ውድ የተልዕኮ ኦን ላይን አገልግሎት ተከታታዮች ላለፉት አምስት ዓመታት ተልዕኮ teleko.org በሚለው ድህረ ገጽ እና የሶሻል ሚዲያ ቴሌግራምና ፌስ ቡክ ተከታታይ የሆኑ ጽሑፎችንና ትምህርቶችን ስናጋራ ቆይተናል፡፡ በዚህ በልደት ሰሞን ‹‹የምሥራች›› በሚል የተዘጋጀ ጽሑፍ ተልዕኮ teleko.org በሚለው ድህረ ገጽ እናጋራችኋለን፡፡ አሁን በዚህ ሳምንት ልደትን ልናከብር እየተዘጋጀን ባለንበት ጊዜ ከቅዱስ ቃሉ በመላእክት በኩል ለሰው ልጆች ሁሉ የሚሆን ‹‹ታላቅ ደስታ›› የምሥራች እንዴት እንደመጣ ታሪኩን አብረን እንድንካፈል ወደድን፡፡
የምንካፈለው ጽሑፍ ርዕሱ ‹‹ ታላቅ ደስታ›› የሚል ሲሆን፣ ታሪኩ የተመሠረተው በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 2፡10 ላይ ‹‹ስለ ኢየሱስ›› መወለድ ይሆናል፡፡ ሉቃስ በዚህ በወንጌሉ ‹‹እነሆ ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኃለሁና አትፍሩ›› በማለት መልአኩ ይዞት የመጣውን መልእክት አስፍሮአል፡፡
ሰው በዚህ ዓለም ሲኖር ከሚፈልጋቸው ነገሮች አንዱ ‹‹ደስታ›› ነው፡፡ ጊዜያዊ ደስታ በተለያዩ ነገሮች ሊገኝ ይችል ይሆናል፣ ነገር ግን ጠፊ ነው፣ ዘላቂ አይደለም፣ ለውስጠኛው ልባችን አይደርስም፡፡ ለእረኞቹ የኢየሱስን መወለድ ያበሰረው መልአክ ይዞት የመጣላቸው ‹‹ታላቅ ደስታ የምሥራች›› እንደሆነ ይናገራል፡፡ የዚህን ታላቅ ደስታ የምሥራች ጅማሬ አስቀድመን የምናገኘው በምዕራፍ አንድ ላይ ነው፡፡ ‹‹በስድስተኛው ወር መልአኩ ገብርኤል…ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ፡፡ መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ፡- ደስ ይበልሽ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፣ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት… ማርያም ሆይ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ፡፡ እነሆም ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፡- ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ፡፡ …መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፡- የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል (ሉቃስ 1፡26-35) ይላል፡፡
ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ማርያም ተልዕኮ የነበረው መልአክ፣ በተናገረው መሠረት ጊዜውን ጠብቆ ማርያም ወደ ቤተልሔም ለሕዝብ ቆጠራ በሄደችበት፣ ኢየሱስን ወልዳ የእንግዳ ማረፊያ በማጣቷ በከብቶች ማደሪያ በግርግም አስተኛችው፡፡ በዚህም ጊዜ መንጓቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ፡፡ በዚያም ሌሊት መልአኩ ተገልጦ ለእረኞቹ ይዞላቸው የመጣው የኢሱስን መወለድ ያበሰረላቸው እንዲህ በማለት ነበር፣ ‹‹እነሆ ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፣ ዛሬ በዳዊት ክተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና›› የሚል ነበር (ለቃስ 2፡10)፡፡
ዛሬ ብዙ ሰዎች ‹‹ታላቅ ደስታ›› የሚለውን ቃል እንሰማን፣ ነገር ግን ምን ማለት እንደሆነ ትርጉምን አናውቅም፡፡ ጌታ የተወለደበት ጊዜ ቤታችንን፣ ሱቃችንን፣ ቢሮአችንን እና የገበያ አዳራሾቻችንን በማስጌጥ፣ የፌስቲፋል ዝግጅቶችን በመካፈል፣ ለምንወዳቸው ስጦታ በመስጠት፣ ጊዜውን አሳልፈን፣ ከዚህ ሁሉ መጨረሻ ላይ ከፍ ብሎ የነበረው በቁሳዊ ላይ የተመሰረተው ደስታችን ይጠፋና ባዶ እንሆናለን፡፡
ሌሎቻችን ደግሞ የልደቱን ሰሞን በፍጹም አንወደውም፣ ምክንያቱም ብዙዎቻችን ለጌጣጌጥ ወይም ለስጦታ የሚሆን ገንዘብ የለንም፡፡ አንዳንዶቻችን አብረን የምናከብረው ጓደኞች የሉንም፡፡ በዙሪያችን ባለው ሁኔታ በጥልቀት ስለምንደገፍ በስሜታችን ኃዘናችን የበዛ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ልደት በየዐመቱ ባይመጣ እንመርጣለን፡፡
የሁላችንም ችግር መላእክቶች የተናገሩትን ‹‹ታላቅ ደስታ›› የሚለውን መልእክት በተሳሳተ መንገድ ስለምንረዳው ነው፡፡ ይህ ታላቅ ደስታ የሚገኘው አርትፊሻ በሆነ መንገድ ሳይሆን ጥልቅ በሆነው የጊዜው ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ፣ እኛን ከኃጢአታችን ለማዳንና ወደ ፊት ለዘላለም በሰማይ የሚጠብቀንን እውነተኛውን ደስታ ለማጎናጸፍ ልደት አምላክ ሰው የሆነበት መንገድ ነው፡፡ ቢገባን ያ ነው እውነተኛው የደስታችን ምክንያት ለሆን የሚገባው፡፡ እረኞቹ በዚያ በቀዝቃዛ ሌሊት የሥራ አጋዥ በሌላቸው ጊዜ መላእክቶች የነገሯቸውን ለማየት ሄደው፣ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑና ሲያወድሱ እንመለከታለን፡፡ ‹‹እረኞችም እንደ ተባለላቸው ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ ተመለሱ ይላል ጸሐፊው ሉቃስ (ሉቃስ 2፡20)፡፡
በእርግጥ እውነተኛ የልደት ትርጉም ‹‹ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች›› የሚለው እንደሆነ በምዕራፍ 2፡10 ላይ እናገኘዋለን፡፡ ወንድሜና እህቴ ሆይ ይህ ‹‹ታላቅ ደስታ›› የሆነበት የመጀመሪያው ምክንያት በአዳም ኃጢአት ምክንያት እግዚአብሔር ከእኛ ተለይቶ፣ እኛ ከእግዚአብሔር ርቀን ነበር፣ አሁን ግን እግዚአብሔር ራሱ ሰው ሆኖ በመምጣት በመካከላችን ተገኘ፣ ሁለተኛም የኃጢአታችንን ዋጋ በመስቀል ላይ ደሙን በማፍሰስ ከፈለልን፣ ሕይወትም ሰጠን፡፡ በመጨረሻም አክብሮን በአባቱ ቀኝ አስቀመጠን፡፡ ወደፊትም በክብር መጥቶ የምንወሰድበት ቀን በናፍቆት እንጠብቃለን፡፡
በዚህ በልደት ሰሞን ትልቅ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባን ነገረ ቢኖር፣ ይህ ታላቅ ደስታ በውስጣችን ነው? ወይስ በውጭአችን ባሉ ቁሳቁሶች ላይ የተመሠረተ ይሆን?፡፡ ይህ ታላቅ ደስታ በውስጣችን እንዳይገለጥ የሸፈነብን ነገር መርምረን ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ የዚህ ደስታ ውጤት መላእክቶቹ ‹‹ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ›› ብለው እንደተናገሩት ይሆንልናል፡፡ ታላቅ ደስታና የሰላም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን፡፡
‹‹መልካም ልደት››
0 Comments