‹‹የወንጌል ሸክም››

የንባብ ክፍል፡- ሮሜ 9

‹‹ብዙ ኀዘን የማያቋርጥም ጭንቀት በልቤ አለኝ›› ቁ. 1

ሐዋርያው ‹‹‹‹ብዙ ኀዘን የማያቋርጥም ጭንቀት›› በልቡ ውስጥ እንዳለ ይናገራል፡፡ ይህ ኀዘንና የማያቋርጥ ጭንቀት ቅዠት እንዳይደለ ነገር ግን በተጨባጭ ሁኔታ አብሮት ያለ ነገር እንደሆነ ለማረጋገጥ ሲፈልግ ‹‹በክርስቶስ ሆኜ እውነትን እናገራለሁ፣ አልዋሽም፣ ኅሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል›› በማለት ይገልጻል፡፡

ለሐዋርያው ሸክም ምክንያት የሆነው ምን ይሆን? ቁ.3 የተመለከትን እንደሆነ በሥጋ ዘመዶቹ የሆኑ የእስራኤል  ሰዎች በቀደመው ምንባባችን የተመለከትነውን በክርስቶስ በኩል የተገለጸውን የእግዚአብሔር ፍቅር ችላ ማለታቸው ነበር፡፡ በቁ. 4-5 ላይ እንደምናነበው ለእነዚህ ሰዎች ወደ ክርስቶስ ያደርሳቸው ዘንድ ከእግዚአብሔር የተለየ መብትና መገለጥ ተሰጥቶአቸው ነበር፡፡

ክርስቶስ በመጣ ጊዜ አለመቀበላቸው፣ እምቢተኝነታቸውና ከእግዚአብሔር የተደረገላቸውን ምሕረት አለማወቃቸው ለሐዋርያው ጳውሎስ ሸክም ሆኖበት ነበር፡፡ በእነርሱም ምክንያት የነበረው ኀዘንና ጭንቀት ብዛት ‹‹ምነው እኔ ከክርስቶስ ተለይቼ በተረገምሁና እነርሱ በዳኑልኝ›› እስከ ማለት አድርሶታል፡፡ ይህንን የመሰለውን ጸሎት ሙሴም ጸልዮ ነበር (ዘጸ.32፡32)፡፡

ጳውሎስ ከእግዚአብሔር ፍቅር ለመለየት ስለ ፈለገ ሳይሆን ለእነርሱ ካለው ፍቅርና ሸክም የተነሣ ምን ያህል ለራሱ ጥቅም የሆነውን ለመሰዋት እንኳን የተዘጋጀ መሆኑን ሊያስረዳን ስለ ፈለገ ነው፡፡ ታዲያ እንደዚህ ያለ የነፍሳት ሸክም የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ ለወንጌል መስፋፋት ዓይነተኛ የእግዚአብሔር መሣሪያ መሆኑ አይደንቀንም፡፡ እኛም ዛሬ በልባችን የነፍሳት ሸክም ካለን ወንጌል በጊዜውም አለጊዜውም፣ በየትም ሥፍራ እናሰራጫለን፡፡ ዛሬ በልባችን ስንቶቻችን የነፍሳት ሸክም አለን? ዛሬ በልባችን ያለው ሸክም ምንድነው?

ጸሎት፡- ጌታ ሆይ! የነፍሳት ሸክም በልቤ ውሰጥ የለም፤ የበረደውን ልቤን በመንፈስህ ቀስቅሰው፡፡

‹‹የምሥራች የሚያወሩ እግሮች››

የንባብ ክፍል፡- ሮሜ 10

‹‹መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው›› ቁ. 15

በዚች በምኖርባት ምድር የሰው ልጆች ለተለያየ ዓላማ ሲሯሯጡ ይታያሉ፡፡ ብዙዎች በራሳቸው ጥቅም ብቻ ተወስነው የሚሯሯጡት ሰውን ለማማት፣ በሰው ላይ ተንኮልን ለመሸረብ፣ ወይም የሰውን ደም ለማፍሰስ ነው፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ በ1ቆሮንቶስ 9፡26 ላይ ‹‹… እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም›› ሲል እንደ  ተናገረው ሁሉ ለሰው ልጅ ‹‹የምሯሯጠው ለምንድን ነው? ምን ዓላማና ግብ ለመምታት ነው? ብሎ መጠየቅ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ዛሬ ልንመለከተው ያለን ጥቅስ የተወሰደበት ሥፍራ ስለ ድነት የሚናገር ክፍል ነው፡፡ ታዲያ ይህንን መሠረት በማድረግ የተጻፈው ጥቅሳችን ‹‹መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው?›› ይላል፡፡ የእነዚህ እግሮች ማማር በአቋቋማቸው ወይም በቅርጻቸው ላይ ሳይሆን ተሯሩጠው በሚያበሥሩት መልካም የምሥራች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ወዲያና ወዲህ ተሯሩጠው ‹‹የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል›› በማለት በኃጢአት ውስጥ ለሚማቅቁት ለሰው ልጆች የሚድኑበትን የጌታን ወንጌል ያውጁላቸዋል፡፡ ሜዳውን አቋርጠው፣ ተራራውን ወጥተው፣ ወንዙን ተሻግረው… ኃጢአተኞች አምነው እንዲድኑበት ወንጌልን ይሰብኩላቸዋል፡፡ ለእዚህም መልካም አገልግሎት የተመረጡ ይህንን መልካም የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው?

ወንድሞችና እህቶች እንግዲያውስ እኔና እናንተ የምንሯሯጠው ለምን ዓላማ ነው? ጌታ የሚያየው በእኛ ዓይኖች፣ የሚሠራው በእኛ እጆች፣ የሚያዳምጠው በእኛ ጆሮዎች፣ የሚሯሯጠው በእኛ እግሮች ስለሆነ፣ መልካሙን የምሥራች ለሰው ልጆች ለማዳረስ ከሆነ የምንሯሯጠው እውነትም እግሮቻችን ያማሩ ናቸው፡፡

ጸሎት፡- አምላኬ ሆይ! እግሮቼን ይህን የምሥራች እንዲናገሩ ስላዘጋጀሃቸው አመሰግንሃለሁ፡፡

‹‹አትሰልች››

የንባብ ክፍል፡- ሮሜ 11

‹‹… ምናልባት ከእነርሱ አንዳንዱን አድን እንደሆነ አገልግሎቴን አከብራለሁ›› ቁ. 14

ክርስቶስ ሐዋርያው ጳውሎስን ለወንጌል ሥራ ‹‹የተመረጠ ዕቃ›› አድርጎ እንደ መረጠው በሐዋርያት ሥራ 9፡15-16  እናነባለን፡፡ በተለይ ደግሞ የአሕዛብ ሐዋርያ አድርጎ እንደሸሾመው ሐዋርያው ራሱ በገላትያ 2፡-7-9 ገልጾታል፡፡ ይሁን እንጂ ምንም ጊዜም ቢሆን አይሁዳውያንን ችላ አላላቸውም፡፡ በተመረጠበት አገልግሎት መሠረት ወንጌልን ለመስበክ ወደ አሕዛብ አገሮችና ከተሞች በሚሄድበት ጊዜ የአይሁድ ምኵራብ እንዳለ ጠይቆ መጀመሪያ ወደዚያው ይሄድ ነበር፡፡ ተቃውሞ ስላበዙበት ሐዋ. ሥራ 18፡6 እንደምናነበው ‹‹ከእንግዲህ ወዲህ ወደ አሕዛብ እንሄዳለን›› ብሎ ከወሰነ በኋላም ቢሆን ከዚህ በፊት እንደተመለከትነው በሥጋ ዘመዶቹ ለሆኑት ለአይሁድ ሰዎች ብዙ ኀዘንና የማያቋርጥ ጭንቀት ነበረው፡፡

ስለሆነም በቀጥታ ወንጌልን ለእነርሱ በመስበክ በኩል የሚፈለገውን ያህል ሳይሳካለት በቀረ ጊዜ ለተላከላቸው አሕዛብ ታማኝ ሐዋርያ ሆኖ እነርሱን በብዛት ወደ ጌታ በመመለስ አይሁዳውያንን አስቀንቶ በጌታ በማመን የሚገኘውን የዘላለም ሕይወት እንዲቀበሉ ፍላጎት ሊያሳድርባቸው ፈለገ፡፡ ምን ዓይነት የማይሰለች ፍቅር እንደሆነ ለማስተዋል ያስቸግራል፡፡ ‹‹ብዙ ጊዜ ደክሜላቸው አልሰሙኝምና እኔም ልርሳቸው›› አላለም፡፡ በቀጥተኛ መንገድ ሙከራ አድርጎ ቢያቅተው በተዘዋዋሪ መንገድ የክርስቶስን ወንጌል ወደ ልባቸው የሚያገባበት ዘዴ ዘወትር ይፈልግ ነበር፡፡ ጳውሎስ በሕይወቱ ፍቅርን፣ ትዕግሥትን፣ አሸናፊነትን የተሞላ ነበር፡፡

ዛሬ እኔና እናንተስ እነዚህ ነገሮች በሕይወታችን ውስጥ አሉን ጌታን ለአንተ የማይታክት የታመነ ምስክር እሆን ዘንድ ፍቅርህን አብዛልኝ እንበለው፡፡ ጸሎት፡- ጌታ ሆይ ሳትሰለች በመስቀል ላይ እንደ ተሰቀልህ በመረዳት ቃልህን ባለመሰልቸት እናገር ዘንድ እርዳኝ፡፡      


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *