በባለፈው ጽሑፎች ‹‹ተልዕኮው የት ደርሷል?›› በሚለው ርዕስ ሥር የሐዋርያት ሥራን መጽሐፍ በወንገጌል አገልግሎት ዙሪያ በመዳሰስ፣ የኢየሩሳሌምና የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ታላቁን ተልዕኮ የት እንዳደረሱት ለማየት ሞክረናል፡፡ በዚህ ‹‹ሊቀ ካህኑ›› በሚለው ርዕስ ሥር፣ ጌታ እንደ ረዳን የዕብራውያንን መልእክት በሰባት ክፍሎች(ርዕሶች) ከፍለን እናያለን፡፡ በመጀመሪያ በየክፍሎች መጀመሪያ ላይ የአንባቢያንን (መልእክት ተቀባዮች) ሁኔታና የመልእክቱን ይዘት በአጭሩ ካየን በኋላ ወደ ንዑሳን (ትናንሽ) ርዕሶች ከፋፍለን ማብራሪያዎቹን እንመለከታለን፡፡ 

በዕብራውያን መልእክት የምንመለከተው ዋና ትምህርት፣ ኢየሱስ ብቸኛው የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናችን እንደ ሆነ ነው፡፡ ጸሐፊው፣ በዘሌዋውያን መጽሐፍ የተገለጡትን የመሥዋዕትና የአምልኮው ሥርዓት ፈጻሚዎችን ሁሉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር ሁሉ ጥላ በማለት ይጠራቸዋል፡፡ (ዕብ. 8፡5፣10፡1) በዚህ ምክንያት የአዲስ ኪዳን አማኞች ሁሉ፣ የዕብራውያን መልእክት ልናጠናው የሚገባን በጣም አስፈላጊ መጽሐፍ ነው፡፡ ኢየሱስ ‹‹ብቸኛው ሊቀ ካህን›› በመሆን ፍጹም የሆነውን መሥዋዕት በመስቀል ላይ በማቅረብ፣ ትንቢቶችንና ሕግጋትን ሁሉ ፈጽሞ ያለፈ በመሆኑ፣ ከብሉይ ኪዳን አገልጋዮችና አባቶች ከምንላቸው ሁሉ የበለጠ ወይም የተሻለ መሆኑን ጸሐፊው ያስተምረናል፡፡

የዕብራውያንን መልእክት ስንመለከት ሁለት ዓይነት መሠረታዊ ችግሮች/ጥያቄዎች ይገጥሙናል፡፡ ጸሐፊው ማን ነበረ? መቼ ተጻፈ? የሚሉት ጥያቄዎች ሲሆኑ፣ በእነዚህ ጥያቄዎች ምክንያት እስከ ሦስተኛው ምዕተ ዓመት ድረስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቀኖና (ካኖን) ውስጥ ሳይገባ ቆይቶ ነበር፡፡ ከዚያ የሮምና የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያናት የጳውሎስ ነው ብለው ተቀበሉት፡፡ በጊዜው በነበሩት አበውም ሆነ፣ ዛሬም ቢሆን ይህ መልእክት አከራካሪ ነው፡፡ ጸሐፊው ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ፣ ከውስጥ ማስረጃ ባይገኝለትም መልእክቱን ግን ልንቀበለው ይገባናል፡፡ እውነተኛው የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ የማይታወቅ ቢሆንም፣ የተለያዩ ቤተ ክርስቲያን አባቶችና የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ጸሐፊው እከሌ ነው ለማለት ይሞክራሉ፡፡

     ሐዋርያው ጳውሎስ አልጻፈውም የሚሉት  የሚከተሉትን ማስረጃዎች ያቀርባሉ፡፡

          1ኛ. በመልእክቱ ውስጥ የጳውሎስ ስሙ አልተጠቀሰም፡፡

          2ኛ. ቃሉና አነጋገሩ የጳውሎስን አይመስልም፡፡

           3ኛ. ጳውሎስ የዕብራውያን ሐዋርያ አልነበረም፡፡

           4ኛ. ጳውሎስ ወንጌሉን ከሰው አለመስማቱን እንደ ማስረጃ ያቀርባሉ፡፡  

      ሐዋርያው ጳውሎስ ጽፎታል የሚሉትም የራሳቸውን ማስረጃ ያቀርባሉ፡፡

           1ኛ. ዕብራውያን እንደ ጠሉት ስላወቀ ስሙን ደብቆአል፡፡

          2ኛ. ለዕብራውያን ዘመዶቹ ታላቅ ናፍቆትና ሸክም ነበረው፡፡ (ሮሜ 9፡1-5)

          3ኛ. ጴጥሮስ በሁለተኛ መልእክቱ የጠቀሰው ጳውሎስን ነው ይላሉ፡፡ (2ጴጥ. 3፡15-16)

          4ኛ. የሐዋርያው ጳውሎስን የብሉይ ኪዳን የጠለቀ ዕውቀት፣ እንደ ማስረጃ ለማቅረብ ይሞክራሉ፡፡

 ሌሎችም በርናባስ፣ ሉቃስ፣ አጵሎስ፣ ቀሌምንጦስና እንዲሁም ከእግዚአብሔር በቀር የሚያውቅ የለም የሚሉ አሉ፡፡ የሆነ ሆኖ መልእክቱ በማን እጅ እንደ ተጻፈ በእውነት ባናውቅም እውነተኛው ደራሲው መንፈስ ቅዱስ እንደ ሆነ ጥርጣሬ በፍጹም ሊገባን አይገባም፡፡ የብሉይ ኪዳን ጥልቅ ዕውቀት ያለው ለመሆኑ ከጽሑፉ መረዳት እንችላለን፡፡ ከጥንት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያናት እንደ እግዚአብሔር ቃል አድርገው ተቀብለውታል፤ እኛም የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ ለመቀበል የሚያስቸግረን ነገር የለም፡፡

የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ መልእክቱን የጻፈው ለማን እንደ ሆነ ባይጠቅስም፣ ላመኑ ዕብራውያን ክርስቲያኖች የተጻፈ እንደሆነ ከጽሑፉ መገመት ይቻላል፡፡ ጸሐፊው ኢየሱስ ክርስቶስ ከብሉይ ኪዳን አገልጋዮች የተሻለና የበለጠ ሐዋርያችንና ሊቀ ካህናችን እንደ ሆነና ከመላእክት፣ ከሙሴ፣ ከኢያሱና ከአሮን እንደሚበልጥ ያስተምረናል፡፡ በመቀጠልም እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ  በኩል የተሻለ ቃል ኪዳን እንደ ገባልን፣ የተሻለ ተስፋ እንደ ሰጠንና የተሻለ ኑሮ መኖር እንድንችል እንደ ተደረግን ያስተምረናል፡፡ ጸሐፊው ኢየሱስን አጉልቶ በመሳል፣ ብቸኛው የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናችን እንደ ሆነ፣ ክርስቶስ ብቻ ወደ እግዚአብሔር ህልውና ሊያቀርበን እንደሚችል፣ ወደ ዙፋኑ መቅረቢያ ተዘግቶ የነበረው በር፣ ከኢየሱስ ማንነትና በመስቀል ላይ ከሠራው ሥራ የተነሳ እንደ ተከፈተ ያሳየናል፡፡ የኃጢአት ዋጋ ተከፍሎአልና ወደ  እግዚአብሔር የሚወስደው መንገድም ያለ ምንም ከልካይ ለሚያምኑበት ልጆቹ ክፍት ሆኖአል፡፡

ከባቢሎን ምርኮ በኋላ፣ ታቦቱ ባለ መኖሩ ምክንያት፣ (ተማርኳል፣ ተቃጥሎአል፣ ተደብቆአል እና አሁን አለ የሚሉትን ወደፊት እናነሳቸዋለን) የአይሁድ ሊቀ ካህን የሃይማኖታቸው ምሰሶ ሆነ፣ በእውነት ያለርሱ ሥርዓታቸው በፍጹም ጐዶሎ ነበር፡፡ የብሉይ ኪዳን ሥልጣን ወደር የማይገኝለት ሲሆን፣ ኢየሱስን የእግዚአብሔር ልጅ ከመላእክት፣ ከሙሴና ከአሮን እንደሚበልጥ ብሉይ ኪዳን በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡ በፊተኛው ኪዳን እነዚህ ሦስት ታላላቅ የአገልግሎት ክፍሎች ነበሩ፣ የዕብራውያን ጸሐፊ ከብሉይ ኪዳን እየጠቀሰ ኢየሱስ ከእነዚህ ሁሉ እንደሚበልጥ ያስረዳል፡፡ በውድድር አሸነፋቸው ማለት ሳይሆን፣ እነርሱ ያመለከቱትን ሊያሟላ ችሏል፣ በማለት ያስረዳል፡፡ እነዚህ ሁሉ እርሱን ይጠባበቁና ለመምጣቱ መድረክን ያዘጋጁ ነበር፣ ኢየሱስ ብልጫ ያለው መሆኑንም ይመሰክሩ ነበር፡፡

ክርስትና፣ በኤፌሶን መልእክት 1፡4 ‹‹ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን›› በሚለው መሠረት አዲስ ሳይሆን ከዓለም መፈጠር ጋር የተቀናጀ መሆኑን ሐዋርያው ጳውሎስ ያስረዳል፤ እግዚአብሔር በአዲስ ኪዳን ራሱን በልጁ ለመግለጥ በጀመረ ጊዜ፣ ለልጁ መምጣት ዓለምን በሃይማኖት፣ በባህልና በቋንቋ ያዘጋጃት ነበር፡፡ በሉቃስ ወንጌል መላእክት ሁሉ መምጣቱን አብስረዋል፡፡ በገላትያ መልእክት ላይ ስለ አብርሃምና ቃል ኪዳኑ፣ እንዲሁም የሙሴ ሕግ ለክርስቶስ መምጣትና አዲስ ኪዳን ዝግጅት እንዴት እንዳደረጉ ጳውሎስ በሌሎች መልእክቶቹ በሰፊው ያብራራል፣ ተመሳሳይ ማብራሪያ በዕብራውያን ውስጥ ግን አልተሰጠም፡፡

መዝሙር 110 ኢየሱስን አዲስ ብቸኛው ሊቀ ካህን አድርጎ ይሾመዋል፣ አዲሱ ሊቀ ካህን ደግሞ አዲስ ቃል ኪዳን አቁሟል፡፡ ይህ አዲስ ቃል ኪዳን ፊተኛውን ተክቶታል፡፡ የፊተኛው ዓላማና ግብ ተከናውኖአል፣ ተፈጽሟል፣ ስለዚህ በአዲስ ኪዳን ተተክቶአል፣ አሮጌው ኪዳን ለአዲሱ ኪዳን (ጥላው ለአካሉ) ስፍራ መልቀቁን ያመለክታል፡፡ በዚህ ምክንያት አሮጌው ቃል ኪዳን ተሽሮአል፣(…የቀደመች ትእዛዝ ተሽራለች…ዕብ.7፡18) አሮጌው ሥርዓት ቢሻርም፣ መለኰታዊ መገለጥ እንደመሆኑ መጠን ሥልጣኑ አልተነካም፣ ትምህርት ይሰጣል፡፡ ብሉይ ኪዳን በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለሚገኘው ትምህርት ሁሉ ሥር፣ ግንድና መሠረት ነው፡፡ ያለ ብሉይ ኪዳን አዲስ ኪዳን በፍጹም ሊገባንና ልንረዳው አንችልም፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም በሁለተኛ ጢሞቴዎስ 3፡16 ላይ ‹‹…የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ (ብሉይ ኪዳን) ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል›› በማለት ጠቃሚነቱን በግልጽ አስቀምጦታል፡፡

የክርስቶስ የሆንን ሁሉ የፊተኛው ሳይሆን የኋለኛው ቃል ኪዳን ተሳታፊዎች ነን፡፡ የአዲሱ ቃል ኪዳን ምልክቶች ሁለት  ሲሆኑ፣ እነርሱም 1. ጥምቀት እና 2 . የጌታ ራት ናቸው፡፡ በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ላለው ቃል ኪዳን ምልክት  እንዲሆኑ በጌታ ተሰጥተውናል፡፡ ጥምቀት ለአጥማቂው፣ ለተጠማቂውና ለተመልካች፣ ውስጣዊውን ለውጥ፣ በውጫዊ ለማረጋገጫ ሊሆን ተሰጥቶናል፡፡ ጥምቀት ከክርስቶስ ጋር መሞታችንን የምንመሰክርበት ሲሆን፣ የጌታ ራት ጌታ ያደረገልንን የምናስታውስበትና ምሥጋና የምንሰጥበት የመታሰቢያ ሥርዓት ነው፡፡

በእነዚህ መንገዶች ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ስነገባ፣ እርሱም ኃይል ይሰጠናል፡፡ ከዚህ የተነሣ ኅብረታችን ከምኲራብ ወይም ከቤተ መቅደስ ጋር ሳይሆን፣ ከክርስቲያኖች አንድነት ወይም ጉባዔ ጋር ነው፡፡ ምንም መከራ ቢመጣ መገኘት ያለብን ክርስቶስ በሚገኝበት ማለት ከቤተሰቡ ጋር ነው፡፡ የድሮውን ኪዳን ትተን ወደ አዲሱ ኪዳን ስንገባ ችግር፣ ፈተናና መከራ ሊገጥመን ይችላል፡፡ የዕብራውያንን ክርስቲያኖችን የገጠማቸው ችግር ይህ ነበር፣ ስለዚህ ጸሐፊው በመከራ ውስጥ እንዴት ማለፍ እንዳለባቸው ያስተምራቸዋል፡፡ ጌታ በመከራ ውስጥ ሰላምና እርካታ ይሰጠናል እንጂ ከመከራ ሁሉ ሊያድነን ምንም ተስፋ አልሰጠንም፡፡   

እግዚአብሔር ለመረጣቸው ሰዎች አዲስ ቃል ኪዳን ከሰጠ፣ አረማመዳቸው አዲስ መሆን አለበት፣ የጋራ ኑሮአቸውና ምስክርነታቸው ደግሞ ልዩ ይሆናል፡፡ ይህ ሁሉ ፈጽሞ አዲስ ሳይሆን በብሉይ ኪዳን ተጠቁሞ ነበር፡፡ ዛሬም ጌታ የተናገረውን ተቀብለን በሥራ ላይ እንድናውለው ይፈለግብናል፡፡ ለአዲሱ ቃል ኪዳን መታዘዝ ታላቅ በረከት ያመጣል፡፡ ከዚህ በላይ ከመግቢያው እንዳየነው፣ ጸሐፊውን የሚጠቁም ነገር ባናገኝበትም፣ ትምህርቱ ስለ ክርስቶስ ብዙ እውነቶችን ያስጨብጣል፡፡ ስለዚህ እኔ ለራሴ ሐዋርያው ጳውሎስ ጽፎታል ብዬ መቀበሉ ይቀለኛል፣ ምክንያቱም ጳውሎስ የብሉይ ኪዳን በቂ ዕውቀት ስለ ነበረው ከአዲስ ኪዳን ትምህርት ጋር በማዛመድ ለአማኞች መሠረታዊ ትምህርት፣ ዕውቀትና መረዳት እንዲኖረን አድርጎ ጽፎታል፣ ብዬ አምናለሁ፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *