ውድ የተልዕኮ ኦን ላይን (online) አገልግሎት ተከታታዮች ላለፉት አራት ዓመታት ተልዕኮ teleko.org በሚለው ድህረ ገጽ እና የሶሻል ሚዲያ ቴሌግራምና ፌስ ቡክ ተከታታይ የሆኑ ጽሑፎችንና ትምህርቶችን ስናጋራ ቆይተናል፡፡ በዚህ በትንሣኤ ሰሞን ‹‹መልካም ትንሣኤ›› በሚል የተዘጋጀ ጽሑፍ ተልዕኮ teleko.org በሚለው ድህረ ገጽ እናጋራችኋለን፡፡ አሁን በዚህ ሳምንት ትንሣኤን ልናከብር እየተዘጋጀን ባለንበት ጊዜ ከቅዱስ ቃሉ ‹‹እኔም እወስደዋለሁ›› ያለች የአንዲት ሴት ታሪክ አብረን እንድንካፈል ወደድን፡፡

የምንካፈለው የጽሑፉ ርዕስም ‹‹እኔም እወስደዋለሁ›› የሚል ሲሆን፣ ታሪኩ የተመሠረተው በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 20፡11-18 ላይ  ስለምትገኘው ሴት ይሆናል፡፡ እኔም እወስደዋለሁ የሚለውን ቃል ስንመለከተው ወይም ስናነበው የወሰደ፣ የተወሰደና ሊወስድ ያሰበ እንዳለ እንረዳለን፤ ማነው የወሰደው? ማን ነው? ወይም ምንድን ነው የተወሰደው? ማነው የሚወስደው? ብለን መጠየቅ ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ በተሰጠን የንባብ ክፍል ስንመለከት ‹‹እኔም እወስደዋለሁ›› ያለችው ሰባት አጋንንት የወጣላት መግደላዊት ማርያም ስትሆን፤ የተወሰደው የኢየሱስ ሥጋ (ሬሣ) ሲሆን፤ ወሳጆቹም አልታወቁም (በማርያም አባባል ነው እንጂ፣ ጌታ በማንም አልተወሰደም፤ በራሱ ተነስቶአል እንጂ፣ ነገር ግን መነሣቱን ማንም አላየውም ነበር)፡፡

በመጀመሪያ መግደላዊት ማርያም ማን ነች? የሚለውን ጥያቄ መጠየቅና መልሱንም መመለስ አስፈላጊ ነው፡፡ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 8፡2 ላይ ስንመለከት ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሆኖ በተለያዩ ከተማዎች እየሰበከና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች እየተናገረ በሚዞርበት ጊዜ ከሚያገለግሉት ሴቶች መካከል አንዷ እንደ  ነበረች ሉቃስ በቅዱስ በወንጌሉ ዘግቦልን እናገኛለን፡፡ ሉቃስ ስለዚች ሴት ሲጽፍ መግደላ ከሚባል ከተማ እንደሆነችና በጌታ ‹‹ሰባት አጋንንት የወጡላት›› እንደሆነ ይናገራል፤ በመቀጠልም በምዕራፍ ሰባት ላይ ተጨማሪ ታሪኳን ገልጾ እናገኛለን፡፡ ጌታ አገልግሎት በጀመረበት በቅፍርናሆም በምትባል ከተማ የምትኖር ኀጢአተኛ ሴት እንደሆነች ያመለክታል፡፡ ጌታ በፈሪሳዊ ስምዖን ቤት በነበረበት ጊዜ ‹‹እነሆ በዚያች ከተማ ኃጢአተኛ የነበረች አንዲት ሴት… በማዕድ እንደ ተቀመጠ ባወቀች ጊዜ ሽቱ የሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ አመጣች፡፡ በስተ ኋላውም በእግሩ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመረች፣ በራስ ጠጒርዋም ታብሰው እግሩንም ትስመው ሽቱም ትቀባው ነበረች›› በማለት ታሪኳን አስቀምጦታል፡፡

በመጀመሪያ ወደ ተመለከትነው የንባብ ክፍል ስንመለስ፣ አይሁዶች በባሕላቸው ሰው ከሞተ በኋላ በሦስተኛው ቀን የሰውዬው ነፍስ ከሟቹ የምትለይበት ጊዜ ነው ብለው ስለሚያምኑ፣ ወደ ቀብር ሥፍራ ሄደው ለማልቀስና ለመጨረሻ ጊዜ ስንብት ለማድረግ ወደ መቃብር መሄድ የተለመደ ነበር (ዮሐ. 11፡31)፡፡ በዚህም መሠረት መግደላዊት ማርያም፣ የያዕቆብ እናት ማርያምና (ሌላይቱ ማርያም) ሰሎሜ ሽቶ ቀብተው የመጨረሻ ልቅሶአቸውን አልቅሰው ለመመለስ ዝግጅት አደርገው ወደ መቃብር እንደሄዱ ሦስቱም ወንጌሎች ዘግበውልን እናገኛለን (ማቴ.28፡1-10፣ ማር. 16፡1-11፣ ሉቃ. 24፡12)፡፡

የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ጸሐፊ ይህን ድርጊት በምዕራፍ 20 ላይ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ በዘገበበት ሥፍራ ከሌሎቹ ወንጌሎች  ለየት ባለ መንገድ ወይም ከሦስቱ ሴቶች መካከል የአንዷን ታሪክ ብቻ እንዲህ ሲል አቅርቦታል፡፡ ‹‹ከሳምንቱም በፊተኛው ቀን መግደላዊት ማርያም ገና ጨለማ ሳለ ማለዳ ወደ መቃበር መጣች ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሎ አየች›› ቁ. 1፡፡ በባሕሏ መሠረት ሽቶ ቀብታ አልቅሳ ልትመለስ ነበር የሄደችው፡፡ ወደ መቃብሩ በደረሰች ጊዜ ግን ያልጠበቀችው ነገር ገጠማት፤ ያም የድንጋዩ መፈንቀል ነበር፡፡  ማርያም ግራ ቢገባትም፣ ወደ ጴጥሮስና ዮሐንስ መጥታ ‹‹ጌታን ከመቃብር ወስደውታል፣ ወዴትም እንዳኖሩት አናውቅም›› አለቻቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ደንግጠውና ቸኩለው በሩጫ ወደ መቃብሩ መጡ፡፡ የቀደመው ዮሐንስ ሲሆን ወደ መቃብሩ ሳይገባ አንገቱን አቀርቅሮ ሲመለከት የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፡፡ በመቀጠልም ጴጥሮስ ሲደርስ ወደ መቃብሩ ውስጥ በመግባት በተጨማሪ በራሱ ላይ የነበረውን በአንድ ሥፍራ ተጠምጥሞ አገኘው፡፡ ኢየሱስ ከነበረው ወርቅ ወይም ከጥርሱ ወርቅ ጋር እንደ አንዳንድ ሀብታሞች አልተቀበረም፡፡ ስለዚህ መቃብሩን ለምን ፈነቀሉት ብለው ሳይጠይቁ አልቀርም፡፡ ግራ የገባቸው ቢሆንም፣ ዮሐንስም ወደ መቃብሩ እንደ ጴጥሮስ በመግባት ክርስቶስ በመቃብር ውስጥ እንደሌለ አረጋግጠው ወደ ቤታቸው እንደተመለሱ ጸሐፊው አረጋግጦ እንደ ጻፈ እንመለከታለን፡፡

ዮሐንስ በመቀጠል ታሪኩን ሲተርከው፣ ‹‹ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር›› በዚህ ጊዜ ለጴጥሮስና ለዮሐንስ ያልተገለጠላቸው ነገር ለእርሷ ተገለጠላት፡፡ ያም ሁለት መላእክት የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው ሥፍራ አንዱ በራስጌና አንዱ በእግርጌ ተቀምጠው አየች፡፡ እነርሱም እንደ ጠባቂ ‹‹አንቺ ሴት ስለ ምን ታለቅሻለሽ?›› ብለው ጠየቅዋት፡፡ እርስዋም ‹‹ጌታዬን ወስደውታል ወዴትም እንደኖሩት አላውቅም አለቻቸው፡፡ ይህንም ብላ ወደ ኋላ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ኢየሱስም እንደ ሆነ አላወቀችም፡፡ ኢየሱስም ፡- አንቺ ሴት ስለ ምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ? አላት፡፡ እርስዋም የአትክልት ጠባቂ መስሎአት፡- ጌታ ሆይ አንተ ወስደኸው እንደ ሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ አለችው፡፡ ኢየሱስም ፡- ማርያም አላት››፡፡

በዚህ በትንሣኤ ጊዜ ይህን ጽሑፍ እንዳካፍላችሁ እግዚአብሔር ልቤን የነካውና የቀሰቀሰበት ቃል ‹‹እኔም እወስደዋለሁ›› የሚለው ንግግሯ ነው፡፡ የሞተ ሰው ሬሳ ምን ሊሠራላት ነው? እኔም እወስደዋለሁ የምትለው፡፡ የዚህችን ሴትዮ ታሪክ ቀደም ብለን እንደ ተመለከትነው፤ ኢየሱስ ከሰባት አጋንንት የፈታት ጌታዋ ስለሆነ፤ ምንም እንኳ ሬሳ ቢሆንም ባለ ውለታዋ ስለሆነ፣ ‹‹ጌታዬ›› በማለት እኔም እወስደዋለሁ እንድትል አድርጓታል፡፡ እንዲህ ማለቷ ምናልባት የተለዬ የቀብር ሥፍራ አዘጋጅታለትና እንዲጠበቅ ልታደርግ አስባ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡ ለማንኛውም ኢየሱስ በኅብረተ ሰቡ ዘንድ እንደ ሰው እንድትመላለስ ያደረጋትና የሕይወቷ ጌታና አዳኟ ነው፤ የክርስቶስ ትንሣኤው ባይገባትም፡፡

ትንሣኤ የእምነታችን ዋና መሠረት ነው፤ ሐዋርያው ጳውሎስም ለቆሮንቶስ አማኞች በመልእክቱ ‹‹ወንድሞች ሆይ፣ የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ… እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዬ፡- መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፣ ተቀበረም፣ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ›› በማለት የክርስቶስ ትንሣኤ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በተናገሩለት (ነቢያት) መሠረት፣ ሐዋርያትና ከአምስት መቶ የሚበዙ የመሠከሩለት እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡

መግደላዊት ማርያም ‹‹እኔም እወስደዋለሁ›› ብላ መናገሯ ሲያንሳት ነው፤ በየዘመናቱ ክርስቶስ አልተነሣም የሚሉ ሰዎች ቢነሱም፣ የእርሱ መነሣት የብዙ ሰዎችን ሕይወት እየለወጠ፣ ከአባቱ ጋር እያስታረቀ በሰላምና በደስታ እንድንኖርና ሰማያዊውን ሕይወት ተስፋ እያደረግን  እንድንኖር ያደርገናል፡፡ ክርስቶስን የምናምነው ለዚህ ምድራዊ ሕይወት ለሀብት፣ ለንብረት፣ ሳይሆን ለዘላለም ሕይወት ነው፡፡ ከሞት በኋላ ላለው ሕይወት ዋስትናችን የክርስቶስ ትንሣኤ ነው፤ እርሱ አስቀድሞ ተነስቶ፣ በአባቱ ዘንድ ተቀምጦአል፡፡ እኛም በክርስቶስ ብናምን ከሞት በኋላ በትንሣኤ ተነስተን ከእርሱ ጋር አብረን እንሆናለን፡፡ ስለዚህ እኛም እንደ ማርያም ‹‹እኛም እንወስደዋለን›› ልንል ይገባናል፡፡      ወንድሞችና እህቶች ይህን ጽሑፍ የምታነቡ ሁሉ ኢየሱስን እንደ መግደላዊት ማርያም ‹‹እኔም እወስደዋለሁ›› ብላችሁ የሞተውን ኢየሱስን ሳይሆን ሕያው የሆነውን ጌታ ወደ ሕይወታችሁ ወስዳችሁ አስገብታችሁታል? አስገብታችት ከሆነ፣ መግደላዊት ማርያም ሕያው የሆነውን ጌታ ካገኘች በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሄዳ መነሣቱን እንዳወጀች እናንተም ሄዳችሁ እንደ ኤማሁስ መንገደኞች እየጠወለጉ ላሉት ሁሉ ትንሣኤውን አውጁ፡፡ ይህን ጌታ፣ ጌታ ያላደረጋችሁና እኔም እወስደዋለሁ ብላችሁ ያልወሰናችሁ፣ ልባችሁን ከፍታችሁ አስገቡትና መልካም ትንሣኤ ይሁንላችሁ፡፡ መልካም ትንሣኤ ለሁላችንም ይሁንልን፡፡ አሜን!


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *