በሥጋችሁ ላይ ባለ ሕመም ድንቅ ፈውስ ተመኝታችሁና ናፍቃችሁ ታውቃላችሁ? ይህ የሁላችንም መሻት እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ታማችሁ ፈውስን ፍለጋ በየቦታው ስትባዝኑ ከርማችሁ ባለማግኘታችሁ ምን ተሰማችሁ?  ማንን ረዳት አገኛችሁ? ባለ መፈወሳችሁስ ግራ አልተጋባችሁም? አላዘናችሁም? ተስፋ አልቆረጣችሁም? ፈውስ እየፈለጉ አለመፈውስ፣ ከበሽታ ነጻ መሆን እየፈለጉ ነጻ አለመሆን፣ መዳን እየፈለጉ አለመዳን፤ ያስለቅሳል፣ ያነጫንጫል፣ ተስፋ ያስቆርጣል፣ እንዲሁም ሞትን ያስመኛል፡፡

የበሽታዬን ምንጭ ሳላውቅ ለ13 ዓመት ያህል የአንጀት ችግር ነበረብኝ፡፡ ሕመሙ የሚጠላው የእግር መንገድና ንግግር ነው፡፡ አንድ ጊዜ ዶ/ር “በሕይወት መኖር ከፈለክ ከንግግር፣ ከእግር ጉዞና ከሥጋ ፈጽሞ መራቅ አለብህ” አለኝ፡፡ ከሥጋ መራቅ እችላለሁ፣ ከንግግርና ከእግር ጉዞ እንዴት እርቃለሁ? በማለት ግራ ተጋብቼ እያለሁ፣ አንድ ውሳኔ ወሰንኩኝ፡፡ አንድ ቀን ፈውስን በጣም ጓጉቼ፣ እፈወሳለሁ ብዬ አምኜና ፈውስ ይመጣልኛል ብዬ፣ የፈውስ ፕሮግራም ወዳለበት ሥፍራ ሄድኩኝ፡፡ በሄድኩበትም ቁጭ ባልሁበት ሥፍራ ፈውስ ይመጣልኛል ብዬ ስጠብቅ ሳይመጣልኝ ቀረ፡፡ ‹‹የሚያማችሁ ወደ ፊት ውጡ›› ሲባል፣ እኔ በጠበቅሁት መንገድ ስላልሆነ፣ ቁጭ ብዬ ቀረሁ(ባለ መፈወሴ አኩርፌ)፡፡ ለነገሩ ከዚህ በፊት ብዙ አገልጋዮች ጸልየውልኛል፣ ቢሆንም ግን ይህ ቀን የፈውሴ ሰዓት እንደሆነ አምኜ ነበር የሄድኩት፡፡ አምኜ ብሄድም ግን፣ ፈውስ ሊመጣልኝ አልቻለም፡፡

እንደ ሶርያው የሠራዊት አለቃ ንዕማን ፈውስ ሳልቀበል ወደ ቤቴ ተመለስኩኝ፡፡ እርሱ ከሶርያ አገር እስራኤል ድረስ መጥቶ ከነብዩ ኤልሳዕ ዘንድ ፈውስ ሳይቀበል ወደ አገሩ ተመለሰ፡፡ (2ኛ.ነገ. 5፡10-12) ከዚያ በኋላ ብሞትም ልሙት ብዬ አገልግሎቴን ለመቀጠል ወሰንኩኝ፡፡ አንድ የቀን መጽሐፍ ቅዱስ ት/ቤት ስለነበረን፣ በሳምንት ሁለቴ   ቀን ሙሉ ለ40 ደቂቃ በእግር እየተጋዝኩኝ አስተምር ነበር፡፡ ሁለቱን ቀኖች ሄጄ ለመስተማር በሁለቱ ቀኖች መካከል አንድ ግማሽ ቀን ምንም ሳልንቀሳቀስ በመኝታ ላይ ማረፍ ነበረብኝ፡፡ በእንዲህ ባለ ሁኔታ ለሁለት ወር ያህል እያስተማርኩ እያለ፣ አንድ አስተማሪ ስለታመመና የትምህርት ቤቱ ኃላፊም ስለ ነበርኩኝ፣ እርሱን ተክቼ ለሁለት ሳምንት በየቀኑ እየሄድኩኝ ቀን ሙሉ ማስተማር ግዴታ ሆነብኝ፡፡ ሕመሜ የሚነሳብኝ የእግር መንገድ ከሄድኩኝና ንግግር ካበዛሁ ከሳምንት በኋላ ነበረና እንደ ልማዴ ያመኛል ብዬ ስጠብቅ፣ ሳያመኝ ሁለተኛውንም ሳምንት ጨረስኩ፡፡

አንድና ሁለት ወሮች እያለፉ፣ ከአራት ወር በኋላ መዳኔን ማረጋገጥ አለብኝ ብዬ ለ13 ዓመት ያህል ያልበላሁትን ጥሬ ሥጋ መብላት አለብኝ ብዬ ወሰንኩኝና ሁለት ጊዜ ያህል በአስራ አምስት ቀን ልዩነት በላሁኝ፡፡ ከዚያም ብዙ የእግር ጉዞና ንግግር ባበዛም ምንም ሕመም አልነበረም፡፡ አሁን አስራ ስምንት ዓመት ሆነኝ እስከ አሁን ድረስ ሕመሙ የለም፡፡ ጌታ እንዴት እንደፈወሰኝ ሳላውቅ ድኜ ራሴን አገኘሁት፡፡ ጌታ አስደናቂ ነው፤ የጌታ እጅ ሳናስበው ድንገት ደርሶ ፈውስ ይሆንልናል፡፡

በዚህ በሐዋርያት ሥራ 3፡1-16 ላይ የምናገኘው የፈውስ ሂደት የእግዚአብሔር ፈዋሽነቱ፣ ኃያልነቱና፣ ተዓምራት አድራጊነቱ የተገለጠበት፤ ሐዋርያትም ለአገልግሎቱ ሲወጡ፣ የእግዚአብሔር እጅ ከእነርሱ ጋር እንደ ሆነ ያረጋገጡበት ፈውስ/ተዓምራት ነበረ፡፡ ከእናቱ ማህፀን ጀምሮ የአካል ጉዳተኛ የነበረ ሰው ማንም ሊረዳው ያልቻለ፣ ጌታ ደርሶለት አስደናቂ ፈውስ አደረገለት፡፡ ሰውዬው የለመናቸው ምፅዋት ነበር፤ እነርሱ ግን በጌታ በመታመናቸው “ብርና ወርቅ የለንም ያለንን እንሰጥሃለን ብለው የኢየሱስን ስም ሰጡት፡፡ ስሙም አስደናቂ ፈውስ ስለሆነለት ሰውዬውም “ተነሳና ተመላለስ” ሲባል ሳይጠራጠር ተነስቶ መመላለስ ጀመረ፡፡ በተለያየ ቦታ ሄዳችሁ ፈውስ ያላገኛችሁ ጌታን ባላችሁበት ሥፍራ ሆናችሁ በትዕግሥት ጠብቁት፣ ጌታ በአስደናቂው ፈውሱ ይደርስላችኋል፡፡ ፈውሳችን ከሰው ሳይሆን፣ በቀጥታ ከጌታ ዘንድ እንደሚመጣልን በማመን መጠበቅ አለብን፡፡ ይህ ፈውስ ለሰውዬው ብቻ ሳይሆን፣ ለሐዋርያቱም እምነት የጨመረና ጌታ ምን ያህል ከእስትንፋሳቸው ይልቅ ቅርብ የሆነ ጌታ እንደሆነ ያዩበት በእጃቸው የተከናወነ የመጀመሪያ የፈውስ ሂደት ነበር፡፡ ዛሬም ፈውስ ለሚያስፈልገን ሳናስበውና ሳንጠብቀው በጊዜውና በሰዓቱ፣  ጌታ ለአካል ጉዳተኛው ድንቅ ፈውስ እንዳደረገለት ለእኛም ያደርግልናል፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *