የአንጾኪያን ቤተ ክርስቲያን ስንመለከት፣ ጸሐፊው መተረክ የሚጀምርልን በአጥቢያይቱ በነበሩት አገልጋዮች ላይ ይሆናል፡፡ በሐዋርያት ሥራ 13፡1 ላይ አምስት ያህሉን ሰዎች በስም በመጥቀስ ከሚዘረዝራቸው መካከል በርናባስና ጳውሎስ ይገኙበታል፡፡ በመቀጠልም፣ በዚህች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የጾምና ጸሎት ጊዜ እየተካሄደ መንፈስ ቅዱስ በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ ብሎ እንደ ተለዩ፣ በተለይም ለሚስዮናዊነት አገልግሎት እንደተጠሩና የመጀመሪያውን የወንጌል ጉዞ እንደ ጀመሩ ሉቃስ ይተርክልናል፡፡ የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ለአገልግሎት የለዩዋቸው ቁልፍ፣ ውድና ተወዳጅ የሆኑ አገልጋዮቻቸውን ነበር አሳልፈው የሰጡት፡፡ ምንም ሳያቅማሙ ተልዕኮን ለማሳካት ከመንፈስ ቅዱስ ለሰሙት ድምጽ ሲታዘዙ እንመለከታለን፡፡ አስደናቂ ውሳኔ ነው፡፡ እኛ ብንሆን እናደርገው ይሆን?   

በቁጥር 1 ላይ የአጥቢያቱን ኀብረ-ብሔርነት ማየት እንችላለን፡፡ እንደ ኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን በአንድ ወገን (ዘር) ብቻ አልተሞላችም፤ ስለዚህ ከወገናዊነት ነጻ ስለ ሆነች፣ በውስጧ የተለያዩ ሰዎችን አቅፋ በመያዟ ተልዕኮዋን ማሳካት እንድትችል ረድቷታል፡፡ ይህም በመሆኑ የምትሰጠው የወንጌል አገልግሎት እጅግ በጣም አድጎላታል፡፡ በውስጧም ያካተተቻቸው የሰዎች ዓይነት የሚከተሉት ናቸው፡፡ (1) አይሁድና አሕዛብ፣ (2) የተማሩና ያልተማሩ፣ (3) ነጮችና ጥቁሮች፣ (4) ድኻና ሀብታም፡፡

እነዚህ ሁሉ ልዩነቶች የወንጌልን ሥራ እንዳትሠራ እንቅፋት አልሆኑባትም፡፡ እዚህ ላይ ጳውሎስ ማንቁርቱን ተይዞ በመለወጡ ብዙ ውጤታማ የሆነባቸው ሥራዎች አሉት፡፡ ዜግነቱን በመጠቀም ያለምንም ችግር ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ወንጌልን ሰብኮአል፡፡ በተለይም ጳውሎስ እንደ ዘዴ አድርጎ የተጠቀመበት በዋና ዋና ከተማዎች እየዞረ ወንጌልን መስበክ ነበረ፡፡ የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያንም ይህን ዘዴ በመጠቀሙ፣ ወደ አንጾኪያ መጥቶ ሪፖርት በሚያደርግበት ጊዜ እንደ ምታበረታታው እርግጠኛ ነኝ፡፡ ምክንያቱም ከአጥቢያቱ ጋር ምንም እሰጥ-አገባ ሳይባባል በጥቂት ቀናት ውስጥ ምንም ጊዜ ሳያባክን ወደ አገልግሎቱ እንደገና ሲወጣ እናየዋለን፡፡

ለምሳሌ፣ እንደ ኤፌሶን ባሉት ዋና የአውራጃ፣ የወረዳ ከተሞችና የወደብ  ከተሞች ብዙ ሰዎች ለንግድ፣ ለጉብኝት፣ ለመኖርና  በተለያየ ምክንያት ወደ ከተሞች ሲመጡ ብዙ ነገር ይዘው ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ፡፡ ይዘው ከሚሄዱት አንዱ ወንጌልን ነበረ፡፡ ስለዚህ  ጳውሎስ ይህን ዘዴ በመጠቀም ወንጌልን ይዞ ወደ ተለያዩ ስፍራዎች በመሄድ ወንጌልን ይሰብክ ነበረ፡፡ ከተሞች ለወንጌል ሥራ ምቹ መሆናቸውን የሚቀጥሉት ጥቅሶች ያረጋግጡልናል፡፡

