ጳውሎስና በርናባስ በኢየሩሳሌም በነበረው ጉባኤ ተካፍለው ወደ አንጾኪያ እንደ ተመለሱ ቀደም ብለን ተመልክተናል፡፡ በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ጥቂት ቀን ተቀምጠው (ዓመት ፈቃድ) ሕዝቡን እያስተማሩ ከቆዩ በኋላ፣ ሁለተኛውን የወንጌል ጉዞ ለመጀመር ሲነሱ በዚህ ምዕራፍ 15 መጨረሻ ላይ እናገኛለን፡፡ በዚህም በ2ኛው ጕዞ ጳውሎስ ሲላስን ይዞ ሲወጣ፣ በርናባስ ማርቆስን ይዞ በተለያየ አቅጣጫ እንደ ወጡ ቃሉ ይነግረናል (የሐዋ. 15፡36-41)፡፡
የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን 2ኛውን የወንጌል መልእክተኛነት (የሚስዮናዊ) ጕዞአቸውን እንዲያደርጉ ለእግዚአብሔር ጸጋ አደራ በመስጠት በጸሎት ባርካ ላከቻቸው (15:40)፡፡ ጳውሎስ 2ኛውን የወንጌል ጕዞ ያደረገው በመጀመሪያ ጕዞው ወደ መጨረሻ ላይ ወንጌል የሰበከባቸውን ሥፍራዎች መነሻ በማድረግ እየጎበኘና እያጸናቸው ወደ እስያ በማምራት ሲሆን፣ መንፈስ ቅዱስ ግን በዚያ እንዳይናገሩ ከለከላቸው፡፡ በመቀጠልም፣ በገላትያ አድርገው ወደ ቢታንያ ሄደው ለመናገር ሲሉ፣ አሁንም ተከለከሉ (16፡6-10)፡፡
ጳውሎስም በራዕይ ርዳታ ሲጠየቅ ባየው መሠረት እስያን ለቀው ወደ ፊልጵስዩስ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ወንጌልን ይዘው ወደ አውሮፓ ከተማ ደረሱ፡፡ በፊልጵስዩስ ከተማ የሰዎች መዳን የሐር ነጋዴዋ ሊድያና የወህኒ ቤቱ ጠባቂ ከነቤተሰቡ ወንጌልን ተቀብለው መዳናቸው የሚያስደንቅ የወንጌል ሥራ እንደተሠራ ማየት ይቻላል (16፡11-34)፡፡
ይህ የሚያስደንቅ የወንጌል ሥራ ቢሠራም፣ የሚያሳዝን መከራና እስራት ደረሰባቸው፡፡ ቢሆንም ግን፣ የሥራው ባለቤት እግዚአብሔር ስለ ሆነ፣ ይበልጥ ወንጌሉን ለማስፋት ተዓምር ሠርቶ እነጳውሎስን ከእስር ቤት አወጣቸው፡፡ ከእስር ቤት ቢወጡም መከራ ፈርተው አገልግሎታቸውን አላቆሙም፣ በመቀጠል የተለያዩ ከተሞችን አልፈው ወደ ተስሎንቄ ከተማ ደርሰው፣ በዚያ ለሦስት ሰንበት ያህል በመቀመጥ ወንጌልን ሲሰብኩ፣ አሁንም ስደትና መከራ ደረሰባቸው (17፡1-9)፡፡
ሰው በተደጋጋሚ ችግር ሲደርስበት የእግዚአብሔር ፈቃድ ላይሆን ይችላል ብሎ አገልግሎቱን ሊያቆም ይፈተናል፣ ጳውሎስ ግን ለማቆም በፍጹም ሲያስብ አንመለከትም፡፡ በዚህ ጊዜ አገልግሎቱን ሳይጨርስ ያለ ጊዜው እንዳይሞት ብለው፣ ወንድሞች ጳውሎስንና ሲላስን ወደ ቤሪያ በሰደዱአቸው ጊዜ ከደረሰባቸው መከራ ትንሽ ማረፍ ሲገባቸው፣ እነርሱ ግን ወደ ምኵራብ ገብተው ቃሉን ማስተማር ሲጀምሩ፣ ብዙዎች ግሪኮች (አሕዛቦች) በጌታ አመኑ (17፡10-15)፡፡
ጀግናው የወንጌል አርበኛ ጳውሎስ ምንም እንኳን መከራና እስራት ቢደርስበትም፣ አሁንም ዕረፍት ያስፈልገኛል ሳይልና የዓመት ፈቃድ ሳይወስድ፣ ከአቴና ወጥቶ ወደ ቆሮንቶስ ከተማ በመምጣት ከሲላስና ጢሞቴዎስ ጋር ሆነው በዚያ እያገለገሉ ሳለ፣ አሁንም ተቃውሞ ደረሰባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ደረሰበትን ተቃውሞ ሲመለከት ወንጌልን መስበክ እንደማይችል በስሜቱ ስለ ተረዳ፣ የእግሩን ትቢያ አራግፎ ሊወጣ ሲል፣ ጌታ በሌሊት በራዕይ ተገልጦለት እንዳትወጣ ገና ብዙ ሰዎች አሉኝ ብሎ ተነናገረው፡፡ በዚህም ምክንያት አንድ ዓመት ከስድስት ወር ተቀምጦ በማስተማር አሳለፈ፣ የበረከት ጊዜም ነበራቸው፡፡(18፡9-10)
እኛም ከሚደርስብን ችግር የተነሳ በስሜታችን አንድ ውሳኔ ልንወስን እንችላለን፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ ግን፣ እኛ በዙሪያችን ከሰማነውና ከሚደርስብን ተነስተን ከወሰንነው ውሳኔ ጋር የተለያየ ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ እንደ ጳውሎስ ቆም ብለን የጌታን ድምጽ በትክክል መስማትና ማዳመጥ ይኖርብናል፡፡ ጳውሎስም ጌታ የተናገረውን በመስማት ውሳኔውን አስተካክሎ አገልግሎቱን በመቀጠሉ ብዙ ፍሬ ሊያገኝ ችሎአል፡፡ በዚህም መከራው ሲበዛበት፣(18፡12-17) በሶርያ አድርጎ ወደ ኤፌሶን ቀጥሎም በቂሣርያ አድርጎ 2ኛውን የወንጌል ጕዞ ለመጨረስ ወደ አንጾኪያ ከተማ መጣ (18፡22)፡፡
ከጥቂት ቀንም በኋላ ቆይቶ ሦስተኛውን የወንጌል ጕዞ ለመጀመር ዝግጅት አድርጎ ተነሳ፡፡ ለዚህም ነው የወንጌል አርበኛ ያልኩት፣ እኔ ባልለውም ጌታው ብሎት በቀኙ አስቀምጦታል፡፡ የዓመት ፈቃድ ይሙላ አይሙላ አናውቅም፣ ቃሉ ግን “ለጥቂት ቀን” በማለት ይገልጸዋል፡፡ ከጥቂት ቀን በኋላ ወደ ጦርነት ሜዳው ገብቶ መፋለም ጀመረ፡፡ ጥቂት ቀን ካለ፣ ከሳምንት እስከ ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚያን ዘመን የዓመት ፈቃድ ይኑር አይኑር ያደረግሁት ጥናት የለም፡፡ ስለዚህ እንደ ዓመት ፈቃድ ታስቦለት ይሁን ወይም ሰው በተፈጥሮው ስለ ሚደክመው ትንሽ ዕረፍት አድርግ ብለውት ሊሆን ይችላል፣ እነዚያን ጥቂት ቀን ያረፈው፡፡ ለነገሩማ እነዚያ ጥቂት ቀናትም ያረፈባቸው ሳይሆኑ ዘገባ ያቀረበባቸው፣ ያስተማረባቸው፣ ምዕመኑን የመከረበትና ያጽናናባቸው ቀናት ነበሩ (18፡22-23)፡፡
ጳውሎስም እንደገና ወደ ኤፌሶን በመሄድ ሁለት ዓመት ተቀምጦ እንደ ልማዱ ወደ ምኵራብም እየገባ ባገለገለ ጊዜ ጌታ ብዙ አስደናቂ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ እነጳውሎስ ዋጋ ለመክፈል ወስነው ሲገቡ፣ ጌታም አስደናቂ የሆኑ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ ጳውሎስም እጁን የሚጭንባቸው ሰዎች ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ይወርድባቸውና በልሳኖችና ትንቢትም ይናገሩ ነበር፣ ከጳውሎስም በሚወሰድ ጨርቅ ብዙ ሰዎች ይፈወሱ ነበር፣ ደግሞ አስማተኛ የሆኑ መጽሐፋቸውን እያቃጠሉ ጌታን እናምናለን እያሉ ያምኑ ነበር (19፡1-20)፡፡
በዚህም ሥፍራ (በኤፌሶን) ተቃውሞ ስለ በዛበት፣ ወደ መቄዶንያ መሄድ ፈልጎ ወደ ሚሊጢን መጣና ለኤፌሶን ሽማግሌዎች መጋቢያዊ፣ አባታዊና ወንድማዊ ምክርና ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ በዓለ ኀምሳን በኢየሩሳሌም ለመዋል ተንበርክኮ ከሁላቸው ጋር ጸልዮ፣ እነርሱም እያለቀሱ እስከ መርከብ ድረስ ሸኝተውት፣ ተሰናብቶአቸው ሄደ (20፡1-38)፡፡ ጳውሎስ የዓመት ፈቃድ ወስዶ ማረፍ ሲገባው ጊዜው ሁሉ ያሳለፈው ከሥፍራ ወደ ሥፍራ በመሄድ ነበር፡፡ ከጳውሎስ ሕይወት ምን ተማርን? ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮቿ ጤናማ አገልግሎት እንደ ሰጡ፣ የዓመት ፈቃድ መስጠት ይኖርባታል፡፡ የዓመት ፈቃድ ወስዶ ማረፍና መታደስ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ስናርፍ ግን የቦታና የሥራ ለውጥ ማድረግ እንጂ፣ እንዲሁ ተኝቶ ጊዜ በማባከን መሆን የለበትም፡፡
0 Comments