ማን ነህ? አትበሉኝ፣ ስም አልወጣልኝም፡፡
የት ነህ? አትበሉኝ፣ ሀገር አትጠይቁኝ፣ አድራሻ የለኝም
እኔ በእኔነቴ ምንም ታሪክ የለኝ፡፡
ማን ነህም? የት ነህም? ተውኝ አትበሉኝ፣
ከጠየቃችሁኝ ካስጨነቃችሁኝ፣
እኔ ስለ ራሴ አንድ የምለው አለኝ፤
በሕይወት ዘመኔ አንድ ነገር አውቃለሁ፣
ከነገድ፣ ከቋንቋ፣ ከወገን፣ ከጎሣ ጥንት እንደ ተለየሁ፡፡
እርሱ ድሮ ቀረ ዘር ትውልድ መቁጠሩ፣
ዕገሌን ዕገሌን ብሎ መዘርዘሩ፡፡
በወልድ ብቻ ሆነ የሕይወት ምሥጢሩ፣
የሰው ሰው መሆኑ አለኝታና ክብሩ፡፡
ከነገድ፣ ከቋንቋ፣ ከዘር፣ ከሃይማኖት በደሙ የዋጀን፣
አርማችን እርሱ ነው የማንነታችን፡፡
ምን ነው? በየኬላው ማን ነህ ባዩ በዛ፣
አያዩትም እንዴ የያዝሁትን ቪዛ፤
የደሙ ማህተም የታተመበትን፣
ከአደጋ ከጥፋት ይለፍ የሚለውን፤
ድንበር ማይከልለው፣ ዘመን የማይሽረው፣
የይለፍ ቪዛዬ የኢየሱሴ ደም ነው፡፡
ማን ነህ? አትበሉኝ፣ ስም አልተሰጠኝም፤
የት ነህ? አትበሉኝ፣ አድራሻ የለኝም፤
አድራሻ ‘ሚነግረኝ የትውልድ ሐረጌን፣
ሊያስረዳኝ የሚችል በግልፅ ማንነቴን፣
ፈልጌ አስፈልጌ የሚነግረኝ አጣሁ፣
ወዴት እንደምሄድ፣ ከየት እንደ መጣሁ፡፡
ለካ ማንነቴ ፍፁም ተሠውሯል፣
አሮጌውን ትቶ፣ አዲሱን ሰው ለብሷል፡፡
ትናንት በምታውቁት አትፈልጉኝ ዛሬ፡፡
ታላቅ የምሥራች !
አንድ ማስረጃ አገኘሁ ቆፍሬ ቆፍሬ፣
መሆኑን የሚገልፅ በሰማይ ሀገሬ፡፡
ሰማያዊ ዜጋ የምገኝ በምድር፣
ለልዩ ተልዕኮ ለጊዜው የምኖር፣
በዘመናት መሃል አዋጅ እንድናገር፣
እኔው ተሻግሬ፣ ሰዎች እንዳሻግር፤
የሕይወትን መንገድ ለሰዎች እንዳሣይ
ዕድል የተሠጠነኝ ከአባቴ ከሰማይ፤
ከነገድ ከቋንቋ ከዘር ተለይቼ፣
ወንጌልን እንድሰብክ ወጣሁ ተጠርቼ፡፡
ታዲያ! ምን ማንነት አለው እንደዚህ ላለ ሰው፣
ማን ነህ? የት ነህ? ብለን ዛሬ ልንጠይቀው፣
ስሙም ማንነቱም ሀገሩም ርስቱም፣
በሰማይ ነው እንጂ፣ በዚህ ምድር የለም፡፡
ማን ነህ? አትበሉኝ ዛሬ እንደ ትናንቱ፣
የት ነህ? አትበሉኝ ዛሬም እንደጥንቱ፣
ዓለምን፣ ሰይጣንን፣ ሥጋዬንም ክጄ፣
ሌላ ሰው ሆኛለሁ ዳግም ተወልጄ፡፡
ዘመዴ ወገኔ መባሉ ቀረና፣
ሁሉም የእግዚአብሔር ልጅ በክርስቶስ ሆነና፣
ስማችን ቋንቋችን አንድ አደረገና፡፡
የእግዚአብሔር ልጅ ወልድ
የአባቱ ካህናት፣ የተለየ ወገን፣
ሁላችን እንድንሆን በደሙ ቀደሰን፡፡
የእናንተና የእኔ የማንነታችን፣
አርማችን እርሱ ነው፣ ልላ ምንም የለን፡፡
ማን ነህ? አትበሉኝ
ማን ነህ? አትበሉኝ፣ ማንነቴ ቀርቷል፣
ስሜም አድራሻዬም ሁሉም ተለውጧል፡፡
ማን ነህ? አትበሉኝ፣ ማንነት የለኝም፣
ማንነቴ እርሱ ነው ዛሬም ለዘለዓለም፡፡
ሞቴን የሞተልኝ፣ መከራዬን ሁሉ የተሸከመልኝ፣
ከነገድ፣ ከቋንቋ፣ ከዘር፣ ከሃይማኖት ለይቶ ያወጣኝ፣
ማንነቴ እርሱ ነው የምታወቅበት፣
በደሙ የዋጀኝ ከዘለዓለም ጥፋት፡፡
ሙሉ ማንነቴን በእርሱ ለውጫለሁ፣
ከእርሱ በቀር ሕይወት እንደሌለ ዐውቃለሁ፡፡
አድራሻዬን ሁሉ እርሱ ቀይሮታል፣
እኔ እንዳልሞትበት፣ በእኔ ምትክ ሞቷል፡፡
መኖሪያዬ እርሱ ነው ሀገሬም ርስቴም፣
ዕድል ፈንታዬም ነው እስከ ዘለዓለም፡፡
እውነትም እርሱ ነው ‘ምተማመንበት፣
መንገድም እርሱ ነው ጽዮን ‘ምገባበት፣
ታዲያ ከእርሱ ውጭ የት አለ ማንነት? ከምንውዬለት ጌታሁን (የኤማሁስ የቦርድ አባል)
0 Comments