በቀደሙት የዕብራውያን ጥናቶቻችን ጸሐፊው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በማተኮር ከነብያትና ከመላእክት፣ ከሙሴ፣ ከኢያሱና ከአሮን አገልግሎት ሁሉ አገልግሎቱ እንደሚበልጥ አሳይቶናል፡፡ አሁን ደግሞ በመቀጠል እግዚአብሔር በኢየሱስ በኩል የገባልን ቃል ኪዳን የላቀ መሆኑን ያሳየናል፡፡ በፊተኛው ቃል ኪዳን ሰዎች በሁለት መንገዶች ተካፋዮች ነበሩ፡፡ እያንዳንዱ የአይሁድ ቤተሰብ በግዝረት የቃል ኪዳን ተሳታፊ ነበር፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የቃል ኪዳን ተሳታፊ ለመሆን የልብ መስማማት አስፈላጊ ነበረ፡፡ በቃል ኪዳን ውስጥ ላሉት እግዚአብሔር ሁለት ነገር ሰጣቸው፡፡ ሀ) ኃጢአት እንዳይሠሩ ሕግጋትና ሥርዓት ሰጣቸው፣ ለ) ለሠሩት ኃጢአት በመሥዋዕቶች አማካኝነት ጊዜአዊ መሸፈኛ ሰጣቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነበሩ፣ ምንም ስሕተት አልነበረባቸውም፡፡ ከቃል ኪዳን አንድ ክፍልና የመለኰታዊ መገለጥ አንድ ገጽታ ስለነበራቸው፣ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ስብከት ክርስቶስን ያመለክቱ ነበር፡፡
ነብዩ ኤርሚያስ ስለ አዲስ ቃል ኪዳን ትንቢት ተናገረ፣ በዚህ አዲስ ቃል ኪዳን ውስጥ ኢየሱስ ሊቀ ካህን ነው፡፡ ከዚህ የተነሣ የሚሻል ተስፋ፣ የሚሻል ኪዳንና የሚሻል አገልግሎት ተገኝቶአል፡፡ በብሉይ ኪዳን መሠረት ኢየሱስ ሊቀ ካህን ወይም ተራ ካህን እንኳ ሆኖ ለማገልገል አይችልም ነበር፡፡ በፊተኛው ቃል ኪዳን ያሉት ነገሮች ሁሉ ወደፊት የሚሆነውን ያመለክቱ ነበር፡፡ አገልግሎቱ ጊዜአዊ ነበረ፣ አንባቢው እንደሚተው ዓይነት የፊደል አቆጣጠር ነበር፡፡ ጌታ አዲስ መሪ፣ ቃል ኪዳንና መጠሪያ ሰጥቶናል፡፡ ስለዚህ አሮጌው ውስጥ ገብተን መያዝና መጠመድ የለብንም፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለኃጢአት ይቅርታ የተዘጋጀው መፍትሔ ፍጹም ነው፡፡ እስከዚህ ጊዜ ድረስ የሰዎች ኃጢአት ተሸፍኖ ነበር፣ አሁን ግን ፍቱን መድኃኒት ስለተገኘለት ተደምስሷል፡፡ ፍቱን መድኃኒቱም ኢየሱስ ያቀረበው የተሻለ መሥዋዕት ነው፡፡
8፡1-13 አዲስ ቃል ኪዳን
ሁለቱ ሊቃነ ካህናት፡- ቁ.1-2 በቀድሞዎቹና በአዲሱ ሊቃነ ካህናት መካከል የተደረገው መወዳደር የማይቻል ነው፡፡ የፊተኞቹ ያደረጉት ሁሉ ያልተሟላ ነበር፣ የአገልግሎት ዘመንና ያቀረቡት አስተዋጽኦ ፍጹም አልነበረም፣ ኢየሱስ በምዕራፍ ሰባት እንዳየነው፣ ያደረገው ከፍጹምነቱ የተነሳ፣ የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ሆኖ፣ በግርማው ቀኝ ተቀምጧል፡፡ እግዚአብሔር በነብዩ ኤርምያስ እንደ ተናገረው ለሕዝቡ አዲስ ቃል ኪዳን በመግባት የአዲስ ኪዳን ብቸኛው ሊቀ ካህን በመሆን አገልግሎት መጀመሩን ጸሐፊው ያመለክተናል፡፡
ካህንና መሥዋዕት፡- ቁ. 3-6 ብሉይ ኪዳን አንድ ካህን መሥዋዕት ካላቀረበ ካህን አይባልም፡፡ በአይሁድ ሥነ ሥርዓት ኢየሱስ ካህን ለመሆን አይችልም ነበር፡፡ ምክንያቱም እርሱ ከአሮን ዘርና ከሌዊ ወገን ስላልነበረ፡፡ ለሙሴ ምሳሌ እንደ ተሰጠ ሁሉ የፊተኞቹ ካህናት ሥራ ሁሉ ምሳሌያዊ፣ ጊዜያዊና ጥላ ነበረ፡፡ በኢየሱስ የሚሻል ተስፋ፣ የሚሻል ኪዳን፣ መካከለኛነትና የሚሻል አገልግሎት ተገኝቶአል፡፡ አማኞች ሁላችንም ወደ እግዚአብሔር ዙፋን በእምነት ቀጥተኛ የሆነ መግቢያ በር አለን፡፡ በዮሐንስ ወንጌል 10፡9 ላይ ‹‹በሩ እኔ ነኝ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፣ ይገባልም ይወጣልም መሰማሪያም ያገኛል›› ጌታ ራሱ እንደ ተናገረው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በሩ ክፍት ነው፡፡ በሁሉ መንገድ አገልግሎቱ ፍጹም ነው፡፡ ትንቢት፣ ያቀረበው አገልግሎትና ያገኘነው ልምድ ይህን ያረጋግጣል፡፡
የተሻለው ቃል ኪዳን፡ ቁ. 7-13 በኤርምያስ 31፡31-34 ላይ የተነገረው ትንቢት ‹‹እነሆ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል … ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፣ በልባቸውም እጽፈዋለሁ … ባለው መሠረት ጸሐፈው ትንቢቱ መፈጸሙን ያሳያል፡፡ ይህ ክፍል ከቁ.6 ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ክፍሉ የፊተኛውን ኪዳን/ብሉይ ኪዳን ነቀፋ እንዳለው እያመለከተ፣ የሁለተኛው ኪዳን/አዲስ ኪዳን ያለነቀፋ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ይህ ክፍል ገና ወደፊት የሚሆነውን ሊጠቁም አይችልም፣ ቁ.8 በግልጥ ክርስቲያኖችን ያመለክታል፡፡ እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን እንዳደረገ ሁሉ እንዲሁም በልጁ በኩል ከእኛ ጋር አድርጎአል፡፡ በዚህ በኤርምያስ 31 ላይ በተተነበየው አዲስ ቃል ኪዳን መሠረት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሲሞት አዲስ ኪዳን ተመሠረተ፤ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከእግዚአብሔር ጋር በቃል ኪዳን ተሣሥረናል፡፡ አዲስ ኪዳን ብሉይ ኪዳንን በመተካቱ የተነሳ ቃሉ በልባችን ተጽፏል፣ እግዚአብሔርን በሚገባ እውቀናል፣ ፍጹም የኃጢአት ይቅርታ አግኝተናል፡፡ ‹‹አሮጌና ውራጅ›› ማለቱ መቅደሱና የአምልኮው ሥርዓት በሰባ ዓመተ ምህረት ላይ በሮማውያን መጥፋቱን በመንፈስ ሳይረዳ አልቀረም፡፡ አዲሱ ኪዳን ከውጫዊ የአምልኮ ሥርዓት፣ ወደ ውስጣዊ የአምልኮ ሥርዓት፣ እግዚአብሔርን በመንፈስና በእውነት ወደ ምናመልክበት አሸጋግሮናል፡፡
9፡1-22 ምድራዊና ሰማያዊ አምልኮ
የፊተኛው አምልኮ፡ ቁ. 1-5 በማደሪያው ድንኳን በእያንዳንዱ ክፍል ውስጥ ያሉት ዕቃዎች ሁሉ ምሳሌያዊ ትርጉም ነበራቸው፡፡ በእውነት እንደ አረማውያን አምልኮ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ወደፊት የሚሆነውን ስላመለከተ፣ ያ ሲደርስ መቅረቱ የታወቀ ነው፡፡ ከፊተኛው አምልኮ ሥነ ሥርዓት አስፈላጊ ሥፍራ ነበረው፡፡ የፊተኛው ኪዳን ዝግጅት ብቻ ነበረ፣ ፍጻሜው (አዲሱ) ከመጣ በኋላ ወደ እርሱ መሄድ አስፈላጊ ነው፡፡ ብሉይ ኪዳን ይህንን አዲስ ኪዳን በምሳሌ፣ በትንቢትና በሥዕል ጠቁሞት ነበር፡፡ በአዲሱ ውስጥ ይቅርታ ተገኝቷል፣ መንፈሱን አፍስሷል፣ ሕጉን በልባችን ውስጥ አኑሯል፡፡
ጊዜአዊ መሥዋዕት፡ ቁ. 6-10 በብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህንና ካህናት ልዩ ልዩ አገልግሎት ነበራቸው፡፡ ካህናት በየዕለቱ በፊተኛይቱ ድንኳን (በቅድስት) እየገቡ የተለያየ አገልግሎት ሲሰጡ፣ ሊቀ ካህኑ በዓመት አንድ ጊዜ በደም አማካኝነት በሁለተኛይቱ ድንኳን (በቅድስተ ቅዱሳን) በመግባት መሥዋዕት ለራሱም ለሕዝቡም ያቀርባል፡፡ እነርሱ በሚያገለግሉበት አገልግሎት ዘለቄታ ያለው መሥዋዕት አልቀረበም፡፡ በሙሴ ሥርዓት የነበራቸው አገልግሎቶች ሁሉ ያልተሟሉ ሆነው የክርስቶስን መምጣት ይጠባበቁ ነበር፡፡ የነፍስ እርካታን ለመስጠት አልቻሉም፣ ዘለቄታ አልነበራቸውም፡፡ ስለዚህ ደካማ የሆነውን ሊቀ ካህን ብርቱና ዘላለማዊ በሆነው ሊቀ ካህን በኢየሱስ ክርስቶስ፣ መገናኛውን ድንኳን በመንግስተ ሰማያት መተካት አስፈላጊ ሆነ፡፡
ፍጹም መሥዋዕት፡ ቁ. 11-14 ኢየሱስ ክርስቶስ ብቸኛው ሊቀ ካህን ሆኖ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች በእውነተኛይቱ ሰማያዊ ቤተ መቅደስ በማቅረቡ፣ ፍጹም መሥዋዕት መገኘቱን ጸሐፊው በታላቅ ደስታ ያበስራል፡፡ የክርስቶስ መሥዋዕት የተሟላና የማይደገም ነው፡፡ ሌሎች መሥዋዕቶች ለማድረግ/ሊያስገኙ ያልቻሉትን የክርስቶስ መሥዋዕትነት አድርጓል/አስገኝቶአል፡፡ የእርሱ መሥዋዕት በማር. 7፡21-22 ላይ የተጠቀሱትን ‹‹… ዝሙት፣ መስረቅ፣ መግደል፣ ምንዝርነት፣ መጐምጀት፣ ክፋት፣ ተንኮል፣ መዳራት፣ ምቀኝነት፣ ስድብ፣ ትዕቢትና ስንፍና የመሳሰሉትን ርኵሰቶችን ሊያጥብ ይችላል፡፡ ወደ ሞት ከሚያደርሱ ሥራዎች ገላግሎን፤ ሕያውን አምላክ እንድናገለግል ነፃ አውጥቶናል፡፡ ይህም በሕይወታችን ሥነ ምግባራዊ ለውጥ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ፍጹም መሥዋዕት በመገኘቱ ደስ ይበለን፡፡
ፍጹም ቃል ኪዳን፡ ቁ. 15-22 አዲሱ በአሮጌው ላይ ሲቀመጥ ለፊተኛው ፍጹም ልዩ የሆነ መልክ ይሰጠዋል፡፡ የክርስቶስ መሥዋዕታዊ ሞት ያስታርቃል፣ ደግሞም ነፃ ያወጣል፡፡ የክርስቶስ ሞት ከኃጢአት እድፈት ያነፃል፡፡ ይህም ለአዲስ ኪዳን አማኞች ብቻ ሳይሆን በተስፋ ለሞቱት ለብሉይ ኪዳን አማኞች ሁሉ መቤዠትን አስገኝቶአል፡፡ ደግሞ በተቀባዩና በእግዚአብሔር መካከል አዲስ ቃል ኪዳን እንደ ተመሠረተ ያረጋግጣል፡፡ ብሉይ ኪዳን ሕይወትንና ሞትን የሚያመለክት ነበረ፣ ቀላል ነገር አልነበረም፡፡ አዲሱ በእንስሳ ደም ሳይሆን፣ ኢየሱስ የራሱን ደም መሥዋዕት አድርጎ በማቅረቡ፣ እንዲሁ ቃል ኪዳኑ ጽኑ ነው፡፡ አንዴ ተሳታፊ ከሆነ በኋላ ሰው ሊያፈርሰው አይችልም፡፡
9፡23-27 የክርስቶስ መሥዋዕት
የክርስቶስ ሞት ለኃጢአት ፍቱን መድኃኒት ነው፡፡ በሞቱ አማካኝነት የሞት ውጤቶች ሁሉ ተወግደዋል፡፡ እንግዲህ ለሌሎች ካህናት ምን ሥራ አለ? የኃጢአት ውጤቶች ከተወገዱ የፊተኞቹ ሥርዓቶች ምን ዋጋ አላቸው? ለኃጢአት ፍጹም መልስ ተገኝቷል፣ ክርስቶስ ሞትን በሞቱ አሸንፎታል፡፡ የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህን በዓመት አንድ ጊዜ በስርየት ቀን ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን እንደሚገባ፣ ኢየሱስም በራሱ ደም ወደ እውነተኛይቱ ሰማያዊ መቅደስ ገባ፡፡ ኃጢአታችንን ለማንፃትና እውነተኛ ሊቀ ካህናችን ሆኖ ሊያማልደን፣ በመጨረሻም ወደ ቤታችን ሊወስደን ተመልሶ ይመጣል፡፡ እርሱን ለተቀበሉት ታላቅ የደስታ ጊዜ ሲሆን፣ እርሱን ላልተቀበሉት ደግሞ ፍርድ የሚሰጥበት ጊዜ ይሆናል፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም የምናገኘው እንዴት ነው? ከሕያውና ፍጹም ሊቀ ካህናችን አርኪ አገልግሎት በማግኘት ነው፡፡ የት እንሂድ? ማንን እንጠይቅ? የሚባሉት ጥያቄዎች የማይጠየቁ ናቸው፡፡ የፊተኛው አገልግሎት ጥቅም ምን ነበረ? ጊዜአዊ አገልግሎት እየሰጠ ገና የሚሆነውን እንዲመለከቱ ሰዎችን ያሳስብ ነበር፡፡ ወደ እርሱ ለመመለስ የማይቻል ነው፡፡ ክርስቶስ ምንን አከናውኗል? ኃጢአትን አስወግዷል፡፡ መሥዋዕታዊው ሞት ኃጢአትን ከነሥሩ አሽቀንጥሮ ጥሎታል፡፡ ፍቱን መድኃኒት ተገኝቶአል፡፡ ከዚህ ከተሻለ ቃል ኪዳን ወዴት እንሄዳለን?
0 Comments