“በሁለተኛውም ሰንበት ከጥቂቶቹ በቀር የከተማው ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰሙ ዘንድ ተሰበሰቡ” (የሐዋ.13፡44)፡፡ “በዚያችም ከተማ ወንጌልን ሰብከው …ወደ ልስጥራን ወደ ኢቆንዮንም ወደ አንጾኪያም ተመለሱ” (14፡21-22)፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ አንዳንድ ሚስዮናውያን ገጠር ገጠሩን እየሄዱ ወንጌልን እየሰበኩ ብዙ ዓመትም ቢያሳልፉም፣ ወንጌል ሊሰፋና ሊያድግ አልቻለም፡፡ ምክንያቱም በገጠር የሰው ኃይል፣ የገንዘብ ኃይልና የማቴሪያል (የቊሳቊስ) አቅርቦት ከከተማው ጋር ሲነጻጸር በጣም አነስተኛ ስለ ሆነ ነው፡፡ ስለዚህ ከገጠር ይልቅ  በከተማ ለሚኖሩ በቀላሉ ወንጌልን ብናሰራጭ፣ ከላይ የጠቀስናቸውን ነገሮች በቀላሉ አግኝተን ወንጌልን ለገጠሩም ማዳረስ እንችላልን፡፡ ጳውሎስ ይህን ምሥጢር ስለ ተረዳ፣ የወንጌሉን ሥራ ያተኮረው በከተሞች ላይ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ውጤታማ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

እኛም በአሁኑ ጊዜ በከተማ ብቻ እናተኩር ማለት ሳይሆን፣ ጌታ በልባችን እንዳስቀመጠው ሸክም መሠማራቱ ውጤታማ ያደርገናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ አንድ አገልጋይ ‹‹መንፈስ ቅዱስ ለእንዲህ ያለ አገልግሎት ጠርቶኛል›› ቢል ምን ያህል ተቀባይነት ያገኛል፡፡ ኧረ ለመሆኑ ስንቶቻችን ነን መንፈስ ቅዱስ ለዩልኝ ብሎ ለአገልግሎት የወጣን? ጥሪው ደርሶንስ ከወጣን በኋላ ከቢሮ ሳንወጣ ለብዙ ዓመት ተቀምጠን ያለን ስንቶች እንሆን? ቤተ ክርስቲያናትም እንደነ ጳውሎስ  በመንፈስ ቅዱስ የተጠሩትን አንቀን የያዝን ስንቶች እንሆን? ተልዕኮን ለማሳካት ሁላችንም መንፈስ ቅዱስ የሚለንን መስማት ይኖርብናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ስሜታችን ከመንፈስ ቅዱስ መልእክት ጋር ሊጋጭብን ስለሚችል፣ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል፡፡ ስሜት እንደ ሙቀት መለኪያ አንድ ጊዜ ከፍ  ሌላ ጊዜ ደግሞ ዝቅ ሊል ይችላል፣ የመንፈስ ቅዱስ ድምጽ ግን ያለማቋረጥ ሳይጠፋ የልብ ሸክም ሆኖ ይቆያል፡፡ ባለፉት አርባ አምስት ዓመታት በጌታ የተሰጠኝን ተልዕኮ ለማሳካት አነስተኛ ክፍያ (አገልግሎት የጀመርኩት በሠለሳ ብር ስለ ነበር)፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ሕመም፣  ኃጢአት … የመሳሰሉት ሁሉ ተልዕኮውን በአግባቡ እንዳልወጣ ፈታኝ ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ ቢሆንም ግን፣ በተለያዩ ውጣ ውረዶች ውስጥም እያለፍኩና በጌታ ዕርዳታ ለመወጣት ጥረት እያደረኩ እዚህ ደርሻለሁ፡፡ ምንም እንኳን እንደ ጳውሎስ የጎላ አስተዋጽዖ ባላደርግም፣ በአቅሜና በተሰጠኝ ጸጋ መጠን፣ ቃሉን ለማስተማር፣ ሥልጠናዎችን ለመስጠት ከባሌና ከጋምቤላ በስተቀር በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች በመዞር፣ የተሰጠኝን ተልዕኮ ለመወጣት ጥረት አድርጌአለሁ፡፡ ተልዕኮውን ለማሳካት የት ላይ እንዳደረስኩትም ቆም ብዬ ራሴን እየፈተሽኩ ወደፊት ለመሮጥ ሞክሬአለሁ፡፡ አሁንም ከሦስት ወር በኋላ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በዕድሜ ምክንያት ባቆምም፣ በዚህ በተከፈተልኝ በር ጌታን የበለጠ በማገልገል ተልዕኮውን አሳካለሁ ብዬ አስባለሁ፤ ሁላችንም ተልዕኮውን ለማሳካት በጌታ እርዳታ ጥረት እናድርግ፣ ጌታም  ጸጋውን በመስጠት ይረዳናል፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *