በዘመናት ስንመለከት ቤተ ክርስቲያንን በጣም የሚያሰቸግራት፣ የሚያደክማት፣ የሚከፋፍላትና የሚያጠፋት የውጭ ችግር ሳይሆን፣ የውስጥ ችግር ነው፡፡ ከሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 3 ጀምሮ እስከ 5 መጨረሻ ድረስ ቤተ ክርስቲያንን እያስቸገራት የመጣው የውጭ ችግር ቢሆንም፣ እያሸነፈች፣ እየሰፋችና እያደገች ሄዳለች፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የውስጥ ችግሮች እየተፈታተኗት መምጣት ጀመሩ፡፡ የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ያላትን በማምጣት፣ በማካፈልና አብሮ በመብላት የምትታወቅበትን መልካም ነገሮቿን የሚሸረሽሩና የሚያጠፉ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መጡ ፡፡
በተለይም ምዕራፍ 4ን ስንመለከት፣ “…በመካከላቸውም አንድ ችግረኛ አልነበረምና፣ …እንደሚያስፈልግ መጠን ለእያንዳንዱ ያካፍሉት ነበር” ይላል (ቁ.34-35)፡፡ አንድ ሰው ካመጣው በላይ ወይም በታች መጠቀም እንደሚችል “እንደሚፈልግ” የሚለው ቃል ያሳየናል፡፡ አንድ ሺህ ብር ያመጣ ሁለት ሺህ ብር ሊወስድ ይችላል፡፡
አሁን ግን ምዕራፍ 5 ላይ ገንዘብ የሚደብቁ አማኞች እንደነበሩ ሉቃስ ይተርክልናል፡፡ “ባልና ሚስት ከአንድ ባሕር ይቀዳሉ” እንደሚባለው፣ ሐናንያና ሰጲራ የተባሉ ባልና ሚስት ሌሎች ክርስቲያኖች እንደሚያደርጉት መሬታቸውን ሸጠው ወደ ሐዋርያት እግር አጠገብ አመጡት፡፡ ሸጠው ያመጡትን ገንዘብ ግማሹን አስቀርተው ሙሉ በሙሉ ሰጡ እንዲባሉ፣ የሸጥነው ለዚህ ብቻ ነው ብለው አስረከቡ፡፡
በዚህ ጊዜ ጴጥሮስም ሐናንያን እግዚአብሔርን/መንፈስ ቅዱስን በማታለሉ በገሠጸው ጊዜ ያላሰበውና ያልገመተው ነገር ደረሰበት፡፡ ለንስሐ ጊዜ ሳያገኝ በድንገት ወድቆ ሞተ፡፡ ከሦስት ሰዓትም በኋላ ባለቤቱ ሰጲራ ፈጠን እያለች፣ ዛሬ ትልቅ ምሥጋና ሳናገኝ አልቀረንም እያለች በልቧ እየተደሰተች መጣች፡፡ ጴጥሮስም እንደ ልማዱ አገኛትና፣ “መሬቱን ለዚህ ያህል ብቻ ነው የሸጣችሁት” ብሎ ሲጠይቃት፣ የባሏን ሁኔታ ያላወቀች ምስኪኗ ሰጲራ፣ “አዎን” ብላ መለሰች፡፡ በዚህ ጊዜ ወዲያውኑ ባለቤቷ እንደ ወደቀ እርሷም በድንገት ወድቃ ሞተች፡፡ ባሏን የቀበሩ ሰዎች እርስዋንም ወስደው ቀበሩዋት፡፡
የሐናኒያና የሰጲራ ኃጢአታቸው ገንዘብ ቀንሰው መስጠታቸው አይደለም፣ መዋሸታቸው እንጂ፡፡ የሸጥነው ለዚህ ያህል ነው፣ መስጠት የምንፈልገው ይህን ያህል ነው ብለው ቢሰጡ ምንም ችግር አልነበረም፡፡ ነገር ግን ችግር ያመጣባቸው መሬታችንን ሸጠን ሙሉ በሙሉ ሰጠን ማለታቸው ነው፡፡ ስምና ዝና ለማግኘት ሲሉ የዋሹት ኃጢአት ነው ቅጣት ያመጣባቸው፡፡ እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ካልሰጣችሁኝ አልቀበልም አይልም፣ የሰጠነውን ይቀበላል፡፡
ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ያለንና የምንገኝ አንጠፋም፡፡ አሥራትና ምፅዋት የማንሰጥ፣ ለዝና የምንሰጥ፣ ከሚሰበሰበው አሥራትና ምፅዋት ቀንሰን የምንወስድም አንጠፋም፣ ከሰው ተበድረን አለመክፈል፣ ውሸት፣ ጥላቻ፣ ሐሜት፣ በመሳሰሉት ሁሉ ጌታ በእንዲህ ያለ ቅጣት ቢገናኘን ስንቶቻችን በሞት ቅጣት እናልቅ ነበር፡፡ አሁን ጸጋውና ምህረቱ ሰፊ ስለ ሆነ እንደ እነርሱ በሥጋ ሞት ባንቀጣም፣ በሕይወታችን ሰላምና በረከት ማጣት ሊገጥመን ይችላል፤ ወደ ፊትም በጌታ ዘንድ የሥራችንን ዋጋ እንዳናጣ ልንጠነቀቅ ይገባናል፡፡
ወደ ምዕራፍ 6 ስንገባ ወደ ዋናው የእርስ በርስ ችግር እንደገቡ ሉቃስ አስፍሮአል፡፡ ችግራቸውም “መበለቶቻችን በምግብ ዕደላው ችላ ተባሉብን” የሚል ነበር፡፡ ሁለቱም ሕዝቦች/ወገኖች አይሁዶች ናቸው ችግሩ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? ብለን ስንጠይቅ በአገር ቤት የኖሩና በስደት የኖሩ የሚለው ሀሳብ የለያያቸው ይመስላል፤ አሊያም የተማሩና ያልተማሩ፣ የሰለጠኑና ያልሰለጠኑ፣ በአይሁድ ባህልና በግሪክ ባህል የኖሩ ተባብለው ተከፋፍለውም ሊሆን ይችላል፡፡
ቤተ ክርስቲያንም ችግሩን ለመፍታት በማዕድ የሚያገለግሉ በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብ የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች መርጠው በማቅረብ እጅ ጭነው በመጸለይ ችግሩን ቶሎ ማቃለል ችለው ነበር፡፡ የተመረጡትም አገልጋዮች ውጤት እንዳመጡ በሚቀጥሉት በሚለቀቁት ጽሑፎች ማየት እንችላለን፡፡ ይህ የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ችግርን ለመፍታት የወሰደችው እርምጃ፣ ከጠንካራ ጎኖቿ አንዱ ነበር፡፡
ዛሬ እኛ በምናመልክባት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምን የውስጥ ችግር አለ? ችግር ካለስ፣ ችግሩ እንዴት ተፈጠረ? የችግሩ መሠረት ምንድነው? በችግሩ ምን ያህል ቆሰላችሁ? ተጎዳችሁ? ከቤተ ክርስቲያን ራቃችሁ? ወይስ ጸንታችሁ ቆማችሁ? ችግሩ ቤተ ክርስቲያንን ለሁለት ከፈላት ወይስ በሰላም ተፈታ? ከኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ምን እንማራለን? ብዙ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን የውጭ ችግሮች ሲያጠነክሩዋት የውስጥ ችግሮች ግን እንደ ትዕቢት፣ ወገናዊነት፣ የገንዘብ ጥቅም፣ አድልዎ፣ ያለማወቅና ያለ እኔ አዋቂ የለም …የሚሉት ነገሮች ለመከፋፈል ምክንያቶች ይሆናሉ፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎች ስንከፋፈል የእግዚአብሔር ስም በእኛ ምክንያት ይሰደባል፡፡ ስለዚህ የጌታ ስም ከሚሰደብ እኛ ብንበደል ይሻላል፡፡ በተቻለ መጠን ነገሩን በሰላማዊ መንገድ እንደ ኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን በሰላም ልንፈታው ይገባል፡፡ ችግር ፈጣሪ ከመሆን፣ ችግር ፈቺ ጌታ ያድርገን፡፡
0 Comments