ባለፈው ጥናታችን ለመግቢያ ያህል የተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ ስናነብ ወይም ስናጠና ቃሉ እንዳይገባን ከሚያደርጉት ብዙ ምክንያቶች ውስጥ ዋና ናቸው ከምላቸው ውስጥ ሦስቱን ብቻ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ የትምህርቱን ዓላማ፣ አስተዋፅዖና መመልከት ከምንለው ክፍል  የመጀመሪያውን በሰባት መጠይቆች እየጠየቅን እናጠናለን፡፡

የትምህርቱ ዓላማ፡- አንባቢዎችን ስለ ግል የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥነ-አፈታትና አጠናን ዘዴ ለማስተማር ነው፡፡

 አንባቢዎች ትምህርቱን ሲጨርሱ ማወቅ ያለባቸው፡-

 1. አንባቢዎች ከአንድ ጥቅስ ጀምረው እስከ አንድ መጽሐፍ ድረስ አንድ ነጠላ (ዋና) ሀሳብ ይዘው በመመልከትና በመተርጎም ትርጉሙንና መልዕክቱን እንዲያጠኑት ለማድረግ ነው፡፡

 2.  አንባቢዎች የአተረጓጎምን ዘዴ በመረዳት የትርጉም ችግራቸውን ማቃለል እንዲችሉ ነው፡፡ 

 3. አንባቢዎች የማዛመድን መመሪያ በመረዳት ከማንኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ክፍል ወስደው መልእክቱን ከራሳቸው ጋር ማዛመድና መተግበር እንዲችሉ ነው፡፡

 የትምህርቱ አስተዋፅዖ፡-

 ሀ. መመልከት

  1. በሰባት የመጠየቂያ ቃላት መጠየቅ
  2. የተለያዩ ምልከታዎች ማድረግ
  3. የሐሳቡን መዋቅር(Structure) ማየት
    1. ሰዋሰውን ማየት
    1. ሥነ-ጽሑፉን ማየት

   ለ. መተርጎም

  1. ቃላትን
  2. ሰዋስውን
  3. ባህልን/ታሪካዊ መሠረትን
  4. ትምህርተ መለኮትን

    ሐ. ማዛመድ/ሥራ ላይ ማዋል

  1. በእኔና በእግዚአብሔር መካከል ስላለው ግንኙነት ምን ያስተምረኛል ብሎ መጠየቅ
  2. በእኔና በቤተ ሰቤ መካከል ስላለው ግንኙነት ምን ያስተምረኛል ብሎ መጠየቅ
  3. በእኔና በቤተ ክርስቲያኔ መካከል ስላለው ግንኙነት ምን ያስተምረኛል ብሎ መጠየቅ
  4. በእኔና በኅብረተ-ሰቤ መካከል ስላለው ግንኙነት ምን ያስተምረኛል ብሎ መጠየቅ

በእነዚህ ዘዴዎች በመጠቀም ማጥናት እንችላለን፡፡

ጌታ እንደ ረዳንና ዕድሜ እንደ ሰጠን መጠን፣ እነዚህን በአስተዋፅዖው ላይ ያየናቸውን ሁሉ ተራ በተራ ለመዳሰስ ጥረት እናደርጋለን፡፡ በዛሬው ዕለት የመጀመሪያውን ክፍል መመልከት በሚለው ርዕስ ሥር ካሉት ወስደን እንመለከታለን፡፡

 አንድ ወንድ አንዲትን ሴት ለማግባት ሲፈልግ፣ ዝም ብሎ ዘው ብሎ ከመግባቱ በፊት የሚመለከታቸው ነገሮች አሉት፡፡ አንዳንዱ መልክ፣ ሙያ፣ የቤተሰብ ሁኔታ፣ ዘር፣ የትምህርት ደረጃ፣ ባሕሪይና መንፈሳዊነቷን ይመለከታል፡፡ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ንባብና ጥናት ስንመጣም የምንመለከታቸው ብዙ ነገሮች ይኖራሉ፡፡

 በመመልከት ሥር የምናያቸው ዋናዎቹ ሦስት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው የምናነበውን ምንባብ በሰባት የመጠየቂያ ቃላት በመጠቀም መላልሶ መጠየቅ፣ ሁለተኛው የተለያዩ ምልከታዎች ማድረግ ሲሆን፣ ሦስተኛው የሐሳቡን መዋቅር ማየት ናቸው፡፡ አሁን አንድ ክፍል ወስደን በሰባት መጠየቂያ ቃላት እየጠየቅን እናጠናለን፡፡  

ሀ. መመልከት

  1. በሰባት የመጠየቂያ ቃላት መጠየቅ

 ቃሉን በተገቢው መንገድ ለመረዳትና ወደ መጽሐፉ ሐሳብ  እንድንደርስ ረጋ ብለን በማስተዋል ክፍሉን መመልከት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በምናጠናበት ጊዜ በመጀመሪያ ምንባቡን ቢያንስ ሦስት ጊዜ ማንበብ ይጠበቅብናል፡፡ ከዚያ በኋላ ያነበብነውን ክፍል በሚከተሉት ጥያቄዎች መጠየቅ አለብን፡፡ እነዚህ የመጠየቂያ ቃላት በየቀኑ የምንጠቀምባቸው ልምምዶቻችን ናቸው፡፡ ማን ነው የሄደው? ሄዶ ምን ተፈጸመ? የት ሄደ? መቼ ሄደ? እንዴት ሄደ? ለምን ሄደ? በማለት ተጠቅመን ሰዎችን የምንጠይቅባቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ የምናውቃቸውን የመጠየቂያ ቃላቶች ለመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችንና ጥናታችን እንድንጠቀምባቸው፣ አሁን በፊታችን ቀርበዋል፡፡

   ማን? – ብለን ስንጠይቅ የድርጊቱን ባለቤት ለማግኘት

   ምን? – ብለን ስንጠይቅ ድርጊቱን ለማግኘት

   የት?  – ብለን ስንጠይቅ ድርጊቱ የተፈጸመበትን ሥፍራ  ለማወቅ

  መቼ?  – ብለን ስንጠይቅ ድርጊቱ የተፈጸመበትን ሰዓት፣ ቀን፣ ወር፣ ዓመትና ዘመን ለማወቅ

  እንዴት? – ብለን ስንጠይቅ ድርጊቱ የተፈጸመበትን መንገዱን ለመረዳት

  ለምን ?  – ብለን ስንጠይቅ ድርጊቱ የተፈጸመበትን ምክንያቱን ለመረዳት

  ከዚያ በኋላ?  – ብለን ስንጠይቅ ድርጊቱ ያመጣውን ውጤቱን ለማግኘት ይረዱናል፡፡

  ከዚህ በላይ ያየናቸውን የመጠየቂያ ቃላቶች ቀለል ወዳለውና ወደ ለመድነው ጥቅስ ሄደን፣ በመጠየቅ ጥቅሱን በሚገባ  ለመረዳት እንሞክር፡፡ በሐዋርያት ሥራ 1፡8 ላይ ‹‹…ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፣ በኢሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ›› የሚለውን ጥቅስ በማየት እስቲ ተግባራዊ እናድርጋቸው፡፡ ማን ተናገረው? – ኢየሱስ፣ ለማን ተናገረው? – ለደቀ መዛሙርት መልሱ ቁጥር 1 ላይ  ይገኛል፡፡ ምን ተደረገ? – ጌታ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ ጌታ ምን ብሎ ተናገረ? – በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ፣ – ምስክሮቼ ትሆናላችሁ፣ (ሁለት መልሶች አሉት) የት ሆኖ ነው የተናገረው? – በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ቁ.12፣ መቼ ነው የተናገረው?  – ከትንሣኤ በኋላ በዐርባኛው ቀን መጨረሻ ላይ – ሊያርግ ሲል፣ (ሁለት መልሶች አሉት)፣ እንዴት ተናገረው? ብለን ስንጠይቅ -መልስ ማግኘት አንችልም፣ ምክንያቱም በቃሉ ላይ አልተጠቀሰምና፡፡ (ነገር ግን በቀስታ፣ እየጮኸ፣ እያቃሰተ፣ ትንፋሹ ቁርጥ ቁርጥ እያለ፣ እያለቀሰ፣ እያዘነ … ከሚሉት ሁሉ አንዱ ለጥያቄው መልስ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡) የመጨረሻው ለምን? ብለን  የምንጠይቀው ጥያቄ ሲሆን፣ መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና የሚገጥመን ከባዱ ጥያቄ ነው፡፡ ቁ.8ን ለምን ተናገረው? መልሱ ቁ. 6 ላይ ነው የሚገኘው – ለጠየቁት ጥያቄ መልስ ነው የሰጣቸው::

ብዙ ጊዜ ተማሪዎችን በተለያየ ቦታ የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ ሳስተምር ቁ. 8 ን የት ሆኖ ተናገረው? የሚለውን ጥያቄ ስጠይቃቸው በኢየሩሳሌም ብለው ይመልሳሉ፣ ለምን ተናገረው ለሚለው ጥያቄም መልስ መመለስ ይቸገራሉ፡፡ ይህ ረጋ ብለን ካለማየትና ትኩረት ካለመስጠት የሚመጣ ችግር ነው፡፡ እናንተም ይህ መልስ ሳይሰጥ ቀደም ብሎ ብትጠየቁ፣ ሳትቸገሩ አትቀሩም ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ለማንኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብና ጥናት፣ በእነዚህ መጠየቂያ ቃላት በመጠቀም፣ እስክንረዳው ድረስ መልሰን መላልሰን በመጠየቅ ብንጠቀምባቸው ውጤታማ የሆነ ውጤት እናገኛለን፡፡ በዚህ መንገድ እየተጠቀምን፣ ጌታ እንዲረዳን እየጸለይን ብናጠና መንፈስ ቅዱስም አብርሆቱን (ይገልጽልናል) ይሰጠናል፡፡ ለሚቀጥለው ጊዜ መዝሙር 1፡1-6 ያለውን ክፍል በሰባቱ መጠየቂያ ቃላት በመጠቀም፣ ለጥያቄዎቹ መልስ የሚሆን ፈልጋችሁ ያዙና እንገናኝ፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ምልከታዎችንም አብረን እናደርጋለን፡፡ 


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *