ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ተልዕኮው ሲነግራቸው በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያና በዓለም ዳርቻ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ፤ ብሎ የተልዕኮውን አድማስ ሲያሳውቃቸው ወደማይወዷቸው ሕዝቦች እንደ ተላኩ፣ ሳይገባቸው የቀረ አይመስለኝም፡፡ ጌታ ይህን ሲናገር ግን ሳይደነግጡ አልቀሩም፤ ነገር ግን ጌታ ለዘጠኝ መቶ ዓመት ተይዞ የነበረ ባሕል አፍርሶ፤ ወደ ሰማርያ ሄዶ ለሴቲቱና በእርሷ ምስክርነት ለመጡት ሰዎች ወንጌልን እንደ መሰከረ አይተዋል፡፡ ጌታ የተጠሉትን ወዳጅ ሲያደርግ፣ ሲፈውስ፣ ኃጢአትን ይቅር ሲል ብዙ አይተዋል፣ ተምረዋል፡፡ ሌሎች ምን ይሉናል በሚል የግብዝነት ሀሳብ ተይዘው ካልሆነ በስተቀር፣ ለጌታ ብዙ ዋጋ እየከፈሉ በስደትና በመከራ፣ በጥላቻና በስድብ ውስጥ እያለፉ የዘረኝነትን ቀንበር መስበር እንዴት አቃታቸው? ከዚህ በፊት እንዳየነው ጌታ ኢየሱስ የሰጣችው ታላቁ ተልዕኮ ከኢየሩሳሌም ጀምሮ እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ እንደ ነበረ ልብ የምንል ይመስለኛል፡፡ በታዘዙት መሠረት ባለመፈጸማችው የጌታ ልብ እጅግ ሳያዝን አልቀረም፡፡ ጌታም አዝኖ ዝም ብሎ አልተመለከተም፡፡ የሥራው ባለቤት ራሱ ስለሆነ ሌላ እቅድና የአሠራር ስልት ሲቀይስ እንመለከታለን፡፡
ጌታም የቀየሰውን ዕቅድ ከማየታችን በፊት፣ ከምዕራፍ 8-11 ያለውን የድርጊትና የአጻጻፍ ቅደም ተከተል ማየቱ ሀሳቡን ግልጽ ያደርግልናል፡፡ በድሪጊት ምዕራፍ 8፣11፡19-20፣ ምዕ.10፣ 11፡1-18፣ ምዕ.9 ሲሆን፣ በአጻጻፍ ምዕ.8፣9፣10፣11 ሆኖ ተዘግቦአል፡፡ በዚህ መሠረት በምዕራፍ 10 ላይ ጴጥሮስን ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት ለመላክ መልአኩን ልኮ ሲያዘጋጀውና ቆርኔሌዎስንም ሲያዘጋጀው በጥበብና በዘዴ ሲጠቀም እናያለን፡፡ ጴጥሮስ ጸሎቱን ጨርሶ ሲመለስ ርቦት ሳለ ምግብ እየተዘጋጀለት ሳለ ተመስጦ መጥቶበት ከሰማይ ታላቅ ሸማ የሚመስለው ነገር ሲወርድ፣ አራት እግር ያላቸው አራዊት ሁሉ ታዩት ፡፡ በዚህ ጊዜ አርደህ ብላ ሲባል እንቢ በማለቱ፣ ሦስት ጊዜ ድምጹ ተደጋግሞ መጣለት፣ “እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው የሚለው ድምጽ ወደ እርሱ መጥቶ ዕቃው ወደ ሰማይ ተወሰደ ፡፡” (የሐዋ. 10፡15-16)
ጴጥሮስም ስላየው ራዕይ ሲያወጣና ሲያወርድ፣ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች ወደ ጴጥሮስ ቤት መጥተው በደጅ ቆመው መንፈስ ጴጥሮስን እርሱን ሰዎች እንደሚፈልጉትና ከእርሱ የተላኩ ስለሆነ አብሮአቸው መሄድ እንዳለበት ያዘዋል፡፡ ጴጥሮስም እንደ ታዘዘው ስድስት ወንድሞችን ይዞ ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት ሄደ፡፡ ለጴጥሮስ ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት መሄድና ከእርሱ ጋር መብላት ሃሌሉያ ባያሰኘውምና ቢከብደውም፣ ጌታ በጥበብና በዘዴ ስላሳመነው ሄዶ አገልግሎቱን ሲወጣ እናያለን፡፡ በጴጥሮስ ሕይወት ውስጥ ለዘመናት ተንሰራፍቶ የነበረ አንድ ትልቅ የባህል ግንብ ወደ ሰማርያ በሄደ ጊዜ ፈርሶለት ስለነበረ፣ በገላትያ 2፡11-14 ላይ ደግሞ እንደምናገኘው ከባህል እስራት ተላቅቆ ከአሕዛብ ጋር መብላት እንደጀመረ ቃሉ በሚገባ ያረጋግጥልናል፡፡ ቢሆንም ግን ከአይሁድ የሆኑት በአጠገቡ በሚሆኑበት ጊዜ ከአሕዛብ ጋር ለመብላት ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ ጳውሎስ ስለ ግብዝነቱ ይገስጸዋል፡፡
“ ነገር ግን ኬፋ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምኩት፣ ይፈረድበት ዘንድ ይገባ ነበርና፡፡ አንዳንድ ከያዕቆብ ዘንድ ሳይመጡ ከአሕዛብ ጋር አብሮ ይበላ ነበርና በመጡ ጊዜ ግን ከተገረዙት ወገን ያሉትን ፈርቶ ያፈገፍግ ነበርና ከእነርሱ ተለየ፡፡ …ነገር ግን እንደ ወንጌል እውነት በቅንነት እንዳልሄዱ ባየሁ ጊዜ በሁሉ ፊት ኬፋን፡- አንተ አይሁዳዊ ሳለህ በአይሁድ ኑሮ ያይደለ በአሕዛብ ኑሮ ብትኖር፣ አሕዛብ በአይሁድ ኑሮ ሊኖሩ እንዴት ግድ አልሃቸው? አልሁት” (ገላ. 2፡11-14)::
አንዳንድ ጊዜ ወደ ግብዝነትና ወደ ስህተት ስንገባ የሚገስጽ ሰው መኖሩ እንዴት ጥሩ ነገር ነው፡፡ ሰው ምን ይለኛል፣ ሰውን እናሳዝናለን፣ የራሱ ጉዳይ ብለን የምናልፈው ነገር ለብዙ ነገር መበላሸት ምክንያት ይሆናል፡፡ ጳውሎስ ጴጥሮስን በመገሠጹ ወደ ፊት የተስተካሉ ነገሮች እንደመጡ መገመት እንችላለን፡፡
ጴጥሮስ ከብዙ ክርክር በኋላ ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት ሄዶ ተልዕኮውን ከፈጸመ በኋላ፣ በምዕራፍ 11፡1 ላይ በቆርኔሌዎስ ቤት በሆነው ነገር ተደንቆና ተገርሞ ጌታን እያመሰገነ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፡፡ በምዕራፍ 11፡1 ላይ ሐዋርያትና በይሁዳም የነበሩት ወንድሞች አህዛብ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰሙ ይላል፡፡ በአሕዛብ መዳን ደስ ብሎአቸው ይሆን? የእግዚአብሔር ቃል በአንድ ኃጢአተኛ መዳን ምክንያት በሰማይ በመላእክት ዘንድ ታላቅ ደስታ እንደሚሆን የሚናገረውን ማስተዋል አልቻሉም ፡፡ ስለዚህ ጴጥሮስንም ይህ ደስታ የገጠመው አይመስልም፤ የጠበቀው ተቃራኒ ነበር፡፡
በቁጥር 2 ላይ ግን እጅግ የሚደንቀኝና የሚገርመኝ ነገር ተፈጠረ፡፡ ጴጥሮስ በቆርኔሌዎስ ቤት ውስጥ ስለ ሰጠው አገልግሎትና በኃጢአተኞች መዳን፣ በጨለማ ውስጥ የነበሩ ብርሃን በማግኘታቸው ጌታን እያመሰገኑ፣ እያከበሩ፣ ሃሌሉያ፣ እልል … እያሉ መቀበል ሲገባቸው እንዲህ አላደረጉም፡፡ ቁጥር 2 ላይ ስለ ሰጡት ምላሽ እንዲህ ይላል፣ “ጴጥሮስም ወደ ኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ ከተገረዙት ወገን የሆኑት ሰዎች ከእርሱ ጋር ተከራክረው ወዳልተገረዙ ሰዎች ገብተህ ከእነርሱ ጋር በላህ አሉት” (11፡2)፡፡ ይህ ማለት ‹‹ከአሕዛብ ጋር ለምን በላህ?›› ማለታቸው ነው፡፡ በእኔ አረዳድና አመለካከት እንዲህ ማለታቸው እንደሆነ አስባለሁ፡፡ “አንተ ዘር አሰዳቢ፣ ብለህ ብለህ ከውሾች ጋር በላህ፣ እንዴ?”
ጴጥሮስም ምንም እንኳን እንዲህ ያለ ውርጅቢኝ ቢወርድበትም፣ ለገጠመው ችግር ስለ ሁኔታው በእርጋታ በዝርዝር ለማስረዳት ይጀምራል፡፡ ጴጥሮስም በጸሎት ላይ እያለ ስለታየው ራዕይ እግዚአብሔር እንዴት እንዳዘጋጀው፣ መንፈስም ሳይጠራጠር መሄድ እንዳለበት እንደነገረው፣ በመቀጠልም በተላከበት ቤት ውስጥ ቃሉን እየተናገረ በማንም ላይ እጁን ሳይጭንባቸው ‹‹ውሾች›› ብለው በሚጠሯቸው ሰዎች ላይ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ወርዶላቸው በልሳን እንደ ተናገሩና እግዚአብሔርን እንዳመሰገኑ ተረከላቸው፡፡
በመቀጠልም በምዕራፍ 11 ከቁጥር 15 ላይ ጴጥሮስ እንዲህ ይላል፣ “ለመናገርም በጀመረኩ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ደግሞ በመጀመሪያ እንደ ወረደ ለእነርሱም ወረደላቸው፡፡” ከበዓለ ኀምሳ ቀን በኋላ መንፈስ ቅዱስ ሐዋርያትን እየደጋገመ ቢሞላቸውም፣ እንደ በዓለ ኀምሳው ቀን ያለ ግን ለ10 ዓመት ያህል እንዲህ ወርዶ አያውቅም፡፡ በቆርኔሌዎስ ቤተሰብ (‹‹ውሾች›› በተባሉት) ላይ የወረደው የበዓለ ኀምሳውን ቀን እንደሚመስል አስረግጦ መሰከረላቸው፡፡ እግዚአብሔርንም መከልከል እንዳልቻለ በአሥር ጣቱ ፈርሞ የማረጋገጥ ያህል እግዚአብሔር በአይሁድና በአህዛብ መካከል እንደማያዳላ ሁለቱም ሕዝቦቹ እንደሆኑ መንፈሱን በመስጠት መሰከረ ብሎ ሪፖርቱን አቀረበላቸው፡፡ ሪፖርቱንም የሰሙት ሁሉ የሚከተለውን ምላሽ ሰጡ፡- “የሰሙትም ሐዋርያትና ወንድሞች ዝም ካሉ በኋላ እንኪያስ እግዚአብሔር ለአሕዛብ ደግሞ ለሕይወት የሚሆን ንስሐን ሰጣቸው እያሉ እግዚአብሔርን አከበሩ” (የሐዋ. 11፡18) እግዚአብሔር በአዲሱ ዕቅድ በጴጥሮስ ያከናወነው አገልግሎት ዘለቄታ ያለው ለውጥ ባያመጣም፣ ያቀረበው ሪፖርት አሳማኝ በመሆኑ ሐሳቡን የተቀበሉት ይመስላል፡፡
0 Comments