‹‹በብዙ መከራ››
የንባብ ክፍል፡- የሐዋርያት ሥራ 14
‹‹ወንጌል ሰብከው ብዙዎችን ደቀ መዛሙርት ካደረጉ በኋላ የደቀ መዛሙርተን ልብ እያጸኑ፣ በሃይማኖትም ጸንተው እንዲኖሩ እየመከሩ፣ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል፤ እያሉ ወደ ልስጥራን፣ ወደ ኢቆንዮንም፣ ወደ አንጾኪያም ተመለሱ›› ቁ. 21-22፡፡
ጳውሎስና በርናባስ በዚህ ምዕራፍ እንደምንመለከተው ከነበሩበት ሀገር ተሰደው ወደ ኢቆንዮን እንደመጡና በዚያም በሚያሳድዷቸው ጊዜና በሚሄዱበት ሁሉ ወንጌሉን ይሰብኩ ነበር፡፡ ቁ. 6
ወንጌላቸውም በብዙ ድንቅና ምልክት ወደ ሰዎች ይደርስ ነበር ቁ. 9-17፡፡ ይህንንም ተዓምር ባዩ ጊዜ አማልክት ሊያደርጓቸው ወደዱ ነገር ግን እግዚአብሔር አምላካቸውን እያከበሩ የሳቱትን ሰዎች ንስሓ እንዲገቡ ወንጌልን ሰበኩላቸው፡፡
ጳወሎስም በዚያው ሥፍራ መከራን ተቀበለ የሞተም መስሎአቸው ከከተማ ውጭ እስኪጥሉት ድረስ ሆኖም ግን በነጋታው ከበርናባስ ጋር ወደ ከተማ ገብቶ ብዙዎችን ደቀመዛሙርት አደረገ፡፡
በዚህ ምዕራፍ ጳውሎስን በብዙ የችግር ሁኔታዎች ሁሉ የእግዚአብሔርን ወንጌል እንዲያስፋፋ ስንመለከት በእርግጥ በወንጌሉ አላፈረም፡፡ በተሰጠውም አደራ ታማኝ ነበር፡፡ ይህንንም በሕይወቱ መስክሯል ስለዚህ ነው ጳውሎስ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና፣ በወንጌል አላፍርም ያለው፡፡
ክርስቶስ በብዙ መከራ ውስጥ አልፎ እንዳዳነን እንዲሁም ጳውሎስ የጌታውን ፈለግ በመከተል ወንጌልን በየሥፍራው በብዙ መከራ መሰከረ፡፡ እኛም የጌታችንንና የእነጳውሎስን ፈለግ መከተል አለብን፡፡ ካመንበት ጊዜ ጀምሮ ለክርስቶስ ምን ደርሶብናል? የተቀበልነውን ተልዕኮ ለመፈጸም ተዘጋጅተሃልን? በሁኔታዎች ሁሉ በወንጌል አታፍርምን? እግዚአብሔር ለሰጠህ አደራ ታማኝ እንድትሆን ትጸልያለህ?
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ በተሰጠኝ የወንጌል ማዳረስ ተልዕኮዬን እንድፈጽም በሁኔታዎች ሁሉ በወንጌል እንዳላፍር የመንፈስ ቅዱስ ኃይልን ስጠኝ፡፡
‹‹እንንገራቸው››
የንባብ ክፍል፡- የሐዋርያት ሥራ 17
‹‹እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ›› ቁ. 23
ሰው በኃጢአት ከወደቀበት ጊዜ ጀምሮ ውስጣዊ ባዶነት ስለሚሰማው አንድ ነገር ማምለክ ይፈልጋል፡፡ ባዶነቱ የመጣበት ከፈጣሪው በመለየቱ ነው፡፡ የፈጣሪውን ሥፍራ የሚተካለት ነገር የማምለክ ፍላጎት አለው፡፡ ዛሬ በዘመናችንም ከእግዚአብሔር ሌላ አማልክት የሚያመልኩ አሉ፡፡
ጳውሎስ የአቴና ሰዎች የሚያመልኳቸውን አማልክት ሁሉ እየተመለከተ ሲያልፍ ከተመለከታቸው መካከል አንዱ ‹‹ለማይታወቅ አምላክ›› የሚል መሠዊያ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ እውነትም የማያውቁት ነበር፡፡ ነገር ግን አማልክት የተባለውን ሁሉ ስለሚፈሩና ሌሎች እንደሚያመልኩ ስላወቁ ብቻ ነበር ያን መሰዊያ በዚያ ያኖሩት፡፡
እነዚያ ብዙ አማልክቶች ነገር ግን አንዳችም ሕይወት የሌለባቸው በልዩ ልዩ ጌጥና ወርቅ የተሸለሙ፣ ሲያዩዋቸው የሚያምሩ፣ የሚያስፈሩ፣ የሚያንጸባርቁና ልዩ ልዩ ቅርጽ የያዙ ሲሆኑ ሰዎችም በዚያው በሞተ መንፈሳቸው ቦታ ሰጥተዋቸው የሚያመልኳቸው ነበሩ፡፡ በዚያ መካከል ነበር ያ የክርስቶስ መልእክተኛ ሕይወትን ያገኘ፣ እውነትን ያወቀ የእነዚያን ፍርሃት የተረዳው፡፡ ያ እነርሱ የማያውቁት አምላክ በእርሱ ውስጥ ኃያል ነበር፡፡ ስለዚህም ዝም ማለት አልወደደም፤ የማያውቁትን ሳያውቁ እንዲቀሩ አልፈለገም፡፡ ስለዚህም በእነርሱና በአማልክቶቻቸው መካከል ቆሞ ተናገረ፡፡ የአምላኩን ኃያልነትና አዳኝነት መሰከረ፡፡
እኛ ዛሬ ያየነውንና ያወቅነውን ኃያል አምላክ በማያውቁት ሰዎች መካከል ይዘን ዝም እንል ይሆን? ከሌሎች አማልክቶች ጋር ሊወዳደር የማይቻለውን አምላክ አንፈርበት፣ አናሳንሰው ይህን አምላክ እንደ ጳውሎስ ‹‹እኔ እነግራችኋለሁ›› እንበል፡፡
ጸሎት፡- አምላኬ ሆይ! ኃያልነትህ በውስጤ ከሁሉ በላይ ይሁን፡፡
‹‹ለመናገር አትፍራ››
የንባብ ክፍል፡- ሐዋርያት ሥራ 18
‹‹እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፣ ማንም ክፉ ሊያደርግብህ የሚነሣብህ የለምና ‹‹አትፍራ››፣ ነገር ግን ተናገር ዝምም አትበል››
ቁጥር 9 ፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ የሐዋርያነትን ሥራ ከመጀመሩ በፊት በሥጋው በጣም የተማረ ሰው ነበር፣ ክብር ያለውና
የተፈራም ነበረ፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ቀርቦ በአሕዛብ ፊት ስሙን የመሸከም ኃላፊነት ከሰጠው ወዲህ ራሱን ክዶ፣ የጀመረውን ሩጫ ለመጨረስ፣ አገልግሎቱን ለመፈጸም፣ ነፍሱንና ክብሩን እንደ ጉድፍ ቆጠረ፡፡ እግዚአብሔርም በራዕይ ተገለጠለት፣ በአካቢውና በከተማው መዳን ለሚገባቸው የእግዚአብሔር ሕዝብ ዝም ሳይል የኢየሱስን ወንጌል እንዲናገር በጉዞውም ላይ ማንም በእርሱ ላይ ሥልጣን እንደሌለው አረጋገጠለት (ሐዋ.18፡9-10)፡፡
ዛሬ የራሳችንን ክብር ንቀን ዝቅ ብለን እንደ ጳውሎስ ‹‹ጌታ ሆይ፣ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ ወይም እኔን ላከኝ›› (ኢሳ. 6፡8) የምንል አለን ወይ ? ራስን የማቅረብ መንፈስ ስለሚጠሩትም ሆነ ስለ እግዚአብሔር ሥራ መገለጥን ለማግኘት ዕለት ዕለት መትጋት ያስፈልገናል፡፡ እግዚአብሔርም ዛሬ በአካባቢያችን ያሉትን ያልዳኑትን ከመንጋው ለመቀላቀል ከሞት ጐዳና ከጨለማና ካሉበት ከሰይጣን እሥራት ለማላቀቅ ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን ይህን ታላቅ ጥሪ ተቀብለው ሳያፍሩበት በድፍረት መልእክቱን የሚያደርሱ ሰዎች ይፈልጋል፡፡ ጳውሎስ እንደ ገለጠለት ማንነቱን ሊገልጥለት ድምፁን ለማሰማት፣ ፈቃዱን በእርሱ ሊገልጥ ይፈልጋል፡፡ ታዲያ የእግዚአብሔር ፈቃድ የሚገለጥበት ሰው ማን ይሆን? እኔ እሆን? አንተ ትሆን? አንቺ ትሆኚ? ሁላችንም ዝግጁ እንሁን፡፡
ወንጌሉን ለማድረስ ከተነሣን ማንም በእኛ ላይ ሥልጣን እንደሌለው ይህን የድነትን በር ሊዘጋ እንደማይችል እግዚአብሔርም ሁልጊዜ ከእኛ ጋር እንደሚሆን ቃሉ ያረጋግጥልናል፤ ኢየሱስ ‹‹እስከ ዓለም ፍፀሜ ከእናንተ ጋር ነኝ›› ብሏልና፡፡ ስለዚህ በወንጌል ሳናፍር ቃሉን ለሌሎች ለመናገር እንዘጋጅ፣ አንነሣ፤ እግዚአብሔር ኃይላችን ነው፡፡ ነገር ግን በእርሱ የምናፍር ከሆነ ኢየሱስ በአባቱና በመላእክት ፊት ያፍርብናል፤ በማስተዋልና በመጠንቀቅ እናድርግ(ሉ ቃ. 9፡26)፡፡ ጸሎት፡- ጌታ ሆይ ወንጌልህን ለማስፋፋት ድፍረትንና እምነትን ስጠኝ፡፡
0 Comments