‹‹የማንን?››
የንባብ ክፍል፡- ገላትያ 1
‹‹ ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁ? ወይስ ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንኩም›› ቁ. 10
እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ፣ ሁሉን የሚያውቅ፣ በሁሉ ቦታ የሚገኝ፣ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው፣ አልፋና ኦሜጋ የሆነ የሚታዩትን በኅዋና በጠፈር ውስጥ ያሉትን ፍጥረታት ሁሉ የፈጠረና የሚያዛቸውም አምላክ ነው፡፡
እርሱ የእውነት ዐምድ ነው፤ ሰው ግን በእግዚአብሐር አምሳል ቢፈጠርም በሠራው ኃጢአት ምክንያት ፍጹምነት የለውም፡፡ ሰው ውሱን ስለሆነ ሁሉን ነገር አያውቅም፤ የሚያውቃቸውንም ነገሮች ከማያውቃቸው ነገሮች ጋር ሲያወዳድር ምንም አለማወቁን ይረዳል፡፡ ይሁን እንጂ በኃጢአት ከወደቀበት ጊዜ ጀምሮ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ራሱን ሲያስተካክልና ሲያወዳድር በዐመጽም ብዛት ከፈጣሪው ጋር ሲጣላ ቆይቶአል፡፡
ቢሆንም በዘመናት ሁሉ ለእግዚአብሔር የሚታዘዙና የሚቆሙ ብዙዎች አሉ፡፡ በዚህም በሰይጣን ብዙ ጊዜ ፈተናና ችግር ይደርስባቸዋል፡፡ እነርሱም ‹‹እኔና ቤቴ እግዚአብሔርን እናመልካለን›› በማለት የድል ሕይወት በመኖር አልፈዋል፡፡ እኛም ከእነርሱ ጋር በእምነት ሰውን ከመስማት እግዚአብሔርን መስማት፣ ለሰው ከመታዘዝ ለእግዚአብሔር መታዘዝን መምረጥ አለብን፡፡ ለሐሰት ከመቆም ይልቅ ለክርስቶስ ክብር መቆም አለብን፡፡ ለወንጌል መቆም ክብራችን፣ ሕይወታችን፣ ከዚያም መሞትም ጥቅማችን ነው፡፡ ስለዚህ ማንን ልስማ ማንን ልታዘዝ የሚለውን ዛሬውኑ ውሳኔ ማድረግ አለብን፡፡ ዘማሪው ያለውን እኛም አብረን እንበል፡፡
ከዓለም ዝናን ከብርን ከማተርፍ፣
መስቀል ልሸከም ላንተ ልነቀፍ፡፡
ስለ ቅዱስ ስምህ ብጣል ብወቀስ፣
ይፈስልኛል የክብር መንፈስ፡፡
‹‹በምስክርነትህ አትፈር››
የንባብ ክፍል፡- 2ጢሞቴዎስ 1
‹‹እንግዲህ በጌታችን ምስክርነት ወይም በእስረኛው በእኔ አትፈር፣ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ኃይል መጠን ስለ ወንጌል አብረኸኝ መከራ ተቀበል›› ቁ. 8
ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ቃል ለጢሞቴዎስ የሚጽፈው በእስር ቤት ውስጥ ሆኖ ነው፡፡ በሕይወቱ ጌታን ካገኘበት ቀን ጀምሮ በብዙ ፈተናና ችግር፣ በራብና በጥማት፣ በመታሠርና በመገረፍ ለጌታው የሚጠቅም ዕቃ ሆኖአል፡፡ በቤት፣ በጉባኤ፣ በእስር ቤት ውስጥ ሆኖ ጌታ የጣለበትን ዐደራ በሚገባ በምስክርነቱና በስብከቱ ፈጽሞአል፡፡ አሁንም የሕይወቱ መጨረሻ በደረሰበት ጊዜ በመጨረሻ መልእክቱ ለጢሞቴዎስ ምክር ይሰጠዋል፡፡
ጢሞቴዎስ የጳውሎስ የወንጌል ሥራ ጓደኛው በመሆን ብዙ ጊዜ አብሮት ሠርቶአል፡፡ የቤተ ክርስቲያንም እረኛ በመሆንና ሽማግሌዎችን፣ ዲያቆናትን በመሾም በትልቅ ኃላፊነት የሚያገለግል የክርስቶስ ወታደር ነበር፡፡ አሁን ጳውሎስ ሊያሳስበው የፈለገው በጌታችን ምስክርነትና በእስረኛው በጳውሎስ እንዳያፍር የጀመረውን ምስክርነት እስከ መጨረሻው እስከ ሞት ድረስ እንዲቀጥል ያበረታታዋል፡፡
እኛም ቢሆን ዛሬ ይህን የሕይወት ጉዞ ጀምረናል፤ በቤት ቢሆን፣ በሥራ ቦታ፣ ባለንበት ቦታ ሁሉ ስለ ክርስቶስ ለመመስከር ፍላጎት አለን፡፡ እስከ አሁንም ስለ ክርስቶስ ወንጌል ምንም ዓይነት መከራ አልደረሰብንም፡፡ ጳውሎስ በድፍረትና በኃይል ያለበትን ድርሻ አበርክቶ አልፎአል፡፡ ቀጥሎም ለጢሞቴዎስ በዐደራ መልክ በማስጠንቀቅ አስረክቦታል፡፡ እንደዚህ እያለ ወንጌል እኛ እስካለንበት ዘመን ድረስ ደርሶአል፡፡
ዛሬ ለዚህ ወንጌል ምስክሮች ልንሆን የሚገባን እኛ ነን፡፡ ለሚቀጥለው ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት አለብን፡፡ እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ ሰጥቶናል፡፡ ስለዚህም ለዚህ ጌታ ለመመስከር ማፈር የለብንም፡፡ በጌታ ሕይወት ተስፋ ስላለን ይህን ለሌሎች ለማካፈል በእምነት እንነሣ፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ! በጣም ደካማ ነኝና ኃይልህና ክንድህ ያበርታኝ፡፡
‹‹ቃሉን ስበክ››
የንባብ ክፍል፡- 2ጢሞቴዎስ 4
‹‹ ቃሉን ስበክ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፣ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም›› ቁ. 2
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም ድነት የሚሆነውን ቤዛነት ሁሉ ከፍሎ ጨርሷል፡፡ ቤዛነቱን ሰምተውና ተረድተው ያመኑ ብቻ ድነትን ያገኛሉ፡፡ ነገር ግን በዓለማችን ላይ የወንጌልን የምሥራች ሳይሰሙ ወይም ሳይረዱ የቀሩ እጅግ ብዙዎች ስለሆኑ ያላቸው ዕድል ጥፋት ብቻ ነው፡፡ እነዚህም ሰዎች ከእግዚአብሔር ሳይታረቁ የሚቀሩትና የሚጠሩት ለመጥፋት ስለፈለጉ ሳይሆን ነገር ግን የመዳንን መንገድ የሚነግራቸውና የሚያስረዳቸው ባለማግኘታቸው ነው፡፡
የእግዚአብሔር ዓላማም ሰዎች በክርስቶስ ተከታዮች አማካኝነት ወንጌልን እንዲሰሙና እንዲረዱ ሲሆን፣ በእኛ በክርስቲያኖች ቸልተኝነት ምክንያት ብዙዎች ወደ ሞት እየተጓዙ ናቸው፡፡ አንተም ራስህ ያ ወንድም ወይም ያች እህት ወደ ድነት መንገድ ባይመሩህ ኖሮ እስከ አሁን በዓለም ውስጥ ትገኝ ነበር፡፡ ስለዚህ አንተም ለሌላው እንዲሁ ባለ ዕዳ ነህ፤ አንቺም እንደዚሁ፡፡
የምሥራቹን ላልሰሙና ላልተረዱት ልናደርስ የምንችልበት ዋናው መንገድ በአንደበታችን በመናገር በመስበክና በማስተማር ብቻ ነው፡፡ ስለ ኢየሱስ በሄድክበት ሥፍራ ሁሉ ለመናገር አትፍራ፡፡ ለጊዜው ፌዘኞች የመሰሉ ቢያጋጥሙህም የምትለውጣቸው አንተ ሳትሆን የእግዚአብሔር መንፈስ ስለሆነ ቢሰማህም ባይሰማህም፣ በጊዜውም አለጊዜውም የእግዚአብሔርን ቃል ስበክ፡፡
የአምላካችን ቃል ድንጋይ የሆነውን ልብ ይሰብራል፡፡ ስለዚህ በቃሉ ላይና በመንፈሱ ኃይል እንተማመንና እንናገር እንጂ አንፈርበት፡፡ ኢየሱስ ስለ እኛ በመስቀል ላይ እርቃነ ሥጋውን ሲሰቀልልን እንኳ አላፈረም፡፡ አንድ ቀንም በአባቱ ቀኝ ስንገናኝ ይመካብናል እንጂ አያፍርብንም፡፡ ጸሎት፡-አምላኬ ሆይ! በጊዜውም አለጊዜውም ቃልህን እንድናገር ኃይልህን ጨምርልኝ፡፡
0 Comments