ባለፈው ጥናታችን ምዕራፍ ሦስትንና አራትን ስንመለከት ኢየሱስ ከሙሴና ከኢያሱ እንደሚበልጥና የላቀ ዕረፍት እንደ ሰጠን ተመልክተናል፡፡ በመቀጠል በምዕራፍ አምስትና ስድስት ኢየሱስ ከአሮን ሊቀ ካህንነት እንደሚበልጥ እናጠናለን፡፡ የአሮን ቤተሰብ ታሪክና አገልግሎት ለአንባቢያን (መልእክቱ ለተጻፈላቸው) ሁሉ የታወቀ ነበረ፡፡ የሊቀ ካህን ልዩ ሥራ በተለይም በዘሌዋውያን ምዕራፍ 16 ላይ የተዘረዘረውን በደንብ ያውቃሉ፡፡ አንባቢያን ወደዚያ አገልግሎት የማፈግፈግ ሀሳብ ስለ ነበራቸው፣ አንዴ ከምኵራብ ተለይተው ከክርስቲያኖች ጋር ኅብረት ከፈጠሩ በኋላ፣ ሁሉም ወደ ምኵራብ ብንመለስ ምናለበት የማለት ሀሳብ ነበራቸው፡፡ በመጀመሪያ ውሳኔያቸውን ስንመለከት የሀሳብ ብቻ ይመስለናል፣ ነገር ግን የሀሳብ ውሳኔ ሁሉ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ውጤቶች አሉት፡፡ እነዚህን ለማስተያየት/ለማመዛዘን አልቻሉም፡፡ የተመለከቱት የጊዜው ችግራቸውን እንጂ ወደፊት የሚያጡትን ሕይወትና በረከት አልተመለከቱም፡፡
ሰላምና ይቅርታ የሚገኙት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ብቻ ነው፡፡ ሰው ሁሉ እነዚህን ሁለት ነገሮች ስለሚፈልጉ፣ በተለያዩ መንገዶች ሊያገኙአቸው ይጣጣራሉ፡፡ የብሉይ ኪዳን ዘመን ሰዎች በእርግጥ አግኝተናቸዋል ለማለት አልቻሉም፡፡ ስለዚህ ወደኋላ የማፈግፈግ ምርጫ ውስጥ ቢገቡም፣ እውነተኛ ምርጫ ሊሆንላቸው አይችልም፡፡ ለምሳሌ የሎጥን ሚስት ሁለት ምርጫ ውስጥ በመግባቷ ችግር ውስጥ ወደቀች፡፡ ከዚህ ቀደም የእስራኤል ሰዎች በልባቸው ወደ ግብፅ በመመለሳቸው የሞት ቅጣት ተከተላቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ጸሐፊው ለዕብራውያን አማኞች በሁለቱ ኪዳኖች በአንድ ጊዜ ተሳታፊ መሆን እንደማይችሉ ያሳያቸዋል፡፡ ብሉይን ወይም አዲስ ኪዳንን የመምረጥ ግዴታ እንዳለባቸው ያሳስባቸዋል፡፡ ከሕፃንነት ወደ ፍጹምነት እንዲመጡ፣ ጀምረውት የነበረውን ሌሎችን ማገልገል እንዲቀጥሉበት ይመክራቸዋል፡፡ የእግዚአብሔር ተስፋ ፈጽሞ የማይወድቅ መሆኑን በማሳየት፣ ቃሉ ባሕርዩን ስለሚያንጸባርቅ፣ የተናገረውን የግድ ይፈጽማል በማለት የጌታን ለቃሉ ታማኝ መሆንና የሚታመኑበትንም እንደሚያከብርና እንደሚታመንባቸው ይመክራቸዋል፡፡
በብሉይ ኪዳን ሥርዓት ውስጥ ፍጹም ይቅርታ ለማንም አልተሰጠም፣ የእኛ ብቸኛው ሊቀ ካህን አንድ ጊዜ ብቻ ፍጹም መሥዋዕት በማቅረቡ ከእግዚአብሔር ጋር አስታርቆን ይቅርታ አስገኝቶልናል፡፡ ይህ መለኰታዊ ይቅርታ ኃይል ያለውና የተቀባዩን ሕይወት የሚለውጥ ነው፡፡ የተቀበልነውን መለኰታዊ ይቅርታ ስናስታውስ ጸንተን ለመቆም ያስችለናል፡፡ በጌታ እርዳታ ጽናታችን ወደ ፍጻሜ እንድንደርስ ያደርገናል፡፡
5፡1-10 የኢየሱስ ሊቀ ካህንነት
የሊቀ ካህን አመራረጥ፡- 5፡1-4 ዘፀዓት 6፡16-20 እና 1ዜና.6፤1-3 የአሮንን የትውልድ ዝርዝር ይሰጣሉ፡፡ ሊቀ ካህን ስለመሆኑ ወደ ዘፀዓት 39 እና ዘሌዋውያን 8 ተመልከቱ፡፡ አሮን ሥራውን አልመረጠም፣ እግዚአብሔር ግን ለሥራው መረጠው፡፡ አሮን ራሱ በጣም ደካማ ሰው ነበር፡፡ ዘፀዓት 32፡5 ለሕዝቡ ኃጢአት መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ ለራሱም ኃጢአት ያቀርባል፡፡ ኢየሱስም በእግዚአብሔር የተመረጠ ሲሆን፣ ስለ ራሱ መሥዋዕት አላቀረበም፡፡
እንደ አሮን ለሥራው ተመርጦ ነበር፡- 5፡5-6፣ መዝሙር 2፡7፣ 110፡4-5 ጸሐፊው የኢየሱስን መመረጥ ለማሳየት ሁለት የብሉይ ኪዳን ጥቅሶችን ጠቅሶ ያረጋግጣል፡፡ አሮን ለሥራው እንደተመረጠ፣ ኢየሱስም ለሥራው ተመረጠ፡፡ በኢየሱስ ጥምቀት ጊዜ መመረጡ በአባቱ ተነግሮ ነበር፡፡ ‹‹… በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው›› ማቴዎስ 3፡17፣ 12፡18፣ ማርቆስ 1፡11፣ 9፡7፣ ሉቃስ 3፡22፡፡ ኢየሱስ መዝሙር 110ን በማርቆስ 12፤36 ላይ የጠቀሰው፣ የራሱን ሥራ ባብራራ ጊዜ ሊቀ ካህን ለመሆኑ ማስረጃ ለማድረግ ነው፡፡ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅና ዘላለማዊው ብቸኛው ሊቀ ካህን በመሆኑ ለመሞት ከተዳረገውና ሰው ብቻ ከሆነው ከአሮን ይበልጣል፡፡
ፍጹም ስለመሆኑ፡- 5፡7-10 ሊቀ ካህን ለመሆን ሰው መሆን ያስፈልግ ነበርና፣ ኢየሱስ ሰው ሆኖ መጣ፡፡ መለኰታዊ ሰብዓዊ ሲሆን ገና መለኰታዊ ነበረ፡፡ ሰብዓዊ መለኰታዊ ሲሆን ገና ሰብዓዊ ነበረ፡፡ በአንድ ጊዜ ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክ ነበር፣ ‹‹ና›› ብለን መጨመር አያስፈልገንም፡፡ ያቀረበው ፍጹምና የተሟላ መሥዋዕት ነበር፡፡ ከአባቱ ቁጣ የተነሳ፣ በብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን ወደ አባቱ አቀረበ፡፡ አባቱን በመፍራቱና በመታዘዙም ጸሎቱ ተሰማለት፡፡ እኛን ለማዳን የመከራ ገፈት ተቀበለ፣ ሞተ፣ ተቀበረ፣ ተነሣ፣ ዐረገ፡፡ በታዛዥነቱ ምክንያት ለዘላለም መዳን ምክንያት ሆነልን፡፡ ጸሐፊው ለዕብራውያን አማኞች እነዚህን እውነቶች በማሳየት፣ ኢየሱስ ብቸኛው ሊቀ ካህናቸው እንደ ሆነ በማሳየት የበለጠ ወደ እርሱ እንዲጠጉ ያደርጋል፡፡
5፡11-6፡12 ወደኋላ ስለ ማፈግፈግ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
የበሰላችሁ መሆን ነበረባችሁ፡- 5፡11-14 መዋዠቃቸው ከኃጢአት የተነሣ ሳይሆን በሀሳባቸው ጸንተው ባለመቆማቸው ምክንያት ነበር፣ በ1ኛ ቆሮንቶስ 3፡2 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹ገና ጽኑ መብል ለመብላት አትችሉም ነበርና ወተት ጋትኋችሁ›› በማለት የቆሮንቶስን አማኞች እንደ ወቀሰ፣ ለዕብራውያን አማኞችም ሥነ ምግባራዊ ብስለት በሕይወታቸው ማሳየትና መግለጥ እንደሚጠበቅባቸው ያሳያቸዋል፡፡ የዕብራውያን ክርስቲያኖች በክርስትና ሕይወታቸው የቆዩ ቢሆኑም፣ ስለ ቃሉ ያላቸው እውቀት ውስን ስለ ነበር፣ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ሕፃንነት ይታይባቸው ነበር፡፡ ፍጹም የሚለው ቃል የአእምሮን ብስለት የሚያመለክት ነው፡፡ ፍጹም ክርስቲያን ማለት በሀሳቡ የማያወላውል ቁርጥ ውሳኔ ያለው ማለት ነው፡፡
እደጉ፡- 6፡1-3 ቀላል የሆኑትን ልዩነቶች ብቻ ሳይሆን በጥልቁ ብሉይንና አዲስን መለየት እንዲችሉ ጸሐፊው ይመኝላቸዋል፡፡ ሕፃንነታቸውንም በመገሰፅ ወደ እድገት እንዲመጡ ያሳስባቸዋል፡፡ ዛሬም ቢሆን ብሉይና አዲስ ኪዳን እንዴት እንደ ተሳሠሩ ብዙ ክርስቲያኖች አያውቁም፣ ባለማወቃቸው ምክንያት ብዙ የስሕተት ትምህርት ተሰራጭቷል፡፡ አንዳንዶች ብሉይ ኪዳን ተሸሮእል ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ ብሉይም አዲስ ኪዳን አያስፈልገንም፤ እንደ ወረደ ከእኛ ትሰማላችሁ፣ ይላሉ፡፡ ከዚህ የተነሳ፣ በዚህ ዘመን ያለን አማኞች የቃሉ እጥረት ይታይብናል፡፡ ጸሐፊው ወደ ‹‹ፍጻሜ እንሂድ››፣ እንደሚላቸው እኛም በመንፈሳዊ ሕይወታችን ቃሉን እየተመገብን ወደ እድገት መምጣት አለብን፡፡
ሊሆን የማይችለው ነገር፡- 6፡4-6 የኢየሩሳሌም ተቀማጮች ወንጌል አማኞችን ከወገሩአቸው በ70 ዓ.ም ሊመጣ ካለው ቁጣ እንዴት ሊድኑ ይችላሉ? በሐዋርያት ሥራ 2፡23 ላይ ‹‹ እርሱንም በእግዚአብሔር በተወሰነው አሳቡና በቀደመው ዕውቀቱ ተሰጥቶ በዓመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት›› በማለት ኢየሱስ በአይሁዶች ተጠልቶ እንደ ነበረና እንደ ገደሉት እናያለን፡፡ ጌታም በማቴዎስ 6፡24 ላይ ሁለት ነገሮችን በአንድ ጊዜ መምረጥ አስቸጋሪ እንደ ሆነ ተናግሮ ነበር፡፡ ሳኦል ንስሐ ለመግባት እንቢ ካለ ምን ተስፋ አለው? 1 ሳሙኤል 15 እውነተኛ ድነትን ካገኙ በኋላ፣ ድነት እንዴት ሊጠፋ ይችላል ? ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አከራካሪ ከሆኑ ጥቀሶች አንዱ ነው፡፡ ወደ ደህንነት ከመጣን በኋላ እስከ ፍጻሜ የሚያጸናንና የሚያበረታን ከጌታ ዘንድ ጸጋ ስላለን እሰከ መጨረሻው ጸንተን መጨረስ ይፈለግብናል፡፡
ምሳሌ፡ 6፡7-8 ጸሐይ ጭቃውን ሲያጠነክር፣ ሰምን ደግሞ ያቀልጣል፡፡ ውጤቱ ከባሕርያቸው የተነሣ የተለያየ ነው፡፡ እግዚአብሔር ጸጋውን ሲያዘንብልን ትህትናን ወይም ኩራትን ሊያበቅል ይችላል፣ በሮሜ 2፡4 ላይ ‹‹…የእግዚአብሔርን ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን?›› በማለት እግዚአብሔር እንደ አቀራረባችን እንደሚሠራ ይናገራል፡፡ እግዚአብሔር ከባሕርዩ ጋር የማይስማማባቸውን ነገሮች ለመቀበል አይችልም፡፡ ይህ በመጨረሻ ዘመን የሚሆን ብቻ አይደለም፡፡ ዛሬም ሰው በፈቃዱ ድነትን ሊቀበል ወይም ላይቀበል ምርጫውና መብቱ የራሱ ነው፡፡ እግዚአብሔር እንደ ጳውሎስ ያሉትን ለአገለግሎቱ ስለሚያስፈልጉ ከማስገደድ በስተቀር፣ ማንንም አያስገድድም፣ በፈቃደኝነት የሚመጡትን ይቀበላል፡፡
ደህና ናችሁ፡ 6፡9-12 መልእክት ተቀባዮች ክርስቲያኖች ነበሩ፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናቸውን ጸሐፊው ምንም ሳይጠራጠር ወዳጆች እያለ ይጠራቸዋል፡፡ በስደት ላይ ያሉትን ቅዱሳን ሁሉ በፍቅር እንዳገለገሉ እየመሰከረላቸው፣ ጌታም ዋጋቸውን እንደማይረሳም ያሳስባቸዋል፡፡ ነገር ግን በትምህርት፣ በኅብረትና በአካሄዳቸው ጉድለት ታይቶባቸው እንደ ነበር ይገልጻል፡፡ ያም ጉድለታቸው የነበረው ጸንቶ መቆም ነበር፡፡ ይህንንም ከክርስቶስ ምሳሌነት እንዲማሩ ያሳስባቸዋል፡፡ እኛም በእምነታችን እስከ መጨረሻው ጸንቶ መቆም ይጠበቅብናል፣ ለዚህም የጌታ ጸጋው ይብዛልን፡፡
6፡13-20 የእግዚአብሔር ተስፋ ቃል
አብርሃም የአይሁድ ሕዝብ የሥጋ አባት ብቻ ሳይሆን በእምነት የእግዚአብሔር ቤተሰብ ለሚሆኑ ሁሉ ጭምር የመንፈስ አባት ነው፡፡ እግዚአብሔር በዘፍጥረት 12፡2-3 ላይ ባለው መሠረት የገባለትን ቃል እንደ ፈጸመለት ይህ ክፍል ያስረዳል፡፡ የተስፋ ቃሉንም የፈጸመለት በራሱ በመማል ነው፡፡ መሐላው ለአብርሃም የሰጠውን የበረከት ቃል ኪዳንና የቃል ኪዳኑን እውነተኛነት ያስረገጠበት ሲሆን፣ እነዚህ ሁለቱ የማይለወጡ እውነቶች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ሊዋሽ ስለማይችል፣ በተናገረው ቃል ላይ ሁለት ነገሮች ተጨምረዋል፤ እነዚህ ተስፋና መሐላ የተሰጡት ድነታችን እርግጥና ጽኑ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ የዚህ ክፍለ ምንባብ ውጤቶች በምዕራፍ 7 ላይ በሰፊው ተዘርዝረዋል፡፡ አዲስ ሊቀ ካህን ከመጣ አዲስ ቃል ከተስፋ ጋር መምጣቱ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለአብርሃም ቃሉን እንደፈጸመለት፣ ለእኛም በኢየሱስ የገባውን ቃል ይፈጽምልናል፡፡ ለዚህም ኢየሱስ ቀዳሚ ሆኖ ገብቶ እየማለደልን ይገኛል፡፡ የይቅርታን ታላቅነት እንገንዘብ! ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት የመጀመሪያና የመጨረሻ ማስረጃ ሊሆን ይችላል፡፡ የመለኰታዊ ይቅርታ ተቀባይ መሆንህን የሚያረጋግጥ ምልክቶች ለማሳየት ትችላለህ? ወደኋላ አትመልከት! አዲሱንና አሮጌውን ለማደባለቅ አይቻልም፣(ማር.2፡21-22)፡፡ ሁለቱንም ለመለየት ተማሩ፣ ወደ አሮጌው ኪዳን እንዳንመለስ እንጠንቀቅ፡፡ ሁልጊዜ ተስፋዎችን እናንብብ! እነዚህ ተስፋዎች ለአንድ ትውልድ ብቻ የተሰጡ አይደሉም፣ የእኛም ናቸው፡፡ እንደ አብርሃም ፍጻሜአቸውን ያገኙትን የአባቶችን ታሪክ ማጥናትና ማሰላሰል ለክርስትና ሕይወታችን በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ከአሮን የሚበልጠው ብቸኛው ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማያዊ ቤተ መቅደስ ለእኛ ቀዳሚ ሆኖ ገባ፡፡ በዚያም ስለ እኛ በመማለድ ላይ ይገኛል፡፡ አሜን!
0 Comments