ውድ የተልዕኮ ኦን ላይን አገልግሎት ተከታታዮች ላለፉት ስድስት ዓመታት ተልዕኮ teleko.org በሚለው ድህረ ገጽ እና የሶሻል ሚዲያ ቴሌግራምና ፌስ ቡክ ተከታታይ የሆኑ ጽሑፎችንና ትምህርቶችን ስንጋራ ቆይተናል፡፡ ባለፈው ዓመት በአንዳንድ ምክንያቶች ማቋረጤ ይታወቃል፤ በዚህ በምንጀምረው አዲስ ዓመት ‹‹የዕረፍት ዓመት›› በሚል ጽሁፍ ላካፍላችሁ በእቅድ ላይ ነኝ፣ ጸልዩልኝ፡፡ አሁን በዚህ ሳምንት አዲስ ዓመትን ልናከብር እየተዘጋጀን ባለንበት ጊዜ፣ ‹‹መልካም አዲስ ዓመት›› እያልኩ ከቅዱስ ቃሉ አብረን እንድንካፈል ወደድሁ፡፡

በዚህ በአዲስ ዓመት መግቢያ ላይ የማካፍላችሁ ቃል እግዚአብሔር ሙሴን በሲና ተራራ ላይ ሆኖ የተናገረውን ከዘሌዋውያን መጽሐፍ ምዕራፍ 25፡1-7 ላይ ያለውን ይሆናል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ የምናገኘው ዋናው ሐሳብ የእስራኤል ልጆች ወደ ተስፋይቱ ምድር በሚያገባቸው ጊዜ ሊያደርጉት የሚገባቸውን ነገር በሙሴ በኩል ይናገራቸዋል፡፡ በቁጥር 2 ላይ ‹‹እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ ምድሪቱ ለእግዚአብሔር ሰንበት ታድርግ›› ብሎ ያዛቸዋል፡፡ ምድሪቱ ስታርፍ እነርሱም ያርፋሉ፤ ምክንያቱም ማረስ፣ መዝራት፣ መኰትኮት፣ ማጨድ፣ መከመር፣ መውቃት፣ መቁረጥ፣ መጭመቅ … የመሳሰሉት ነገሮች ስለማይኖሩ ለእነርሱም ትልቅ የዕረፍት ጊዜ ይሆንላቸዋል፡፡

ይህ ትእዛዝ በእውነቱ ከባድ ነው፤ ምክንያቱ ለአንድ ዓመት ምንም ሳያርሱ መቀመጥ ቀላል አይደለም፣ እምነት ይጠይቃል፡፡ በሰባተኛው ዓመት ካላረሱ፣ በስምንተኛው ዓመት የሚያርሱት የሚደርስላቸው በዘጠነኛው ዓመት ነው፡፡ በስድስተኛው ዓመት ያረሱትን ለሁለት ዓመት እንደሚበሉት አድርጎ ይባርክላቸዋል፡፡ ስለዚህ ይህን ትእዛዝ ተግባራዊ ለማድረግ በእግዚአብሔር መታመንን ይጠይቃል፡፡

ይህን አዲስ ዓመት ከመጀመራችን በፊት እንዲህ ዓይነት አትረስ፣ አትነግድ፣ አትሥራ፣ አትማር፣ … የሚል ትእዛዝ እግዚአብሔር ቢሰጠን ኖሮ፤ በዚህ በኑሮ ውድነት ጊዜ ምን ይውጠን ነበር? ለማንኛውም ይህን ከእስራኤል ልጆች በስተቀር ለማንም ትእዛዝ አልሰጠም፤ ለእነርሱም ቢሆን አዲስ ኪዳን ከመጣ ወዲህ ከእነርሱም ላይ ተነስቷል፡፡ እነርሱም ለረጅም ዓመታት በሮማውያንና በተርክሽ (ቱርክ) ከተገዙ ወዲህና በ1948 ነጻነታቸውን አግኝተው ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ ወዲህ ይህን ትእዛዝ መጠበቃቸውን ትተውታል፡፡

ይህ የምንጀምረው አዲስ ዓመት ብዙ የሚያሳስቡ፣ ግራ የሚያጋቡ፣ የሚያስጨንቁ፣ የሚፈትኑ ነገሮች ቢኖሩም በእግዚአብሔር ተደግፈን ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እየቀረብን የምንኖርበት ‹‹የዕረፍት ዓመት›› ይሁንልን፡፡ አሜን!

ጌታ 2016 ‹‹የዕረፍት ዓመት አድርጎልኝ አሳልፎኛል፤ አሁንም ይህ አዲስ ዓመት በመቀጠል ለሁላችንም ‹‹የዕረፍት ዓመት›› እንዲሆንልን ምኞቴና ጸሎቴ ነው፡፡ ይህን መልእክት ለምታነቡ ሁሉ እጄን ወደ እርሱ ወደ ዙፋኑ ፊት በመዘርጋት እጸልያለሁ፡፡ ጌታ ለሁላችንም 2017 ‹‹የዕረፍት ዓመት›› ያድርግልን፤ ጌታ ይባርካችሁ፣ እወዳችኋለሁ፡፡  በጌታ ወንድማችሁ ወ/ዊ አምበርብር ገብሩ


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *