በሰው ሕይወት አዲስ ነገር መጀመር በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው፣ በተለይም በዕድሜ እንደ እኔ ገፋ ላደረጉ ሰዎች በጣም ይከብዳል፡፡ ከለመድነው የአሠራር መንገድ ለወጥ ለማድረግ፣ ሥራ ለመቀየር፣ አዲስ ጓደኛ ለመያዝ፣ አዲስ ንግድ ለመጀመር፣ እና የመሳሉትን ሁሉ ለማድረግና ለመቀየር በጣም እንቸገራለን፡፡ በተለይም፣ በቤተ ክርስቲያን አመራር ላይ ላለን ሰዎች አዲስ የአሠራር መንገድ መቀየር በጣም ይከብደናል፡፡

በሐዋርያት ሥራ 11፡19-20 ላይ በስደት ምክንያት የተበተኑት አማኞች ቃሉን ከአይሁድ በስተቀር ለማንም በማይናገሩበት ጊዜ፣ የቆጵሮስና የቀሬና ሰዎች ወደ አንጾኪያ ወርደው ወንጌሉን ለግሪክ ሰዎች እንደተናገሩ ቃሉ ይነግረናል፡፡ ወንጌል ለአሕዛብ ሲሰበክ ይህ አዲስ ጅማሬ ነው፡፡ ስለዚህ በአንጾኪያ የአይሁድና የአሕዛብ  ድብልቅ የሆነች  ቤተ ክርስቲያን ተመሠረተች፡፡ ጳውሎስና በርናባስ በዚህ አዲስ ጅምር ውስጥ እንደ ገቡ የሚቀጥለው ምዕራፍ ያሳየናል፡፡ በምዕራፍ 13 ላይ ስንመለከት፣ በቤተ ክርስቲያን መምህራንና ነብያት እንደነበሩ ሲነግረን፣ ከእነዚህም መካከል በርናባስና ጳውሎስ እንዳሉበት እንረዳለን፡፡ እነርሱም በዚች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትልቅ ለውጥ አምጥተዋል፡፡ 

ባለፈው ትምህርት እንደ ገለጽኩት፣ በርናባስ ሳውልን ወደ አንጾኪያ አምጥቶ ለአንድ ዓመት ያህል በቤተ ክርስቲያን በመሰብሰብ ምዕመኑን ሲያስተምሩና ሲመክሩ ከቆዩ በኋላ፣ አንድ የአዲስ ነገር ምዕራፍ ጅማሬ ሆነ፡፡ ከተለመደ ወደ አልተለመደ የስም አጠራር ለመምጣት የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ውሳኔ አደረገች፡፡ በአንጾኪያ የነበሩ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችም በነገሩ በመስማማት አዲሱን ስያሜ ተቀበሉት፡፡ በክርስቶስ የሚያምኑ ደቀ መዛሙርት ለመጀመሪያ ጊዜ ክርስቲያን ተባሉ በማለት ሉቃስ  አዲስ ዜና ያበስርልናል፡፡

አማኞች ከዚያ በፊት ለ10 ዓመት ያህል ምን ተብለው ነበር የሚጠሩት የሚሉ ጥያቄዎች ሊመጣባችሁ ይችላል፡፡ ብዙ ከማሰባችሁ በፊት ነገሩ እንዲህ ነው፣ አማኞች በመጀመሪያ ደቀ መዛሙርት እየተባሉ ይጠሩ ነበር፣ አሁን ግን ክርስቲያን ተባሉ፡፡ ክርስቲያን ማለት በግሪክኛ ቋንቋ “ክርስቲያኖስ” ማለት ሲሆን፣  የሁለት ቃል ጥምር ነው፣ ‹‹ክሪስቶ›› ክርስቶስ ማለት ሲሆን፣ “ኢያኖስ” ደግሞ ባሪያ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ክርስቲያኖስ ማለት “የክርስቶስ ባሪያ” ማለት ነው፣ ስለዚህ የማያምኑት ቃሉን የሚጠቀሙበት አማኞችን ለመስደብ ሲሆን፣ የአንጾኪያ ክርስቲያኖች ግን የክብር ስም አድርገው ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀበሉት፡፡

አሁን ግን በአንጾኪያ ያሉ ደቀ መዛሙርት (አማኞች) ክርስቲያን ተብለው በመጠራታቸው የስድቡን ስም የክብር ስም አድርገው ዐወጁት፡፡ አዲስ ጅማሬ ይልሃል ይሄ ነው፡፡ የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይሆናል ብላ ሳታንገራግር አዲስ መጠሪያ አወጣች፡፡ በእኛ ዘመን ‹‹ካቶሊክ››፣ ‹‹ሚሽን›› እና፣ ‹‹ጴንጤ›› ብለው ለማጥላላት እንደሚጠቀሙበት ማለት ነው፡፡

በመቀጠልም፣ ሌላ አዲስ ነገር ስትጀምር እንመለከታታለን፡፡ በዓለም ላይ ታላቅ ረሀብ እንደሚነሳ አጋቦስ የሚሉት ነብይ ተናግሮ ስለነበረ፣ በዚህ በአንጾኪያ ያሉ አማኞች በይሁዳ ለሚኖሩት አማኞች ገንዘብ አዋጥተው፣ እነጴጥሮስ ለነጳውሎስ ቀኝ እጃቸውን ሰጥተዋቸው አደራ ባሉዋቸው መሠረት፣ በርናባስና ጳውሎስ አደራውን ተቀብለው የተዋጣውን ገንዘብ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው በታማኝነት ማድረሳቸውን የሚቀጥለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ያስረዳናል፡፡ ‹‹… ደቀ መዛሙርትም እያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን አዋጥተው በይሁዳ ለሚኖሩት ወንድሞች እርዳታን ይልኩ ዘንድ ወሰኑ እንዲህም ደግሞ አደረጉ፣ በበርናባስና በሳውልም እጅ ወደ ሽማግሌዎቹ ሰደዱት›› (የሐዋ.11፡27-30)፡፡ ይህም ሰውን በሁለንተናው የማገልገል አገልግሎት ጅማሬ እንደሆነ እናያለን፡፡ አገልግሎታቸውን ጨርሰው ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ሲመለሱ ሌላ አዲስ ነገር አደረጉ፡፡ ይህም የአገልጋይ ጭማሪ በማድረግ ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስን የአገልግሎታቸው ረዳት እንዲሆን ይዘውት መጡ (12፡25)፡፡ ጴጥሮስ ታስሮ በነበረበት ጊዜ በማርቆስ እናት ቤት ስለ እርሱ በጌታ ፊት ፀሎት ይደረግ ነበር (12፡12-17)፤ ማርቆስ በዚያ ስለነበረ በርናባስ እንደ ልማዱ ጳውሎስን ለአገልግሎት እንዳበቃውና ይዞት  እንደወጣ፣ ማርቆስንም የአገልግሎታቸው አጋር እንዲሆን ከጳውሎስ ጋር ሆነው ይዘውት ወጡ፡፡ በርናባስ ትዕግስተኛ ስለሆነ አገልጋዮችን ማባረር ሳይሆን ማቅረብ የሚችልበት ጸጋ ተሰጥቶታል፡፡ እንዲህ ያለ ጸጋ በኖረኝ ብሎ የሚያስቀና ሰው ነው፡፡ የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን የሚስዮናዊ ጉዞ በማድረግ ጀማሪዋም እርሷ ናት፡፡ ተልዕኮው የት እንደ ደረሰ ማወቅ ትችላለች፣ አትቸገርም፡፡ እኛም አዳዲስ ጅማሬ በሕይወታችን ሲገጥመን እንዳንደናገር፣ ራሳችንን ለሁኔታዎች ማስገዛት እንዳለብን፣ ከአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን መማር ይኖርብናል፤ ጌታም ጸጋውን ያበዛልናል፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *