በምዕራፍ አሥርና አሥራአንድ ላይ ያየነው በኢየሱስ የተሻለ ተስፋ እንዳገኘን ነው፡፡ በዛሬው ዕለት በምዕራፍ አሥራሁለትና አሥራሦስት የምንመለከተው በኢየሱስ የተሻለ ኅብረት(ኑሮ) እንዳገኘን ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ከአይሁድ ወገን ያመኑት ሰዎች ወደ ድሮ አገልግሎት እንዲመለሱ ወገኖቻቸው ይገፏፏቸው ነበር፡፡ ይህ ባህላዊ ግፊት ብቻ ሳይሆን እውነተኛ መንፈሳዊ ፈተና ነበረ፡፡ እንደገና ወደ ምኵራብ ቢመለሱ የኢየሱስን ሥራ እንደ መካድ ይሆንባቸዋል፡፡ የደረሰባቸው መከራ ያልተጠበቀ አልነበረም፡፡ ያላመኑት አይሁድ የብሉይ ኪዳንን መለኰታዊ ሥልጣን በእውነት ሊጠቅሱ ይችሉ ነበር፣ ነገር ግን ከዚያ ዘላቂ ይቅርታን አላገኙም፣ የብሉይ ኪዳንን ምሳሌዎችንና ትንቢቶችን አልተገነዘቡም፡፡

እግዚአብሔር ስለሚወደን ልንሸከም የምንችለውን ሰፍሮ ይሰጠናል፡፡ የሚመጣብን ሁሉ ከእርሱ እጅ ነው፡፡ መከራው ከእርሱ ስለ መጣ ደስ ብሎን መቀበል አለብን፡፡ ወደኋላ የማፈግፈግ ችግር እውነተኛ ነው፡፡ በተንሸራተቱት ላይ ፍርድን ብቻ ሊያስከትል ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ለሰጠን መልእክት ታማኞች እንሁን፡፡ የታዛዥነት ሕይወት የሚታይ በግልና በጋራ አኗኗራችን ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቤተሰብ መሆናችንን በምናፈራው ፍሬ እናሳያለን፡፡

   12፡1-11 እግዚአብሔር አባታችን ነው

      ምስክሮች፡ ቁ. 1-2 በዚህ ዓለም ስንኖር በብዙ ተመልካቾች ዘንድ እንኖራለን፡፡ በምዕራፍ 11 ላይ የተጠቀሱት የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን በምሳሌነታቸው ሊያበረታቱን ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ አምነው ዋጋ ከፍለው መሥዋዕት ሆነው ያለፉ ሲሆኑ፣ ገና ወደፊትም ዋጋ እየከፈሉ የሚያልፉ ይኖራሉ፡፡ የክርስትና የሕይወት ጉዞ በሩጫ ተመስሏል፤ ሩጫውም እንደ አጭር መቶ ሜትር ሳይሆን እንደ ረጅም ሩጫ ማራቶን ነው፡፡ ኢየሱስ ራሱ የእምነታችን ራስና ፈጻሚ ዋና ምሳሌያችን ነው፡፡ እርሱ መከራ እንደ ተቀበለ ሁሉ መከራ ስለምንቀበል፣ ኢየሱስን እየተመለከትን በትዕግሥት እንሩጥ፡፡ ጌታ ኢየሱስ የጠራን በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በኅብረት የሥራው ባልደረባዎችና የምስክርነቱ ተካፋዮች እንድንሆን ነው፡፡ የጋራ ምስክርነታችንን የሚያረክሱትንና የሚያዳክሙትን ነገሮች ሁሉ ማስወገድ ያስፈልገናል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ተከፋፍለን ብንገኝ ምስክርነታችን በዚያ መጠን የደከመና ዋጋ ቢስ እናደርገዋለን፡፡   

     ቅጣታችን፡ ቁ. 3-11 በምዕራፍ 10፡32-39 የተቀበሉት መከራ ባጭሩ ተጠቅሶ ነበር፡፡ በዚህ ክፍለ ምንባብ ውስጥ  ጸሐፊው ሁለት አሳብ ጨምሯል፡፡ 1. እውነተኛ የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባል ቅጣት ይቀበላል፣ (ምሳ.3፡11-12)፡፡ የእግዚአብሔር እንክብካቤ ነፀብራቅ ነው፡፡ ትክክል አለመሥራት ቅጣትን የሚያስከትል የመሆኑን ሐቅ መዘንጋት  የለብንም፡፡ 2. የደረሰባቸው መከራ ካንድ በኩል ቅጣታቸው ነበረ፣ ወደ ምኲራብ መመለሳቸው ጥፋት ስለ ነበረ፡፡ የሰውን ቁጣ ሳይሆን እግዚአብሔርን መፍራት ነበረባቸው፡፡ ቁ.10-11 የተሰጣቸው ቅጣት ለጥቅማቸው ነበረ፡፡ ቅጣት ሁለት መልክ ይኖረዋል፣ በኃጢአት ምክንያት የሚደርስና ለልምምድ እንዲሆንና ወደ ክርስትና ዕድገት የሚያመጣ ሊሆን እንዲችል በሕይወታችን በጌታ ፈቃድ የሚወሰን ይሆናል፡፡ 

 12፡12-29 መመሪያና ማስጠንቀቂያ    

   ንስሐ እንግባ፡ ቁ. 12-17 በግልና በጋራ ደረጃ ድክመቶች ነበሩባቸው፣ እርዳታ ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ የተጠራቀመ ኃጢአት ክርስቲያንን በአደገኛ ሁኔታ ላይ ይጥለዋል፡፡ ንስሐ ለመግባት የማይችልበት ሰዓት ሊደርስበት እንደሚችል ዔሳውን ምሳሌ አድርጐ ያቀርባል፡፡ ንስሐ ስንገባ ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነታችን የተስተካከለና ጤናማ ሲሆን፣ ሕይወታችን ደስተኛና በቀላሉ የጸሎት መልስ ማግኘት የሚንችል እንሆናለን፡፡

  አዲሱ ይበልጣል፡ ቁ. 18-24 በኢየሱስ በኩል የተሰጠው መገለጥ በደብረ ሲና እንደተሰጠው ዓይነት የሚያስደነግጥ አልነበረም፡፡ ጸሐፊው ሁለቱን በፍጹም ሊያወዳድር አልሞከረም፡፡ የአዲስ ኪዳኑ መገለጥ እንደ ብሉይ ኪዳኑ አስደንጋጭና አስፈሪ ባይሆንም ግን አዲሱ እጅግ ይበልጣል በማለት ይገልጠዋል፡፡ ክርስቲያኖች እንደሚገባ ባንኖርበትም የተካፈልነው አዲሱ ሰማያዊ ኅብረት በቀለም፣ በጾታ፣ በዕውቀት፣ በትምህርት፣ በሥልጣንና በዘር፣ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን፣ በመስቀሉ ላይ በፈሰሰው ደም አማካኝነት የተመሠረተ ኅብረት ነው፡፡ ስለዚህ ልንጠብቀው፣ ልናከብረውና ልንጠነቀቅለት ያስፈልጋል፡፡

  የሚበልጠውን እንስማ፡ ቁ. 25-29 የአዲሱ ቃል ኪዳን መመሪያዎችን መጠበቅ ያስፈልገናል፡፡ የአዲስ ኪዳን ተካፋዮች ስለሆንን አኗኗራችን ፈጽሞ ልዩ መሆን አለበት፡፡ የተለወጥንና የተመረጥን ስለሆንን ለየት ባለ ኑሮ የመኖር ግዴታ አለብን፡፡ በፈተና ሰዓት እንዳንናወጥ በእምነት ኑሮ ጸንተን መቆም አለብን፡፡ የአዲስ ኪዳን ካህናት ስለሆንን ምሳሌነት ያለው ኑሮ ይጠበቅብናል፡፡ ይህን የሚበልጠውን አዲስ ኪዳን የሚለንን ልንሰማው ይገባናል፣ ባንሰማው እግዚአብሔር የሚባላ እሳት ስለሆነ ወደ ፍርድ ሊያስገባን ይችላል፡፡ ስለዚህ የሚበልጠውን እንስማ!

 13፡1-25 እግዚአብሔርን የማስደሰት ዘዴ

    በኅብረት እንኑር፡ 13፡1-9 የክርስትና ኅብረታቸው የተጠበቀና ፍሬ የሚያፈራ መሆን አለበት፡፡ የቤተሰብ ሕይወት ደግሞ የተከበረ ይሁን፣ እግዚአብሔር የሚያስፈልጋቸውን ይሰጣቸዋል፣ የታሪካቸውን ዓላማ ማሰላሰል ይኖርባቸዋል፣ ከእግዚአብሔር ጋር መልካም ኅብረት ካለን ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር መልካም ኅብረት ይኖረናል፡፡ አንዱ የአንዱን ሸክም መሸከም ይገባዋል፡፡ በሕብረት ብንኖር እግዚአብሔር ይባርከናል፣ ይደሰትብናል፣ ያከብረናል፣ ያነግሠናል፡፡

 መሥዋዕት እናቅርብ፡ 13፡10-16 መሥዋዕቶችስ ምን ሆኑ? የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች ቢቀሩም በአዲሰ ኪዳን የምናቀርባቸው መሥዋዕቶች አሉን፡፡ ለክርስቲያኖች በተሰጠው መሠዊያና በሚያቀርቡት መሥዋዕቶች የአይሁድ ካህናት ምንም ክፍል የላቸውም፡፡ ኢየሱስ መከራ እንደ ተቀበለ ሁሉ መከራ ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለብን፡፡ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ስለሆነ፣ ሁላችንም የምስጋና መሥዋዕት ማቅረብና ለሌሎች ማካፈል ይጠበቅብናል፡፡ 

 በጸሎት እንተጋገዝ፡ 13፡17-25 ለመሪዎች በመጸለይ፣ ደግሞ እርስ በእርሳችን ጸሎት በማድረግ እንተጋገዝ፣ እንተሳሰብ፡፡ እየተጋገዝን ስንቆም ማንኛውንም ፈተና በድል ለመጋፈጥ እንችላለን፡፡ የመደምደሚያው ሀሳብ ከጠቅላላው መጽሐፍ ሀሳብ ጋር ተስማሚ ነው፡፡ አንዳንድ ታሪካዊ መረጃዎች ደግሞ ይሰጠናል፡፡ ለመሪዎች መታዘዝ እንደሚገባ፣ ስለ መልካም ሕሊና መኖር፣ መልካም በማድረግ ፍጹም ስለ መሆንና ስለ ጢሞቴዎስ ከእስር ተፈትቶ ስለ መምጣቱ በመናገር ጸጋ እንዲበዛላቸው ያሳስባቸዋል፡፡ እኛም በጸሎት እርስ በእርሳችን መተጋገዝ ያስፈልገናል፡፡

 ሕይወታችን በጌታ እጅ ስለሆነ ምንም ችግር ቢደርስብን ጌታ የሚጠብቀን መሆኑን ልንገነዘብ እንችላለን፡፡ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሁሉ ያለ እርሱ ፈቃድ ስለማይሆን፣ በችግር ውስጥ ሰላም ይሰጠናል እንጂ ከዚያ ሁሉ አያድነንም፡፡ ምርጫ የማድረግ ኃላፊነት ስላለብን ለምናደርጋቸው ምርጫዎች ተጠያቂዎች ነን፡፡ ኅብረትን ችላ ብንል ሕይወታችን ጥቅመቢስ ሊሆን ይችላል፡፡ የጋራ ሕይወታችን ደግሞ ዋጋ ያለው ነው፡፡ የግል ሕይወታችን ዋጋ የሚገለጠው አብረን በምንሠራበት ጊዜ ነው፡፡ ከኅብረታችን ኃይል እናገኛለን፡፡

ማጠቃለያ፡- ይህ በዚህ ገጽ ላይ የምንመለከተው ሥዕላዊ መግለጫ የዕብራውያንን የመጽሐፉን ጠቅላላ ይዘት በአጭሩ እንድንመለከተው ይረዳናል፡፡ የመልእክቱን ዋና ሀሳብና የየምዕራፉን ሀሳብ በቀላሉ መረዳትና ማስታወስ ያስችለናል፡፡

የዕብራውያን መልእክት መላእክት፣ ሙሴና አሮን ለኢየሱስ ጥላ እንደነበሩ በማሳየት፣ ክርስቶስ እውነተኛ አካል መሆኑን በመግለጥ ከእነርሱ ይበልጣል በማለት ያስተምራናል፡፡ ከግራ ያሉት ቀስቶቹ (መላእክት፣ ሙሴና አሮን) ወደ አካሉ በማመልከት እነርሱ ጥላ መሆናቸውንና እውነተኛው አካል ክርስቶስ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ከቀኝ ያሉት ቀስቶቹ በኢየሱስ ያገኘናቸውን (ቃል ኪዳን፣ እምነትና ኅብረት) በረከቶች ያመለክታሉ፡፡ ኢየሱስ ከመላእክት፣ ከሙሴና ከአሮን ይበልጣል፣ በኢየሱስ የተሻለ ቃል ኪዳን፣ እምነትና ኅብረት አግኝተናል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን ለኃጢአታችን ማስተሰሪያ አድርጐ ባቀረበው የተሻለና ብቸኛው ሊቀ ካህናችን በሆነውና አዲስ ቃል ኪዳን በገባልን፣  አዲስ ተስፋ/እምነት በሰጠንና  የላቀውን ክርስቲያናዊውን ኑሮን እንድንኖር ባደረገው ጌታ ላይ ታምነን በእምነት መኖርና እርሱን በኅብረት ማገልገል ይገባናል፡፡ ለዚህም ጌታ ይርዳን፣ ጸጋውንም ያብዛልን፡፡  በዚህ ዓለም ስንኖር መከራ እንዳለብን ጌታ ራሱ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 16፡33  ‹‹በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፣ ነገር ግን አይዟችሁ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ ›› ብሎ ተናግሮአል፡፡ ለዚህ እውነት የዕብራውያን ክርስቲያኖችና ዛሬም በዘመናችን ያሉ የእግዚአብሔር ቅዱሳን የደረሰባቸው መከራ ትምህርት ሆኖን በክርስትና ሕይወታችን በሚደርስብን ችግርና መከራ ሁሉ በትዕግስትና በጽናት የእምነታችንን ጀማሪና ሐዋርያ እየተመለከትን ወደፊት በእምነት መሄድ ይገባናል፡፡ እርሱ ድል አድራጊና አሸናፊ ስለሆነና ሁልጊዜ ሊረዳን ዝግጁ በመሆኑ፣ በእርሱ ብቻ ብንታመን ድል አድራጊዎች እንሆናለን፡፡ ድል አድራጊው ጌታ ከእኛ ጋር ስለሆነ የሕይወታችንን ጉዞ በድል ለመጨረስ ጌታ እንዲረዳን ጸሎቴ ነው፡፡

ኢየሱስ እውነተኛው ሊቀ ካህናችን


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *