበር፡፡ ቀደም ብላችሁ ስለ ሠራችሁት ዋናውን ሐሳብ አግኝታችኋል፡፡ ስለዚህ ይቀላችኋል ብዬ አስባለሁ፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ጠቅላላውን ሐሳብ የሚጠቁሙን ቁጥር 17 እና 20 ናቸው፡፡ እነርሱም እንዲህ ይላሉ ‹‹እኔ  ሕግንና ነብያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም፡፡›› ቁ.17 በመቀጠል ‹‹ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም፡፡›› ቁ.20. በዚህ ክፍል ላይ ስንመለከት ጠቅላላው ሐሳብ ‹‹ሕግና ጽድቅ›› የሚሉት ሲሆኑ፣ ማመንዘር፣ ፍቺ፣ መሐላ፣ በቀልና ጠላትን መውደድ የሚሉት ዝርዝር ሐሳቦች ናቸው፡፡

7) ትዕዛዝ/ማስጠንቀቂያ ፡-

    በመቀጠል ዛሬ ሦስት ምልከታዎችን እንጨምራለን፡፡ እነዚህም ምልከታዎች ቀለል ያሉ ናቸው፡፡ መጀመሪያው ትእዛዝና ማስጠንቀቂ ሲሆኑ፣ መጽሐፍ ቅዱሳችን ብዙ ቦታ በቀጥታ ትዕዛዝ ወይም ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፣ ሁለቱንም በአንድ ላይ ወይም ለየብቻ ሊሰጥም ይችላል፡፡ በትእዛዙ ውስጥ ውዴታና ግዴታም ይኖረዋል፡፡ በአፌሶን 4፡25-32 

                       – ውሸትን አስወግዱ                 

                       – እውነትን ተነጋገሩ                 

                       – ኃጢአትን አታድርጉ

                  – በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ                       

                  – የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ

                  – መልካምን እየሠራ ይድከም

                  – ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ

                  – የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ

                  – … ከእናንተ ዘንድ ይወገድ       

                  – ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ

                  – ይቅር ተባባሉ የተባሉት ሁሉ ትእዛዞች ናቸው፡፡

  ሁለተኛው ምልከታ የምናደርገው ማስጠንቀቂያ የሚለውን ይሆናል፡፡ ይህንንም በቀላሉ ብዙ ቦታ ላይ እናገኘዋለን፡፡  ሐዋርያው ጳውሎስ የፊልጵስዩስን አማኞች እንዲህ እያለ ያስጠነቅቃል፡፡ ‹‹ከውሾች ተጠበቁ›› ‹‹ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ›› ‹‹ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ›› ፊልጵስዩስ 3፡2. ከዚህ በላይ ያየናቸው ትእዛዞችና ማስጠንቀቂያዎች ትኩረት እንድንሰጣቸው የሚገባንን የሚጠቁሙን ምልከታዎች ናቸው፡፡

 8)  የተስፋ ቃል ፡-

    በመቀጠል ምልከታ የምናደርገው ‹‹በተስፋ ቃል›› ይሆናል፤ መጽሐፍ ቅዱሳችን ከዘፍጥረት ጀምሮ በእያንዳንዱ መጽሐፍ ውስጥ የተስፋ ቃል እናገኛለን፡፡ ወደፊት ሊሰጠንና ሊያደርግልን ያሰበውን የተስፋ ቃል ሲይዝ ትኩረት ልንሰጠው ይገባል፡፡ በኢያሱ 1፡3 ላይ እግዚአብሔር በኢያሱ በኩል ለእስራኤል ሕዝብ የገባውን የተስፋ ቃል እናገኛለን፡፡ ‹‹ለሙሴ እንደ ነገርኩት የእግራችሁ ጫማ የሚረግጠውን ቦታ ሁሉ ለእናንተ ሰጥቻለሁ፡፡››

 በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14፡ ቁጥር ላይ 14 ‹‹ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ››፣ ቁጥር 15 ‹‹እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል››፣ ቁጥር 27 ‹‹ሰላምን እተውላችኋለሁ፣ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፣ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም፡፡››  የተስፋ ቃል ካገኘን በውስጡ ያለውን እውነት ስለሚጠቁመን ትኩረት ልናደርግበት ይገባል፡፡ ያንንም ተስፋ እንዴት ማግኘት እንዳለብንም ማሰብ አለብን፡፡

9) ጸሎት/ልመና፡-

    ዛሬ በመጨረሻ የምናደርገው ምልከታ ጸሎትና ልመና የሚል ይሆናል፤ ብዙ ጊዜ ሲሰበክ የምንሰማውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የካህንነቱን ጸሎት እንመለከታለን፡፡ ወደ እግዚአብሔር የሚደረግ ጸሎት ወይም ልመና ሲያመለክት በውስጡ ያለውን ሐሳብ ለመረዳት አያስቸግርም፡፡ ዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 17 ላይ ምልከታ ስናደርግ፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ጸሎትና ልመና እናገኛለን፡፡ ጸሎቱ በሦስት ይከፈላል፤ ከቁጥር 1-5 ስለ ራሱ ይጸልያል፣ ከቁጥር 6-19 ባለው ክፍል ላይ በአጠገቡ ስለ አሉ ደቀ መዛሙርት ይለምናል፣ ከቁጥር 20-26 ባለው ክፍል በአጠገቡ ስለ ሌሉ ደቀ መዛሙርት ይለምናል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እርሱ ተመልሶ እንከሚመጣበት ጊዜ ድረስ በእርሱ ለሚያምኑት ሁሉ ወደ አባቱ ልመና አቅርቧል፡፡ ለእኔና ለእናንተም ስለ ተጸለየለን ደስ ይበላችሁ፡፡

 ለሚቀጥለው ሳምንት ሠርተን የምንመጣው፣ የቤት ሥራ ሆኖ ታርሞ ማርክ ባይኖረውም፣ የራሳችንን መረዳት ለማሳደግ ሠርተን ብንጠብቅ መልካም ነው፡፡ ለሌሎችም የተማራችሁትን ብታካፍሉ የበለጠ ትማሩበታላችሁና ሞክሩት፡፡

  1. ዘዳግም ምዕራፍ 28 ን በሙሉ ምልከታ በማድረግ ትእዛዞችን ለማውጣት ጥረት አድርጉ፡፡
  2. ኤፌሶን ምዕራፍ 1፡16-23 ያለውን ተመልከቱና ያለውን ጸሎትና ልመና አውጡ፡፡

ዮሐንስ ራዕይ ምዕራፍ 3፡12-13 ያለውን ተመልከቱና የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል አውጡ፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *