ባለፈው ጥናታችን ኢየሱስ የተሻለ ቃል ኪዳን እንደ ገባልን በምዕራፍ ስምንትና ዘጠኝ ተመልክተናል፡፡ አሁን ደግሞ በምዕራፍ አሥርና አሥራአንድ በኢየሱስ የተሻለ ተስፋ/እምነት እንደ ተቀበልን እንመለከታለን፡፡ ከአይሁድ ወገን ያመኑት ክርስቲያኖች የአሮን ቃል ኪዳን መለኰታዊ መሆኑን ማመናቸው ትክክል ነበረ፡፡ አሻሚ ጥያቄአቸው አሁን ይህ ቃል ኪዳን እንዴት ዋጋ ቢስ ሆኗል? የሚለው ነበረ፡፡ እግዚአብሔር ሀሳቡን ለውጧል ማለት ነውን? ያ መገለጥ ሥልጣን የሌለው ሆኗልን? አዲሱና አሮጌው ሁለቱም አብረው ሊያገለግሉ እንደማይችሉ ግልጥ ነው፡፡ አንዱ በሌላው ላይ ተጭኗል፡፡ ሁለተኛው አንደኛው ለመስጠት የማይችለውን ሊሰጥ ይችላል፡፡ ለአዲሱ ቃል ኪዳን ምን ዓይነት መልስ መስጠት እንደሚገባቸው ግራ አጋብቶአቸዋል፡፡ ከችግራቸው ለመዳን ወደ አይሁድ ሥርዓት ለመመለስ ይፈልጉ ነበር፡፡
ማንኛውም ሰው ሊጠይቅ ከሚችለው ጥያቄዎች ዋነኛው የሚከተለው ነው፡፡ በአዲስ ቃል ኪዳን መሠረት ኃጢአት ምን ሆኗል? በምዕራፍ 10 የሚገኘው መልስ የክስ መሠረት ተወግዷል የሚል ነው፡፡ የፊተኛው መሥዋዕቶች የጠቆሙት ተከናውኗል፡፡ ለዚያ ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ተገኝቷል፡፡ አሁን አንከሰስም፣ ጸድቋል የሚለው ቃል የእምነታችን መሠረት ነው፡፡ ከተፈታን ዘንድ እንዴት እንኑር? እንደ እግዚአብሔር ቃልና እንደ ቤተሰብ መኖር አለብን፡፡ እንግዲህ አሁን ምን ማድረግ ያስፈልገናል? ለእግዚአብሔር ቃል እየታዘዙ መኖር ነው፡፡ የነፍሳችን ምርኵዝ ምንድር ነው? እምነትና መታዘዝ ሲሆኑ፣ ሁለቱ ልዩ ናቸው፡፡ እምነት ማለት እግዚአብሔር በተናገረው ቃል ተደግፎ መኖር ነው፡፡ በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተ በመሆኑ እምነት መሠረት አለው፡፡ እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል መስማት፣ መቀበልና በሥራ ማዋል መታዘዝ ነው፡፡ ይህ ግን አዲስ ትምህርት አይደለም፣ የአዲስ ኪዳን መሠረት በእውነት የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡
10፡1-39 አዲሱ መንገድ
የሕጉ ጥላነት፡- 10፡1-10 የኢየሱስ አገልግሎት ከሌዊ ካህናት አገልግሎት የሚሻልበቱ ደግሞ በመሥዋዕቱ ነው፡፡ በዚህ መሥዋዕት ፍጹም የኃጢአት ይቅርታ አግኝተናል፤ ባቀረበው በሥጋው በኩል ተቀድሰናል፡፡ የፊተኛው ቃል ኪዳን ኃይል ያልነበረው መሆኑን በመዝሙር ውስጥ ያስረዳል፡፡ ‹‹ …መሥዋዕትንና ቁርባንን አልወደድህም ሥጋን አዘጋጀህልኝ የሚቃጠለውንና ስለ ኃጢአት የሚቀርበውን መሥዋዕት አልሻህም›› (መዝ. 40፡6-8)፡፡ አሁን የብሉይ ኪዳን መሥዋዕት አቅራቢው ኃጢአት፣ በክርስቶስ መሥዋዕት ነጽቷል፡፡ በኃጢአተኛውና በፈጣሪው መካከል የነበረው ግርግዳ ፈርሷል፡፡ የጥፋተኛነት መሠረት ከኃጢአተኛው ተወግዷል፡፡ የብሉይ ኪዳን ሕግ ለአዲስ ኪዳን ሕግ ጥላ ነበር፣ አሁን እውነተኛው አካል ስለ መጣ፣ ሥፍራ ለቆአል፡፡
አዲሱ መሥዋዕት፡- 10፡11-18 በአዲስ ኪዳን ተጨማሪ መሥዋዕት ፈጽሞ አያስፈልግም፡፡ አዲሱ ቃል ኪዳን ፍጹም ለመሆኑ ኤርምያስ በትንቢቱ እንዲህ ተብሎ ተጠቅሷል ‹‹ …አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል …ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፣ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል›› (ኤር.31፡31-34) ያንን መሥዋዕት የተቀበሉት ሁሉ ጥፋት እንደሌላቸው ተቆጥረዋል- ቁ.14 ክርስቶስ በሠራው ሥራ ላይ ምንም ሊጨመር አይቻልም፡፡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከአባቱ ጋር የሚያስታርቀውን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ ተቀባይነት አግኝቶ፣ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦአል፡፡ ስለዚህ አዲሱ መሥዋዕት አማኞችን ለዘላለም ፍጹም አድርጎናል፡፡
አዲሱ መንገድ፡- 10፡19-25 የክርስቶስ ሥራ ተሳታፊዎች ሁሉ ባለ ዕዳዎች ናቸው፡፡ ቁ.19-25 ማድረግ የሚገቡን ነገሮች ይዘረዝርልናል፡፡ ክርስቶስ በመሥዋዕታዊው ሞት ያከናወነው ክንውን ተግባራዊ ነው፡፡ ስንት ነገር ለማድረግ ታዝዘናል? በተረዳንበት እምነት በቅን ልብ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ፣ የተስፋችንን ምሥክርነት መጠበቅ፣ እርስ በርሳችን ለፍቅርና ለመልካም ሥራ መነቃቃት፣ መሰብሰባችንን አለመተው፣ ይጠበቅብናል፡፡
ወደኋላ ማፈግፈግ፡- 10፡26-31 ይህ ክፍለ ምንባብ ምዕራፍ 6፡1-12ን ይመስላል፡፡ አውቆ ኃጢአትን መሥራት ፍርድን ብቻ ያስከትላል፡፡ በዚህ ላይ ጸሐፊው ወደኋላ በማፈግፈግ የምንንቀውን ይጠቁማል፡፡ የክርስቶስን የድነት ሥራ ከናቅን ምንም ሌላ መፍትሔ ልናገኝ አንችልም፡፡ ብሉይ ኪዳንን ያልታዘዙ ወደ ከባድ ፍርድ ከገቡ የክርስቶስን ድነት የናቁ እንዴት ይሆኑ? በማለት ያስጠነቅቃቸዋል፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች የሆንን የእግዚአብሔርን ልጅ በእግራችን መርገጥ፣ የኪዳኑን ደም እንደ ርኩስ ነገር መቁጠርና የጸጋውን መንፈስ ማዋረድ እንዴት ይሆንልናል?
እምነታችሁን አትጣሉ፡- 10፡32-39 ይህ ክፍለ ምንባብ የአንባቢያንን ሁኔታ ይገልጻል፡፡ ክርስቲያኖችን ያሳደዱአቸው አይሁዶች ሳይሆኑ አልቀሩም፡፡ በጌታ ላይ ያላቸውን ድፍረት/መታመን በመከራው ምክንያት እምነታቸውን እንዳይጥሉ ይመክራቸዋል፤ ምክንያቱም በእምነታቸው ብዙ ዋጋ እንደ ከፈሉ ስለሚያውቅ ነፍሳቸውን ከሚያድኑት ወገን ስለ ሆናችሁ በእምነታችሁ ወደ ፊት ቀጥሉ በማለት ያበረታታቸዋል፡፡ ይህን ያህል ዋጋ ከፍለው ወደኋላ ቢመለሱ ሞኝነት እንደሚሆንባቸው ያሳያቸዋል፡፡ ለጌታ ታማኝ ሆነው እስከ መጨረሻው በጽናት ቢቆሙ ታላቅ ዋጋ/ሽልማት እንዳላቸው ይነግራቸዋል፡፡ እኛም ዛሬ በተለያየ ችግርና ፈተና ውስጥ ብንሆንም ጌታን ለማስከበርና ዋጋችንን ለመቀበል እምነታችንን ሳንጥል በጽናት መቆም ይጠበቅብናል፡፡ ጌታም ጸጋውን ያበዛልናል፡፡
11፡1-40 አዲሱ ተስፋ
እምነት፡- 11፡1-7 እምነት ማለት የእግዚአብሔርን ቃል ይዞ ያ ቃል እስኪፈጸም ድረስ አለመልቀቅ ነው፡፡ ምንም ተቃውሞ ቢበዛ እግዚአብሔር ተናገረውን መታዘዝና ማድረግ ነው፡፡ ይህ ዓይነት አቋም ብቻ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው ኑሮ ለእርሱ ልዩ ልዩ ነገሮችን መስጠት ሳይሆን የእርሱን ቃል ጨብጠን ሕይወታችንን በእርሱ መሠረት መምራት ነው፡፡ እነዚህን ተስፋዎችን እንዳንይዛቸው የሚከለክሉት ነገሮች ሁሉ በክርስቶስ ፍጹም መሥዋዕት ተሸንፈዋል፡፡ የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን በእምነት እንደተመላለሱ ሁሉ እኛም በእምነት ለመመላለስ እንችላለን፡፡ እምነት እንዲኖር ትክክለኛ የሆነ መሠረት ያስፈልጋል፤ በተረዳነው እውነት ላይ መመሥረት፣ ለዚያ እውነት ራሳችንን አሳልፎ መስጠትና በተግባር መግለጽ ይጠበቅብናል፡፡ የእምነት ምሳሌ የሆኑትን እንድንመለከት አቤልን፣ ሄኖክን፣ ኖኅን አቅርቦልናልና ከእነርሱ እንማር፡፡
ተስፋን በእምነት መጠበቅ፡- 11፡8-16 በዚህ ክፍል አብርሃም እግዚአብሔር ሲጠራው በእግዚአብሔር ላይ ያለውን እምነቱን ልጁን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ ምሳሌነቱን አሳይቶአል፡፡ እምነት ወዲያው መልስ ለማግኘት አይቃጣም፡፡ አብርሃም እንደ ተፈተነ እኛም ልንፈተን እንችላለን፣ እግዚአብሔር የሚሠራው ሥራ ስለሚኖረው የሚሠራውን እስኪጨርስ ድረስ መታገስና መጽናት ይጠይቃል፡፡ እግዚአብሔር ያቀደውን እስኪሠራ ድረስ እምነት ይታገሣል፡፡ የተስፋው ፍጻሜ ምንጊዜም አጠያያቂ አይሆንም፡፡ እግዚአብሔር አብርሃምን ከፈተነው በኋላ የሕዝቦች አባት እንዲሆን ዘሩን አብዝቶ ባረከው፡፡ ተስፋ እስኪ መጣ ድረስ፣ እንደ አብርሃም ብዙ ፈተና ሊገጥመን ስለሚችል በእምነት መጠበቁ አስፈላጊ ነው፡፡
እምነት ሲፈተን፡- 11፡17-22 እምነት ለመፈተንና መከራ ለመቀበል ሁልጊዜ ዝግጁ ነው፡፡ መንገዱ ቀላል መሆኑን ተስፋ አያደርግም፡፡ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ተስፋዎች ጨብጦ እምነት ተቃውሞን ይጋፈጣል፣ ሞትንም ይቀበላል፡፡ በእምነት ስንመላለስ መከራ እንቀበል ይሆናል፣ ምናልባትም ወዲያውኑ ወደ ግባችን አንደርስም ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር የተናገረውን ያደርጋል ከሚለው አቋም ፍንክች ማለት የለብንም፡፡ እምነት ከችግራችን በላይ ወደፊት የሚሆነውን አሻግረን እንድናይ ይረዳናል፡፡ ከሁሉ በላይ ታላቅ የሆነው ተስፋ የክርስቶስን ሥራ የሚያመለክተው ነው፡፡
በእምነት መራመድ፡- 11፡23-31 እምነት አስቸጋሪ ሥራ ሊሠራ ይፈቅዳል፡፡ የመሳፈሪያውን ትኬት ገዝቶ ቁጭ ብሎ ተዘልሎ እንደ መቀመጥ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ያዘዘውን ለመሥራት ጥረት ይጠይቃል፡፡ እውነተኛ እምነት መሆኑ የሚታወቀው ግቡን ሲመታ ነው፡፡ በቃሉ ላይ የምናያቸው የእምነት አርበኞች ወደ ድል የመጡት ወደፊት የሚጠብቃቸውን ብድራታቸውን በእምነት በማየት ነው፡፡ እኛም ከጌታ የምናገኘውን በእምነት አተኩረን በማየት በድል መራመድ እንችላለን፡፡ ከጋለሞታይቱ ረዓብ ያነሰ እምነት ሊኖረን አይገባም፡፡
እምነት ዋጋ ያስከፍላል፡- 11፡32-40 እምነት ዘበትን፣ ስድብን ሥቃይን ወይም ሞትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ የእግዚአብሔር እቅድ ለግለሰብ ብቻ ሳይሆን ቤተሰቡን የሚሸፍን ነው፡፡ ፍጹምነቱን ልንገነዘብ የምንችለው ጠቅላላውን እቅድ ስንመለከት ነው፡፡ በዚህ ክፍል የተዘረዘሩትን የእምነት አርበኞች ስንመለከት፣ በሰው ዓይን ዕይታ አንዳንዶቹ በድል ያለፉ፣ ሌሎቹ በመሸነፍ ያለፉ ይመስላሉ፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ዓይን ሁሉም ድል አድርገው ያለፉ የእምነት ጀግኖች ናቸው፡፡ ክርስቶስ የሠራው ሥራ ታሪካዊ ሐቅ ሲሆን በሕይወታችን ውስጥ የምንለማመደው እውነት ነው፡፡ ብሉይ ኪዳን ችግሩን ጠቆመ፡፡ አሁን ለችግሩ ፍጹም መፍትሔ ተገኝቷል፡፡ እውነተኛ ሰላም ለሰው ልጅ ይገኛልና፡፡ ይህ ሰላም በልምምድ የተመሠረተ ሳይሆን እግዚአብሔር በተናገረው ቃል ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የማፈግፈግ አማራጭ የሚያስፈራ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ ተናገረ ያን ቃል ጨብጠን መኖር አለብን፡፡ ያንን ቃል ተደግፈን ስንኖር ብዙ ችግር ሊገጥመን ይችላል፣ ቃሉ እውነት ላይመስለን ይችላል፡፡ ነገር ግን ብዙ ተቃውሞና መከራ መቀበል ቢያስፈልገንም ያንን ተስፋ ቃል አጥብቀን በእምነት መያዝ አለብን፡፡ እግዚአብሔር በእምነት መደሰት ብቻ ሳይሆን እምነትን በመጠቀም ለእርሱ አስገራሚና አስደናቂ ሆኑ ነገሮችን እንድናደርግለት ችሎታን ይሰጠናል፡፡
0 Comments