ባለፈው ጥናታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ መልከ ጼዴቅ፣ ለዘላለምና በመሐላ ሊቀ ካህን በመሆኑ ብቸኛው ሊቀ ካህን በመሆኑ ከመልከ ጼዴቅ እንደሚበልጥ ተመለክተናል፡፡ በዛሬው ጥናታችን ደግሞ በምዕራፍ አንድና ሁለት ኢየሱስ ከመላእክት እንደሚበልጥ እንመለከታለን፡፡ በብሉይ ኪዳን አንባቢያን አመለካከት የመላእክት አስፈላጊነት (ምልጃ) መካከለኛ ከሚለው ርዕስ ጋር የተያያዘ ነበረ፡፡ አረመኔዎች ጣዖትን ሲያመልኩ አምላካችን ቅርባችን ነው ማለታቸው ነበረ፡፡ ባንጻሩ አይሁዶች እግዚአብሔርን በጣም ከፍ ስላደረጉት ከራሳቸው አራቁት፡፡ እግዚአብሔር ስለ ራሱ ከገለጸው በላይ ከመጠን በላይ ከፍ አደረጉት፡፡ እግዚአብሔር በመላእክት ይጠቀማል፣ አገልግሎታቸው ግን የተወሰነ ነው፡፡ የዚህ መልእክት አንባቢያን የብሉይ ኪዳን አገልግሎት ያከተመ መሆኑን ሊረዱ አልቻሉም፡፡ በጣም ስላደነቁት የአዲስ ኪዳን አገልግሎት ተክቶታል የማለትን ትምህርት በሙሉ ልባቸው ለመቀበል አዳገታቸው፡፡
በፊተኛው ዘመን የመላእክት አገልግሎት ተገቢና አስፈላጊ ነበረ፡፡ ነገር ግን በፊተኛው ዘመን ውስጥ እንኳ ልጁ ከመላእክት የበለጠ ክብር እንደነበረው የሚገልጥ ብዙ ነጸብራቆች ነበሩ፡፡ መላእክት በክብራቸው ከእርሱ በታችና እርሱን የሚያገለግሉ ነበሩ፡፡ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ በክብሩ ሳይሆን ራሱን ዝቅ አድርጎ መጣ፡፡ ሕልውናው ከእነርሱ ያነሰ በመሆኑ ሳይሆን የአብርሃምን ልጆች እንዲያድናቸው ነበረ፣ ሰው ሆኖ የመጣው፡፡ የባሪያን መልክ (ሰው ሆኖ) ይዞ በመምጣት እውነተኛውንና ፍጹሙን መሥዋዕት በማቅረብ አዳነን፡፡
1፡1-3 መቅድም፡– ይህ ክፍል ለጠቅላላው የዕብራውያን መጽሐፍ መግቢያ ሀሳብ ነው፡፡ እግዚአብሐር በብሉይ ኪዳን ፈቃዱን ለማሳወቅ በነብያቶች በኩል ይናገር ነበር፤ በአዲስ ኪዳን ግን ነብያት ሥፍራቸውን ለወልድ ሰጥተዋል፡፡ ተዘዋዋሪ የነበረው ንግግር አሁን በክርስቶስ በኩል ቀጥተኛ ሆኗል፡፡ እግዚአብሔር በዚህ በመጨረሻው ዘመን ማንነቱንና ፈቃዱን በልጁና በቃሉ በኩል ገለጠ፣ ይህም ልዩ መገለጥ ነው፡፡ እግዚአብሔር ልጁን በመላክ ባህርይውን፣ ፈቃዱንና የድነት (ደህንነት) መንገዱን በግልጽ በዓይናችን እንድናየው አድርጓል፡፡
ኢየሱስ የፍጥረት ተሳታፊ መሆኑ በዮሐንስ ወንጌል ተገልጾአል፡፡ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ነው፡፡ ኢየሱስ ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡(ዮሐ.1፡3) ጸሐፊው የእግዚአብሔርን በኢየሱስ መገለጥ ታላቅ የሚያደርጉትን ሰባት እውነቶች በግልጽ አሰቀምጦአል፡፡ 1) የሁሉም ወራሽ ነው፣ 2) የዓለማት ፈጣሪ ነው፣ 3) ክብሩን የሚገልጥ ነፀብራቅ ነው፣ 4) የባህርዩ ምሳሌ ነው፣ 5) ሁሉን በሥልጣኑ ቃል ይደግፋል፣ 6) ኃጢአታችንን ያነጻል፣ 7) በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀምጦአል፡፡ በአሁኑ ዘመን የሚገኙት አገልግሎቶች ማለት ይቅርታ መስጠትና አማላጅ መሆን የእግዚአብሔር ናቸው፡፡ ከመላእክት በኩል የመጣው ቃል መለኰታዊና ሥልጣን ያለው ነው ብለን ካመንን፣ ኢየሱስ ከብሉይና ከአዲስ ኪዳን ነብያቶች ሁሉ የበላይ ስለሆነ፣ ይበልጥ ኢየሱስ የተናገረው ጽኑና የማይለወጥ ቃል ስለሆነ መስማትና መቀበል አለብን፡፡
1፡4-14 መላእክት፡– የመጽሐፍ ቃል ወሳኝ በመሆኑ ነጥቡን ለማስረዳት ከብሉይ ኪዳን ልዩ ልዩ ጥቅሶች ቀርበዋል፡፡ ስለ ምድራዊ ልደቱና አገልግሎቱ ሳይገልጽ፣ ግን ስለ ሥልጣኑና ክብሩ ብቻ ይገልጻል፡፡ የተቀነባበሩት ጥቅሶች ሁሉ አንድ ዓላማ አላቸው፣ ለወልድ የተሰጠው ክብርና ማዕረግ መላእክት ካላቸው እጅግ በጣም የበለጠ ነው፡፡ ይህን ገልብጦ ለመላእክት የበለጠውን ክብር መስጠት ቃሉን መቃረን ነው፡፡ አይሁድ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ከመላእክት ያነሰ ነው በማለታቸው፣ በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት ለመተው ያስቡ ነበር፡፡ በእውነት ላይ ሳይሆን በልማድና በአፈ ታሪክ ላይ ብቻ ከተመሠረቱበት እንዲላቀቁ ያሳስባቸውና፣ ኢየሱስ ከመላእክት እንደሚበልጥ ሰባት ማስረጃዎችን ያቀርብላቸዋል፡፡ 1) የእግዚአብሔር ልጅ ነው፣ 2) በኵር (ከሁሉ በፊት ነበረ) ነው፣ 3) መላእክት ይሰግዱለታል (የእዚአብሔር ልጆችንም ያገለግላሉ)፣ 4) በዙፋን ተቀምጦ የሚገዛ ዘላለማዊ አምላክ ነው፣ 5) ከጥንት ጀምሮ ጸንቶ የሚኖር፣ 6) በአብ ቀኝ ተቀምጦአል፣ 7) ንጉሥ ነው፡፡ እኛም እነዚህን እውነቶች ልንቀበላቸው የሚገቡ ናቸው፡፡
2፡1-4 ሁለት መልእክቶች፡– በዚህ ክፍል ውስጥ በመላእክትና በክርስቶስ በኩል የመጡትን ሁለት መልእክቶች እያነጻጸረ አቅርቦአል፡፡ ቁ. 1 የአንባቢያን ሁኔታ በግልጽ ያሳያል፡፡ ከመሠረታቸው ለመውደቅ ተቃርበዋል፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን የመጣ መልእክት በእውነት በተዘዋዋሪ መንገድ የመጣ ነበረ፣ ነገር ግን በሰሚዎች ላይ የደረሰው ፍርድ ያ መልእክት መለኰታዊ ኃይል የነበረው መሆኑን አረጋግጦአል፡፡ አዲሱ መልእክተኛ፣ ኢየሱስ ቀጥተኛ ነው፣ ቁ. 3 ከዚህ በላይ ደግሞ መለኰታዊ ለመሆኑ ልዩ ልዩ ማረጋገጫዎች ተሰጥተዋል፡፡
2፡5-9 ብልጫ፡– በምዕራፍ 1፡5-14 የሚገኘው ሀሳብ እንደገና ቀርቧል፡፡ ኢየሱስ ሰው እንኳ ሆኖ ከመላእክት ይበልጣል፡፡ መዝ.8፡4-6 ለማስረጃ ቀርቧል፡፡ ይህ ጥቅስ እንዴት እውነት ይሆናል? በኢየሱስ በምናገኘው ሕይወት እውነት ነው፡፡ እርሱ የእግዚአብሔርን ኃይል በልዩ መጠን ተቀብሎ ልዩ ክብር ተሰጥቶታል፡፡ ከዚህ የተነሣ የዕብራውያን ክርስቲያኖች ልዩ መልእክትና የተሻለ መልእክተኛ ነበራቸው፣ እኛም አለን፡፡ ነገር ግን ይህን እንኳ ያለመረዳት ችግር ያለባቸው ይመስላል፡፡ ይህ የእነርሱ ችግር ብቻ ሳይሆን፣ የእኛም ነው፡፡ ከመላእክት ይልቅ ኢየሱስ ሰው ሆኖ በመምጣቱ የችግራችን ተካፋይ መሆን በመቻሉ፣ ከመላእክት ብልጫ አለው፣ ይህን እውነት መረዳት አለብን፡፡
2፡10-13 ሥቃይ፡– በብዙ የብሉይ ኪዳን ክፍሎች የተነገሩት ትንቢቶች በኢየሱስ መለኰትነት ተፈጽመዋል፡፡ ኢየሱስ ኃይልና ክብር ቢኖረውም በቀራንዮ አልሞተም? ይህ የቀረበውን ማስረጃ አይቃረንም? አይሁዶች ኢየሱስን አልተቀበሉትም፣ አወገዙት፡፡ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ክብር የሚገኘው በሥቃይ አማካኝነት ነው የሚለው ትምህርት በተደጋጋሚ ይገኛል፡፡ በሥቃይ በኩል ነው ድነት ለሰው ሁሉ የደረሰው፣ ኢሳይያስ 52፡13–53፡12፡፡ የመጨረሻ ውጤት ክብርና ድል በመሆኑ በመንገዱ ላይ ምንም እክል እንደ ሌለ ያስረዳል፡፡ እርሱ ከብሮ እኛንም አከበረን፡፡ ዛሬ ሙሉው ክብራችን ለሰዎች ባይታወቅም አንድ ቀን ጌታ ሲመጣ እውንና ፍጹም ይሆናል፡፡
2፡14-18 እውነተኛ መገለጥ፡– በዚህ ክፍል ውስጥ ብዙ መፅናናት እናገኛለን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምዕራፍ ከመላእክት በጥቂት አንሶ ሰው ሆኖ እንደ መጣ ቢናገርም፣ ከመላእክት የሚበልጥበት መንገድ አለው፡፡ ይህም ሰው ሆኖ የመጣው በመጀመሪያ የኃጢአት ዋጋ ሞት ስለ ሆነ መሞት እንዲችል፣ ሁለተኛ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን ሰይጣንን ድል ለማድረግ፣ ሦስተኛው የችግራችን ተካፋይ/ረዳት ለመሆን፣ አራተኛ ሊቀ ካህን ለመሆን፣ አምስተኛ ኃጢአትን ለማስተስረይ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ የኢየሱስ አገልግሎት እውነተኛ እንደነበረ መረዳት እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ የተገልጋይ ሕዝብ ችግር በደንብ እንዲያውቅ ብቸኛው ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ እንደ እኛ ሰው በመሆን ራሱን አዋረደ፡፡ ራሱን ማዋረዱ ብቻ ሳይሆን ችግራችን ስለሚገባው የችግራችን ተካፋይና ረዳት ሆነ፡፡ ክብሩን ለቆ በመዋረዱ ሰይጣንን ድል መትቶ ተገልጋዩን ሕዝብ ከእርሱ እጅ አዳነን፡፡ ድል አድራጊ በመሆኑ ይቅርታ ሰጭ ነው፣ ከዚህ በላይ ደግሞ ሊያማልደን ይችላል፡፡
በክርስቶስ በኩል የመጣልን መገለጥ ወሳኝ ነው፡፡ ከምንም ሌላ ትምህርት ጋር ልናደባልቀው ብንሞክር እናፈርሰዋለን፡፡ ኢየሱስ በማርቆስ ወንጌል 2 ላይ ተመሳሳይ ትምህርት አቅርቦ ነበር፡፡ ያቀረበውን ድነት ስንቀበል ከሰጪው ጋር ተባብረናል፡፡ ሊሰጥ የሚፈልገውን ይቅርታ በተቀበልን ጊዜ የቤተሰቡ አባል ሆነናል፡፡ ክርስቶስን የምናውቀው ለኛ ሲል በመስቀል ባደረገው ሥራ አማካኝነት ነው፡፡ መልእክቱ ስለ ሥቃይ ነው፡፡ ይቅርታ የሚገኘው በክርስቶስ መሥዋዕታዊ ሥቃይ በኩል ብቻ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ተከታዮቹ አነስ ባለ ደረጃ ቢሰቃዩ የሚያስደንቅ አይደለም፡፡ ጸሐፊው የዕብራውያን አማኞች ይህ እውነት እንዲገባቸው ለማድረግ በብዙ ማስረጃ ኢየሱስ ከመላእክት እንደሚበልጥ ያሳቸዋል፡፡ እኛም በዚህ ዘመን የምንገኝ አማኞች ኢየሱስ ክርስቶስ ከመላእክት እንደሚበልጥ አውቀን፣ ተቀብለንና አምነን ስግደትና አምልኮን ለእርሱ ብቻ ማድረግ እንዳለብን መረዳት ይኖርብናል፡፡ በሚቀጥለው ጥናታችን በምዕራፍ ሦስትና አራት ኢየሱስ ከሙሴ እንደሚበልጥ የሚቀርቡትን ማስረጃዎች እንመለከታለን፡፡
0 Comments