‹‹ብትቃወም ይብስብሃል››
የንባብ ክፍል፡- የሐዋርያት ሥራ 9
‹‹አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ፣ የመውጊያውን ብረት በትቃወም ለአንተ ይብስብሃል›› ቁ. 5
መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት በአይሁድ አገር እርሻ በሚያርሱበት ጊዜ አንድ የሚያደርጉት ነገር አለ፡፡ የሚያርሱበት በሬ በጣም ኃይለኛ ሆኖ የሚዋጋና የሚፈራገጥ ከሆነ፣ የሚያሰለጥኑበት ዘዴ አላቸው፡፡ በሬውን በተለያዩ ዘዴ ይዘው ከጠመዱት በኋላ እየተራገጠ ሲያስቸግርና ቀንበሩን አልጐትት በሚልበት ጊዜ ከኋላ ከጭኑ አጠገብ የሚወጋው የሾለ ብረት ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ቀንበሩን ላለመሳብና ላለማረስ ፈልጐ በኋላ እግሩ ለመራገጥ ሲሰነዝር ሹሉ ብረት ይወጋዋል፡፡ መላልሶ ከተራገጠ ስለሚቆስል ላለመቁሰል ሲል ቀጥ ብሎ ቀንበሩን ይጐትታል፡፡
በጳውሎስ ሕይወት ላይ የደረሰው ይህን ይመስላል፤ ጌታም በሚያውቀው ምሳሌ አድርጎ አስተማረው፡፡ ጌታ የጠፉ ሰዎችን ወደ እርሱ ለማምጣት መሣሪያ አድርጎ ሊጠቀምበት ሲፈልግ ሳለ፣ እርሱ ክርስቲያኖችን ያሳድድ ነበር፡፡ ጌታ እንደ መረጠውና ለምን ዓላማም እንዳጨው አላወቀም፡፡ ስለዚህ ለማሳደድ በሚሄድበት ጊዜ በታላቅ ብርሃን ተገናኘው፡፡ በዚያን ጊዜ ጌታ ሲናገረው፣ ጳወሎስም መልስ ሲሰጥ ሳለ ‹‹የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል›› አለው፡፡ እርሱም ጌታ የሚፈልገውን ለማድረግ እንቢተኛ ሳይሆን ፈቃደኛ ሆኖ ወደ ከተማ ገባ፡፡ ለእግዚአብሔር የተመረጠ ዕቃ በመሆን ሲያገለግል ቆይቶ በመሥዋዕትነት ያለፈ የእምነት ሰው፣ ቆራጥ፣ የድል መሪ ሆነ፡፡
ዛሬ እግዚዘብሔር እያንዳንዳችንን ወደ ደህንነት (ድነት) ሲጠራን የምንቃወም ስንቶች ነን፤ ጳውሎስ በቅናት በኢየሱስ የሚያምኑትን ያሳድድ ነበር፡፡ እኛስ ዛሬ ፊት ለፊት ባይሆን በልባችን የምናሳድዳቸው ክርስቲያኖች አሉን ጌታ ለጳውሎስ የተናገረውን ቃል ለእኛም ይናገረናል፡፡ ‹‹… ብትቃወም… ይብስብሃል›› ስለዚህ የመውጊያውን ብረት የምንቃወም ካለን ብንተወው መልካም ነው፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ ያንተን ጥሪ እንዳልቃወም ወደ ድነት ምራኝ፡፡
‹‹ለሁሉ እንመስክር››
የንባብ ክፍል፡- የሐዋርያት ሥራ 10
‹‹ለሕዝብም እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ እርሱ እንደሆነ እንመሰክር ዘንድ አዘዘን›› ቁ. 42
ሰዎች በኃጢአት ውድቀት ውስጥ ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ በዘር፣ በወገን፣ በቀለም፣ በቋንቋ በመለያየት ራሳቸውን ከፋፍለው ይገኛሉ፡፡ ሰውን ሁሉ የፈጠረ እግዚአብሔር እንጂ፣ ራሱን የፈጠረ ወይም ያስገኘ ሰው የለም፡፡ ሁላችን የእርሱ የእጆቹ ሥራዎች ነን፡፡
እግዚአብሔር ሰውን ሁሉ እንደፈጠረ፣ አዳኙም ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ዓለም ሲልክም፣ ለሰው ሁሉ መድኃኒት ይሆን ዘንድ ልኰታል፡፡ ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ ስለሆነ ወንጌል የማያስፈልገው ሰው የለም፡፡ ሁሉ በአዳም ምክንያት ኃጠአተኛ ስለሆነ፣ ሁሉ በክርስቶስ በኩል መዳን ያስፈልገዋል፡፡ ወንጌል ለአይሁድም ለአሕዛብም የሚያስፈልግ ነው፡፡ ስለዚህም በዛሬው ምንባባችን የምንመለከተው ወንጌል አሕዛብ ለሆነው ቆርኔሌዎስ እንዴት እንደ ደረሰው ነው፡፡
እግዚአብሔር ለሰዎች ንስሓ የሚገቡበት በተለያየ ጊዜና ሰዓት ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ የንስሓ ጊዜ ሳይሰጠው የሚሞት ሰው የለም፡፡ የሚሰጠውን የንስሓ ጊዜ ተጠቅሞ ወደ ክርስቶስ ከመጣ የዘላለም ሕይወት ያገኛል፡፡ እኛም እንደ ቆርኔሌዎስ ወደ ድነት ለሚጠራቸው ሰዎች እንደ ጴጥሮስ በመላክ ሄደን ስለ ወንጌል ልንመሰክርላቸው ይገባናል፡፡ ወንጌልን ለመመስከር ዘር፣ ወገን፣ ቋንቋ … የመሳሰሉት ግርግዳ እንዳይሆንብን እንጠንቀቅ፡፡ ጴጥሮስ በአሕዛብ ቤት ገብቼ እንዴት እመሰክራለሁ እያለ ከእግዚአበሔር ጋር ይከራከር ነበር፡፡
ጴጥሮስ የተከራከረበት ሐሳብ ትክክል እንዳልሆነ በመረዳት ሄዶ አሕዛብ ለሆነው ቆርኔሌዎስ ወንጌልን ሰበከለት፡፡ እኛም ዛሬ ወንጌል ለሰው ሁሉ እንደ ተሰጠና እንደሚያስፈልገው በማወቅ፣ እንድንመሰክር የታዘዝነውን ትዕዛዝ መፈጸም አለብን፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ ወንጌል ለሰው ሁሉ በክርስቶስ በኩል እንደ መጣላቸው አውቄ ልመሰክር እርዳኝ፡፡
‹‹የመዳን ቃል››
የንባብ ክፍል፡- የሐዋርያት ሥራ 13
‹‹… ከእናንተ መካከልም እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ፣ ለእናንተ የዚህ የመዳን ቃል ተላከ›› ቁ. 26
ባለፈው የተመለከትነው ወንጌል ለሰው ሁሉ የመጣ እንደሆነ፣ ሰው ሁሉ ኃጠአተኛ ስለሆነም በወንጌል አምኖ መዳን እንደሚገባ ተመልክተናል፡፡ ወንጌል ክርስቶስ የሰውን ልጆች ከኃጢአት ከፍርድ ለማዳን እንደመጣ የሚያበስር ነው፡፡
እግዚአብሐር አስቀድሞ በአይሁድ በኩል ለመሥራት ስለፈለገ መርጦአቸው ሕዝቦቹ አደረጋቸው፡፡ እነርሱም ሊጠቀምባቸው የመረጣቸው መሆኑ ስላልገባቸው በከንቱ በራሳቸው በመመካት ብቻ በትዕቢት ከውድቀት ደረሱ፡፡ እግዚአብሔርም ልጁን በላከላቸው ጊዜ አልተቀበሉትም፡፡ የሚሰሙትንም የመዳን ቃል በመናቅ ችላ ብለው አሳለፉት፡፡ በዚህ ጊዜ ክርስቶስም ወደሚቀበሉት ዘወር አለ፡፡ ለሚቀበሉትና ለሚያምኑበትም የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣን ሰጣቸው፡፡
ጳውሎስና በርናባስም ይህን የመዳን ቃል ለማሰራጨት ከጌታ ጥሪ ከተቀበሉ በኋላ በአይሁድ ዘንድ ወንጌል ለመስበክ ተሰማሩ፡፡ የወንጌል ጉዞአቸውን በአይሁድ ዘንድ ሲጀምሩ እንመለከታለን፡፡ በዚህ ጊዜ አይሁድ ግን ይህን የመዳን ቃል ለመቀበል ፈቃደኞች አልሆኑም፡፡ ከመካከላቸው አንዳንዶች ቃሉን ለመስማት በሚሰበሰቡበት ጊዜ በቅንዓት በመሞላት እነ ጳውሎስን በመንገዳቸው ሁሉ ያውኳቸው ነበር፡፡
በዚህ በቁጥር 46 ላይ እንደምንመለከተው ጳውሎስ ለመቀበል ፈቃደኞች አለመሆናቸውን ከተረዳ በኋላ ወደ አሕዛብ ዘወር ለማለት እንደፈለገ እንረዳለን፡፡ እኛም ዛሬ ያለብንን የተልዕኮ ኃላፊነት ካደረስን በኋላ ሰዎች ቢቀበሉን ባይቀበሉን ግድ የለም፡፡ ቢቀበሉን መልካም ነው፣ ባይቀበሉን ግን ትቢያችንን አራግፈን ዘወር ማለት ይገባናል፡፡ የመዳን ቀን እንደተላከላቸው አውቀው ወደ ጌታ ለሚመጡት መናገር ያስፈልገናል፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ ይህን የመዳን ቃል ራሴ ተቀብዬ እንደሆነ ላልተቀበሉት ለመስጠት ኃይልን ስጠኝ፡፡
0 Comments