ብዙ ጊዜ ይህን ትምህርት ማስተማር ከመጀመሬ በፊት፣ መጽሐፍ ቅዱስን ስታነቡ ምን ያህል እንደሚገባችሁ በመቶኛ (በፐርሰንት) አስቀምጡ ብዬ አዛቸዋለሁ፡፡ ትምህርቱን ከጨረስን በኋላ እንደገና እንዲያስተያዩት ሳደርጋቸው፣ ውጤቱ በጣም የተለያየ ሆኖ ያገኙታል፡፡ እናንተም ይህን ጽሑፍ የምታነቡ መጽሐፍ ቅዱስን ስታነቡ ምን ያህል እንደሚገባችሁ በመቶ (በፐርሰንት) አስቀምጡና ትምህርቱን ስትጨርሱ፣ ካስቀመጣችሁት ጋር አስተያዩት፡፡
አንድ ሰው ከመሬት ተነስቶ ከሰው ሳይመለከት ወይም ትምህርት ቤት ገብቶ ሳይማር ወይም አጫጭር ሥልጠናዎች ሳይወስድ ልብስ ልስፋ፣ ሰዎችን ቀዶ ህክምና ላድርግ፣ መኪና ላሽከርክር፣ አውሮፕላን ላብርር ቢል በፍጹም ትክክል አይደለም፣ ደግሞም አይችልም፡፡ አንዳንድ ነገሮች እንደ ልብስ ስፌት ያሉትን ብዙ ነገሮችን አበላሽተን ወደ መልካም ውጤት ልንደርስበት እንችል ይሆናል፤ እንደ ቀዶ ህክምናና አውሮፕላን ማብረር ያሉትን ግን ሳንማር ወይም የሚረዳን ሰው ሳይኖር በፍጹም ልንሠራቸው አንችልም፡፡
ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ለአምልኮ ኢየሩሳሌም ደርሶ ሲመለስ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ በሰረገላ ላይ ተቀምጦ ሲያነብ ሳለ፣ ከሰባቱ ዲያቆናት አንዱ የነበረው ፊልጶስ ወደ እርሱ ቀረበና ‹‹በእውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን? ብሎ ጠየቀው፡፡ እርሱም ‹‹የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል? ብሎ መለሰለት፡፡
መጽሐፍ ቅዱስን በማንኛውም ቋንቋ ቢሆን ስናነብ ምን ያህል ነው የሚገባን? ምናልባት ሁላችንም በቋንቋችን ስለምናነብ ሁሉ ነገር ይገባናል ብለን እናስብ ይሆናል:: ነገር ግን ወደ ውስጡ ስንገባ ማን ጻፈው? ለማን ተጻፈ? መቼ ተጻፈ? እንዴት ተጻፈ? ለምን ተጻፈ? ምን ትምህርት ይሰጠናል? የሚሉትን ሀሳቦች ለመረዳት አስቸጋሪ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በተለይም መልእክቱ በተጻፈላቸው (ቀዳሚ አንባቢዎች)ና በእኛ (የአሁኑ ዘመን አንባቢዎች) መካከል የጊዜ ርቀት፣ የባህል ልዩነት፣ ቋንቋ ልዩነት፣ የአመጋገበብና የአለባበስ ልዩነቶች አሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ተረድቶ የቃሉን እውነት አውቀን በሕይወታችን ለመታዘዝና ተግባራዊ ለማድረግ እንቸገራለን፡፡
የአብርሃምን ልጅ ለመሠዋት መዘጋጀት፣ የሶርያ ንጉሥ የሠራዊት አለቃ እንደ ንዕማን፣ የጴጥሮስን በውኃ ላይ መሄድና የይሁዳን ራሱን ሰቅሎ መሞት የመሳሰሉትን ድርጊቶች እንዴት ነው በሕይወታችን የምንፈጽማቸው? ልጆቻችንን ወደ ጫካ ይዘን ሄደን መሠዋት አለብን ማለት ነው? እንደ ንዕማን ወንዝ ሄደን ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ እያልን እንጠመቅ? እንደ ጴጥሮስ ሁላችንም ወደ ባሕር ሄደን በውኃ ላይ መሄድ አለብን ማለት ነው? እንደ ይሁዳ ራሳችንን መስቀልና መሞት አለብን ማለት ነው? እነዚህን የመሳሰሉትን ታሪኮችና ድርጊቶች ስንቶቻችን ተቸግረንባቸው ይሆን? በዚህ ጊዜ እኛም እንደ ጃንደረባው የሚመራን ሳይኖር ይህን መረዳት እንዴት ይሆንልናል ማለታችን አይቀርም፣ ብዬ አስባለሁ፡፡
ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ የቀረበው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶችና በኮሌጅ ገብቼ ከተማርኳቸውና በአርባ አምስት ዓመት የአገልግሎት ዘመኔ ካገኘኋቸው ዕውቀቶች፣ ይጠቅማሉ ብዬ ያሰብኳቸውን ቀለል ባለ ዘዴ ለማካፈል አስቤ ነው፡፡ ይህ ጥናት ለማንኛውም ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና ለማጥናት ለምንፈልግ ሁሉ፣ በራሳችንና በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ፣ መረዳት እንድንችል ሆኖ በቀላል መንገድ የተዘጋጀ ትምህርት ነው፡፡
እንዲሁም አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት መተርጎምና ከሕይወቱ ጋር ማዛመድ እንዳለበት ሳይማር ወይም የሚረዳው ሰው ሳይኖር፣ አስተምራለሁ ቢል ብዙ ስሕተት ውስጥ ይገባል፡፡ ምንም እንኳን ቃሉ የተጻፈው በቋንቋችን ስለሆነ ልናነበውና ልናስተምረው እንችላለን ብለን ብናስብም፣ ብዙ የማናውቃቸውና የምንስታቸው እውነቶች ይኖራሉ፡፡ ኢየሱስ ቃሉን እናውቃለን የሚሉትን ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ‹‹መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ›› እንዳላቸው እኛም እንዳንባል ልንጠነቀቅ ይገባናል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር የተሰጠን የሕይወት መመሪያችን ነው፡፡ ስለዚህ አማኞች ሁላችን መጽሐፍ ቅዱስን በግላችን እንድናነበው፣ እንድንማረው፣ እንድንረዳውና እንድንታዘዘው ያስፈልጋል፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ብርቱና ጠንካራ ሆነን ለመገኘት፣ አማኞች ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ገብተን መማር አይጠበቅብንም፤ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስን በግላችን በዘዴ ማጥናት ይጠበቅብናል፡፡ ቃሉን በግልም ሆነ በቡድን በዘዴ ማጥናት ለግል ሕይወታችንም ሆነ ለአገልግሎታችን እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስን በዘዴ ማጥናት ያለብን፣ ቃሉን ስናነብና ስናጠና እንዳይገባን የሚያደርጉ ብዙ ችግሮች ሲገጥሙን በቀላሉ ለመረዳት የሚያስችለን ስለሆነ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ገብተን ላልተማርነው ቀርቶ፣ ገብተን ተምረን ለወጣነው እንኳን ብዙ የማይገቡን ነገሮች አሉ፡፡ ቃሉን እንዳይገባን የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች ቢኖሩም፣ እኔ ዋና ናቸው የምላቸውን ሦስቱን ብቻ አቅርቤአለሁ፡፡
በመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ብሉይ ኪዳን በዕብራይስጥና ጥቂት ክፍሎች በአረማይክ ሲሆኑ፣ አዲስ ኪዳን ደግሞ በግሪክኛ ስለሆነ፣ እነዚህ ቋንቋዎች የሚያስተላልፉትን እውነቶች ሌሎች ቋንቋዎች ማስተላለፍ ያለመቻላቸውና አቻ ቃላትን መፍጠር አለመቻላቸው አንዱ ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ የዕብራይስጡ ቋንቋ ‹‹እግዚአብሔር›› ለሚለው ቃል ሦስት ቃሎችን ይጠቀማል፡፡ የመጀመሪያው ‹‹ኤሎሄም›› ሲሆን የብዙ ቁጥር ሆኖ ትርጉሙ አምላክ፣ ፈጣሪ፣ ገዥ ማለት ነው፡፡ (ዘፍ.1፡1) ሁለተኛው ‹‹ያህዌ›› ሲሆን ትርጉሙ ያለና የሚኖር፣ አዳኝ፣ ራሱን በራሱ ያኖረ ማለት ነው፡፡ (ዘጸ.3፡13-15፣ 6፡6) ሦስተኛው ‹‹አዶናይ›› ጌታ የሚለውን በትንቢት መጻሕፍት ውስጥ ‹‹የሠራዊት ጌታ›› በሚለው ሥፍራ ሁሉ አዶናይን ያመለክታል፡፡
እግዚአብሔር የሚለውን ቃል በአማርኛችን ስንመለከት፣ የዕብራይስጡ ቃላቶች የሚያስተላልፉትን ሐሳብ አይሰጠንም፡፡ አይደለም አማርኛችን የዓለም ቋንቋዎች ሁሉ ለእነዚህ ስሞች አቻ ቃል የላቸውም፡፡ እግዚአብሔር የሚለው ቃል ከግዕዝ የመጣ የሁለት ቃላት ጥምር ነው፡፡ እግዚእ-ጌታ ማለት ሲሆን፣ ብሔር- ባሕር፣ ሕዝብ ማለት ሲሆን፣ እኛ የምንጠቀመው እግዚአብሔር- የሕዝቦች (ዓለም)ጌታ በሚለው ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ በላይ ለጠቀስናቸው የዕብራይስጥ ቃሎች አቻ ቃሎችና ትርጉም የሚሰጡ የሉንም፡፡ የመደበኛው መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ ተርጓሚዎች በመግቢያው ላይ የሠሩትን ተመልከቱና እነዚህን ስሞች በሚገባ ተጠቀሙበት፡፡ በእያንዳንዱ እግዚአብሔር ለሚለው ቃል የትኛውን የዕብራይስጥ ቃል (ስም) እንደ ተጠቀመ ያመለክተናል፡፡ ለእኛ ለአስተማሪዎች ትልቅ ሥራ አቃለውልናል፣ ጌታ ይባርካቸው፡፡
ሁለተኛው ምክንያት መጽሐፍ ቅዱሰን ስናነብና ስናጠና ሳለ፣ የዛሬ አርባና ሀምሳ ዓመት በተረጎሙና በየዘመናቱና ዛሬም ባለነው አንባቢ መካከል ለአንድ ቃል የምንሰጠው ትርጉም ከመለያየቱ የተነሳ ቃሉ አይገባንም፡፡ በማቴዎስ 22፡40 ላይ ‹‹በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነበያትም ተሰቅለዋል›› የሚል ቃል እናገኛለን፡፡ ተሰቅለዋል የሚለውን ቃል ሳነብ፣ በመጀመሪያ ጌታ በመስቀል ላይ ሆኖ የተሰቀለው፣ ሌሎቹ መንግሥት የሰቀላቸውና ራሳቸውን የሰቀሉ ሰዎች፣ አይቼ ስለ ነበረ የእነርሱ ሥዕል ይታየኛል፡፡ ነገር ግን የዛሬ ሃምሳ ዓመት ይህን መጽሐፍ ቅዱስ በተረጎሙ ሊቃውንት ዘንድ ግን በቃሉ ውስጥ መሞት የሚል ትርጉም በፍጹም አይሰጠንም፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ማህበር በ80 ዓ.ም ባሳተመው እትሙ ላይና በሌሎችም ትርጉሞች ስንመለከት ‹‹ተሰቅለዋል›› ያሉትን ምን ለማለት እንደሆነ በትክክል ያስቀምጡታል፡፡ ተሰቅለዋል ሲሉ ተመሥርተዋል፣ ተቀምጠዋልና ተጠቃለዋል ለማለት እንጂ የመሞትን ጉዳይ አያሳይም፡፡ ዛሬም አንዳንዶቻችን ‹መኪና ላይ ስቀለኝ› ብለን ቃሉን እንጠቀምበታለን፡፡ መኪናው ላይ አስቀምጠኝ ማለታችን እንጂ፣ ግደለኝ ማለታችን አይደለም፡፡
ሦስተኛው ምክንያት ቃሉ እንዳይገባን የሚያደርጉ የቃሉና የእኛ ማንነት ናቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የተጻፈው በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ስለሆነ ያለ መንፈስ ቅዱስ ርዳታ ዳግም ሳንወለድ ብናነበው፣ እንደ ጋዜጣ ስለሚሆንብን አይገባንም፡፡ እኛም ያለን የትምህርት ደረጃ፣ አስተሳሰባችን፣ የመረዳት ችሎታችንና አካባቢያችን ሁሉ አስተዋፅዖ አላቸው፡፡ በማንበብና በመጻፍ፣ በመጀመሪያና በሁለተኛ ደረጃ፣ በኮሌጅ፣ ቲዎሎጂን (ትምህርተ መለኮት) በተማርንና ዕብራይስጥና ግሪክኛን በሚረዱት አንባቢዎች መካከል መጽሐፍ ቅዱስን እኩል የመረዳት ችሎታ የለንም፡፡
‹‹መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ›› (ማቴ.22፡29) የሚለውን ቃል ኢየሱስ የተናገረው ቃሉን እናውቃለን ለሚሉ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ነው፡፡ ፈሪሳውያን ቃሉን የሚያውቁ፣ የሚያስተምሩና የሚተረጉሙ ሲሆኑ ሰዱቃውያንም ከእነርሱ የሚተናነስ ዕውቀት የላቸውም፡፡ የሚለዩበት ነገር ቢኖር ፈሪሳውያን ብሉይ ኪዳንንና ትንሣኤን ሲቀበሉ፣ ሰዱቃውያን አምስቱን የሙሴን መጻሕፍት ብቻ መቀበላቸውና በትንሣኤ አለማመናቸው ነው፡፡ እነዚህ የእግዚአብሔርን ቃል የሚያውቁ ትስታላችሁ ከተባሉ እኛ ደግሞ ምንም የማናውቀው ከዚህ የሚብስ እንደምንባል የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን በዘዴ ልናነበውና ልናጠናው ይገባናል፡፡ ዘዴው ምንድን ነው? ብለን ብንጠይቅ፣ ዘዴው መጽሐፍ ቅዱስን 1. በመመልከት 2. በመተርጎምና 3. በማዛመድ ማጥናት ነው፡፡ እነዚህን ዘዴዎች ወደፊት በስፋት እንመለከታቸዋለን፡፡ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ‹‹… አማኞች ለመናገርና ለመስማት መማር አለባቸው›› ይላል፡፡ ስለዚህ ቃሉን በዘዴ ካጠናነው ሁላችንም አንድ ዓይነት መረዳት ባይኖረንም የሚያቀራርበን ሀሳብና መረዳት ይኖረናል፡፡
0 Comments