‹‹እርሱን … እንዳውቅ››                                 

 የንባብ ክፍል፡- ፊልጵስዩስ 3

 ‹‹እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳወቅ በመከራውም እንድካፈል … እመኛለሁ›› ቁ. 10-11

ሐዋርያው ቀደም ሲልም፡- ክርስቶስን በማወቅ ስለሚገኘው የከበረ እውቀት ይናገራል፡፡ ክርስቶስን ማወቅ ከንቱ ውዳሴ የሆነ የአእምሮ እውቀት፣ ቃሉን መጠቃቀስና የታሪክ እውቀት አይደለም፡፡ ስለ አንዳንድ ሰው የምናውቀው ሐቅ፣ ኑሮና ልማድ፣ የመሳሰለ እውቀት አይደለም፡፡ የአንድን ሰው እውነተኛ ውስጣዊ ሕይወት፣ ባሕርይ፣ ግላዊ በሆነ መንገድ መረዳት ነው፡፡

ክርስቶስን ማወቅ፣ ፍጹም የሆነ አንድነትና ወዳጅነት፣ የመንፈስ ውኅደት ነው፡፡ በዕለቱ መለኮታዊ ኃይሉንና ምሪቱን መለማመድ፣ ድምጹን መስማትና መታዘዝ ነው፡፡ ክርስቶስን ማወቅ፣ የትንሣኤውን ኃይል ማወቅ ነው፤ ይህም ማለት የዘላለማዊ ሕይወትን ማረጋገጫ ማግኘት፣ በእርሱ ሕያውነት የሕያውነትን ተስፋ መጨበጥ ነው፡፡ እርሱ ሞትን ድል ነስቷልና እኛም በድል እንነሣለን፡፡ ሥጋዊ ሞት የነገር ሁሉ ማክተሚያ አይደለም፤ በሰማይ ክርስቶስ ሥፍራ እያዘጋጀልን ነው፡፡ ከእርሱ የሚነጥለን ሞት ሆነ፣ ሌላ ኃይል የለም፡፡

ክርስቶስን ማወቅ፣ በመከራው መካፈል ነው፡፡ ክርስቲያን በዚች ምድር ላይ በእምነቱ ምክንያት በተሰደደ ቁጥር፣ የሆነ መከራ በተቀበለ ቁጥር የክርስቶስ መከራ ተካፋይ ይሆናል (1ቆሮ. 1፡5)፡፡ ስለሆነም ክርስቲያን ለክርስቶስ መከራ ሲቀበል ዕድለኛነት እንጂ  ወንጀለኛነት አይሰማውም፡፡ ለኃያሉ ጌታ መሰደድ ክብሩ ነውና፡፡

ክርስቶስን ማወቅ፣ በዕለቱ ሞቱን  በሚመስል ሞት እየመሰልነው መሄድ ነው፡፡ ክርስቶስ በሄደበት ጐዳና መሄድ፣ የኖረውን ሕይወት መኖር፣ የሞተውን ሞት መሞት፣ በመጨረሻ ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ እስክንመስለው ድረስ እርሱን ማወቅና ከእርሱ ጋር መተባበር ይኖርብናል፡፡

ጸሎት፡- ጌታ ሆይ!! በሚገባ አንተን አውቄና ካንተ ጋር በመተባበር በድል አድራጊነት ወዳዘጋጀህልኝ ቤት መግባት እንድችል እርዳኝ፡፡

የጳውሎስ ትምክህት

የንባብ ክፍል፡- ፊልጵስዩስ 4

‹‹ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ ቁ. 13

ሶቅራጥስ የተባለው ፈላስፋ አንድ ጊዜ፡- ‹‹ባለ ጸጋ ሰው ምን ዓይነት ሰው ነው?›› የሚል ጥያቄ ቀርቦለት ነበር ይባላል፡፡ የሰጠው መልስ፡- ‹‹ባለችው ትንሽ ነገር የሚረካ ባለጸጋ እርሱ ነው፣ በራስ መመካት የተፈጥሮ ሃብት ነውና›› የሚል ነበር፡፡

በራሳቸው የሚመኩ በእርግጥ በዓለም ላይ ብዙዎች አሉ፡፡ በኃይላቸው ፣ በንብረታቸው፣ በሥልጣናቸው፣ በእውቀታቸው እንኳ እየተመኩ፣ ራሳቸውን የራሳቸው ጌታ፣ ዳኛና ፈጣሪ ያደረጉ አያሌዎች አሉ፡፡ በራሳቸው ሥራ የሚታበዩ፣ በፈቃዳቸው የሚኖሩ፣ የኅሊና ዳኛ እንኳ የሌላቸው በዙሪያችን ይገኛሉ፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ ግን ሌላ መታመኛ ነበረው፡፡ ትክክለኛውን መታመኛ ያገኘ ሰው ነበር፡፡ እርሱም የሰማይና የምድር ገዥ፣ የኃይልና የሥልጣን፣ የሞትና የሕይወት ቁልፍ የሆነው፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ከጌታ ጋር የቆመ ያሸንፋል፣ ይከናወንለታልም፡፡ የጳውሎስ ብቃት ይህ መለኮታዊ ክንድ ነበረ፡፡ ‹‹ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ፣ አልፋና ኦሜጋ›› መታመኛው የሆነ አያፍርም፡፡

ጸሎት፡- ‹‹የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ›› እንደሚለው ቃልህ አምላኬ ሆይ፡- ከአንተ በቀር መመኪያ እንዳይኖረኝ ከልክል፡፡

ሰዓቱ አሁን ነው

 የንባብ ክፍል፡- ዮሐንስ 5፡1- 29

‹‹ እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ሙታን የእግዜአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፣ እርሱም አሁን ነው›› ቁ. 25

ጊዜው ጌታ ኢየሱስ ለሁለተኛ ጊዜ በኢየሩሳሌም ከተማ የነበረበት ሰሞን ነው፡፡ ክርስቶስም በዚያ አጋጣሚ ለ 38 ዓመታት በሕመም ሲማቅቅ የኖረ አንድ በሽተኛ ፈወሰ (ቁ. 1-9)፡፡ በፈውሱ የተነሣ አይሁድ ኢየሱስን ፡- ‹‹በሽተኛ በሰንበት ፈውሰሃል›› ሲሉ ይከሱት ጀመር፡፡ ይባስ ብለው፡- ‹‹እግዚአብሔር አባቴ ነው›› በማለቱ ሊገድሉት አድማ መቱ፡፡ ስለዚህም አድማቸውን ባለ መፍራት የሕይወትና የትንሣኤ መሠረት መሆኑን ዘረዘረላቸው፡፡ (ቁ. 19-29)

ያች ጊዜ በእርግጥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ነበረች፡፡ ሙታን በሥጋ የሞቱ ብቻ አይደሉም፡፡ ይልቁን በኃጢአታቸውና በመተላለፋቸው ምክንያት የከፋውን የመንፈስ ሞት የሞቱ ሁሉ ናቸው፡፡ የእነርሱ ተስፋ የሕይወት እስትንፋስ የሆነውን ጌታ ኢየሱስን በመስማት ብቻ የሚገኝ ነው፡፡

ዛሬም የጌታን ማንነት መቃወም፣ ተዓምራቱንም መካድ፣ እውነትን መቃወምና ሕይወትን መጥላት ነው፡፡ መለኮታዊ ብርሃኑና የትንሣኤውም ኃይል በሕይወታችን እንዳይሠራ ያግደዋል፡፡ የመጨረሻውን የእግዚአብሔር ልጅ ድምፅ ከመስማታችን በፊት፣ ዛሬ ቃሉ በተለያየ መንገድ ወደ እኛ ሲመጣ እንስማው፤ ምላሽም እንስጥ፡፡ ጸሎት፡- የሕይወቴ አለኝታ ሆይ፡- ድምፅህን ዘወትር እንድሰማ ፈቃድህ ይሁንልኝ፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *