‹‹ለመናቅ››
የንባብ ክፍል፡- የሐዋርያት ሥራ 5
‹‹… ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቈጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ›› ቁ. 41
ስለ ስሙ መነቀፍ፣ በመከራና በስደት ውስጥ ማለፍ የእያንዳንዱ እውነተኛ ክርስቲያን ጽዋ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ የነበረውን ተልዕኮ በብዙ መናቅና ስደት እስከ ሞት ድረስ የታመነ በመሆን የአባቱን ትእዛዝ ፈጽሟል፡፡ ሐዋርያትም የእርሱን ፈለግ በመከተል በሕይወታቸው በሚደረገው ነቀፋ ሁሉ የአምላካቸው ክብር እንደሚገልጽ ስለ ተረዱ፣ ለእርሱ ክብር ሲሉ የራሳቸውን ክብርና ጥቅም አስወገዱ፡፡ ስለ ስሙ መነቀፍ በሕይወታቸው ልዩ ደስታና እርካታ ሰጣቸው፡፡ ተንቀው ሳሉ የአምላካቸውን ኃይልና ሥልጣን በገሃድ አዩት፡፡ ብድራታቸውን አስተውለውት ስለነበር ስለ ስሙ ምክንያት በነቀፋና በመከራ ውስጥ ማለፍን መረጡ፡፡
ሕይወታችንን በደሙ የዋጀውን ጌታ ማንነቱን አውቆ ስለ እርሱ መናቅና መጠላት በጣም የሚያስደስትና የሚያረካ ሕይወት ነው፡፡ ስለ ስሙ መናቅና መከራ የማይደርስበት ክርስቲያን ቢኖር ከዓለም ጋር መስሎ መኖርን የመረጠና ከጌታው ክብር ይልቅ የዚህን ዓለም ክብር የወደደ ብቻ ነው፡፡ የእርሱ የሆኑ ሁሉ ከዓለም ጋር ምንም ሕብረት ስለማይኖራቸው ስለ ስሙ ምክንያት መናቅና መሰደድ እንደሚገጥማቸው ቃሉ ይናገራል፡፡ ስለሆነም እያንዳንዱ ክርስቲያን በስሙ ምከንያት መዳን ብቻ ሳይሆን መናቅና መጠላትም እንደሚገጥመው ማወቅ አለበት፡፡
ዛሬም ሕይወታችን ከሚፈተንባቸው ነገሮች አንዱ በነቀፌታ ውስጥ በሚቀርብልን መታረም ነው፡፡ በምንነቀፍበትና በምንጠላበት ጊዜ በክርስቶስ ላይ እንደገፋለን፤ እርሱ መልሳችን መሆኑን እንናገራለን፡፡
ጸሎት፡- አምላኬ ሆይ በስምህ ምክንያት የሚገጥመኝን ፈተና ሁሉ እንድቋቋም ጸጋህን አብዛልኝ፡፡
‹‹በጥበብ››
የንባብ ክፍል፡- የሐዋርያት ሥራ 6
‹‹… ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም፡፡ ቁ. 10
ለሰማያዊው ጥሪና ተልዕኮ በድል ለመመላለስ ሰማያዊ የሆነ ጥበብና ሰማያዊ የሆነ የእግዚአብሔር መንፈስ በየዕለቱ በሕይወታችን እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአገልግሎቱ በፊት ‹‹በሰማይና በምድር ሥልጣን ተሰጠኝ›› በማለት በማን ኃይል እንደሚሠራና ያለውንም ዓላማ በግለጽ እንደ ተናገረ እንመለከታለን፡፡ ሰማያዊ የሆነ አገልግሎቱን የጀመረው ‹‹የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና›› በማለት ነው፡፡ አገልግሎትንም እንደ ጀመረ በምድር ላይ የሰው ኃይል የማያደርገውን በሰማያዊ ጥበብና ኃይል ማድረጉን ከቃሉ እንመለከታለን፡፡
ዛሬም የእግዚአብሔርን መንግሥት ለሌሎች የምንናገር ሁሉ መሪያችንና ሠሪው የእግዚአብሔር መንፈስ መሆኑን መረዳት አለብን፡፡ ይህ መንፈስ በሕይወታችን ካለ ጌታችን እንዳለው ማንም ሊቃወመውና ሊከራከረው የማይችለው ጥበብና ኃይል ይኖረናል፡፡ መንፈሳውያን አገልግሎት ልንቀበልና ያለ ፍርሃት ለማገልገል የምንችለው ሰማያዊውን ጥበብና መንፈስ ከተቀበልን ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር የፍርሃት መንፈስ ስላልሰጠን በየትም ቦታ ብንሆን እርሱ እንደ ፈቀዱ በሚሰጠን ጸጋ ብዛት በቃሉ በመታመን ለአምላካችን ክብር መመላለስ ይኖርብናል፡፡
ሰማያዊውን ጥበብና ኃይል የተሞላ ሁሉ ሁልጊዜ ለማንኛውም ፍላፃ የተዘጋጀ መልስ ይኖረዋል፡፡ የሚያጋጥመውን ሁሉ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይቀበላል፡፡ በሕይወቱ አምላኩን በማንኛውም መሥዋዕትነት ለማስከበር ቊርጥ ውሳኔ ያደርጋል፡፡ ሰማያዊውን መንፈስና ጥበብ ስለ አገኘ ‹‹ምን እናገራለሁ›› በማለት ራሱን አያስጨንቅም፡፡ ሁልጊዜ ለድልና በድል ይመላለሳል፡፡
ጸሎት፡- አምላኬ ሆይ! በሕይወቴ ሁሉ ያንተ ጥበብና መንፈስ እንዲበዛልኝ እርዳኝ፡፡
‹‹የተዘጋጀህ ሁን››
የንባብ ክፍል፡- የሐዋርያት ሥራ
‹‹አፉን ከፈተ… ወንጌልንም ሰበከለት›› ቁ. 35
እግዚአብሔር እኛን ኃጢአተኞች የነበርነውን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እንድንታረቅ አድረጓል፡፡ ለዚህም የምንከፍለውና የምንሰጠው ምንም ስጦታ የለንም፡፡ ልናደርግ የምንችለው ምስጋና መስጠት ብቻ ነው፡፡
በእርግጥ ለተደረገልን ምሕረትና ቸርነት በዋጋ የሚተመን ብር ቢሆን ወርቅ ሰብስበን ብንሰጠው ምንም አይጠቅመውም፡፡ ብርና ወርቁ የእርሱ ስለሆነ ለተከፈለው ሕይወትም በቂ ሊሆን አይችልም፡፡ ዋጋውን ለመከፈል ባንችልም ልናደርገውና ልንፈጽምለት የሚገባን ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የመጀመሪያውና ትልቁ ወንጌልን ለሰዎች መናገር ነው፡፡ እኛ ያገኘነውን ለሌሎች ላላገኙ ማካፈል አለብን፡፡
በዕለቱ ምንባባችን ውስጥ የምንመለከተው በኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ስደት ሆኖ ደቀ መዛሙርት ሁሉ እንደ ተበታተኑ ነው፡፡ በስደቱም ፊልጶስ ከኢየሩሳሌም ወደ ሰማርያ ሄዶ ወንጌል ሲሰብክ እንመለከተዋለን፡፡ በስብከቱም ብዙዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንደመጡ ከቃሉ ለመረዳት እንችላለን፡፡ ፊልጶስ ከጌታ ያገኘውን ላላገኙት በማካፈል ላይ እያለ መንፈስ ቅዱስ ድንገት ከሰማርያ በጋዛ በኩል ወደሚገኘው ምድረ በዳ ሲደርስ አንድ ትርጉሙ የማይገባው ጃንደረባ የእግዚአብሔርን ቃል ሲያነብ አገኘውና አፉን ከፍቶ ወንጌልን ሰበከለት፡፡ ጃንደረባውም ወዲያው በማመን ወደ ወንዝ ወርዶ ለመጠመቅ ፈቃደኛነቱን ገለጸ፡፡ ፊልጶስም አጠመቀው በኋላም ደስ ብሎት ወደ መንገዱ ሄደ፡፡
እኛስ ወንድሞችና እህቶች ዛሬ ለራሳችን ከጌታ ምን አግኝተናል? ያገኘነው ካለን ለሌሎች አካፍለናል? ወንጌልን ለመናገር ስንቶቻችን የተዘጋጀን ነን? የተዘጋጀን ካለን በቤታችን፣ በጎረቤታችን፣ በሥራ ቦታችን የምሥራቹን ቃል ለማካፈል እንነሣ፡፡ ጌታ ይባርካችሁ፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ በቃልህና በመንፈስህ የተሞላ አፍና ልብ ስጠኝና የምሥራችህን ልናገር፡፡
0 Comments