‹‹አደራን መፈጸም››
የንባብ ክፍል፡- የሐዋርያት ሥራ 20
‹‹… ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልኩትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔር ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴ በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ›› ቁ. 24
ጳውሎስ በእስያ አያሌ ቀናት ከተቀመጠ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሊሄድ እንዳሰበ በምዕራፉ ውስጥ እንመለከታለን፡፡ በእስያ በነበረበት ጊዜ ሁሉ ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ማመንና ወደ እግዚአብሔር መመለስን ያስተምራቸው ነበር፡፡ በተለይም እነርሱን ከሚጠቅም ነገር አንዳች እንዳላስቀረባቸው ይናገራል፡፡
ከጌታ የተቀበለውን ተልዕኮ ሲፈጽም ‹‹በብዙ ችግርና መከራ በትህትናና በዕንባ›› በደረሰበት ፈተና ሁሉ ራሱን ለጌታ ያስገዛ ነበር፡፡ ጳወሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ሊሄድ በመንፈስ ቅዱስ ቢረዳም በዚያ ችግርና እስራት እንደሚጠብቀው ተነግሮታል፡፡ መንፈስ ቅዱስንም በመታዘዝ ተልዕኮውን ለመፈጸም ከጌታ የተሰጠውንም አደራ ይኸውም የወንጌሉን መልእክት ኢየሱስ ክርስቶስን ለሰዎች ለማዳረስ ቆረጠ፡፡ በብዙ ጭንቅ ውስጥ ቢያልፍ እንኳን ነፍሱን እንደ ከንቱ ነገር እንደ ቈጠረ ይናገራል፡፡
በተሰጠው መልእክት የሚኮራ የማያፍር ነበር፡፡ ስለዚህም በሚቀጥሉት ምዕራፎች እንደምንመለከው በነገሥታትና በባለሥልጣናት ፊት እንኳን ስለ ተልዕኮው ታላቅነት ይናገር፣ ያስታውቅ ነበር፡፡
እኛም የእርሱን በጎነት እንድንናገር ተመርጠናል፤ የክርስቶስ መልእክተኞችም ነን፡፡ ታዲያ በችግሮችና በሁኔታዎች ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል እንናገራለንን? በተሰጠንስ ተልዕኮ ታማኞች ነን? ከጳውሎስ ጋር የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና በወንጌል አላፍርም እንላለን?
ጸሎት ፡- ጌታ ሆይ! ተልዕኮዬን እንድፈጽም እርዳኝ፡፡
‹‹በወንጌል አትፈር››
የንባብ ክፍል፡- የሐዋርያት ሥራ 22
‹‹ባየኸው ና በሰማኸው በሰው ሁሉ ፊት ምስክር ትሆንለታለህና›› ቁ. 15
ሳውልም በመጀመሪያ ለእግዚአብሔር የሠራ፣ ያሰበ የቀናም እየመሰለው በተሳሳተ መንገድ እግዚአብሔርን ያገለገለ እየመሰለው ለእግዚአብሔር የሆነውን ነገር ሁሉ በመቃወም ብዙ የማይጠቅም የምድረ በዳ ጉዞን ተራመደ፡፡ ለእግዚአብሔር ክብር የቆሙትን ሐዋርያት እንደነ እስጢፋኖስ የመሳሰሉትን ያስጨረሰ፣ የአመጽ ሰው በየቦታው ያሉትን ክርስቲያኖች በእስር ሲያሰቃይ ከቆየ በኋላ ወደ ደማስቆ በዚያ ያሉትን ለማሳሰር ሲሄድ፣ በመንገድ ላይ ጌታ በታላቅ ብርሃን ተገናኘው፡፡ የሚሠራው ሁሉ እንደማያስደስተው በተሳሳተ መንገድ እንደሄደም ተመለከተ፡፡ ከብርሃኑ የተነሣ ዐይኑ በታወረበት ጊዜ ወደ ወንድሞች እንዲሄድ በዚያም ማድረግ ያለበትን እንደሚነግሩት ነገረው፡፡
ደማስቆ በደረሰ ጊዜ በጸሎት የሚተጋው ሐናንያ የተባለው ሰው ወደ ሳውል ቀረበ፡፡ ሐናንያም ለጳውሎስ ማድረግ ያለበትን ሲነግረው ስለ ክርስቶስ ያየኸውን የተመለከትከውን የጨበጥከውን ከዚህም ሌላ የሰማኸውን በሕይወትህ የሆነው ለውጥ እንኳን ሳይቀር ለአንድ፣ ለሁለት ሳይሆን በሰው ሁሉ ፊት ለክርስቶስ ምስክር ትሆንለታለህ አለው፡፡ ጳውሎስ ያየውንና የተረዳውን በካህናት፣ በነገሥታት፣ በጠቢባን በትንንሽና በትልልቅ ሰዎች ፊት ያለማፈር በፍቅር፣ በድፍረት፣ በሥልጣን እንደመሰከረ ስለ ወንጌል እስከ ሞት እንደ ተጋደለ መመልከት እንችላለን
እኛም ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ክርስቶስን የምናመልክ ሰዎች መልእክቱ ለሐዋርያው ጳውሎስ ብቻ ሳይሆን ለእኛም እንደሆነ እያሰብን ድነት ላላገኙ፣ ሕይወትን ለተጠሙ፣ ሰላም በመፈለግ ለሚቅበዘበዙ ወገኖቻችን ያየነውን የሰማነውን በሁኔታዎች ሁሉ መመስከር እንደሚገባንም ማወቅ አለብን፡፡ ይህን ለማድረግ ከእግዚአብሔር የሚያስፈልገንን ተቀብለን ተልዕኮአችንን ማድረስ አለብን ፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ! አዳኝነትህን ለመናገር እንድችል መንፈስ ቅዱስህ ይርዳኝ፡፡
‹‹አዲስ መገለጥ››
የንባብ ክፍል፡- የሐዋርያት ሥራ 23
‹‹…ጌታ በአጠገቡ ቆሞ…ትመሰክርልኝ ዘንድ ይገባሃልና አይዞህ›› ቁ. 11
ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ራዕይ ከማግኘቱ በፊት በአይሁድ ሸንጎ ፊት ቀርቦ የምስክርነቱን ቃል በሰጠ ጊዜ የሆነውን ሁሉ ከምንባቡ መረዳት ይቻላል፡፡ በሐዋርያው ሕይወት ላይ አደጋ እንዳያደርሱበት ሻለቃው ስለፈራ ወደ ሠፈራቸው እንዲወስዱት ወታደሮችን አዘዘ፡፡ በዚያው ዕለት ጌታ በሌሊት በራዕይ ተገለጠለት፡፡
አስቀድሞም ሐዋርያው ጳውሎስ ለጌታ ታማኝ ሆኖ በኢየሩሳሌም እንደመሰከረና ጌታም በምስክርነቱ እንደ ተደሰተ ይገልጻል፡፡ ይህንንም ምስክርነት በሌላ ሥፍራ እንዲደግመው ይፈልጋል፡፡ ‹‹ከዚህ በኋላ ምን እሆን ይሆናል›› ብሎ በማሰላሰል ላይ ለሕይወቱ ያለውን ዓላማ ሲገልጽለት፣ የበለጠም የምስክርነት በር እንደ ከፈተለት ያስታውቀዋል፡፡ ‹‹በወንጌል አላፍርም›› ብሎ ሕይወቱን ለጌታ ምስክርነት ያስረከበ ሰው ምንም ቢደርስበት ሕይወቱ በጌታ እጅ ውስጥ መሆኑን ያምናል፡፡ በጣም የሚያስደስተው ደግሞ ባለንበት ቦታና ሁኔታ በታማኝነት ለጌታ ከመሰከርን ጌታ የበለጠ የምስክርነት በር የሚከፍትልንና የበለጠ የመመስከር ኃላፊነት የሚሰጠን በመሆኑ ነው፡፡ በጠላታችን በዲያቢሎስ ላይ ድል የምንቀዳጀው አንደበታችንን በመዝጋት ሳይሆን በወንጌል አላፍርም በማለት ሁልጊዜ ለጌታ በመመስከር ብቻ ነው፡፡
‹‹በአጠገቡ ቆሞ… አይዞህ አለው›› ቅርብና ከእኛ ጋር ያለ እንጂ የሩቅ አምላክ አይደለም፡፡ ስለሆነም ስለ ስሙና ስለ ወንጌል በመከራ ላይ ለነበረው ባሪያው በሌሊት ራዕይ ተገልጾ አጽናናው፡፡ ለሕይወቱ ያለውን እቅድ ከገለጸለት በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ‹‹ እነሆ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ›› እንዳላቸው ሁሉ ለታማኙ ምስክር ለሐዋርያው ጳውሎስም ‹‹ጳውሎስ … አይዞህ›› እኔ ሁልጊዜ በአጠገብህ እሆናለሁ በማለት አጽናንቶታል፡፡
ጌታ ዛሬ በእኛ ምስክርነት ምን ያህል ይደሰትብን ይሆን? ጌታ በመከራችን ውስጥ አዲስ ራዕይ እንዲያሳየንና መገለጥን እንዲሰጠን እንጸልይ፡፡ ጸሎት፡- ጌታ ሆይ! የሚፈለግብኝን ሁሉ በታማኝነት እንድፈጽም እርዳኝ፡፡
0 Comments