ባለፈው ትምህርታችን እንደ ተመለከትነው፣ ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም ሁለቱን ቡድኖች አስወጥተው ውይይት አደረጉ፡፡ በውይይቱም መካከል ጴጥሮስ ተነስቶ ወደ አሕዛብ (ቆርኔሌዎስ) ቤት ሄዶ እንዲያገለግል እንዴት እንደ ተመረጠና እግዚአብሔርም ሳያዳላ መንፈስ ቅዱስን ለአይሁድ (ሐዋርያት) እና ለአሕዛብም (ቆርኔሌዎስ) እንደ ሰጠ መሰከረላቸው (ቁ.6-11)፡፡

ከዚያም በኋላ እንደገና ጳውሎስና በርናባስ ዕድል ተሰጥቷቸው ለሕዝቡ (ለጉባኤው) ሲያስረዱ ሁሉም ጸጥ ብለው ይሰሙ ነበር፡፡ በመጨረሻም፣ የጉባኤው ሰብሳቢ ያዕቆብ (የጌታ ወንድም) ተነስቶ ማጠቃለያ ሐሳብ ሰጠ፡፡ “እነርሱም ዝም ካሉ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ብሎ መለሰ፡- ወንድሞች ሆይ ስሙኝ፡፡ እግዚአብሔር ለስሙ የሚሆንን ወገን ከአሕዛብ ይወስድ ዘንድ አስቀድሞ እንዴት እንደ ጎበኘ ስምዖን ተርኮአል፡፡ ከዚህም ጋር የነብያት ቃል ይስማማል፣ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፡- …በስሜ የተጠሩት አሕዛብ ሁሉ ጌታን ይፈልጉ ዘንድ እመልሳለሁ…ስለዚህ ከአሕዛብ ወደ እግዚአብሔር የዞሩትን እንዳናስቸግራቸው፣ ነገር ግን ከጣዖት ርኩሰትና ከዝሙትም ከታነቀም ከደምም ይርቁ ዘንድ እንድንጽፍላቸው እቈርጣለሁ›› (የሐዋ. 15፡13-20)፡፡

ቀጥሎም ሐዋርያት፣ ሽማግሌዎችና ሕዝቡም ሆነው ወደ አንጾኪያ የሚላኩትን ሰዎች መርጠው ከነጳውሎስ ጋር ሆነው የተወሰነውን ውሳኔ እንዲያሳውቁ አደረጉ፡፡ “ያን ጊዜ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ከቤተ ክርስቲያኑ ሁሉ ጋር ከእነርሱ የተመረጡትን ሰዎች ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር ወደ አንጾኪያ ይልኩ ዘንድ ፈቀዱ፤ እነርሱም በወንድሞች መካከል ዋናዎች ሆነው በርስያን ይሁዳና ሲላስ ነበሩ፡፡ እንዲህም ጽፈው በእነርሱ እጅ ላኩ፡- ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ወንድሞችም በአንጾኪያና በሶርያ በኪልቅያም ለሚኖሩ ከአሕዛብ ወገን ለሆኑ ወንድሞች ሰላምታ ያቀርባሉ፡፡ ያላዘዝናቸው ሰዎች ከእኛ ወጥተው፡- ትገረዙ ዘንድና ሕግን ትጠብቁ ዘንድ ይገባችኋል ብለው ልባችሁን እያወኩ በቃል እንዳናወጡአችሁ ስለ ሰማን፣ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነፍሳቸውን ከሰጡት ከምንወዳቸው ከበርናባስና ከጳውሎስ ጋር የተመረጡትን ሰዎች ወደ እናንተ እንልክ ዘንድ በአንድ ልብ ሆነን ፈቀድን፡፡ ራሳቸውም ደግሞ በቃላቸው ያንኑ ይነግሩአችሁ ዘንድ ይሁዳንና ሲላስን ልከናል፡፡ ለጣዖት ከተሰዋ፣ ከደምም፣ ከታነቀም፣ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናልና፤ ከዚህም ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ፡፡ ጤና ይስጣችሁ›› (የሐዋ. 15፡22-29)፡፡

በዚህ ክፍል ስለ በርናባስና ጳውሎስ ሲናገሩ፣ “…ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነፍሳቸውን ከሰጡት ከምንወዳቸው” በማለት መልካም ምሥክርነት ሲሰጧቸው እናነብባለን፡፡  የተመረጡትም ሰዎች ይሁዳና ሲላስም ከነጳውሎስ ጋር ወደ አንጾኪያ ወርደው የተላከውን ደብዳቤ በማንበብና በቃልም በመናገር ሕዝቡን ደስ አሰኟቸው፡፡ ይሁዳና ሲላስም ነብያት ስለ ነበሩ በመካከላቸው ለተወሰነ ቀን በመቀመጥ ወንድሞችን ሲመክሩአቸውና ሲያጽናኑአቸው ቆይተው ወደ መጡበት ወደ ሐዋርያት ተመለሱ፡፡

ሲላስ ግን፣ እንደ በርናባስ የአንጾኪያን መንፈሳዊ እንቅስቃሴ እንዲመለከት በተላከበት በዚያው ለመቅረት ወስኖ ቀረ፡፡ ለመቅረት የወሰነበት ምክንያት ቤተ ክርስቲያኒቱ የምታሳየው ፍቅር ስቦት እንደ ሆነ ምንም ጥርጥር የለም፡፡ እንኳን አይሁዳዊ ለሆነ ሰው ቀርቶ ለሕዝቦች ሁሉ (ለድኻም ለሀብታምም፣ ላልተማሩም ለተማሩም፣ ለጥቁርም ለነጭም) የምትመች ቤተ ክርስቲያን ነበረች (የሐዋ.15፡30-35)  በሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ችግሮች ወደ አንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ተዛምተው ሊያውኳት ቢሞክሩም፣ እግዚአብሔር ሊጠቀምባት ስለ ፈለገ የነበሩትን ችግሮች ሁሉ  እንደ ጴጥሮስ ባሉ የተለያዩ ሰዎች በመጠቀም ነገሮች ወደ ሰላም እንዲመጡ በማድረጉ፣ የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን የወንጌሉን ሥራ በሚገባ መቀጠል ችላለች፡፡ እኛም ከዚህ ውይይት ትምህርት ወስደን፣ የተቀበልነውን ተልዕኮ የት እንዳደረስነው (ኢየሩሳሌም፣ ይሁዳ፣ ሰማርያ፣ ዓለም ዳርቻ) በመፈተሽ ከውስጥም ይሁን ከውጭ የመጡ ችግሮችን በውይይት መፍትሔ በመስጠት አስወግደን የወንጌልን ሥራ ብቻ ለመሥራት ወደ ፊት እንዘርጋ፡፡ በውይይት የማይፈታ ነገር የለምና ችግሮቻችንን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ እያመጣን፣ በውይይታችን  መካከል ጌታን በመጋበዝ ለውጥ ማምጣት ይኖርብናል፡፡ በተለያዩ ችግሮች ተይዘን ስንነካከስና ስንጣላ፣ ተልዕኮውን ከዳር ሳናደርስ ጌታ በድንገት እንዳይመጣ?


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *