‹‹የተሰቀለውን መስበክ››
የንባብ ክፍል፡- 1ቆሮንቶስ 1
‹‹አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ፣ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፣ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን›› ቁ.22
ጥበብንና እውቀትን ከእግዚአብሔር ነጥሎ ለሚሻ ሰው ወንጌልን መሰበክ እንደ ሞኝነት እንደሚያስቆጥርና ወንጌልም ለማያምኑት ሞኝነት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቁማል፡፡ በሚያምኑት ዘንድ ወንጌል የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ፣ የእውቀት ሁሉ ማኅደር፣ የእውነት ሁሉ ምንጭና የዘላለማዊ ሕይወት መንገድ በመሆኗ ታምነን ልንመሠረት የምንችልባት የመሠረት ዓለት ናት፡፡ ለሚያምኑ ኃይል ለዓለም ሞኝነት ሆኖ በተሰቀለው በክርስቶስ ማመን በሌላ በምንም ዓይነት መንገድ ልናገኘው የማንችለውን ሰላምና ደስታ ስለሚያስገኝልን ያለ ምንም ጥርጥርና ማወላወል አምነን ተቀብለነዋል፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ግን ‹‹የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን›› ብሎ ሲል ከማመንና ከመቀበል ለየት ያለ ተግባርን ያመለክተናል፡፡ ያም መመስከርና መስበክ ናቸው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ለአማኞች የሰጠው ታላቅ ተላዕኮ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ማዳረስ ነው፡፡ የተሰቀለውን ክርስቶስ ለዓለም ቤዛነትን ሊሰጥ የመጣ መሆኑን ማሳወቅ ነው፡፡ በደሙ ስለሚገኘው የኃጢአት ሥርየትና የዘላለም ሕይወት የምሥራቹን ማወጅና ማብሰር አለብን፡፡
እንግዲህ የተሰቀለውን ክርስቶስን ለመስበክ እያንዳንዱ አማኝ ከእርሱ ጋር መሰቀል ያስፈልገዋል (ገላ.2፡20)፡፡ አሮጌው ሥጋውን ሰቅሎ በአዲስ ሕይወት እየተመላለሰ፣ በቃሉ በኑሮውና በተግባሩ ክርስቶስን ሊያስተዋውቅ ይገባዋል፡፡ ለዓለማውያን በሕወታችንና በውስጣችን የተሰቀለውን ክርስቶስን እርሱን ለዓለም ልናሳይ እንድንችል የየዕለቱ ጸሎታችን ይሁን፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ! አንተ ጐልተህ በሕይወቴ ትታይ ዘንድ እኔነቴን ደምስስ፡፡
‹‹የተሰቀለውን ክርስቶስን ማየት››
የንባብ ክፍል፡- 2ቆሮንቶስ 2
‹‹በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደ ተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና›› ቁ.2
መስቀሉ ክርስቶስ ተቸንክሮበት ሰውን ከአምላኩ፣ ፍጡርን ከፈጣሪው ለማስታረቅ የሞተበት የዓለምን ሕዝብ ለድነት የሚጠራበት፣ ፍቅር በተግባር የተገለጠበት፣ የወንጌል መሠረት ማዕከላዊ ሥፍራ ነው፡፡
ዛሬ የመስቀሉ መልእክት የተሰቀለውን ክርስቶስን በማወጅ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ያስተጋባል፡፡ ኃጢአተኞችም ‹‹መጣሁ ወደ መስቀልህ…›› እያሉ በየቀኑ ሲጐርፉ እግዚአብሔር አምላክም ወደ ተሰቀለው ልጁ አይቶ በመስቀሉ ሥር ወደ ተንበረከኩት በይቅርታ ሲመለከት በደላቸውና መተላለፋቸው ከእነርሱ ይደመሰሳል፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ሊያውቀው የሚፈልግና በሰዎችም ሕይወት ሊያየው የሚመኘው የተሰቀለውን ክርስቶስን ነበር፡፡ በዚህ አባባሉ ከሰዎች ሕይወት ውስጥ ስህተትና ድካምን ከመፈለግና ከመመልከት፣ ከመሰናከልም ይልቅ የሚባርከንና የሚጠግነን ታላቁን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንድንመለከት ይጠቁመናል፡፡ ክርስቶስን በማየት በድካማቸው፣ በውድቀታቸው፣ ከመፍረድና ራሳችንንም ከፍርድ ውስጥ ከመጣል ይልቅ እንድንጸልይላቸውና በጌታ ፍቅር እንድንወዳቸው እንዲያውም ልንረዳቸው የምንችልበትን መንገድ መንፈስ ቅዱስ ያሳየናል፡፡
በሌላም መንገድ ከክርስቶስ ይልቅ ሌላውን መመኪያ ለማድረግ ማየትና መጠጋት፣ መታመንም እንደማያስፈልግ ያስተምረናል፡፡ የእኛ ውዳችን፣ ጌጣችንና ክብራችን በመስቀል ላይ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስ ክርስቶስን ብቻ ማየት ነው፡፡ ከእርሱ በቀር ሌላ እንዳናይና እንዳናውቅ ቆርጠን መነሳት አለብን፡፡ አምላካችን ይህንን ውሳኔያችንን በተግባር እንድንገልጸው ይርዳን፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ! በኀዘኔ፣ በችግሬ፣ በውድቀቴና በመከራዬ ሁሉ አንተን ብቻ እንዳይ ዐይኖቼን ክፈት፡፡
‹‹የወንጌል ማኅበርተኛ››
የንባብ ክፍል፡- 1ቆሮንቶስ 9
‹‹በወንጌል ማኅበርተኛ እሆን ዘንድ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ›› ቁ. 23
ወንጌል የምሥራች ቃል ነው፡፡ ‹‹እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና›› የሚለው ቃል ሰው ከአምላኩ ጋር የታረቀበትን መንገድ የሚያበስር ነው፡፡ የወንጌል ማኅበርተኛ ለመሆን ወንጌልን ሙሉ በሙሉ መቀበል ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ ሰው ኃጢአተኛነቱ ወደ ፍርድና ጥፋት እንደሚያደርሰው ተረድቶ ከኃጠአቱ ሊያድነው የሚችለውን ክርስቶስን በማመን ንስሐ መግባት ይኖርበታል፡፡ ቅድስናን የሕይወቱ መመሪያ በማድረግ በሚኖረው ኑሮው ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብር መኖር አለበት፡፡ ክርስቶስ ኃጢአተኞችን ከአብ ጋር እንዳስታረቀ በሰውና በሰው መካከልም ሰላምን እንደመሠረተ ሁሉ የወንጌል ማኅበርተኛ የሆነ ሁሉ ይህንን ተግባር መፈጸም አለበት፡፡
የሰው ሕይወት የሚያንጸባርቀው በሕይወቱ ውስጥ ያለውንና በልቡ ውስጥ የሞላውን ነው፡፡ ስለሆነም ኢየሱስ በልባችን ውስጥ ካለና በመንፈሳዊ ሕይወታችን ቃሉን ከተመገብን እውነተኛ የወንጌል ማኅበርተኛ መሆናችንን ሰዎች ካዩና ካወቁ ከእኛ ብዙ ነገር ይጠብቃሉ፡፡ ስለዚህ ስለ ወንጌሉ እንድንመሰክርና የምሥራቹን እንድናሰራጭ ያስፈልጋል፡፡
የወንጌል ማኅበርተኛ በቅድሚያ ያመነበት ስለሆነ ባለው ኃይል ሁሉ፣ ባለው ጊዜ ሁሉ፣ ባለው ገንዘብ ሁሉ፣ ባለው እውቀት ሁሉና ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ወንጌልን ለማሰራጨትና ለማስተማር ታጥቆ የተነሣ የክርስቶስ አምባሳደር ነው፡፡ ወንጌልም ለችግር ሁሉ ዘላቂ መፍትሔ መሆኑንና ለሰው ሰላምን የሚያመጣ መሆኑን ስለሚያምንበት ያለማፈር ለእግዚአብሔር ክብር ሲል ያለበትን ኃላፊነት ይፈጽማል፡፡ ጸሎት፡- አምላኬ ሆይ! የማምንበትን እንድኖር የምኖርበትን እንድመሰክር፣ የምመሰክረውንም እንዳደርግ እርዳኝ፡፡
0 Comments