‹‹እስራት››

የንባብ ክፍል፡- የሐዋርያት ሥራ 28

‹‹… ስለ እስራኤል ተስፋ ይህን ሰንሰለት ለብሻለሁና›› ቁ. 20

ሐዋርያው ጳውሎስ በአይሁድ ሰዎች ስለ ተከሰሰበት ጉዳይ ትክክለኛ ፍርድ እንደማያገኝ ስላመነበት ወደ ቄሣር ይግባኝ ብሎ ስለነበረ ታስሮ የሮማውያን መዲና ወደ ሆነችው ሮም ተወሰደ፡፡ በሐዋርያው በኩል ወደ ሮም እንዲመጣ ምክንያት የሆነው ‹‹ይግባኝ›› ማለቱ ይሁን እንጂ ወደ ሮም መሄዱ የጌታ ዓላማ ነበር፤ ምክንያቱም ባለፈው ጽሑፋችን እንደተመለከትነው በሮሜ ደግሞ እንዲመሠክርለት የጌታ ፈቃድ ነበርና ነው፡፡

ነገሩ እንደዚህ ሆኖ ሳለ ጌታ ለጳውሎስ ባሰሩት ሰዎች ፊት ሞገስ ሰጠውና ሌሎቹ እስረኞች ወደ መደበኛው ወህኒ ቤት ሲላኩ ሐዋርያው ግን ከሚጠብቀው ወታደር ጋር ለብቻው ይቀመጥ ዘንድ ተፈቀደለት፡፡ ቁጥር 16 ይህ ጌታ ከእርሱ ጋር እንደነበረ ተጨማሪ ማረጋገጫ ነበር፡፡ በወንጌል ምክንያት የጌታ እሥረኛ የሆነው ጳውሎስ በሰንሰለት ውስጥ ሆኖ ሳለ እንኳ ከተማ ለሚኖሩት አይሁዳውያን ብቻ ሳይሆን ወደ እርሱ ለሚመጡት ሁሉ ሳይቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ ስለ ክርስቶስ እጅግ ገልጦ ያስተምር ነበር፡፡

ለሁለት ዓመት ያህል በተከራየው ቤት ውስጥ ወታደሮች እየተለዋወጡ ጳውሎስን በሚጠብቁበት ጊዜ ሕይወታቸው በወንጌል ተነክቶ ስለነበር የሐዋርያው ጳውሎስን ምስክርነት ያዳምጡ ነበር፡፡ ሐዋርያው በወንጌል ምክንያት መታሠሩ እንደ ታላቅ ደስታ ስለቆጠረው እሥራቱን በጌታ ጸጋ ለወንጌል መስፋፋት ምክንያት አድርጐታል፡፡ 

እኛስ ዛሬ ወንጌልን የምናሰራጨው በደስታ ጊዜ ነው ወይስ በመከራችንም ጊዜ? ወንጌልን እንዳንመሰክር የሚያስረን ነገር ይኖር ይሆን? ጳውሎስ እንዳለው በጊዜውም አለጊዜውም ቃሉን እንስበክ፡፡ ለዚህም ጌታ ጸጋውን ያብዛልን፡፡

ጸሎት፡- ጌታ ሆይ! ፈቃድህ በሆነበት ሥፍራ ሁሉ ቃልህን እንድመሰክር እርዳኝ፡፡

‹‹የሚያድን ኃይል››

የንባብ ክፍል፡- ሮሜ 1

‹‹በወንጌል አላፍርምና … ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና›› ቁ. 16

በዚህ ጥቅስ ላይ የተገለጸው ሐሳብ የሐዋርያው ጳውሎስ የሕይወት መመሪያ ነበር፤ የሐዋርያው ‹‹በወንጌል አላፍርም›› ማለት ቃል ብቻ ሳይሆን በድርጊት ተተርጉሟል፡፡ ክርስቶስን ካወቀበትና ጌታም እርሱን ለወንጌል አገልግሎት ‹‹የተመረጠ ዕቃ›› አድርጎ ከመረጠበት ጊዜ አንስቶ በደረሰበት ፈተናና ተቃውሞ ሳይታክት በጋለ ፍቅር የጌታን ወንጌል እንዳሰራጨ ስናስብ፣ እውነትም በወንጌል የማያፍር ታማኝ አገልጋይ እንደነበረ እናረጋግጣለን፡፡

ሐዋወያው ጳውሎስ ‹‹በወንጌል አላፍርም›› ያለበት ምክንያት በዘመኑ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ወንጌልን በአድናቆት ስለተቀበሉት አይደለም፣ ወይም ለሥጋው የተለየ ጥቅም ስላገኘበትም አይደለም፡፡ እንዲያውም ጳውሎስም ሆነ ሌሎች በጊዜው የነበሩ ክርስቲያኖች በጌታ ባመኑ ጊዜና ስለጌታ በመሰከሩ ቁጥር ይህ ነው የማይባል መከራና ስደት ደርሶባቸዋል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በስደትና በመከራ ውስጥም ቢሆን ‹‹በወንጌል አላፍርም›› ብሎ የተናገረበት ምክንያት የእግዚአብሔር የወንጌሉ ኃይል ለማዳን መሆኑን ስለተረዳ ነው፡፡

የኃጢአት ግርግዳ አፍርሶ ሰዎችን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅና የሚያስተዋውቅ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን የሆነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ብቻ ነው፡፡ ለአይሁድም ለግሪክም ያለ ወንጌል መዳን እንደማይገኝ ይገልጽላቸዋል፡፡ እውነተኛ የሕያወት ምንነትና ትርጉም የሚታወቀው፣ ሰላምና ደስታ የዘላለም ሕይወትም የሚገኘው በክርስቶስ ወንጌል ብቻ ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹በወንጌል አላፍርም›› ያለበት ምክንያት የማዳን ኃይሉን በሕይወቱ ስለ ተለማመደውና ለሌሎች ሰዎችም ቢሆን ለተወሳሰበውና ውጥንቅጡ ለጠፋው ሕይወታቸው ከወንጌል በስተቀር ሌላ መፍትሔ እንደማይገኝለት ስለ ተማመነ ነው፡፡

ዛሬ ሰላምና ዕረፍት የሚፈልግ አለን? በወንጌል ኃይል ለመለወጥ የሚፈልግ ወደ ጌታ ይቅረብ፡፡

ጸሎት፡- ጌታ ሆይ! በማዳንህ ኃይል በመተማመን ወንጌልን እንዳሰራጭ እርዳኝ፡፡

‹‹መሥዋዕትነት››

የንባብ ክፍል፡- ሮሜ 8

‹‹ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፣ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን›› ቁ. 36

 የወንጌል ምስክር መሆን ራስን ክዶ ነው፡፡ በሐዋርያት ሥራ 1፡8 ላይ ‹‹ምስክሮቼ›› የሚለው ቃል በግሪክኛ ቋንቋ ‹‹ሰማዕት›› ከሚለው ቃል ጋር አንድ ነው፡፡ ስለዚህ የክርስቶስ ምስክር ለመሆን የተጠራ ሰው ሁሉ ለሰማዕትነት ጭምር የተጠራ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልገዋል፡፡ ሐዋርያው ጰውሎስ ራሱንና ሌሎች ክርስቲያኖች በመጨመር ‹‹ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፣ እንደሚታረዱ በጎችም ተቆጠርን›› በማለት በመዝሙር 43፡22 ያለውን ይጠቀማል፡፡ የክርስቶስ መስክሮች አስፈላጊ ከሆነ ‹‹እሰከሞት ድረስ የታመንክ ሁን›› የሚለውን የጌታ የአደራ ቃል በተግባር ለመግለጽ የተዘጋጁ መሆናቸውን ያረጋግጣል፡፡

የእዚህ ምስጢር የራሳችን ብርታት ወይም ኃይል አይደለም፤ ምስጢሩ የእግዚአብሔር ኃይል ከእኛ ጋር መሆኑ ነው፡፡ አንድያ ልጁን ስለ እኛ አሳልፎ እንዲሰጥ ያደረገው ፍቅሩ በሕይወታችን በመገለጡ ነው፡፡ ምስጢሩ ለአንድያ ልጁ ያልሳሳ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ሁሉን ስለሚሰጠንና ሁሉን ስለሚያስችለን ነው፡፡ ምስክር ማለት ያየነውን፣ የሰማነውን፣ የቀመስነውን ፍቅር የሚያውጅ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ ከሆነም ስለ ፍቅር ሰማዕት ለመሆን የተዘጋጀ ነው፡፡ ይህንን ሁሉ አውቆ ጌታን የተከተለና ከሁሉ በላይ ደግሞ በእግዚአብሔር ፍቅር የተሞላ ክርስቲያን ምንም ዓይነት ኃይል ሊበግረው አይችልም፡፡ ጳውሎስም የዘረዘራቸው ሁሉ በፊቱ ቢደቀኑ ከክርስቶስ ፍቅር አይለዩትም፡፡

ጳውሎስ በክርስቶስ ባለን ፍቅር ከአሸናፊዎች እንደምንበልጥ ነገሩን ሲደመድም ‹‹ልዩ ፍጥረትም ቢሆን… ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንደማይችል ተረድቻለሁ›› ይላል፡፡ ወንድሞችና እህቶች ለክርስቶስ ምስክር በመሆን አሸናፊዎች እንድንሆን የእግዚአብሔርን ኃይል እንጠይቅ፡፡ ጸሎት፡- ጌታ ሆይ! ለአንተ መሥዋዕት እንድሆን የሚያበቃ ፍቅር ስጠኝ፡፡             


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *