- የተለያዩ ምልከታዎች ማድረግ
በሰባት መጠየቂያ ቃላት ከመጠቀም ቀጥሎ የምንመለከተው የተለያዩ ምልከታዎች ስለ ማድረግ ይሆናል፡፡ በዚህ መንገድ እየጠየቅን ስናጠና የነበረውን ማንኛውንም ክፍል፣ እንደገና የተለያዩ ምልከታዎች በማድረግ ማጥናት ያስፈልገናል፡፡ የአንድ ሰው በሽታ የሚታወቀው ልዩ ልዩ ምርመራ በማድረግ ነው፡፡ የተለያዩ በሽታዎች በተለያየ ምርመራ ይገኛሉ፡፡ በሽንት፣ በደም፣ በኤስሬ፣ በአልትራ ሳውንድና በሲቲ ስካን በመሳሰሉት ምርመራዎች ሲገኙ፣ ጨርሶም የማይገኙ በሽታዎችም ይኖራሉ፡፡ ችግሩ ባይገኝም መፍትሔ መፈለጉ ግን አይቆምም፡፡
እንደዚሁም የምናጠናውን ክፍል ለመረዳት በተለያዩ መንገዶች ምልከታ በማድረግ ማየት ይኖርብናል፡፡ አንዳንዱን በቀላሉ በሰባቱ የመጠየቂያ ቃላት በመጠቀም በቀላሉ ዋናውን ሐሳብ ማግኘት እንችላለን፡፡ አንዳንዱን ደግሞ የተለያዩ ምልከታዎች በማድረግ መልሱን እንደርስበታለን፡፡ አንዳንዱን ደግሞ የሐሳቡን መዋቅር በማየት አመርቂ የሆነ መልስ ልናገኝ ወደምንችልበት ደረጃ እንደርሳለን፡፡ ለአንዳንዱ ደግሞ በጥናታችን መልስ የማናገኝላቸው ሐሳቦች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
- የሚወዳደሩ፡-
የተለያዩ ምልከታዎች ከምናደርጋቸው የመጀመሪያው የሚወዳደሩ ነገሮችን ማየት ይሆናል፡፡ በምንባባችንና በምናጠናው ክፍል ውስጥ ተመሳሳይ ሆነው የሚወዳደሩ ነገሮች ካሉ ማየትና ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ መዝሙር 1፡1-6 ያለውን ክፍል በመጠይቆቹ በመጠቀም ጠይቃችሁ ከሆነ፣ ማን ጻፈው? ለማን ተጻፈ? ለምን ተጻፈ? የት? መቼ? እንዴት? ብላችሁ ብትጠቀሙም ረጂ መጻሕፍት ካልተጠቀማችሁ በስተቀር ከክፍሉ ብዙ የምታገኙት ነገር አይኖርም፡፡ ይህ የጽሑፍ ክፍል የሚመደበው ከጥበብ መጻሕፍት (ግጥም) ውስጥ ነው፡፡ እነዚህን መጻሕፍት ወደፊት በስፋት ወስደን እንዴት እንደምናጠናቸው እናያለን፡፡ አሁን ግን የሚወዳደሩና የሚነፃፀሩትን በቀላሉ ለማየት እንዲያስችለን የወሰድነው ክፍል ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ክፍል ለመረዳት ሌሎች ዘዴዎችንና ምልከታዎችን ማድረግ ያስፈልጋችኋል፡፡ የመጀመሪያው የሚወዳደሩና የሚነፃፀሩ ነገሮችን ብናይ ዋናውን ሐሳብ/እውነቱን ማግኘት ያስችለናል፡፡
1. ‹‹ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፣
በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፣
በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ፡፡
2. ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፣
ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል፡፡
3. እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፣
ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፣
ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል
የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል፡፡
4. ክፉዎች እንደዚህ አይደሉም፣
ነገር ግን ነፋስ ጠርጎ እንደሚወስደው ትቢያ ናቸው፡፡
5. ስለዚህ ክፉዎች በፍርድ፣
ኃጢአተኞችም በጻድቃን ማኅበር አይቆሙም፡፡
6. እግዚአብሔር የጻድቃንን መንገድ ያውቃል፣
የክፉዎች መንገድ ግን ትጠፋለች፡፡››
የዚህ ክፍል ዋና ሐሳብ ምንድን ነው? ዋና ሐሳቡን ለመረዳት ምን ዘዴ ተጠቀማችሁ? ዋና ሐሳቡን ለማግኘት በተመሳሳይ መልካቸው የሚወዳደሩ ሁለት ነገሮች አሉ፤ እነርሱን ማወቅ ከቻላችሁ ዋናውን ሐሳብ ማግኘት እንድትችሉ ይረዳችኋል፡፡
ምስጉን(መልካም) ሰው እና መልካም ዛፍ፣ ክፉ ሰው እና ትቢያ በተመሳሳይ መልካቸው ተወዳድረዋል፡፡
ጸሐፊው በዚህ ክፍል መልካም ሰውና መልካም ዛፍን ያወዳደረበት ቃል ‹‹እንደ›› የሚለውን ቃል ሲሆን፣ ሦስት ጊዜ ተጠቅሞበታል፡፡ እንደ ተተከለች፣ እንደምትሰጥ፣ እንደማይረግፍ የሚሉት ቃላቶች ሰውዬው፣ እንደ ዛፉ በሚሠራው ሥራ ሁሉ መከናወን እንደሚሆንለት ያመለክታል እንጂ፣ መልካም ሰው ዛፍ ነው አላለም፣ ተግባሩን ብቻ በተመሳሳይ መልኩ በማወዳደር አቅርቦ እናገኘዋለን፡፡
እንዲሁም ክፉ ሰውና ትቢያን ያወዳደረበትንም ስንመለከት እንደሚወስደው በሚለው ቃል እንደሆነ እናያለን፡፡ እዚህም ላይ ክፉ ሰው ትቢያ ነው አላለም፣ የተግባሩን መመሳሰል ብቻ አቅርቦ እናገኛለን፡፡ ‹‹እንደ›› እና ‹‹ትመስላለች›› የሚሉት ቃሎች ሁለት ተመሳሳይነት ያላቸውን ነገሮች ያወዳድራሉ፡፡
- የሚነፃፀሩ፡-
ሁለተኛ በዚህ ክፍል ቀጥለን ተቃራኒ ሆነው የሚነፃፀሩ ነገሮች ስላሉ እነርሱን ማውጣት ይጠበቅብናል፡፡ መዝሙር አንድ ለመዝሙረ ዳዊት ሁሉ መግቢያ ሐሳብ ነው፡፡ ጸሐፊው በመግቢያው ሁለት ነገሮችን በተቃራኒ መልካቸው በማነፃፀር ለሰዎች በሚገባ መንገድ አቅርቦአል፡፡ በዚህ መዝሙር ውስጥ ምስጉን ሰውና ክፉ ሰው ተነፃፅረዋል፡፡ (1፡1-6) ጸሐፊው ሁለቱን ሰዎች ለማነፃፀር የተጠቀመበት ‹‹ነገር ግን›› የሚለውን ቃል በመጠቀም ሲሆን፣ ቃላቶቹን በቁጥር ሁለትና አራት ላይ እናገኛቸዋለን፡፡ በቁጥር 6 ላይም ‹‹ግን›› በሚለው ቃል የጻድቃንን (መልካም ሰው) መንገድ ያውቃል፤ የክፉዎች መንገድ ግን ትጠፋለች በማለት፣ መልካምና ክፉ ሰውን አነፃፅሮአቸው እናገኛለን፡፡ በምንባባችንና በምናጠናው ክፍል ውስጥ የሚወዳደሩና የሚነፃፀሩ ነገሮች ካሉ ዋናውን ሐሳብ የሚጠቁሙን ይሆናሉ፡፡ ‹‹ነገር ግን›› የሚለው ቃል ሁለት ነገሮችን በተቃራኒ መልካቸው ያነፃፅራል፡፡ በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ እስከ መጨረሻው ድረስ ያሉትን መዝሙሮች ብንመለከት የተቃኙትና የተብራሩት ምስጉን፣ (ብፁዕ፣ የተባረከ፣ ጥበበኛ) ሰውና ክፉ (ሰነፍ) ሰው የሚለውን በማነፃፀር አቅርቦት እናገኛቸዋለን፡፡ (ወደፊት የጥበብን መጻሕፍት ጥናት ተመልከቱ)
- የሚደጋገሙ ፡-
በመቀጠል የምንመለከተው ምልከታ ድግግሞሽ ሲሆን፣ ያም አንድ ሀሳብ፣ ድርጊት፣ ስም፣ ሥፍራ … ተደጋግሞ ሲገኝ ትኩረት ልንሰጠው ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም የአንድ ነገር መደጋገም በጣም ጠቃሚነቱንና ዋናው ሐሳብ ያለው እዚያ ውስጥ እንደሆነ አጉልቶ ይጠቁመናል፣ ያመለክተናል፡፡ ምሳሌ 1ኛ ቆሮንቶስን ምዕራፍ 13 በሙሉ ብንመለከት ያለ ምንም ችግር በቀላሉ ተደጋግሞ የምናገኘው ቃል ‹‹ፍቅር›› ነው፡፡ ስለዚህ የክፍሉ ዋና ሐሳብ ያለው ፍቅር ላይ መሆኑን መረዳት አያስቸግረንም፡፡ በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ ያለውንም ክፍል ጨምረን ብንመለከት የተደጋገመውን ቃል እምነት እንደሆነ፣ አሁንም ሳንቸገር ማግኘት እንችላለን፡፡ አንድ ነገር ከተደጋገመ ጠቃሚ ሐሳብ ያለው መሆኑን ያመለክተናል፡፡
ከዚህ በላይ ተደጋግመው የምናገኛቸው ቃላቶች ናቸው፣ አሁን ደግሞ ድሪጊቶች ሲደጋገሙ የሚያመለክተውን ክፍል እንመለከታለን፡፡ በዘፍጥረት መጽሐፍ በምዕራፍ 12፤13፣እና 20፡2 እና 26፡7 ላይ ‹‹ውሸት›› ሦስት ጊዜ ተደጋግሞ እናገኛለን፡፡ ሁለት ጊዜ የዋሸው አብርሃም ሲሆን፣ አንዱን ጊዜ የዋሸው ልጁ ይስሐቅ ነው፡፡ ጸሐፊው እነዚህን የተደጋገሙ ውሸቶችን የዘገበበት ምክንያት አለው፡፡ ልጆች በቤተሰባቸው በመልካምም ይሁን በክፉ ባሕርይ ተቀርጸው እንደሚወጡ ያስተምረናል፡፡
ለዛሬው እነዚህን ሦስት ምልከታዎች፣ የሚወዳደሩ፣ የሚነፃፀሩና የሚደጋገሙትን ለማየት ሙከራ አድርገናል፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ ተጨማሪ ምልከታዎችን እናደርጋለን፡፡ እስከዚያው ድረስ በየቤታችን ሆነን የምንሠራቸውን አቅርቤአለሁ፡፡ 1) 1ኛ. ጴጥሮስ 1፡18-19 ባለው ክፍል ሀ) የሚወዳደሩትን ለ) የሚነፃፀሩትን ተመልከቱና አውጡ፡፡
2) ማቴዎስ 5፡21-48 የሚደጋገሙትን ሐሳቦች በማውጣት ዋናውን ሐሳብ ለመረዳት ጥረት አድርጉ፡፡ የቻላችሁትን ያህል ሞክራችሁ ራሳችሁን አዘጋጅታችሁ ጠብቁ፡፡ ጌታ ጸጋውን ለሁላችንም ያብዛልን፡፡
0 Comments