የተልዕኮውን መነሻና መድረሻ ስንመለከት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ እንደሆነ ጌታ ከተናገረው ቃል መረዳት ይቻላል፡፡ ሐዋርያትም በኢየሩሳሌም የተሰጣቸውን ተልዕኮ በሚገባ እንደ ተወጡና በዚያው ባሉበት ከተማ በአገልግሎታቸው ውጤታማ እንደነበሩ ማየት እንችላለን፡፡ ነገር ግን በዚህ ጊዜ ጌታ በቃሉ እንደተናገራቸው ሳይሆኑ፣ ከኢየሩሳሌም ሳይወጡ ከአሥር ዓመት በላይ አሳለፉ፡፡ ጌታ ለሦስት ዓመት ያስተማረበትና ያሰለጠነበት ዓላማና የተልዕኮው ስፋት ምን ያህል እንደ ሆነ ምናልባት እንደሚገባ አልገባቸውም ይሆናል፡፡ ጌታ ተልዕኮው በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያም፣ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ነው ቢልም፣ እነርሱ ግን ሳይደነግጡ አልቀሩም፡፡ ምክንያቱም አይሁዶች ሳምራውያንና አሕዛብን(ከአይሁድ ውጭ ያሉት ሕዝቦች) እንደ ጠላት ስለሚያዩዋቸው ነው፡፡

ስለዚህ በዚያችው በኢየሩሳሌም ከተማ ተወስነው በሰጡት አገልግሎት ብዙ ሰዎች ወደ ጌታ መጥተዋል፡፡ በመጀመሪያ በጴጥሮስ ስብከት ሦስት ሺህ፣ የሽባውን ሰው መፈወስ ምክንያት በማድረግ በተሰጠው ስብከት ወደ አምስት ሺህ ሰዎች (ወንዶች ብቻ) ጌታን በማመን ሕይወታቸውን አስረከቡ፡፡ ተራ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ካህናቱም ጭምር ወደ ጌታ መጡ፡፡  የብዙዎች መዳን ያስቆጫቸው ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ላይ ስደቱን አመጡባቸው፡፡ ቃሉም እንደሚናገረው፣ “የእግዚአብሔር ቃል እየሰፋ ሄደ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርት ቁጥር እጅግ እየበዛ ሄደ ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖት የታዘዙ ሆኑ” ይላል (የሐዋ 6፡7)፡፡ 

ጠላት ያመጣባቸው ቢሆንም፣ ጌታ የሰጣቸውን ትዕዛዝ እንደሚገባ ስላልተወጡ እግዚአብሔር በተለየ መንገድ ለመሥራት ብሎ በቤተ ክርስቲያን ላይ የመጣውን ታላቅ ስደት ሊጠቀምበት የፈቀደ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ሂዱ የተባለውን ትእዛዝ ስላልፈጸሙ፣ በስደቱ ምክንያት እንዲበተኑና ወንጌሉን እንዲያሰራጩ ያደረገ ይመስለኛል፡፡                                 

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድ ችግር በሚፈጠርበት ጊዜ ያለ ምክንያት ስለማይሆን፣ ቆም ብለን ራሳችንን ልንጠይቅና ነገሩን በማመዛዘን ልናየው ይገባናል፡፡ ስደቱ መምጣቱ ከኢየሩሳሌም እንዲወጡ አድርጎአቸዋል፡፡ እንደ ተፈለገውም በሐዋርያት ሥራ 8፡1 ላይ፣ “… ከሐዋርያት በቀር ወደ ይሁዳና ወደ ሰማርያ አገሮች ተበተኑ” ይልና በቁ 4 ላይ ደግሞ “የተበተኑትም ቃሉን እየሰበኩ ዞሩ” ይላል፡፡

 በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ሁለት ታላላቅ ነገሮችን ማየት እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢየሩሳሌም ወጥተው ወደ ይሁዳና ወደ ሰማርያ መበተናቸው ሲሆን፣ ሁለተኛው በተበተኑበት ሥፍራ ሁሉ ቃሉን እየተናገሩ መዞራቸው ነው፡፡ ተልዕኮአቸውን ለመወጣት ያደረጉትን ከፍተኛ የሆነ ጥረት ስንመለከት የሚያስመሰግናቸው እንደ ሆነ እንመለከታለን፡፡ በዚህ ከባድ ስደት ውስጥ ሆነው ቤታቸውንና ንብረታቸውን ትተው በማያውቁት አገር እየዞሩ ምን እንበላለን፣ እንጠጣለን፣ ደግሞስ ምን እንለብሳለን ሳይሉ ወንጌልን መመስከራቸውና በጨለማ ያሉትን ወደ ብርሃን ለማውጣት ያደረጉት እርምጃ በጌታ ዘንድ ያስመሰግናቸዋል፡፡ ከተበተኑትም መካከል ፊልጶስ ወደ ሰማርያ ሄዶ ወንጌልን መስበክ ጀመረ፡፡ ፊልጶሰም በኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ከተመረጡት ሰባት አገልጋዮች አንዱ ነበረ፡፡

“ፊልጶስም ወደ ሰማርያ ከተማ ወርዶ ክርስቶስን ሰበከላቸው፡፡ ሕዝቡም የፊልጶስን ቃል በሰሙ ጊዜ ያደርጋት የነበረውንም ምልክት ባዩ ጊዜ፣ የተናገረውን በአንድ ልብ አደመጡ፡፡ ርኩሳን መናፍስት በታለቅ ድምፅ እየጮሁ ከብዙ ሰዎች ይወጡ ነበር፤ ብዙም ሽባዎችና አንካሶች ተፈወሱ፤ በዚያችም ከተማ ታላቅ ደስታ ሆነ” (የሐዋ. 8፡5-7)፡፡

ሐዋርያትም የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንደተቀበሉ ባዩ ጊዜ ጴጥሮስና ዮሐንስን ልከው ወንጌልን እንዴት እንደተቀበሉና ሥራው ምን ያህል እንዳደገ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ ጴጥሮስና ዮሐንስም ሥራውን ከተመለከቱ በኋላ በአገልገሎታቸው በመስማማታቸው፣ እጃቸውን ጭነው ለመንፈስ ቅዱስ ሲጸልዩላቸው መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፡፡ ጴጥሮስና ዮሐንስ ለመንፈስ ቅዱስ መጸለይ ብቻ ሳይሆን፣ በሳምራውያን በብዙ መንደሮችም ወንጌልን ሰብከው ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ሞቀችው ከተማቸው ተመለሱ፡፡

ፊሊጶስም ከጌታ መልአክ ምሪት በመቀበል ወደ ጋዛ ምድረ በዳ በመሄድ ወንጌል ለኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ከሰበከለት በኋላ አጠመቀው፡፡ ከዚያም በኋላ በጌታ መንፈስ በመነጠቅ ከአዛጦን ጀምሮ ቂሣርያ እስከሚደርስ ድረስ ወንገልን እየሰበከ ዞረ፡፡ ከዚህ በላይ የተሠሩትን ሥራዎች ስንመለከት፣ ጌታን በጣም ደስ ያሰኘ ሥራ እንደተሠራና ብርቱ ጎናቸው እንደነበረ እንመለከታለን፡፡ እኛም ዛሬ ጌታን የሚያስደስቱ ብዙ ብርቱ ጎኖች ሊኖሩን ይችላል፡፡ ምናልባት በፐርሰንት(በመቶኛ) አስቀምጡት ብንባል ስንት እንሰጠው ይሆን ?

 በዚህ ሥፍራ ስንመለከት ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ፊሊጶስ ከአይሁድ ውጭ ወንጌልን መመስከራቸው ምን ያህል ከልማዳዊ ጎጂ ባህል እስራት እንደተላቀቁ (FLEXIBLE መሆን እንደቻሉ) ማየት ይቻላል፡፡

አንድ ነገር ተደጋግሞ ሲደረግ ልማድ ይሆናል፣ ልማድ ሲደጋገም ልማዳዊ ጎጂ ባህል ወይም ጠቃሚ ባህል ይሆናል፡፡ ከጎጂ ልማዳዊ ባህል ለመላቀቅ ከጌታ ምሪት መቀበልና ከባህል በላይ ኢየሱስን መምረጥ ይጠይቃል፡፡ ጴጥሮስና ዮሐንስ ያገለገሉት ግማሽ አይሁዶች የሆኑትን ሳምራውያንን ሲሆን፣ ፊሊጶስ ግን ሙሉ በሙሉ አሕዛብ (ከአይሁድ ውጭ) የሆነውን ኢትዮጵያዊ ነበር ያገለገለው፡፡ ፊሊጶስም በቂሣርያና በሌሎች ከተሞችም ወንጌልን እንደ ሰበከ ቃሉ ይነግረናል፣ ቢሆንም ግን የሰበከው ለአይሁዶች ይሁን ለአሕዛቦች ብዙ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ዛሬም ብዙዎቻችን ከከተማ ወጣ ብለን ወንጌልን ማገልገል እየተሳነን ነው፣ ምክንያቱም የታሰርንባቸው ብዙ ነገሮች ስለአሉን፤ ከከተማ ወጣ ሲሉ ብዙ ተስማሚ የሆኑ ነገሮች እንደ መብራት፣ ንፁህ ውኃና ተስማሚ ምግብ፣ የመሳሰሉትን ማግኘት እንደሚያስቸግር የታወቀ ነው፡፡ የቋንቋውም ጉዳይ ሌላ ችግር ነው፡፡ መግባባት ካልተቻለ፣ የግድ አስተርጓሚ ሊያስፈልግ ነው፡፡ ተልዕኮን መወጣት ብዙ ችግር ቢኖርበትም፣ ኃላፊነት ስላለብን ከሞቀ ከተማችን ወጣ እያልን ወንጌልን ላልሰሙት ልናዳርስ ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህም ጌታ ይረዳናልና እኛም ጥረት እናድርግ፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *